Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራ ክልል ውስን ከተሞች የንግድ ተቋማት ተዘግተው ነበር

በአማራ ክልል ውስን ከተሞች የንግድ ተቋማት ተዘግተው ነበር

ቀን:

በአማራ ክልል በሚገኙ ውስን ከተሞች ለሁለት ቀናት የንግድ ተቋማት ተዘግተው እንደነበር ታወቀ፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ በተጠራው ቤት ውስጥ የመዋል አድማ በአማራ ክልል በተለይም በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች የንግድ ተቋማት ተዘግተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከየካቲት 12 እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሁሉም ከተሞች ቤት ውስጥ የመዋል አድማ እንደተጠራ ማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወሩ የነበሩ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ ለዚህ አድማ ምላሽ ለመስጠት ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በሞጣ፣ በቢቸና፣ በደብረ ታቦር፣ በፍኖተ ሰላም፣ በቻግኒና በሌሎች ከተሞች የንግድ ተቋማትን የመዝጋት አዝማሚያዎች እንደነበሩ ታውቋል፡፡

ይህን የንግድ ተቋማትንና የትራንስፖርት አገልግሎትን የማቋረጥ ተቃውሞ በተመለከተ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ብርሃን ንጉሤ ማክሰኞ የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የከተማው አመራር ይህ ችግር ሊፈጠር ይችላል ብሎ ቀድሞ በመገመት ቅዳሜና እሑድ ሲሠራ ስለነበር፣ የነበረውን አዝማሚያ ለመስበር ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡

በባህር ዳር ከተማ ሰኞ እኩለ ቀን ድረስ የንግድ ተቋማትን የመዝጋት አዝማሚያ ነበር፡፡ ነገር ግን የከተማው አስተዳደር የንግድ ተቋማትን ማሸግ ሲጀምር አብዛኛዎቹ ተቋማት እንደተከፈቱ ወ/ሮ ብርሃን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከሰዓት በኋላ ሁሉም የንግድ ተቋማት ተከፍተዋል፤›› ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ብርሃን ይህን ቢሉም፣ የተወሰኑ የንግድ ተቋማት ሰኞ ቀኑን ሙሉ ዝግ ሆነው መዋላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ብዙ የንግድ ተቋማትን ቢያሽግም ለመክፈት ፍላጎት የሌላቸውና የተቃውሞው ተሳታፊ ለመሆን የፈለጉ ብዙ ተቋማት ነበሩ፤›› ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ባለሀብት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ብርሃን ለምንድነው ግለሰቦች የንግድ ተቋሞቻቸውን የዘጉት? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በተጠራው የሦስት ቀናት ተቃውሞ ታሳታፊ ለመሆን  ወይም በሥጋት የዘጉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በባህር ዳር ከተማ ከሰኞ ጀምሮ በነበረው ቤት ውስጥ የመዋል ተቃውሞ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳልተቋረጠ የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ወ/ሮ ብርሃንም በከተማዋ ምንም ዓይነት የትራንስፖርት አድማ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ በነበረው የንግድ ተቋማትን የመዝጋት ተቃውሞ በሰው ሕይወትም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም አክለው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ለሁለት ቀናት ተቃውሞ ከነበረባቸው አካባቢዎች መካከል የጎንደር ከተማ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን፣ ከሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በከተማዋ ያሉት የንግድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ተዘግተው እንደነበር የከተማ ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባበል ማክሰኞ የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እየተከፈቱ ያሉ ሱቆች አሉ፡፡ የተለየ ነገር የለም፡፡ ከዚህ በላይ መረጃ ለመስጠት አልችልም፤›› ብለዋል፡፡

ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ በጎንደር ከተማ ሙሉ በሙሉ የንግድ ተቋማት እንደተዘጉና አብዛኛው የከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተቋረጠ የከተማዋ ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ የመዋል ተቃውሞ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የፀረ ሽብር ሕጉን ተላልፈዋል ተብለው በማረሚያ ቤት የቆዩት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእስር ሲፈቱ፣ በጎንደር ከተማ በግርግር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የክልሉ ፖሊስ ጥበቃ ሲያደርግ እንደነበር ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የከተማዋ ፖሊስ መምርያ ባልደረባ ለሪፖርተር ነግረዋል፡፡ በወቅቱ ግርግር ቢያጋጥምም ችግር እንዳልነበረ አክለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...