ወደ ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ቅጥር ግቢ ሲቃረቡ ብዙ ድንኳኖች ይታያሉ፡፡ ድንኳኖቹ የበርካታ ሠዓሊያንን ሥራዎች ይዘዋል፡፡ እያንዳንዳቸው አዲስ አበባ የሚገኙ ጋለሪዎችና ስቱዲዮዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ ነዋሪነታቸው ከአዲስ አበባ ውጪ የሆኑ ሠዓሊያን ሥራዎች ደግሞ አንድ ድንኳን ይዘዋል፡፡ በማዕከሉ አቅራቢያ ከሚገኘው እንጦጦ የቴክኒክና የሙያ ኮሌጅ የተውጣጡ የሥነ ጥበብ ተማሪዎች ሰብሰብ ብለው ሥዕሎቹን ይጎበኛሉ፡፡
ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተሰናዳው ዓመታዊ የሥነ ጥበብ ፌስቲቫል ትኩረቱን ጋለሪዎችን፣ ስቱዲዮዎችንና ዓርት ቪሌጆችን ማስተሳሰር ላይ አድርጓል፡፡ ጋለሪዎች የሚያስተናግዷቸውን ሠዓሊያን ሥራዎች በተናጠል ማቅረባቸው የተለመደ ነው፡፡ ፌሲቲቫሉ ግን አንዳቸው ከሌላቸው ልምድ እንዲቀስሙ በሚል አዋህዶአቸዋል፡፡ ከአርት ቪሌጆች ነፃ ዓርት ቪሌጅ ተጠቃሽ ነው፡፡ ጉራማይሌ የሥነ ጥበብ ማዕከልና ላፍቶ አርት ጋለሪ በፌስቲቫሉ ከተሳተፉ ጋለሪዎች መካከል ናቸው፡፡ ሐበሻ ዓርት ስቱዲዮ ደግሞ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ የሠዓሊያን ስቱዲዮዎች አንዱ ነው፡፡ የሠዓሊያንና ቀራጽያን ማኅበርና የሴት ሠዓሊያት ማኅበርም ተሳተፈዋል፡፡
የላፍቶ አርት ጋለሪ ኩሬተር ሠዓሊ ኑሩ አበጋዝ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ጋለሪዎች እርስ በእርሳቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ መንገድ የከፈተ ፌስቲቫል ነው፡፡ በአምናው ፌስቲቫል በየጋለሪዎቹ ዐውደ ርእይ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ የዘንድሮው በዘርፉ ያሉ ተቋሞችን በማጣመር ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ እድገት አስተዋጽኦ እንዳለው ኑሩ ይናገራል፡፡ ‹‹ጋለሪዎች በየራሳቸው ሥራ ሲወሰኑ ይታያል፤ ዐውደ ርእዮችንም ጥቂት ሰዎች ይታደሙ ነበር፡፡ ውህደቱ ለውጥ ያመጣል፤›› ይላል፡፡
ጋለሪዎች ልምድ የሚጋሩበት መድረክ መፈጠሩ ለወደፊት በኅብረት እንዲሠሩ ያነሳሳቸዋል ሲል አክሏል፡፡ በፌስቲቫሉ ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሥዕል መምህራን ሥልጠና መሰጠቱና የሕፃናት ወርክሾፕ መዘጋጀቱም ለዘርፉ አስተዋፅኦ እንዳለው ሠዓሊው ይናገራል፡፡
ፌስቲቫሎች ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች የተመረቁ አማተር ሠዓሊዎችን ስለሚያሳትፉ ቀጣይ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ ላፍቶ አርት ጋለሪ ከአንጋፋ ሠዓሊዎች በተጨማሪ የሥነ ጥበብ ምሩቃንን እንዲሁም የተማሪዎችን ዐውደ ርእይ ያስተናግዳል፡፡ የእነዚህን ሠዓሊዎች ሥራዎች ይዞ ፌስቲቫሉን እንደተቀላቀለ ኑሩ ይናገራል፡፡ እያንዳንዱ ጋለሪ በሥሩ ያሉ ሠዓሊያንን ሥራዎች ለተመልካች ማቅረቡ ፌስቲቫሉን ያሰፋዋል ይላል፡፡
