ሰላም! ሰላም! እሺ ‘ከጾማችንና ከልማታዊ ባለሀብቶቻችን የተረፈውን ጊዜ እንቀልድበት’ ያለው ማን ነበር? ለነገሩ ዛሬ ጊዜ ማነው? ምንድነው? ምን ነበር? ምን አለ? ቀርቷል። በቃ ‘ፌመስ’ በዝቷላ። ቢያንስ እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ‘ፌመስ ነኝ’ ብሎ ያስባል። ለምሳሌ አንዱ ባለፈው ሰሞን ብቻዬን ወዲያ ወዲህ ስንገዋለል (ስንገዋለልስ አልነበረም ሥራዬ ይዤ ነው) “ምነው ብቻህን? መንግሥት ወረሰህ እንዴ?” ሲል ነገር ጀመረኝ። እንዲህ አለ ብሎ፣ እሱም ያለኝን ጨምሮ ‘ፌስቡኩ’ ላይ ለጥፎ 10,000 ላይክ አገኘ አሉ። ‘ላቭና ላይክ የረከሰበት ዘመን!’ እኔማ ‘ብቻውን የታየ ሁሉ ተብሎ ተብሎ በመንግሥት የተወረሰ ነው ተባለ? የቀረውን ታሪክ?’ እያልኩ ተደምሜ ሳልጨርስ ‘አጠነጠነ እንዴ ይኼ ሰው?’ ብዬ አዘንኩለት። ታዲያስ! ዘንድሮ እኮ ‘ፎርዋርድና ሪዋይንድ’ የተምታታበት ሰው አይቆጠርም። ‘ፕሌይ’ ብሎ በሰከነ አዕምሮ የዛሬው ላይ የሚተጋውማ በጣት የሚቆጠር ሆኗል። ደግሞ አንድም የቤት እጦታችን መባባስና ኪራይ መጨመር ምክንያቱ ይኼ መሆኑን እወቁ። ‘ፎርዋርዱና ሪዋይንዱ’ የተምታታበት ሰው እየተለቀመ ሕክምና ካላገኘ፣ በቁጠባና በዕጣ ጥበቃ የሚቀረፍ አይመስለኝም። ሲሪየስ! ኮምጨጭ አልኩ እንዴ?
የከተማችንን ሰላማዊና ጤነኛ ቤት የለሽ ዜጋ፣ ቤት ኪራይ እያስወደደበት ያለው እኮ ዛሬ ላይ አልሞ በትናንትናው ራሱን አይቶና አጥርቶ በሂስና ግለ ሂስ ወደ ነገ የሚራመደው አይደለም። በተሰበረ ሕሊና እያነከሰ ጊዜያዊ ደስታውንና እፎይታውን ለማግኘት በርጫ ቤትና መጠጥ ቤትን እንደ አሸን ያፈላው ማን መሰላችሁ? ‘ሪዋይንዱና ፎርዋርዱ’ የተደበላለቀበት እኮ ነው። ንገረን ካላችሁ እንዲያውም ትንሽ ቀን ጠብቁ፣ . . . ቱ! . . . ‘ፎር ስታርና ፋይፍ ስታር’ ጫት ቤቶች ማየት ባትጀምሩ ምናለ በሉኝ። እናም እኔ ምናለበት የአዕምሮ ሕመምንና ታማሚውን ችላ እንዳልነው ወሬና አሉባልታው ረስተን ልማት ላይ ብንረባረበብ እላለሁ ብቻዬን ስሆን። ይኼን ሐሳብ ብቻዬን ሆኜ መደጋገሜን ያስተዋለችው ማንጠግቦሽ፣ “አንተስ ምናለበት ብቻህን ሆነህ ማጠንጠንህን ብትተው? እብደት እኮ ሲመጣ አሳስቆ ነው፤” አለችኝ። ይኼው ከዚያን ቀን አንስቶ ብቻዬን ስሆን የጠራኝ ሰው ያለ እየመሰለኝ ‘አቤት!’ ማለት ይቃጣኛል። ጀማመረኝ እንዴ?
