የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ያካተተ የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅና አገሪቱ ለገጠማት ወቅታዊ ችግርም መፍትሔ ከመድረኩ እንዲመነጭ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
ፓርቲዎቹ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ማክሰኞ የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ዋና ጽሕፈት ቤት ‹‹ሕዝቡ የሚፈልገው የሥርዓት ለውጥ እንጂ ተጨማሪ አፈና አይደለም፤›› በሚል ርዕስ በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው የሥርዓት ለውጥ እንጂ ጥገናዊ ለውጥ ስላልሆነ፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጡ ቀርቶ በአገር ውስም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራትን በአጠቃላይ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ያካተተ የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅና መፍትሔም ከመድረኩ እንዲመነጭ እንጠብቃለን፤›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቅርቡ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገሪቱ የገጠማትን ችግር ለመቅረፍ መፍትሔ አይሆንም በማለት አዋጁን የተቃወሙ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ድርጊት ሕዝባችንን ወደ ባሰ የእርስ በርስ ግጭት ያመራዋል ብለን እንሠጋለን፡፡ ስለዚህ በአገራችን ላይ የተጣለው ተገቢ ያልሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲነሳ አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› በማለት አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም የሁሉም ቤተ እምነት አባቶች ዝምታ ከማስገረም አልፎ እንደሚያስተዛዝብ የገለጸው የፓርቲዎቹ መግለጫ፣ ‹‹የሁሉም የቤተ እምነት አባቶች መንግሥት በሕዝቡ ላይ እየፈጸም ያለውን ግፍና መከራ በማውገዝና የሕዝብ አጋርታቸውን በመግለጽ፣ አገሪቱ አሁን ላጋጠማት ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ የመፍትሔ አካል ይሆኑ ዘንድ ለሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤›› በማለት ጥሪውን አቅርቧል፡፡