አዕዋፍ በጥርስ ምትክ ምንቃርን ምግብ ለመያዝ ይገለገሉበታል፡፡ ምንቃራቸውም እንደአመጋገብ ሁኔታቸው የተለያየ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የምንቃራቸው መለያየት የተለያዩ አዕዋፍ ዝርያዎችን ለያይቶ ለመመደብም አጥኚዎች እንደ አንድ ግብዓት ይጠቀሙበታል፡፡ እኒህ የተለያዩ የምንቃር ዓይነቶች ከአመጋገብ አንፃር እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡
ሀ. ጥራጥሬ የሚመገቡት
አጭር፣ አነስተኛ፣ ቆልመም ብሎ ጠንካራ ሲሆን ይህም ጠንካራ ጥራጥሬና ፍሬ ለመስበር የሚያገለግል ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ድምቢጥ
ለ. ሥጋ የሚመገቡት
አጭር፣ ሹል፣ ቆልመም ብሎ እንደመንጠቆ ዓይነት ምንቃር ሲሆን ሥጋን ለመጀንተር የሚያገለግል ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ጥንብ አንሳ፣ ንስርና ጭልፊት
ሐ. አሳ የሚመገቡት
ረጅም፣ ሰፋ ያለ ምንቃር ሲሆን፣ ይህም አሳዎችን በቀላሉ ከውኃ ውስጥ ቀዘፍ አድርጎ ለማንሶት ያገለግላል፡፡
ለምሳሌ፣ ቁንጮ አሳ አጥማጅ (King Fisher) እና ለማሚት (Cormorant)
መ. ከግንድ ላይ ሦስት አፅቄዎች (Insects) የሚለቅሙ ትልቅና ጠንካራ ምንቃር ሲሆን፣ የራስ ቅላቸውም ግንድ እየጠቀጠቁ ሦስት አፅቄዎች (Insects)ን በሚለቅሙበት ወቅት የሚፈጠረውን ንዝረት መቋቋም የሚያስችላቸው ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ግንደ ቆርቁር
ሠ. የአበባ ወለላ የሚመጡ
ረጅምና በጣም ቀጭን ምንቃር ሲሆን በቀጥታይህን ቀጭን ምንቃር ወደ አበባው ልከው ወለላ የሚመጡበት ነው፡፡
ለምሳሌ፣ እዝዝ ወፎች
ረ. ቋት ያለው ምንቃር
ረጅም፣ ቀጥ ያለና ሰፊ ሲሆን በምንቃሩ የኋላ ሥር ቋት የያዘ ነው፡፡ ቋቱም ምግብ ለማጠራቀም ይረዳዋል፡፡
ለምሳሌ፣ ሻሎ
ሰ. ማንኪያ መሳይ
የማንኪያ ዓይነት ቅርጽ ያለው ምንቃር ሲሆን ይህም የተለያዩ ትላትሎችና ሦስት አፅቄዎችን (Insects) ከጭቃና አረንቋ ውስጥ እየጨለፈ ለማውጣት የሚያገለግል ነው፡፡
ለምሳሌ፣ መንቆረ ማንኪያ (Spoon Bill)
- ማንይንገረው ሽንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› (2004)