Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቅድሚያ ለአገር

ወቅታዊው የአገራችን ፖለቲካዊ ትኩሳት የወለዳቸው ችግሮች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ለሦስት ዓመታት የዘለቀው የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ እዚህም እዚያም እሳት እያስነሳ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት ሕልፈት፣ አካል ጉዳትና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል፣ እየሆነም ነው፡፡ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም ጋሬጣ እየሆነ ነው፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለም ጉዳቱ እየገዘፈ መምጣቱ አይቀርም፡፡

ሰላማዊ ሁኔታ የሚሻው የቢዝነስ እንቅስቃሴ፣ በአሁኑ ወቅት ሥጋት ውስጥ ገብቷል፡፡ ገበያው እየተደበላለቀ ነው፡፡ የቢዝነስ እንቅስቃሴውን በተረጋጋ መንፈስ ለማካሄድ፣ የአገር ሰላም ወሳኝ ነው፡፡ የአገር ውስጡ ብቻም ሳይሆን፣ የውጭው ኢንቨስተርም ሥጋት ውስጥ እየወደቀ ነው፡፡ ዜጎች ሥጋት ላይ በመውደቃቸው ሳቢያ አላስፈላጊ ሸመታ እየተካሄደ፣ ገበያውም እየታመሰ መሆኑ ለግብይት ሥርዓቱ መደበላለቅ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

አገሪቱ የገባችበት ችግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ መልቀቂያ እንዲያቀርቡ ማስገደዱን ሰምተናል፡፡ ይህ ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን ተፅዕኖ በጉልህ ያሳየ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ‹‹በቅቶኛል›› መልዕክት ከመተላለፉ ሁለትና ሦስት ቀናት በፊት፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ መንገዶች መዘጋታቸው እንደተሰማ፣ ከመንገድ  የማይመለከታቸው ምርቶች ሁሉ ዋጋ ሲጨምሩ ታዝበናል፡፡ ቀውስ ጥርጣሬና ሥጋትን ይንራልና፣ ዋጋ ቢንር አይቀደንም፡፡ ነገ የባሰ ከመምጣቱ በፊት ሸማቹ ዛሬ ላይ መሸመት የሚችለውን ያህል በመሸት ለነገ ስንቁን ያከማቻል፡፡ በዚህ ሳቢያ በተፈጠረው ከፍተኛ ያልተጠበቀ ፍላጎት ገበያው አብጦ፣ ፍላጎቱን የሚያስተናግድ ምርት ማቅረብ ስለሚሳነው ዋጋ እንዳሻው ያሻቅባል፡፡

የፖለቲካ ትኩሳቱ ከዚህ በኋላ የሚያስከፍለው ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የምርት አቅርቦት እንደ ልብ ሊኖር ባለመቻሉ ገበያው በፍላጎትና በዋጋ ንረት ይወጠር እንጂ፣ መቀዝቀዙም የሚታይ ነገር ነው፡፡ መርካቶ ከወትሮው ድባብ በተለየ እንቅስቃሴው መቀዛቀዙ ሳይበቃ፣ ሌሎችም አካባቢዎች ከግብይት ይልቅ የፖለቲካው አዙሪት ምን ያመጣብን ይሆን የሚለውን ሥጋት የሚያኝኩ ተዋናዮች በሥጋት ሲናጡ ውለው የሚያድሩበት ባዶ ከተማ መስሏል፡፡

ውጥረቱ በነገሠበት ወቅት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ቀድሞው ከሚታየውም በባሰ አኳኋን በአጋጣሚ የመበልፀግ አካሄድ መታየቱ ሊጠቀስ ይገባል፡፡ የምርት እጥረት ሊያጋጥማቸው አይገባም የተባሉ ምርቶች ሁሉ እጥረት እንዲፈጠርባቸው ይደረጋል፡፡ ወትሮም በችግር የታጀለው የግብይት ሥርዓታችንና የአገልግሎት አሰጣጣችን፣ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ሲያገኝ ይብሱን ይበላሻል፡፡ ይህም ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ጎልቶ ታይቷል፡፡ በእርግጥ አገሪቱ የገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ይህንኑ ተከትሎ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መመርያም ለምርት አቅርቦት እጥረት አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

