በጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)
ባለፉት ሳምንታት ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጠሁትን ቃለ መጠይቅና ቃለ መጠይቁን ተከትሎ በሰጠሁት ተጨማሪ ጽሑፍ ማብራሪያ ዙሪያ፣ ወዳጄ አቶ ውብሸት ሙላት ባለፈው ሳምንት አንድ ጽሑፍ በዚሁ ጋዜጣ ላይ አሳትመዋል፡፡ የጽሑፍ ርዕስ ‹‹የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትን ማስፈን ለአገር መረጋጋትና ለዴሞክራሲ የሚኖረው ሚና›› የሚል ሲሆን፣ አቶ ውብሸት ኢትዮጵያ ልትከተለው ስለሚገባት የምርጫ ሥርዓት ያላቸውን አስተያየትና ከእኔ ጋር ያላቸውን የሐሳብ ልዩነት በሰፊው ገልጸውበታል፡፡ በቅድሚያ አቶ ውብሸት በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ገንቢ ሐሳብ በስፋትና በጥልቀት ለሁላችን በማድረሳቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
በዚህ ጽሑፍ አቶ ውብሸት ‹‹የተመጣጣኝ ውክልና›› የምርጫ ሥርዓትን በመደገፍና ‹‹የአንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓትን በመተቸት ላነሷቸው አንዳንድ ክርክሮች ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡
የ‹‹አንደኛ አላፊ›› ምርጫ ሥርዓት በኢትዮጵያ እስከዛሬ
አቶ ውብሸት በተደጋጋሚ ያነሱት አንደኛው የመከራከሪያ ነጥብ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› ምርጫ ሥርዓት እስከዛሬ በኢትዮጵያ ቢያንስ ለ24 ዓመታት የተሠራበት ቢሆንም፣ ሁለት ወይም ሦስት ጠንካራ ፓርቲዎች ነጥረው እንዲወጡ ማድረግ አልቻለም የሚል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አቶ ውብሸት ይህ የምርጫ ሥርዓት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እንዲሁም በሌሎች አገራት አመጣ የተባለው የፓርቲዎች መጠናከርና መዋሀድ በኢትዮጵያ አልታየም ብለው ተከራክረዋል፡፡ እኔ ደግሞ በቃለ መጠይቁና በተጨማሪ ማብራሪያዬ የሌሎች አገሮች ልምድንና በምርጫ ሥርዓቶች ላይ ያጠነጠኑ ንድፈ ሐሳባዊ ምልከታዎችን በማገናዘብ፣ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት የተጠናከሩ ሁለትና ሦስት ፓርቲዎች ነጥረውና ተፎካካሪ ሆነው እንዲወጡ ይረዳል ብያለሁ፡፡ ስለዚህ መነሳት ያለበት ንድፈ ሐሳባዊ ሥነ ጽሑፍና የሌሎች አገሮች ልምድ ከሚያመለክተው በተለየ ሁኔታ፣ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲዎችን መጣመር፣ መዋሀድ ብሎም የጠንካራ ሁለት/ሦስት ፓርቲዎችን መፈጠር ለምን አላመጣም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
ለዚህ ጥያቄ በእኔ አስተያየት ግልጽና ቀጥተኛ መልስ አለ፡፡ ይኼውም የ‹‹አንደኛ አላፊ›› ምርጫ ሥርዓት ንድፈ ሐሳባዊ ጽሑፍ እንደሚያመላክተውና በሌሎች አገሮች የታየውን ዓይነት የፓርቲዎች መጣመር፣ መዋሃድና መጠናከር በሚጠበቀው ልክ በኢትዮጵያ ያላመጣው፣ የምርጫ ሥርዓቱ ዴሞክራሲ መሠረታዊ መብቶች በበቂ ሁኔታ በተከበሩበት ዓውድ ውስጥ ሥራ ላይ ስላልዋለ ነው፡፡ ኢ – ዴሞክራሲያዊ በሆነ ዓውድ፣ መሠረታዊ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ሳይከበሩ በተካሄዱ ምርጫዎች፣ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› ምርጫ ሥርዓት የፓርቲዎችን መጠናከር አላመጣም ብሎ መተቸት አግባብ አይደለም፡፡ በአንፃራዊነት ነፃ በነበረው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ እንደታየው ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ነፃ ከሆነ ጠንካራና ትልልቅ ሁለት/ሦስት ፓርቲዎች ጎልተው መውጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› ምርጫ ሥርዓትን ጥቅሞች ለማግኘት በቅድሚያ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር ተገቢ ነው፡፡ መብት ሳይከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት ሳይጠናከሩ የትኛውንም የምርጫ ሥርዓት ብንከተል ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም›› ነው ነገሩ!