ወደ ወዳጄ ጨዋታ ከመመለሴ በፊት የአብዛኞቻችን ‘ሪዋይንድና ፎርዋርድ’ የማሰብ ሥልቱ የተፋለሰበት የማውጠንጠን ችግር ጎልቶ ስለመምጣቱ ጥቂት እንድንጫወት እፈልጋለሁ። ይገርማችኋል ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር አብዝቼ ስለምውል ይሁን ወይ ‘ዲኤንኤ’ አላስመረምር ብዬ እንጂ የሲግመን ፍሮይድ የሥጋ ዘር ስለሆንኩ ይሁን አላውቅም፣ ዓይተን የማናያቸውና የማናወራባቸው ሥነ ልቦናዊ ችግሮች እየጎሉ ናቸው። ታሞ አስታማሚ ያጣው የበዛውም ለዚያ ይመስለኛል። አንዳንዴማ ስለመጪዎቹ ብሩህ የአገሬ የዕድገት ዘመናት ሳስብ ከለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣን ይኼን የማኅበረሰብ የሥነ ልቦና ቀውስ ከህዳሴው ግድባችን እኩል በማወቅም ባለማወቅም ተባብረን እየገነባነው ነው እላለሁ። ብቻህን ጠይቀህ ብቻህን አትመልስ ከሚለው የውዷ ባለቤቴ (የነፍስ አባት ልበላት? ለምድነው ግን ነፍስ እናት የሌላት? ተወያዩበት እስኪ) ቀጭን ትዕዛዝ መሠረት ጥያቄውን ወደ ባሻዬ ልጅ ወረወርኩት። በማያገባንና ባልገባን ነገር እየገባን የፍርድ ጠጠር ከመወርወር፣ አልገባንም ብለን ጥያቄ መወርወር አይሻልም? ለነገሩ መቼ ጠፍቶን ያውቃል የሚሻለን! አይደለም እንዴ?
በነገራችን ላይ ማንጠግቦሽን ስለቀጭን ትዕዛዝ አሰጣጥዋ አንድ ቀን ከየት ልትለምደው እንደቻለችና እንደተካነችው ጠይቄያት ስትመልስልኝ፣ “ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም” አለችኝ። ‹‹ፈርዶብህ ስትፈጠር ዕድሜና ክፉ ስም ይመረቅልሃል፤›› ይላሉ፡፡ ባሻዬ) አሁን ለምን አመጣሁት መሰላችሁ? በፌዴራሊዝም ያመንኩት ፖለቲካና የአገር አስተዳደራዊ መዋቅርን አውቄ ሳይሆን፣ የማንጠግቦሽን መሰል ወለም ዘለም የማያደርግ ቀጭን ትዕዛዝ እንደምፀየፍ ካረጋገጥኩ ጀምሮ ነው። እንደሰማሁት፣ በወሬ ወሬ የሰሙ አንዳንድ ጆሮ ጠቢዎች ለመንግሥት ‘አንዳንድ በፌደራሊዝም የማያምኑ ተቃዋሚዎችን ለማሳመን መንግሥትን ከሚስቶች ጋር አስዶልተዋል ተብሎ ካንድም ሁለት ሦስት ሰዎች አጫውተውኛል። ይኼን አዳምጠው የጀመሩትን ማኪያቶ ሳይጨርሱ፣ የወሬ ብሎገሮች ፈንታቸውን (እነቆርጦ ቀጥል) ‘ፍቺ የበዛው መንግሥት ፌደራሊዝም በወንዶች ልቦና እንዲሰርፅ በሚስቶች አንደበት በኩል እንዲወጡ በነደፋቸው ቀጭን ትዕዛዞች የተነሳ ነው’ ብለዋል ይባላል። ወይ ተረትና ኑሮ ብላችሁ ሳቁ ብዬ ነው እ? አደራ ደህና ገቢዬን ላሳድግበት! ተባለ እንዴ?