ሠዓሊው ፌስቲቫሉ በአዲስ አበባ መወሰን እንደሌለበት ይገልጻል፡፡ በጥቂት ከተሞች ጋለሪዎች ቢኖሩም በቂ አይደለም፡፡ በየከተማው ያሉ ሠዓሊዎች ሥራዎቻቸውን በጥምረት የሚያቀርቡበት ፌስቲቫል መዘጋጀት እንዳለበት ያምናል፡፡ ‹‹በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ሠዓሊዎች መሳተፍ አለባቸው፤ ወደ ፌስቲቫሉ የሌሎች አገሮች ሠዓሊዎችን በመጋበዝ በምሥራቅ አፍሪካና ከዚያም በላይ ማስፋት ይቻላል፤›› ሲል አስተያየቱን ይገልጻል፡፡
ፌስቲቫሉ የተዘጋጀው በክረምት መሆኑን እንደ አንድ ችግር የጠቀሰው ሠዓሊው፣ ለወደፊት እንዲታሰብበት አሳስቧል፡፡ መገናኛ ብዙኃን ታዳሚዎች እንዲበራከቱ በማድረግ በኩል ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግሮ፣ ተገቢው ትኩረት እንዲቸረው ጠይቋል፡፡
የሠዓሊያንና ቀራጽያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሠዓሊ ሥዩም አያሌው ለሪፖርተር እንደተናገረው፣ ጋለሪዎች ተሞክሯቸውን በመመርኮዝ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የተሰናዳ ፌስቲቫል ከመሆኑ ባሻገር የክልል ከተሞች ሠዓሊያንን ማበረታታት ዓላማው ነው፡፡ በፌስቲቫሉ ከ20 የሚበልጡ ሥዕሎች ከተለያዩ ክልሎች በተውጣጡ ሠዓሊያን የተሠሩ ሲሆኑ፣ በቅጥር ግቢው የመጀመሪያው ድንኳን ተሰጥቷቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሠዓሊያን ፌስቲቫሉን ለጥቂት ቀናት መታደም ችለዋል፡፡ ‹‹ሥነ ጥበቡ በአዲስ አበባ ብቻ ከታጠረ ምሉዕ አይሆንም፤ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት የክልሎች ተሳታፊነት የግድ አስፈላጊ ነው፤›› ይላል፡፡
ፌስቲቫሉ ከ5,000 እስከ 10,000 በሚሆኑ ሰዎች እንደተጎበኘ የገለጸው ፕሬዚዳንቱ፣ ተመልካቾችን ለማስፋት ፌስቲቫሉ አስተዋጽኦ አለው ይላል፡፡ ሥዕል መመልከት እንዲሁም መግዛት በጥቂት ሰዎች መገደቡን በማጣቀስ ‹‹ሥነ ጥበብ የጥቂቶች ከመሆን መውጣት አለበት፤›› ይላል፡፡ ፌስቲቫሉ የሚፈጥረው ንቅናቄ ኅብረተሰቡ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ እንደሚያደርግም እምነቱ ነው፡፡
የዘረፉ ዋነኛ ተዋንያን ሠዓሊዎች ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን ስዩም ይተቻል፡፡ ሠዓሊያን ከፌስቲቫሎች የሚመጣውን ዘላቂ ለውጥ ከግምት ሲያስገቡ አይታይም፡፡ ተሳትፎአቸው ቢጨምር ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ለሥነ ጥበብ ዕድገትም አጋዥ እንደሚሆን አመላክቷል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ በሚቀጥለው ዓመት በተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ፌስቲቫሉን የማካሄድ ዕቅድ አለ፡፡ ስፖንሰር ማግኘት ቢከብድም ማኅበሩ ለማሳካት እንደሚጣጣር ተናግሯል፡፡ ለዘንድሮው ፌስቲቫል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እገዛ አድርጓል፡፡ ፌስቲቫሉ የተከፈተው ግንቦት 24 ሲሆን፣ ለጥቂት ቀናት ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ይሆናል፡፡