በቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ የዛንዚባሩን ክለብ ዚማሞቶን በሐዋሳ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡
የደቡብ ክልልን በመወከል በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የሆነው ወላይታ ዲቻ የሁለተኛ ዙር ጨዋታውን በአዲሱ ሐዋሳ ስታዲየም ያከናውናል፡፡
ዛሬ የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. የሁለተኛ ዙር ጨዋታውን የሚያደርገው ክለቡ ከወዲሁ የማሸነፍ ግምት አግኝቷል፡፡ በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ አንድ አቻ የተለያየው ወላይታ ድቻ ብዙ ተመልካችም በአዲሱ ስታዲየም ይጠብቀዋል፡፡
በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ መጀመርያ ላይ ጥሩ አጀማመር ያልነበረው ክለቡ ዘነበ ፍሥሐን ከቀጠረ በኋላ መሻሻል ማሳየት ጀምሯል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለው ጠንካራ የተጨዋች ስብስብ እንዲሁም ተፎካካሪነት ለካፍ ውድድሮች እስከ ዛሬ መድረስ ተስኖት ነበር፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወገብ ላይ በማጠናቀቅ የሚታወቀው ክለቡ በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ለተቃራኒ ክለብ ቀላል እንደማይሆን ይገመታል፡፡
በፕሪሚየር ሊግ መጀመርያ አካባቢ ነጥቦችን በመጣሉ ለዘጠኝ ዓመታት ክለቡን ሲያሠለጥን የቆየው አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪን ሲያሰናብት አላመነታም ነበር፡፡ ወላይታ ዲቻ በዘንድሮ በፕሪሚየር ሊግ 13 ጨዋታ ተጫውቶ በ16 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የዛንዚባሩ ዚማሞቶ በ2017 ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ መካፈል ቢችልም ከመጀመርያ ማጣሪያ ማለፍ አልቻለም ነበር፡፡ የሁለቱ አሸናፊዎች ከግብፅ ሃያል ክለብ ዛማሊክ ጋር ይገናኛል፡፡