እናም ምን ነበር የማወራው? አስጠፋችሁኝ። በቃ እንቀጥል ዝም ብለን። ይልቅ አሁን ገቢዬን ላሳድግበት ስላችሁ፣ “አንበርብር እስካሁን እንዴት አልወለደም?” እያሉ ያልበላቸውን እያከኩ ጤና ስለነሱኝ ሰዎች ስሞታ ላቅርብ። መቼም የእኛ ሰው ሳያበላ፣ ሳያጠጣ የሰው ሕይወት እንደሚቆፍረው እኔ ነኝ ያለ ኤክስካቫተርም የልማታዊ ሕንፃዎቻችንን መሠረት ሲቆፍር አላየንም። ዓይታችኋል? ዓየን የምትሉ ካላችሁ የሰው ወይስ የማሽን የሚለውን አንዴ ለማጣራት ‘ሪዋይንድ’ አድርጉ። ትንሽ የጨዋታው ‘ቴንፖ’ ስለፈጠነ ዘንድሮ ወሬ ስናወራ ዓላማና ዒላማችን አፍራሽና ተቃራኒ ነገር መዘባረቅ ሆኗል ብዬ እኮ ነው። ‘ፎርዋርዳቸው’ የተዛቡ ማለት እንግዲህ አንዱ ምልክታቸው ይኼውና። እናም ባለፈው ለአንዱ አንድ ‘ኤክስካቫተር’ እያሻሻጥኩ (ገዥ ደንበኛዬ ነው)፣ “በቃ ይኼን ማሽን ቶሎ ካከራየሁት ከሚቀጥለው ዓመት የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ቢያንስ የ‘ተርም’ ዘጋሁ ማለት ነው፤” አለኝ። ‘እንዴ ይኼን የሚያህል ማሽን አከራይቶ የሚያገኘው ገቢ ከፍተኛ ነው። እንዴት የተርም ብቻ?’ ብዬ በመገረም፣ “ለመሆኑ የ‘ተርም’ ስንት ትከፍላለህ?” አልኩት። ኧረ እኔ ቁጥር አልጠራም እናቴ። እሱ ለጠራውም ውኃ ሆኜ በስንት ነፍስ ውጪ ግቢ ነው መለስ ያልኩት። ሆሆ! ብቻ እሱ የጠራውን ሲጠራ፣ “መቶ ብር ቢኖረኝ ኖሮ የክረምት ማጠናከሪያ ያልከኝ እከፍልልህ ነበር። ግን አሁን ከየት አባቴ ልላምጣ?” እየለ አንድ አባት ከልጁ ጋር በአጠገቤ ያልፋል። ይኼ መንገደኛው አባት መመኘቱና ማጣቱ እኩል እየገረመኝ ከጎኔ የቆመው ባለሀብት ይዞ መጨነቁና መሳቀቁ ስለባሰኝ፣ ‘አንበርብር ለምን አልወለደም?’ በተባልኩ ቁጥር የሚያናድደኝ ስሜት በአንዴ ተሻረ። እኔ የምለው ግን ልጆች የእግዜር ስጦታዎች ናቸው ሲባል አይደል እንዴ የሰማነው? ነው እንደለመደብን በአንድ ጆሯችን ሰምተን ተሸውደናል። ‘ተንቀሳቃሽ አገር ውስጥ ገቢም ናቸው’ የሚል ተቀጥላ አለበት ይሆን? ታዲያ በዚህ ዓይነት ሳንወልድ ማርጀታችን ይገርማል ትላላችሁ? እንኳን ሳንወልድ ጠግበን ሳንበላ እያረጀን። እንዲህ ይባላል እንዴ?
አሁን የልጆችን ነገር ሳነሳ መቼም የዘመኑ ልጆች ኮምፒዩተሩን ራሱን ካልቀደምነው ባዮች ናቸው። አንዳንዴ (ስላልወለደ ያሟርታል እንዳትሉኝ ደግሞ) ታዲያ ስለወደፊት ሕይወታቸው፣ አድገው ሙሉ ሰው ሆነው አሁን እየተወለዱና እያደጉ ያሉ ልጆችን ሳስባቸው ያሳዝኑኛል። ከፍጥነታቸው የተነሳ ማቆሚያና መመለሻ የሌለው የታሪክና የባህል ብልሽት እንዳያመጡ ያስፈሩኛል። አውቀው ሳይሆን በቃ ፈጣን ስለሆኑ። እኔ አንዳንዴ ብሩህነታቸውና ቶሎ የመገንዘብ ችሎታቸውን እያየሁ በዘመናቸው፣ ነገ ይህቺን አገር ተረክበው የሚያመጡትን ያልተሸራረፈ፣ ያልተስፈሰፈ የዴሞክራሲ ሥርዓት፣ ባህል ዕድገት፣ ፍትሕ፣ መልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብት አከባበር ዘመን አሳስባለሁ፡፡ ወዲያው ደግሞ አንድ ዓረፍተ ነገር ሳይደነቃቀፉ በሥርዓት አንብበው፣ አራት ነጥቡን ይዘሉና ሁለተኛውን ሲቀጥሉት ሳይ የሚነክሱት ቀንድ ብዛት ወዲያው ድቅን ይልብኛል። ባሻዬ ሁሌ ስለመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ሲያጫውቱኝ፣ ሁሌም የሥርዓተ ነጥቦቹ በተገቢው ቦታ ሥርዓት ይዞ የመገኘት ሚስጥር የሚሉኝን ልንገራችሁ። ሚስጥር በአደባባይ?