የብሔር ተኮር ፓርቲዎች መብዛትና ጎጠኝነት
ሌላው የአቶ ውብሸት መከራከሪያ ‹የተመጣጣኝ ውክልና› ምርጫ ሥርዓት ክልላዊነትን (ጎጠኝነትን) የሚቀንስ ሲሆን የ‹‹አንደኛ አላፊ›› ሥርዓት ግን ብሔር ተኮር ፓርቲዎች እንደ አሸን እንዲፈሉና ጎጠኝነት እንዲስፋፋ ያደርጋል የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ አቶ ውብሸት የተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓትን መዘዝ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት ላይ ለጥፈዋል ባይ ነኝ፡፡ ለዚህ ማስረጃ እንዲሆነኝ አቶ ውብሸት በጽሑፋቸው የጠቀሱትን ‹‹IDEA›› የተሰኘውን ዓለም አቀፍ የምርጫ ተቋም ጽሑፍ በዋቢነት እጠቀማለሁ፡፡ ይህ ጽሑፍ ስለ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት ጥቅም ሲያትት የሚከተለውን ይላል፡-
“It advantages broadly – based political parties in severely ethnically or regionally divided societies. ‘FPTP’ is commended for encouraging political parties to be ‘broad churches,’ encompassing many elements of society…`
[የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሰውነት በብሔርና በአካባቢ የተከፋፈሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ ሰፊ መሠረት ያላቸውን ፓርቲዎች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ የማኅበረሰቡን የተለያዩ ገጽታዎች የያዙ ፓርቲዎችን ያበረታታል፡፡]
ይኼው ጽሑፍ ስለተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ሲያትት፡-
“PR can reflect and facilitate a fragmentation of the party system… Democratizing countries are often fearfur that PR will allow personality based and ethnic cleavage parties to proliferate in their underdeveloped party systems” ይላል፡፡
[የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት የፓርቲ ሥርዓቱ እንዲከፋፈል ያደርጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እያደረጉ ያሉ አገሮች የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ባልዳበረው የምርጫ ሥርዓታቸው ግለሰባዊ ፓርቲዎችና የብሔር ክፍፍልን መሠረት ያደረጉ ፓርቲዎችን እንደ አሸን ሊያፈላ ይችላል ብለው በብዛት ይሰጋሉ]
ስለዚህ የትኛው የምርጫ ሥርዓት ጎጠኝነትንና ጠባብ ብሔርተኝነትን ሊያባብስ እንደሚችል ከላይ በዋቢነት ከተጠቀሰው ጽሑፍ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡ እናም በዚህ ጭብጥ ላይ የወዳጄ አቶ ውብሸት ክርክር አሳማኝ አይመስለኝም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጋናና ቦትስዋናን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ሥርዓትን በመገንባትና የብሔር ልዩነት ወደ ብሔር ግጭት እንዳያመራ በማድረግ እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ የሚችሉ የአፍሪካ አገሮች፣ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓትን የሚከተሉ መሆኑን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
የሐሳብ ብዙኅነት በፓርላማ
