Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልቁሳዊና ባህላዊ ሀብቶች ያደመቁት የቱሪዝም ሳምንት

  ቁሳዊና ባህላዊ ሀብቶች ያደመቁት የቱሪዝም ሳምንት

  ቀን:

  ከሜክሲኮ ወረድ ብሎ የሚገኘውና ይዞታነቱ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል የሆነው ገነት ሆቴል ከወትሮው በተለየ መልኩ ደምቋል፡፡ ከቅርብ ርቀት የሚሰማው የበርካታ ሰዎች ሆታ፣ ጭብጨባና የሙዚቃ ድምፅ በቅጥር ግቢው አንዳች ክብረ በዓል መኖሩን ያመለክታሉ፡፡

  ወደ ቅጥር ግቢው ሲገቡ ፊት ለፊት የሚያጋጥምዎት የጥበቃ ሠራተኛ አይደለም፡፡ ይልቁንስ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የሰፈረባቸው ባለቀለም ሪቫኖች ናቸው፡፡ ከዚያ ለጥቆ በሆቴሉ ከአንደኛው ጥግ የተጣሉት ነጫጭ ድንኳኖች ድግስ እንዳለ ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከመግቢያው ጀምሮ ውርውር ከሚሉና አንዳች ጉዳይ ያጣደፋቸው ከሚመስሉ ግለሰቦች ውጪ በርከት ያሉ ሰዎች አለመታየታቸው ግር ያሰኛል፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ ሆታ ከየት የሚመጣ ይሆን?›› የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡

  ሁነቶቹን በትኩረት ሲከታተሉም የሰዎቹ ሆታ በቅጥር ግቢው በጽድ ዛፎች ከተሸፈነ ሜዳማ ቦታ መሆኑን ይገነዘባሉ፡፡ ሆታው የሚጋብዝ ቢሆንም ድንኳኑ ውስጥ ያሉትን ነገሮች መመልከት ያዝን፡፡ ምንም እንኳ በአብዛኞቹ ድንኳኖች ውስጥ ስላሉ ባህላዊ ቁሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች፣ አልባሳትና ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚያመላክቱ ቢልቦርዶችና ብሮሸሮችን ምንነት የሚያስረዱ ባለሙያዎች ባይኖሩም፣ ብዙ ግር የሚል ነገር አልነበረም፡፡ ‹‹ይህ የዚህኛው ብሔረሰብ መገለጫ ነው፤›› ብለው ማለፍ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሹ ነገሮች በመኖራቸው ባለሙያዎቹን ማግኘት ግድ ነበር፡፡ ‹‹ምናልባት ጭፈራው ሲያልቅ ወደየቦታቸው ይመለሱ ይሆናል፤›› በሚል ግምት ወደ ጭፈራው ሥፍራ አቀናን፡፡

  መጠነኛ ስፋት ባላት ሜዳ ላይ በርካታ ሰዎች ተኮልኩለዋል፡፡ በወጉ መቀመጫ አግኝተው የተቀመጡት በዕለቱ ጥሪ የተደረገላቸው ባለሥልጣናትና በቱሪዝም ሳምንት ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ይዘው ብቅ ያሉት ሌሎች አፍሪካዊ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ግማሹ ሜዳው ላይ ተቀምጦ ከመድረኩ የሚተላለፈውን ትዕይንት ይከታተላል፡፡ የተቀረው የቆመ ሲሆን፣ ፉጨቱና ሆታው በበረታ ቁጥርም ለመመልከት የሚጣጣሩ ሞልተዋል፡፡ ዘለግ ያለ ወጣት በሐረሪ ሙዚቃ ታጅቦና የሐረሪ ባህላዊ አልባስ ለብሶ በመድረኩ ጐርደድ እያለ የመጣበትን አካባቢ አለባበስ አሳየ፡፡ ተመልካቾችም በሆታ ሲደግፉት ነበር፡፡ ሌሎች በርከት ያሉ ወጣቶችም የየብሔራቸውን ባህላዊ አለባበስ አሳይተዋል፡፡ የየብሔረሰቡን ጭፈራም እንዲሁ፡፡

  ባህላዊ ውዝዋዜና አልባሳት የሚታዩበት ፕሮግራም ሲገባደድም ሰውም ፊቱን ወደ ድንኳኑ መለሰ፡፡ ድንኳኖቹም ስለየባህሉ በሚያብራሩ ባለሙያዎችና ታዳሚዎች ተሞሉ፡፡ እኛም ወደ አንደኛው ድንኳን ጐራ አልን፡፡ ድንኳኑ በኦሮሚያ የሚገኙ ብሔሮች አልባሳት፣ ልዩ ልዩ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችንና ወንዞች፣ ትልልቅ ጫካዎች፣ በብሮሸሮችና በቢልቦርዶች ደምቋል፡፡ ከተዘጋጁት ቢልቦርዶች መካከል ‹‹ቦሶናያዮ›› ይገኝበታል፡፡