“ሥርዓተ ነጥብ የአንድ ድምፅ፣ ሐሳብ፣ ምዕራፍ ተወካይ ነው አንበርብር። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሕይወት ተወካይ ነው። አየህ በእያንዳንዳችን የኑሮ ሒደት ሁለት ነጥብ አለች። ፌርማታ በላት። ወይ የዕፎይታ ወይ የወዮታ። በእያንዳንዳችን ሕይወት ነጠላ ሰረዝ አለ። ሌላ ካንተ ውጪ የሆነ ሰው በምክንያት ወደ አንተ ሕይወት የሚመጣበት ሒደት ነው። ታሪካችሁ ሲያልቅ ልብ አድርግ አመጣጣችሁ ተደጋጋፊ እንደነበር የሚታወቅበት ነው። በእያንዳንዳችን ሕይወት አራት ነጥብ አለ። እሱ ደግሞ የማይቀረው ሞት ነው። መዝጊያው ነው። እንግዲህ እነዚህን ሥርዓተ ነጥቦች አክብረህና ተረድተህ ዝም ብዬ ልስገር ካልክ የባህል፣ የታሪክ፣ የእምነት ቀለምህ ተዘበራርቆ ነው የሚነበበው፤” ይሉኛል። ማብራሪያቸው ከየት ከየት እንደሚሳካ ባይገባኝም አንድ ነገር ግን አምናቸዋለሁ። እንፍጠንም እንዘግይም ከእያንዳንዱ ዕርምጃችን ጀርባ የማስተዋል መስኮት፣ የትንፋሽ መውሰጃ በረንዳ ከሌለ ሥልት የሌለው ታሪክ እንደምንጽፍ ጥርጥር የለውም። ምነው ተፈላሰፍኩባችሁ? ትውልድ በፍልስፍና የሚድን ከሆነ ‘ይቅርብን አይዳን’ እንል ይሆናል። ግን ቆይ ደላላ አውግዘን፣ ፈላስፋ አውግዘን እንዴት ይሆናል? ምን እናድርግ ታዲያ?
በሉ እንሰነባበት። ከባሻዬ ልጅ ጋር አንድ አንድ ልንል ወደተለመደችዋ ግሮሰሪ ሄድን። ሰዓቱ ሄዶ ቀኑ መሽቶ እንዳለመምሸት ማለቱን የባሻዬ ልጅ አንስቶ፣ “ታውቃለህ በሌላ አገር ማታ አራት ሰዓት ወደ ቀን አሥር ሰዓት የሚመስለበት ጊዜ አለ። እናም አንዳንዶቹ አገሮች በስምምነት ሰዓቱን ቀንሰው ወይ ጨምረው ይሞላሉ። አይገርምም? በዚህ ሙስና ላይ ‘የሰዓት ሚኒስቴር’ ቢጨመርብን አስበው? ተመስገን ነው፤” ይለኛል። እንዲህ እያወራን ወደ ግሮሰሪያችን ስንገባ ጭቅጭቅ ተነስቷል። “መጀመርያ ብድርህን ክፈል። ከዚያ እንደ ሰው ጠጥተህ እንደ ሰው ስከር። በዕዳ ስካርህ ላይ አረቄ እየጠጣህ አትንበዛበዝብን፤” ይላል አንደኛው። አፉ የሚያያዘው ጎልማሳ ቀበል አድርጎ፣ “ሽንብራና ጤፍ መንገድ ላይ ተገናኙ አሉ፤” እያለ መተረት ጀመረ። “እና ሽንብራ (ጥንብዝ ብሏል) ጤፍን ዞር ብላ ዓይታት ‘አንቺም አሁን እህል ተብለሽ ከእኛ ጋ ትጓዢያለሽ?’ ብትላት ጤፍ የእኔ አዋቂ፣ በነገራችን ላይ ባንጠግባትም አንጡራ ሀብታችን እንደሆነች ዓለም አውቆልናል። ርቦሽም ቢሆን አዳሜ ኩሪ እሺ። ተርቦ መኩራት የኖርንበት ነው፤” አለና ጥቂት ተመስጦ ቆይቶ “… ጤፍ የእኔ አዋቂ ‘ባክሽ ዝም በይ። ሁላችንም ስንፈጭ ዱቄት ነን’ አትል መሰለህ?” ሲል የግሮሰሪያችን ታዳሚዎች በሳቅ አውካኩ። እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይተን ሽንብራም ሆንን ጤፍ ሥር መሠረታዊው ችግራችን ተመሳሳይና አንድ ዓይነት እስከሆነ ድረስ ምን ብንከፋፈል፣ ምን በጥቂቶቻችን ዕድገት ጥቂቶቻችን ብንንጠራራ ያው መሆናችን ገባን። ወይ ሽንብራና ጤፍ? ‹ሁላችንም ስንፈጭ ዱቄት ነን?› እንዲህ ነው እንጂ ሙግት፡፡ መልካም ሰንበት!