አቶ ውብሸት በጽሑፋቸው የእኔ ክርክር ትንሽ ገፋ ሲደረግ ‹‹ፓርላማው ወጥ ሐሳብ የያዙ ሰዎች መሰባሰቢያ ይሁን ማለት ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለእኔ ግን ትንሽ ገፋ ማድረግ የተባለው ትንሽ ገፋ ከማድረግ ይልቅ እጅግ መለጠጥ ሆኖ ታይቶኛል፡፡ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት የተለያዩ ሐሳቦች ያሏቸው ወገኖች በፓርላማ መወከላቸውን አይጠላም፣ አይከለክልም፡፡ በዚህ ምርጫ ሥርዓት የተመረጡ ፓርላማዎች በእንግሊዝ፣ በህንድ፣ በአሜሪካ፣ በጋና እንደምናየው የጦፈ ክርክር ይደረግባቸዋል፡፡ የሐሳብ ልዩነትም በሚገባ ይስተናገድባቸዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ የቀረበው የአቶ ውብሸት ክርክር ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አልታየኝም፡፡
ስምንት ወይም ዘጠኝ ፓርቲዎች
አቶ ውብሸት የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ቢደረግ፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግፋ ቢል ስምንት ወይም ዘጠኝ ፓርቲዎች ጎልተው ሊወጡ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ይህ ሥሌታቸው አሳማኝና ምክንያታዊ ነው፡፡ እዚህ ላይ በርዕዮት ዓለም ዙሪያ የሚመሠረቱ ፓርቲዎች ይህን ያህል ድምፅ ባያገኙም፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሃይማኖት ዙሪያ የሚመሠረቱ ቢያንስ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ደጋፊ ሊያገኙ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አቶ ውብሸት ባመጡት ሥሌት ላይ የሃይማኖት ፓርቲዎችን ስንጨምር የተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ቢመሠረት፣ 12 ገደማ በፓርላማው ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ወንበሮችን ይይዛሉ ማለት ነው፡፡ በሃይማኖትና በብሔር ልዩነት ላይ ያተኮሩ ከአሥር በላይ የሆኑ ፓርቲዎች ሽኩቻ ያለበት ፓርላማ መንግሥት መሥርቶ፣ በጀት አፅድቆ አገር ለማስተዳደር በእጅጉ ይቸግረዋል ብዬ እሠጋለሁ፡፡
አቶ ውብሸት ይህንን በተመለከተ ‹‹ቤልጅየምና ጣልያን መንግሥት መመሥረት ላይ በእጅጉ ሲንገዳገዱ መንግሥታቱም ሲበታተኑ ዓይተናል፡፡ አገሮቹ ግን እንዳሉ ናቸው፤›› በማለት ፓርላማው መንግሥት መመሥረት ቢያቅተው፣ መንግሥት ሰክኖና ተረጋግቶ ሊያስተዳድር ባይችልም፣ ብዙ ሊያስጨንቀን እንደማይገባ ይከራከራሉ፡፡ የመንግሥት አለመረጋጋት ቢከሰትም ደግሞ ፓርላማው ተበትኖ ሕገ መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት በስድስት ወራት ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ስለሚቻል ብዙ ሊያሳስበን አይገባም ብለዋል፡፡
እኔ በበኩሌ እንደ ቤልጅየምና ጣሊያን ኢትዮጵያ የመንግሥት አለመረጋጋትንና ቀውስን ለመሸከም የሚያስችል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትከሻ አላት ብዬ አላስብም፡፡ ከድህነታችን፣ ከአካባቢያዊ ፀጥታ ሁኔታችንና ከብሔር ፖለቲካ ትኩሳት የተነሳ በመንፈቅ ወይም በአንድና በሁለት ዓመት መንግሥት ለመለዋወጥና አዲስ ምርጫ ለማካሄድ የተመቸ ሁኔታ ውስጥ አንገኝም፡፡ የአሁኑ ምርጫ ወደ 419 ሚሊዮን ብር አካባቢ አስወጥቷል መባሉን ሰምቻለሁ፡፡ ይኼ በራሱ ፓርላማውን በትኖ አዲስ ምርጫ ማድረግን በቀላሉ እንዳናይ ግድ የሚለን ይመስለኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለአምስት ዓመታት ሰከን ብሎ የሚያስተዳድር መንግሥት ለኢኮኖሚ መረጋጋትና ዕድገትም ሆነ ለአገር ደኅንነት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ጎርፍ አስቸገረን ብለን ድርቅ እንደማንመኘው ሁሉ፣ የአንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይነት ሲያስቸግረን የአሥራ ምናምን ፓርቲዎች ትርምስን ልንከጅል አይገባም ባይ ነኝ፡፡
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመንን ትልቅ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከቷት ለናዚ ፓርቲና ለሂትለር ወደ ሥልጣን መውጣት ምቹ ሁኔታን ከፈጠሩት ነገሮች አንዱ፣ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትና የሚያስከትለው ቅጥ ያጣ የፓርቲዎች መከፋፈል፣ መብዛትና መካረር መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ውብሸት ሁለት/ሶስት ፓርቲዎች ኖረውም የተረጋጋ መንግሥት ላይኖር ይችላል ብለው ይከራከራሉ፡፡ ለዚህ ክርክር ያቀረቡት ብቸኛ ድጋፍ ሦስት ፓርቲዎች ወደ ፓርላማ ቢገቡ የምክር ቤቱን ወንበር ለሦስት ስናካፍለው ሦስቱም ፓርቲዎች አብላጫ ወንበር ላያገኙ ይችላሉ የሚለው መነሻ ነው፡፡ በቅድሚያ መጠቆም የምፈልገው ሦስት ፓርቲዎች ተፎካክረው አንዱ ፓርቲ ከሌሎቹ በልጦ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስፈልገውን አብላጫ ወንበሮች ሊያሸንፍ ይችላል፡፡ ይህም ባይሆን እንኳን አቶ ውብሸት እንዳሉት፣ ሦስቱ ፓርቲዎች እኩል ወይም በጣም ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸውን መቀመጫዎች ቢያሸንፉ ከሦስቱ ሁለቱ ጥምር መንግሥት መሥርተው አገሪቱን ሊያስተዳድሩ ይችላሉ፡፡ አሥራ ምናምን ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት ለመመሥረት ከሚያደርጉት ሽኩቻ፣ የሁለት ፓርቲዎች ጥምረት መሥርቶ የመቀጠል ዕድል እጅግ የሰፋ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ለተረጋጋ መንግሥትና ለሰከነ የፓርቲ ሥርዓት በማንኛውም መመዘኛ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የሚበጅ ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡
ከተረጋጋ መንግሥትና ከተረጋጋ አገር የቱ ይሻላል?
አንዱ የአቶ ውብሸት የክርክር ሐሳብ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት የተረጋጋ መንግሥት ቢያመጣም፣ ከዚህ አካሄድ ብዙ ዜጎች በፓርላማ ውክልና እንዳይኖራቸው አድርጎ በፖለቲካ ሥርዓቱ ያላቸውን እምነት ሸርሽሮ፣ አገሪቷን ወደ ፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት ሊያመራት ይችላል የሚል ሥጋት ነው፡፡ እናም የአቶ ውብሸት ክርክር ‹‹ከተረጋጋ አገር›› እና ‹‹ከተረጋጋ መንግሥት›› መምረጥ ያለብን እንዲመስለን ያደርጋል፡፡ ይኼ ደግሞ የግድ ያልሆነ ምርጫ የአመክንዮ ግድፍት (False Dilemma Falacy) ነው፡፡ የተረጋጋ አገርና የተረጋጋ መንግሥት ሊኖረን ይችላል፡፡ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ የግድ አይደለም፡፡ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊና የዜጎች መሠረታዊ የሲቪክና የፖለቲካ መብቶች በተከበሩበት ዓውድ ሥራ ላይ ከዋለ የተረጋጋ አገርና የተረጋጋ መንግሥት ይኖረናል፡፡ የተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓት ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ዓውድ ውስጥ ቢተገብር ያልሰከነ የፓርቲ ሥርዓት፣ ያልተረጋጋ መንግሥትና የብሔር/የሃይማኖት ክፍሎችን የማክረር አደጋው ሰፊ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ውሎ አድሮ አገሪቷን ወደ ከፋ ቀውስና አለመረጋጋት ሊወስድ ይችላል፡፡
ጠንካራ መንግሥት ዋስትና ወይስ አደጋ?
አቶ ውብሸት በተጨማሪም የ‹‹አንደኛ አላፊ›› የምርጫ ሥርዓት ጠንካራ መንግሥት የማምጣት ዝንባሌ እንዳለው ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የመንግሥት መጠናከር ችግር/አደጋ እንጂ በጎ ወይም የሚያስፈልገን ነገር ስላልሆነ አይበጀንም ብለው ይከራከራሉ፡፡ በእኔ አመለካከት የመንግሥት ሥልጣን ውስን እንዲሆንና በሕግ እንዲገደብ እንጂ፣ የመንግሥት ደካማ መሆን ለሕዝብ የሚጠቅም ነው ተብሎ ሊፈለግ አይችልም፡፡ የዜጎች ነፃነትና ደኅንነት ዋስትና የሚኖረው ጠንካራና በሕግ ሥልጣኑ የተገደበ መንግሥት ሲኖር ነው፡፡ የሊብራል አስተሳሰብ የሚፈልገው የማስተዳደር አቅምና ብቃት ያለው ጠንካራ፣ ግን ሥልጣኑ በሕግ የተወሰነ መንግሥት እንጂ ደካማና በቀውስ የተልፈሰፈሰ መንግሥት አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ የተነሳውን የአቶ ውብሸት መከራከሪያ መቀበል ያዳግተኛል፡፡
የበቀል አደጋና የምርጫ ሥርዓቶች
ሌላው የአቶ ውብሸት መከራከሪያ ‹‹ኢሕአዴግ አንዱ የሚወቀስበት ተበቃይነቱ ነው›› በሚል መነሻ የ‹‹አንደኛ አላፊ›› ምርጫ ሥርዓት ኢሕአዴግ የተሸነፈባቸው ወረዳዎችን ለበቀል ሲያጋልጥ፣ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ግን መላ አገሪቱን ወይም ክልሎችን እንደ አንድ ምርጫ ክልል ስለሚያይ ከበቀል ይታደጋል የሚል ሐሳብ ነው፡፡ እዚህ ላይ አቶ ውብሸት የዘነጉት ነገር አለ፡፡ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ክልሎች ወይም አገሪቷ እንደ አንድ የምርጫ ክልል ቢታዩም፣ በየመንደሩና የሠፈሩ የምርጫ (የድምፅ መስጫ) ጣቢያ መኖሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የበቀለኝነት አባዜ ያለበት ገዥ ፓርቲ ለመበቀል ከተነሳ፣ በየምርጫ ጣቢያው በተመዘገበው ውጤት ‹‹ማንን ልበቀል?›› ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት መራጩን ከፖለቲካ በቀል ይታደገዋል ማለት ዘበት ነው፡፡
እርማትና ማጠቃለያ
ሐሳቤን ከማጠቃለሌና መልሴን ከመቋጨቴ በፊት አንድ እርማት ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ በቃለ መጠይቁና በጽሑፍ ማብራሪያዬ የምርጫ ሥርዓቶችን የ‹‹FPTP›› (አንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት) እና የ‹‹PR›› (የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት) ወይም ቅይጥ ሥርዓቶች ብዬ ማስቀመጤ በጣም ግርድፍና አንባቢያንን የሚያስት አገላለጽ ነው፡፡ ስለዚህ ማስተካከያ ለማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ የምርጫ ሥርዓቶች ብዙኃን ተኮር (Plurality Majoritizim)፣ የተመጣጣኝ ውክልና ተኮር፣ ቅልቅል የሆኑና ሌሎች ተነጥለው ሊከፋፈሉ ይችላሉ፡፡ የ‹‹Alternative Voting (AV)›› (አማራጭ ድምፅ) የምርጫ ሥርዓት ከ‹‹FPTP›› ጋር በብዙኃን/አብላጫ ተኮር የምርጫ ሥርዓቶች የሚካተት ስለሆነ፣ አጠጋግቼ ግርድፍ በሆነ አገላለጽ የምርጫ ሥርዓቶቹን መፈረጅ ስህተት ነው፡፡ ለዚህም አንባቢያንን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ይህን ስህተቴን እንዳርም ምክንያት ለሆኑኝ አቶ ውብሸትም ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህ ስህተት ግን የክርክሩ ዋና ጭብጥ ላይ ያቀረብኩዋቸውን መነሻዎችና መደምደሚያዎች የማይንድ መሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
በመጨረሻ ሙግቴን ሳጠቃልል አትኩሮት ልንሰጠው የሚገባ የሚመስለኝን አንድ ሀቅ ላንሳ፡፡ ይኼውም ለኢትዮጵያ ‹‹ዴሞክራሲ ክሳት›› መንስዔው የምርጫ ሥርዓት አለመሆኑን ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የ‹‹ዴሞክራሲ ክሳት›› መንስዔዎች ቢዘረዘሩ የምርጫ ሥርዓታችን ዝርዝሩ ውስጥ መግባት ያለበት አይመስለኝም፡፡ የችግሩ ምንጭ ሌላ ሆኖ በምርጫ ሥርዓቱ ላይ የምናካሂደው ክርክር ‹‹ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ!›› የሚለውን ተረትና ምሳሌ ያስታውሰኛል፡፡ ስለዚህ ትኩረታችንን ከምርጫ ሥርዓቱ አንስተን ወደ ሌሎች ጥያቄና ጉዳዮች ብናዞር ይሻላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