  ‹‹ቦሶናያዮ›› ያዮ የተሰኘ ጫካ ከአዲስ አበባ 564 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኢሉአባቦራ ይገኛል፡፡ በ167,021 ሔክታር መሬት ላይ አርፏል፡፡ ልዩ ልዩ አገር በቀል ዛፎች፣ አዕዋፋት፣ የዱር እንስሳት መጠለያ ነው፡፡ በተጨማሪም ፏፏቴ በውስጡ ይዟል፡፡

  የሶፍዑመር ዋሻ፣ የድሬ ሼክሁሴን መስጊድ፣ የፊንፊኔ ከተማ የኦሮሞ የባህል ማዕከል፣ የገዳ ሥርዓትና ሌሎችም የክልሉን ቁሳዊ ባህልና የተፈጥሮ ሀብቶች የሚያስተዋውቁ ቢልቦርዶችና ብሮሸሮች ተዘጋጅተዋል፡፡

  ወጣት ሐቢብ መሐመድ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም የመረጃና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ነው፡፡ እንደ እሱ ገለጻ፣ ጥቂት የማይባሉ በክልሉ የሚገኙ ፏፏቴዎች ሥራ ላይ አልዋሉም፡፡ ለምሳሌ የሶር ፏፏቴ የተለያዩ ሎጆች ቢገነቡበት ባለው የቱሪስት መስህብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ይችላል፡፡ ጭልሞ ፏፏቴም እንዲሁ በጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ በቅርቡ በተደረገ የማስተዋወቅ ሥራም በሶናያዮ ባለው ከፍተኛ የብዝኃ ሕይወት ቁጥር በዩኔስኮ ለመመዝገብ ጥቂት እንደቀረው ይናገራል፡፡ በክልሉ የሚገኙ በርካታ የተፈጥሮ ደኖችም ጥቅም ላይ መዋል አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል፡፡

  የኦሮሚያን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶች ከሚያስተዋውቀው ዳስ ትይዩ፣ ከአዲስ አበባ 661 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘውን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚያስተዋውቁ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ በአካባቢው የነበሩ ነገሥታት ቤተ መንግሥቶችን በፎቶግራፍ መረጃ የያዘ ዳስ አለ፡፡

  የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ባለሙያ አቶ አይቼው ካሴ ናቸው፡፡ ስለክልሉ ባህላዊ እሴት ለማስተዋወቅ ካላቸው ጉጉት ጋር ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ፤›› ሲል በፈገግታ እንግዶቹን ተቀበሉ፡፡

  ከፊት ለፊት ወደሚገኙት የዕደ ጥበብ ውጤቶች በጣታቸው እያመላከቱ ስለእያንዳንዱ ያብራሩም ጀመር፡፡ ሁሉም ከሸክላ የተሠሩና ለልዩ ልዩ ግልጋሎት የሚውሉ ናቸው፡፡ በመጠን ከሌሎቹ ከፍ የሚለውን ‹‹አልብሪክ›› ስለተሰኘው ባህላዊ የውኃ ማቀዝቀዣ የተወሰነ አብራሩ፡፡ ማቀዝቀዣው እስከ አምስት ሊትር የሚይዝ ይመስላል፡፡ ውኃ የተሞላበት ሲሆን፣ ዙሪያው ረጥቧል፡፡ በጣም ይቀዘቅዛል፡፡ ለጥቆ የሚገኘው ‹‹አል መብራ›› ብለው የሚጠሩት የዕጣን ማጨሻ ነው፡፡ በተለያዩ መጠኖች ተዘጋጅቷል፡፡ ሁሉም አሠራራቸው ተመሳሳይ ሲሆን፣ ለአያያዝ እንዲመችም አናታቸው ላይ ማንጠልጠልያ ተበጅቶላቸዋል፡፡ ጢሱ የሚወጣበት ቀዳዳዎችም አሉት፡፡ ‹‹አል መርከብ›› የአካባቢው ነዋሪ የሚጫሟቸው ጫማዎች ናቸው፡፡ በባህላዊ መንገድ በቤት ውስጥ ይዘጋጃል፡፡

  በክልሉ አምስት ነባር ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ ‹‹የቱሪዝም ሀብቶቻችን የነባር ብሔረሰቦች ባህላዊ ትውፊቶችና የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ናቸው፤›› የሚሉት አቶ አይቼው፣ ከዕደ ጥበብ ውጤቶቹ በተጨማሪ የብሔረሰቦቹን የበርታ፣ የጉሙዝ፣ የማኦ፣ የኦሞና የሺናሻ የጭፈራና የአለባበስ ባህል የሚያሳዩ ፎቶግራፎችና ቢልቦርዶች አዘጋጀተዋል፡፡ የተለያዩ አካባቢ ነገሥታት አብያተ መንግሥትም በፎቶ ዐውደ ርዕዩ ቀርበዋል፡፡