የውጭ ምንዛሪ በኮታ እንዲሰጥ መደረጉ ብቻም ሳይሆን፣ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ይሁንታ ካልሰጠ በቀር፣ ባንኮች ለተለያዩ ቢዝነሶች የሚሰጡትን የውጭ ምንዛሪ  መገደቡም ከባንኮቹ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ደጅ የሚጠናውን ነጋዴ እየደቆሰው ነው፡፡ ባንኮች ያበደሩትን ገንዘብ ለማስመለስ እየገጠማቸው ያለው ችግርም ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በተጓዳኝ የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ግርግር በተፈጠረ ቁጥር በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ከአትክልትና ፍራፍሬ ጀምሮ እስከ ተሽከርካሪ ያሉት ምርቶች ላይ የሚጫነው ዋጋ የስግብግብነትን ጥግ የሚያሳይ ሲሆን፣ ከዚህ የከፋ ጉዳይ ቢገጥመን ምን ልንሆን እንደምችንል የሚያሳስብ ነው፡፡ በግብይት ብቻም ሳይሆን፣ ከትራንስፖርት አገልግሉት አንፃርም ሰሞኑን ያየነው ዕንግልት፣ አጋጣሚዎችን ተጠቅመን በግርግሩ አትራፊና ጥቅመኛ ለመሆን መፈለጋችንን አደባባይ ያወጣንበትን ጠባይ አስተውለናል፡፡

በተለይ ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ላይ ታክሲዎችና ባጃጆች አዲስ ዋጋ አውጥተው ተገልጋዩን ሲበዘብዙ ማየት ያስተዛዝባል፡፡ ካለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ሌላው ችግር፣ የመብት ጥያቄን ለማሰማት በሚል ሰበብ በንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመት ነው፡፡ ዜጎች መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚያነሱት ጥያቄ ንብረት በማውደም መገለጽ የለበትም፡፡ መብትን ለመጠየቅ መብት መረገጥ አይኖርበትም፡፡

በዚህ መንገድ የሚገኝ ጥቅም የለም፡፡ የሚከበር መብትም የለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግብር የሚከፍለው ሕዝብና ዜጋ ነው ፍዳውን የሚያየው፡፡ የጠፋውንና የወደመውን ንብረት መልሶ ለመተካት አገር ብዙ ዋጋ ትከፍላለች፡፡ ተቋውሞና የመብት ጥያቄ የሌሎችን ደኅንነት አደጋ ውስጥ ሳይጥል፣ ሰዎችንም ለሞትና ለጉዳት ሳይዳርግ፣ ንብረትም ሳይጠፋ ቢደረግ እንዴት ባማረበት፡፡ መብት ጠያቂውም ሕግ አስከባሪውም በየጎራቸው ሲነሱ በቅድሚያ ለሚደርስ ጉዳት ጥንቃቄ ቢያደርጉ ምንኛ በሠለጠንን ነበር፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የተፈጠረው ውጥረትና ያለመረጋጋት ሁሉንም ወገን ባስማማ የሕዝብን ድምፅ ባገናዘበ መልኩ እንዲፈታና እየተንሸራተተ ያለውን ኢኮኖሚ እንዳይፈጠፈጥ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፍ ግድ ነው፡፡ ነገ ለንትርክ የማይጋብዝ አካሄድ በመከተል፣ ኢኮኖሚውም የበለጠ እንዳይናጋ ለማድረግ፣ ነገሮችን በአርቆ ተመልካችነትና በሆደ ሰፊነት ለመቀበል በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መንገድ ከሥልጣን መልቀቅ እንደተባለው ለለውጥና አገርን ለማዳን ከሆነ፣ ከዚህ በኋላ የሚወሰነው ውሳኔም የአገሪቱን የወደፊት ዕድል የሚወስን ነው፡፡ ቅድሚያ ለአገር ጉዳይ ሰጥቶ ችግሩን በቶሎ ለመፍታት መረባረብ፣ ሁሉንም ማሳተፍ፣ ከራስ ይልቅ ለሕዝብና ለጋራ ጥቅም መንቀሳቀስ ለአገርና ሕዝብ ውለታ ማኖር ነውና ሁሉንም በማስተዋል እናድርግ፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት