Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአዝጋሚው ጉዞ

አዝጋሚው ጉዞ

ቀን:

‹‹እናንብብ›› ውኃ ሰማያዊ ኮፍያ ላይ የሰፈረ መሪ ቃል ነው፡፡ መሰል ቀለም ያለው ካናቴራ ላይ ‹‹ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል›› እና ‹‹አንባቢ ትውልድ ለአገር ልማት›› የሚሉ መፈክሮችም ይነበባሉ፡፡ በኤግዚቢሽን ማዕከል የተገኙ ኮፍያና ካናቴራዎቹን አድርገው ይዘዋወራሉ፡፡ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከነዩኒፎርማቸው ነበር ወደ ማዕከሉ ያቀኑት፡፡ ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡ ታዳሚዎችም ተካፋይ ነበሩ፡፡

የግቢውን እኩሌታ የያዙት ነጫጭ ድንኳኖች መጻሕፍት ተሞልተዋል፡፡ ሻጮች፣ በንባብ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራት፣ አሳታሚዎች የትምህርት ተቋሞችና ደራሲያን ያለ እረፍት ታዳሚዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ በየድንኳኖቻቸው የተቋሞቻቸውን ሥራዎች የሚያስተዋውቁም በሥራ ተጠምደዋል፡፡

ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይና ባዛር መክፈቻ ዕለት ድባብ ነው፡፡ ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጀምሮ ለስድስት ቀናት ዘልቋል፡፡ አዲስ አበባ ሲካሄድ ሁለተኛው ሲሆን፣ መቐለ፣ ባሕር ዳርና ሐዋሳም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ መጻሕፍት ከ20 እስከ 30 በመቶ ቅናሽ ተደርጎ ቀርበዋል፡፡ አንባቢና ደራሲያን ፊት ለፊት እንዲገናኙና መጻሕፍት ላይ ያተረኮ ሥራ የሚከውኑ ተቋማት ሥራዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ያለመ ዝግጅት ነው፡፡ መጸሐፍ ተኮር ውይይቶች፣ የሥነ ጽሑፍ ውድድሮችና ጥናታዊ ጽሑፎችም ተስተናግደውበታል፡፡

 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሰል የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች በቁጥር እየጨመሩ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያዘጋጀው ዓመታዊ ዐውደ ርዕይ ተጠቃሽ ነው፡፡  ዐውደ ርዕዮችና ባዛሮች ልዩ ልዩ ዘውግ ያላቸው መጻሕፍትን ያስተናግዳሉ፡፡ የተወሰነ ፐርሰንት የዋጋ ቅናሽ ስለሚደረግ አንባቢያን ሲሳቡ ይስተዋላል፡፡ ገበያ ላይ የማይገኙና የጠፉ መጻሕፍትም ይገኙባቸዋል፡፡

ዐውደ ርዕዮቹ አንባቢዎችን የሚያበረታቱና ለመጸሐፍ ሻጮችም ጥሩ አጋጣሚ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የኅብረተሰቡ የንባብ ልማድ አመርቂ አይደለም የሚል ትችት በተደጋጋሚ በሚሰነዘርበት አገር መሰል ዝግጅቶች በመጠኑም ቢሆን ለውጥ እንደሚያመጡ የሚያምኑም አሉ፡፡ በአንፃሩ ዐውደ ርዕዮቹ በጥቂት ቀናት የተገደቡና ውስን ሰዎች የሚጎበኟቸው ናቸው የሚል አስተያየት የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ የዐውደ ርዕዮቹ ቁጥር ቀስ በቀስ መጨመር መልካም ቢሆንም ዘርፉ አሁንም በቂ ትኩረት የተሰጠው ነው ብሎ ለመናገር እንደሚዳግትም ይገለጻል፡፡

በዚህ ዐውደ ርዕይ ትልቅ ችግር ሆኖ የተስተዋለው የታዳሚዎች ቁጥር ማነስ ነው፡፡ በመክፈቻው ቀን በርካቶች ቢኖሩም የተመልካቹ ቁጥር በቀጣይ ቀናት ቀንሷል፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ወቅቱ ተማሪዎች ፈተና የሚወስዱበት በመሆኑ ዐውደ ርዕዩ እንደተቀዛቀዘ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሪድስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቃልኪዳን ሸጠማን ያገኘናት የድርጅቱን ቤተ መጻሕፍት ስታስተዋውቅ ነበር፡፡ በአነስተኛ የመጸሐፍ መደርደሪያ በድርጅቱ የተሰናዱ የሕፃናት መጻሕፍት ይታያሉ፡፡ በመሰል ዐውደ ርዕዮች ሲሳተፉ አምስተኛቸው ሲሆን፣ ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ስለ ቤተ መጻሕፋቸው እንዲያውቁ ይጋብዙበታል፡፡ የሚያገኟቸው ምላሾች አሠራራቸውን እንዲፈትሹ እንደሚያግዟቸው ትናገራለች፡፡ በዐውደ ርዕዮች ለሕፃናት መጻሕፍት በቂ ትኩረት እንደማይሰጥ ትገልጻለች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ዐውደ ርዕዮችና ባዛሮች ሲተዋወቁ ለሕፃናት ቦታ ስለመኖሩ አይገለጽም፡፡ በብዛት የሚሳተፉትም አዋቂዎች ናቸው፡፡ ዐውደ ርዕዮች ተማሪዎች ትምህርት ወይም ፈተና በሌላቸው ጊዜ ቢካሄዱ ተደራሽነታቸው ይሰፋል ትላለች፡፡ ‹‹ማስታወቂያው እንዲሁም ወቅቱ ልጆችን ያማከለ ሲሆን፣ በቀጥታ ከታዳጊዎች ጋር የመገናኘት ዕድል ይፈጥራል፤ የበለጠ ውጤታማም ያደርጋል፤›› ትላለች፡፡

የዕውቀት በር መጻሕፍት መደብር ለረዥም ዓመታት በመጻሕፍት ሽያጭ  ይታወቃል፡፡ ሻጩ ደመላሽ ከበደ አዲስ አበባ ውስጥና ውጪ በሚዘጋጁ ዐውደ ርዕዮች እንደሚሳተፉ ይናገራል፡፡ ከገበያ የጠፉ መጻሕፍት ማግኘት ስለሚቻል ገዥዎች እንደሚሳቡ ይናገራል፡፡ የዋጋ ቅናሽ አንባቢዎች በርካታ መጻሕፍት እንዲገዙ ቢያበረታታም አንዳንዴ ለሻጩ እንቅፋት ይሆናል ይላል፡፡

የዋጋ ቅናሹ እንደየመጸሐፉ ይለያያል፡፡ ከገበያ የጠፉ መጻሕፍት ብዙ ቅናሽ አይደረግባቸውም፡፡ ዋጋ ተጨምሮ የሚሸጥበትም ጊዜ አለ፡፡ ዘወትር የሚገኙ መጻሕፍት ግን እስከ 50 በመቶ በሚደርስ ቅናሽ ይሸጣሉ፡፡ ይህን ካልተገነዘቡ ገዥዎች ጋር መስማማት ያስቸግራል ይላል፡፡ ዐውደ ርዕዮች ከአዲስ አበባ በተሻለ ክልል ከተሞች ላይ አዋጭ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ነዋሪዎች መጻሕፍት ለመሸመት ያላቸው ዕድል ጠባብ በመሆኑ በዐውደ ርዕዮችን ተጠቅመው በርካታ መጻሕፍት ይገዛሉ፡፡

መጻሕፍትን የመግዛትም ይሁን የማንበብ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢዳብርም በቂ አይደለም ይላል፡፡ በዐውደ ርዕዮች የሚሳተፉ ደራሲያን የሕዝብን አስተያየት ማግኘት ስለሚችሉ ለቀጣይ ሥራዎቻቸው ይረዳቸዋል ሲል ያስረዳል፡፡ የመጸሐፍት ዐውደ ርዕዮች ትኩረት ሊቸራቸው፣ በቂ ማስተዋወቂያ ሊሠራላቸው፣ ሰፊና ለሕዝብ ግልጽ የሆነ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል ይላል፡፡ ብዙዎች ዐውደ ርዕይ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ውስን መሆን የለባቸውም ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከስድስት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ፣ ከጥቁር አንበሳና ከኤግዚቢሽን ማዕከል ውጪም መካሄድ አለባቸው፡፡ በዐውደ ርዕዮቹ ደራስያን በብዛት አለመታደማቸውንም ይተቻሉ፡፡

ደራሲ እንዬ ሺበሺን ያገኘናት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ያሳተማቸውን መጻሕፍት እየሸጠች ነው፡፡ የእሷ መጸሐፍ ‹‹የገቦ ፍሬ›› እና ‹‹ያልጠራ ደም›› በቦታው ይገኛሉ፡፡ በዓላትን ወይም ሌሎች ዝግጅቶችን አስታከው የሚሰናዱ ዐውደ ርዕዮች ላይ የሚገኘው ሰው ቁጥር ከመጻሕፍት ባዛር አንፃር ሲታይ በጣም ትንሽ ነው ትላለች፡፡ እንደ እንዬ ገለጻ፣ በባዛሮች ላይ አንድ ሰው መጸሐፍ ባይገዛም መመልከቱ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ‹‹በቀጣይ መጸሐፍ ለመግዛት ያነሳሳል፤ መጻሕፍት መግዛት አስፈላጊነቱን ያመላክታል፤›› ትላለች፡፡

እንደ ደራሲ ስትመለከተው መጻሕፍቶቻችን እንዲተዋወቁ ይረዳናል ትላለች፡፡ ደራሲያን፣ አሳታሚዎችና አከፋፋዮች ዓላማቸውን በኅብረት ያስተዋውቁበታል የምትለው ደራሲዋ፣ ‹‹በተናጠል ከመሥራት በጋራ መሆን ተሰሚነት ያስገኝልናል፤ ዐውደ ርዕይ ሲበራከት የንባብ ጠቀሜታም ይገናል፤›› በማለት መሰባሰቡን ታበረታታለች፡፡

በመጸሐፍት ባዛሮች ስፖንሰሮች በብዛት ሲሳተፉ አይስተዋልም፡፡ የፕሮሞተሮች ማነስም በተያያዥ ይጠቀሳል፡፡ ለመጻሕፍት የሚሰጠውን ትኩረት ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ አንዱም ይኼው ጉዳይ ነው፡፡

 

አቶ ኮነለነ መርኃጽድቅ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት የእንግሊዝኛ መምህር ናቸው፡፡ ዐውደ ርዕዮችን አዘውትረው ይካፈላሉ፡፡ ‹‹የተወሰኑ መጻሕፍትን ገዝቶ የተቀሩትን በዓይን ማየት አርኪ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ዘመኑ ያመጣቸው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በአጭር ጊዜ፣ በአነስተኛ ዋጋ መረጃ ማቀበላቸው ለመጻሕፍት የሚሰጠውን ዋጋ እንደሸረሸረው ያምናሉ፡፡ ወጣቱ አሁን ያለውን የንባብ ፍላጎት እሳቸው ወጣት ሳሉ ከነበረው ጋር ማነፃፀርም ይከብዳቸዋል፡፡

ከአንባቢው በተጨማሪ ደራሲያንም ኃላፊነት አለባቸው ይላሉ፡፡ መጻሕፍት ሲታተሙ ከይዘቱ ይልቅ የሚገኘው ገንዘብ ቅድሚያ ሲሰጠው ይስተዋላል፡፡ ሌላው ዐውደ ርዕዮች ስፖንሰር አልባ መሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ለተለያዩ ክንውኖች ስፖንሰር ለማግኘት አይከብድም፤ የሁሉም ነገር መሠረት ለሆነ ዕውቀትም የስፖንሰሮች እጅ ቢፈታ መልካም ነው፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡

መሪጌታ ብርሃኑ አበራ በወመዘክር የመዛግብት፣ የኢትዮጵያ ጥናትና የሕግ ክምችት አገልግሎት የመረጃ አሰጣጥ ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው፡፡ ያገኘናቸው ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውን 12 የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች እያስጎበኙ ነው፡፡ መጸሐፈ ሔኖክ፣  በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈው አርባእቱ ወንጌል፣ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈው የጳውሎስ መልክታት፣ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈውና በኢትዮጵያ የመጀመርያ ዕትም የሆነው መዝሙረ ዳዊት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ቅርሶቹ የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠሩና የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሁነት የሚያንፀባርቁ በመሆናቸው መተዋወቅ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ቅርሶች የሚተዋወቁባቸው መድረኮች ውስን በመሆናቸው መሰል ዐውደ ርዕዮች  የጎላ ጠቀሜታ አላቸው ይላሉ፡፡ ዐውደ ርዕዮች ጥናትና ምርምር ለማነሳሳትና ገቢ ለማግኘት አስፈላጊ ስለሆኑ መስፋፋት አለባቸው የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡

የሕፃናት ተረት መጸሐፍ ከጓደኞቹ ጋር ሲገዛ ያገኘነው የ12 ዓመቱ እስቅኤል አበበ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ዐውደ ርዕይ ሲታደም የመጀመርያው ነው፡፡ ‹‹መጻሕፍትን ማንበብ ዕውቀት ስለሚያስጨብጠኝ ነው ለመግዛት የመጣሁት፤›› ይላል፡፡ ታዳጊው ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ከየቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ሲጠይቁ የመረጡትን መጸሐፍ መግዛት እንደሚሹ አሳምነው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ወደፊት በሚኖሩ ዐውደ ርዕዮች የመሳተፍ ጉጉት እንዳለው ነግሮናል፡፡ ዐውደ ርዕዮች እስቅኤልን የመሰሉ ታዳጊዎችን ያማከሉና ትውልዱ ለንባብ ቦታ የሚሰጥ እንዲሆን የሚያነሳሱ መሆን አለባቸው የሚሉ ባለሙያዎች ጥቂት አይደሉም፡፡