  ከሳርና ከጡብ የተሠራው ‹‹የሼህ ዑጀሌ›› ባህላዊ የፍርድ መስጫ አዳራሽ በፎቶ ከቀረቡት መካከል ነው፡፡ አዳራሹ የጐጆ ቤት ቅርጽ ሲኖረው ከመሬት ሰባት ሜትር ከፍታ አለው፡፡ ‹‹የአመሥራ›› መስጊድም በፎቶ ቀርቦ ነበር፡፡ መስጊዱ በመሆሞ ልዩ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፣ በዓመት በርካታ ጐብኚዎች ወደ ሥፍራው ብቅ እንደሚሉ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡

  በ1936 ዓ.ም. በጉባ ወረዳ የተገነባው የደጃች መሐመድ ባንጃው ቤተ መንግሥት የሚያሳይ ፎቶ ግራፍም ቀርቧል፡፡ በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑት መካከል እንደሆነም ተገልጿል፡፡

  የአካባቢው ባህላዊ ምግብ ‹‹ጭምቦ››ም በፎቶ ግራፍ ከቀረቡት መካከል ነው፡፡ ‹‹ጭምቦ›› ከወተት፣ ከማሽላ ቂጣ፣ ከእርጐ፣ ከቅቤና ከዳጣ የሚሠራ የክልሉ ተወዳጅ ምግብ ነው፡፡ እንደ አቶ አይቼው ገለጻ፣ አካባቢው የተለያዩ የቱሪስት መስህብነት ያላቸው ሀብቶች ቢኖሩትም፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች ባለመሟላታቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚጠበቅባቸውን ጥቅም መስጠት አልቻሉም፡፡ ይሁን እንጂ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ አስመልክቶ የመንገድ ግንባታ ተደርጓል፡፡ የበረራ ትራንስፖርትም ተጀምሯል፡፡ ይህም ለቱሪዝም ፍሰቱ መንገድ መጥረጉን ይናገራሉ፡፡

  በአዘቦት ቀንና በበዓላት የሚለበሱ ባህላዊ አልባሳትን ይዘው ብቅ ያሉት የሐረሪ ክልሎችም የዐውደ ርዕዩ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

  ‹‹ቄጠል›› በሠርግ ዕለት ሙሽራው የሚይዘው አለንጋ ነው፡፡ በሠርጉ የሚጠበቅባቸውን ያህል የማይጨፍሩትንና የሠርጉ አጃቢዎችን እየገረፈ ያስጨፍርበታል፡፡ አለንጋውን የያዘ ሰው ሠርገኛ መሆኑ ይታወቃል የሚሉት፣ ክልሉን ወክለው የተገኙ የቱሪዝም ባለሙያ ናቸው፡፡ ‹‹ገይገናፊ››ም ሙሽሪቷ ከውስጥ የምትለብሰው ሱሪ ነው፡፡ አጥላስ የምትከናነበው ሻርፕ ሲሆን፣ ዘርገፍ ከላይ የምትለብሰው እስከ ጉልበቷ የሚደርስ ሰፊና ያጌጠ ቀሚስ ነው፡፡ በአንገቷ የምትደረድራቸው ጌጦች ሲኖሩ በግንባሯም እንዲሁ የምታጠልቀው ጌጥ ይኖራታል፡፡ ሌሎችም የክልሉን ባህል የሚወክሉ ልዩ ልዩ የሠርግ አልባሳትና ጌጣጌጦች በዐውደ ርዕዩ ቀርበዋል፡፡

  ሀጨሪራዝ የሐረሪ ልጃገረዶች በሠርግና በሌሎች በዓላት የሚለብሱት ልብስ ሲሆን፣ ጉዶራሪዝ ደግሞ የሐረሪ ጉብሎች የሚጠቀሟቸው አልባሳት ናቸው፡፡ የሐረሪ ክልል መለያ የሆነው የጀጐል ግንብ፣ ልዩ ልዩ ስፌቶችና ሌሎችም በዐውደ ርዕዩ ቀርበዋል፡፡

  ዐውደ ርዕዩ ዘንድሮ ‹‹ቱሪዝም ቋንቋችን መስተንግዶ ባህላችን›› በሚል ለሦስተኛ ጊዜ የተከበረው የቱሪዝም ሳምንት አካል ነበር፡፡ ከግንቦት 24 እስከ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስም ለዕይታ ክፍት ሆኖ ቆይቷል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...