Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ተረጋግቶ ሥራውን እንዲያከናውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ሰጡ

የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ተረጋግቶ ሥራውን እንዲያከናውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ሰጡ

ቀን:

በአገሪቱ በተፈጠሩ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮችንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ማክሰኞ የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ አሁን በተፈጠሩት የፖለቲካ አለመረጋጋቶችና ለውጦች የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ሥጋት ሊገባው እንደማይገባ አሳሰቡ፡፡

በሸራተን ሆቴል በተካሄደ ውይይት ላይ ከሚኒስትሩ በተጨማሪ ሚኒስቴር ዴኤታዋ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ ተገኝተው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያካተታቸውን ክልከላዎች ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከሚኒስትር ዴኤታዋ ማብራሪያ በኋላ ሚኒስትሩ አገሪቱ ሰላም በመሆኗ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ሥጋት እንዳይገባው ከመግለጻቸው በተጨማሪ፣ በአገሪቱ የሚገኙ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ ነው ብለዋል፡፡ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ገዥው ፓርቲ በአገሪቱና በፓርቲው ሕግ መሠረት እያከናወነ ያለው ሥራ ያለምንም ችግር እየሄደ እንደሆነ በመግለጽ፣ ዲፕሎማቶቹ ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲያከውኑ ነግረዋቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸው በአገሪቱ ፖለቲካ ታሪክ አዲሱ መሆኑን ለዲፕሎማቶቹ እንደነገሯቸው፣ ይህም ለአገር ጥቅም ተብሎ የተላለፈ ውሳኔ መሆኑን ማስረዳታቸው ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በስብሰባው ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ቶማስ ኩዌሲ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ከራሷ አልፎ ለአካባቢውም ከዚያም በላይ አልፎ የሚሄድ በመሆኑ መንግሥት አሁን የጀመራቸውን የማሻሻያ ዕርምጃዎች እንደሚደግፉ፣ ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል ከሁከትና ከግርግር በመታቀብ መንግሥት የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በዋነኛነት የሰላምና መረጋጋት ጉዳይን እንዳነሱ ጠቁመው፣ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ሆነ ለአኅጉሪቱ አገሮች ወሳኝ እንደሆነ መግለጻቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ከመሆኗም በላይ በአንፃራዊነት ትርምስ፣ ጦርነት፣ ረሃብና እርዛት በማያጣት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ያላት አገር ናት፡፡ በብዙ አገሮች ሰላም አስከባሪ ኃይልም ያሰማራች አገር ናት፡፡ እንደዚህ ዓይነት ክፍለ አኅጉራዊም ሆነ አኅጉራዊ ኃላፊነት ያለባት አገር ችግር ሲያጋጥማት ባያሳስብ ነው ዜና የሚሆነው፤›› በማለት አቶ መለስ የዲፕሎማቶቹ ሥጋት ኢትዮጵያ ካላት አኅጉራዊ ሚና የመነጨ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና ሌሎች አምባሳደሮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣቱን ደግፈዋል ያሉት አቶ መለስ፣ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይም በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን፣ ዴሞክራሲ እንዲያብብና በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ ፍላጎት እንዳለው መግለጹን ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ክፉኛ መተቸቱን እንዴት እንደሚመለከቱት ተጠይቀው፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል፡፡ በመንግሥት በኩል የሚወሰዱት ዕርምጃዎች ይኼኛውን ወይም ያኛውን ወገን ለማስደሰት ተብሎ የሚወሰድ አይደለም፤›› በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዕለቱ የተካሄደውን የሚኒስትሮቹና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ውይይት ለመዘገብ በሥፍራው የተገኙት ጋዜጠኞች የመክፈቻ ንግግሩን ካዳመጡ በኋላ ‹‹ግልጽ ውይይት ማድረግ ይቻል ዘንድ›› በሚል ምክንያት፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎችና የሚኒስትሩን ምላሾች መዘገብ እንደማይቻል ተገልጾላቸው አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...