አቶ ያሬድ ተፈራ በወመዘክር የሪፈረንስና ዶክመንቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክተርና የዐውደ ርዕዩ አስተባባሪ ናቸው፡፡ የዐውደ ርዕዩ ዓላማ አንባቢ ማኅበረሰብን ለመፍጠር እንዲሁም ባለድርሻ አካላቱ ደራሲያን፣ አሳታሚዎች፣ አታሚዎች፣ ሻጮችና አንባቢ መካከል ትስስር መፍጠር ነው ይላሉ፡፡ ግንኙነታቸው መጥበቁ በዘርፉ ፈጣን ለውጥ እንዲመጣ ያግዛል ይላሉ፡፡ በዐውደ ርዕዩ የሚቀርቡ የጥናት ጽሑፎች መወያያ መድረክ በማመቻቸት ረገድ ሁነኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ ዐውደ ርዕዩ ለምን በተማሪዎች ትምህርት ወቅት እንደተደረገ ጠይቀናቸዋል፡፡ እሳቸውም ማዕከሉ የሰጣቸውን ጊዜ ከመጠቀም ውጪ አማራጭ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡

በዐውደ ርዕዩ ሰባት የአፍሪካ አገሮች ጥሪ ተደርጎላቸው ነበር፡፡ መሳተፍ የቻሉት ግን የግብፅና የዩጋንዳ ተወካዮች ብቻ ናቸው፡፡ አቶ ያሬድ እንደሚናገሩት፣ ከዚህ በፊት ሌሎች አገሮችን ለማሳተፍ የተደረጉ ሙከራዎች ስላልነበሩ መጣጣራቸው ይበረታታል፡፡ በቀጣይ በርካታ አገሮችን ለማሳተፍ ጥረት እንደሚያደርጉም አመላክተዋል፡፡

ዐውደ ርዕዩ የተዋወቀው በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በከተማው ዋና ዋና ቦታዎች በተሰቀሉ ባነሮች ነው፡፡ ዳይሬክተሩን ባነጋገርንበት ዕለት (ሰኔ 3) በሞባይል አጭር የጽሑፍ መልዕክት ለመላክ እየተዘጋጁ ነበር፡፡ በዛው ማዕከል ከሳምንት በፊት ከተካሄደው የአይሲቲ ዐውደ ርዕይ ጋር ሲነፃፀር የታዳሚው ቁጥር ዝቅ ብሎ ታይቷል፡፡ አቶ ያሬድ እንደሚሉት፣ በቂ ማስታወቂያ አለመሠራቱ የታዳሚውን ቁጥር  አሳንሶታል፡፡ ለወደፊት የሚዘጋጁ ዐውደ ርዕዮች ሙሉ በሙሉ ግባቸውን እንዲመቱ ባለድርሻ ተቋሞች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ በተለይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናከር እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ካሳ መጻሕፍት በአንድ ቦታ  ላይ ባነሰ ዋጋ መሸጣቸው ዘርፉን የሚያነቃቃ ነው ይላሉ፡፡ እሳቸው እንደሚገልጹት፣ በሌሎች አገሮች እንደሚስተዋለው አሳታሚዎች ከፍተኛ ድርሻ መውሰድ ይገባቸው ነበር፡፡ አሳታሚዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ግን ጠንካራ ተሳታፊነት አላሳዩም፡፡

በሌላ በኩል ዐውደ ርዕዩ በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን አመላካች ነው ይላሉ፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የመጸሐፍ ፖሊሲ መቅረፅ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መገንዘቡን ነው፡፡ ተጋባዥ አገሮች መጻሕፍቶቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ቀረጥ ተጠይቀዋል፡፡ ይህ አካሄድ መለወጥ እንዳለበትና ሌሎችም ማነቆዎች መወገድ እንዳለባቸው ዐውደ ርዕዩ አመላክቷል ይላሉ፡፡

‹‹ማኅበራዊ ዕድገት የሚመጣውና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማስመዝገብ የሚቻለው የሚያነብ ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው፤›› የሚሉት አቶ ደስታ፣ ዐውደ ርዕዮች ባይዘጋጁ ዘርፉን አላላውስ ያሉ ተግዳሮቶች አይታወቁም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ የሚመለከታቸው ተቋሞች ተረባርበው የቅድመ ዝግጅት ሥራው መጠናከር እንዳለበት ከአቶ ያሬድ ጋር ይስማሙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...