Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕክምናው ተምሳሌት

የሕክምናው ተምሳሌት

ቀን:

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አዳራሽ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለግማሽ ቀን ያህል ለየት ያለ ድባብ ታይቶበታል፡፡ ለየት የሚያደርገውም በመማር ማስተማሩና በሕክምና ዘርፎች የተሠማሩት ምሁራንና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ማስተናገዱ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በታየው አዳራሽ ፊት ለፊት መድረክ ላይ የልሂቁ ሐኪም ፕሮፌሰር እደማርያም ፀጋ ፎቶግራፍ ተቀምጧል፡፡

በአዳራሹ መግቢያ በር አጠገብ ደግሞ ፕሮፌሰሩ በሕይወት ዘመናቸው የጻፏቸው መጻሕፍት፣ ልዩ ልዩ የምርምር ውጤቶችን የያዙ መጽሔቶች ለዕይታ በሚያመች መልክ በጠረጴዛ ላይ ተደርድረዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዝግጅት በቅርቡ ከዚህች ዓለም በሞት የተለዩትን እኚህኑ ሊቅ መምህር ሐኪምና ተመራማሪውን ፕሮፌሰር እደማርያምን ለመዘከር የተዘጋጀ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በዚህ መልኩ በተከናወነው ዝግጅት ላይ ፕሮፌሰሩ በሕይወት በነበሩበት ዘመን በመማር ማስተማሩና በሕክምናው ዘርፎች ያከናወኗቸው ተግባራት የሚያንፀባርቅ ጽሑፍ በንባብ ተሰምቷል፡፡ ከቀረበውም ጽሑፍ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ፕሮፌሰር እደማርያም ፀጋ ለ23 ዓመታት ያህል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንተርናል ሜዲሰን መምርያ ከረዳት ፕሮፌሰርነት ጀምሮ እስከ ሙሉ ፕሮፌሰርነት፣ ከዚያም የመመርያው የበላይ ኃላፊና በመጨረሻም የሕክምና ፋካልቲው ዲን ሆነው አገልግለዋል፡፡

ካናዳ በሚገኘው ዝነኛው ማጊል ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርታቸውን ከ1961 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ዓመታት ሲከታተሉ ቆይተው በ1965 የዶክትሬት ዲግሪ ለማግኘት በቅተዋል፡፡ ከዚያም ከ1965 እስከ 1971 ዓ.ም. ደረስ በውስጥ በሽታና ጋስትሮአንትሮሎጂ ትምህርት የካናዳ ሮያል ኮሌጅ የሐኪሞ ማኅበር አባል ለመሆን በቅተዋል፡፡ ቀጥሎም ከምድር ወገብ በታች በሚገኙ አገሮች የሚገኙ በሽታዎችን ከሚያጠናው ለንደን ውስጥ ከሚገኘው የለንደን ኃይጅንና ትሮፒል ሜዲሲን ማዕከል ከሁሉም የላቀ ተማሪ በመባል የፍሬዴሪክ መርጋትሮይድ ሽልማት አሸናፊ በመሆን በዲፕሎማ (ዲሲምቲ) ተመርቀዋል፡፡ እንዲሁም በ1991 ዓ.ም. በቫይሮሎጂ ጥናት ስዊዲን ከሚገኘው ከሉንድ ዩኒቨርሲቲ በፒችዲ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የመጀመርያውን የኤንዶስኮፒ ማዕከል አቋቁመዋል፡፡ ይህ ማዕከል እንደተቋቋመ ወዲያውኑ አያሌ ዶክተሮችና ነርሶች በኤንዶስኮፒ ሙያ እንዲሠለጥኑ አድርገዋል፡፡ ሥልጠናው አሁንም ቀጥሎ ይገኛል፡፡ ይልቁንም ይህ ሙያ በአሁኑ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ገጠር የሕክምና ማዕከሎችም ዘልቋል፡፡ ፕሮፌሰር እደማርያም ጎንደር የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ የሚገኘው የኢንዶስኮፒ ማዕከል እንዲሻሻልና አገልግሎቱን እንዲሰጥ በማድረጋቸው እነሆ በአሁኑ ጊዜ የጎንደር ከተማ ኗሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የወረዳና አውራጃ ኗሪዎችም ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሕክምና ትምህርት መስጠት የተጀመረው በውጭ አገር ዜጎች ነበር፡፡ በሙያቸው ብቃት የነበራቸው መሆኑ ቢታወቅም ቅሉ መምህራኑ ለአገሩ ቋንቋና ባህል ግን ባዕድ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆኑ መምህራንም ቢሆኑ ለሥልጠና መጀመርያ የሚሄዱት ወደ ውጭ አገር ነበር፡፡ ይህን ሁኔታ ለመቀየርና ኢትዮጵያን ለዘለቄታው ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ፕሮፌሰር እደማርያም የድኅረ ምረቃ ሥልጠና የሚሰጥ የሕክምና ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም በኢትዮጵያ እንዲቋቋም አደረጉ፡፡ ሌሎች በተመሳሳይ መልክ ለመደራጀት የሚፈልጉ የትምህርት ዘርፎችንም ዕርዳታቸውንና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

ከዚህም በላይ ጊዜያቸውን በምርምር ጥናት ላይ በማተኮር ስለ ጉበት በሽታ 37 የምርምር ጽሑፎች፣ ስለ አንጀትና ሆድ ዕቃ በሽታዎች 18 ጽሑፎች፣ እንዲሁም ከአንጀትና ሆድ ዕቃ ውጪ የሆኑ በሽታዎችን የሚመለከት 31 ጽሑፎች በዓለም አቀፋዊ መጽሔቶች በማሳተም ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በእነዚህ ሥራዎቻቸው ዓለም አቀፍ ዕውቅና አትርፈዋል፡፡ ከሌሎች የሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመተባበር ሌሎች ጽሑፎችንም አበርክተዋል፡፡ እንዲሁም በሙያቸው በቆዩበት ዘመን ሁሉ ወጣት ዶክተሮች የእሳቸውን የምርምርና ጽሑፍ ፈለግ እንዲከተሉ አጥብቀው ያበረታቱ ነበር፡፡

ፕሮፌሰር እደማርያም አገር ውስጥና ውጭ በሚገኙ አያሌ የሙያ ማኅበራትና የውይይት ክበቦች በአባልነት ተሳትፈዋል፡፡ በተለያዩ ኮንፈረንሶች በአባልነትና በአዘጋጅነት በመሳተፍ ያካበቱትን ልምድ ለሌሎች ወገኖች አካፍለዋል፡፡ ከዚህም በቀር ከኬንያና ከሱዳን የሕክምና ኮሌጆች ተመራቂ ለሆኑ ተማሪዎች የውጭ ፈታኝ በመሆን አገልግሎታቸውን አበርክተዋል፡፡

በተጨማሪም የሕክምና ሙያ ሥነ ምግባርን አስመልክቶ ግልጽነት ያለው መመርያ ለኢትዮጵያ ዶክተሮች አስፈላጊ መሆኑን ተረድተው የሥነ ምግባር ትምህርት ከመደበኛው የሕክምና ትምህርት ጋር እንዲካተት አድርገዋል፡፡ ይህ ትምህርት ለመጀመርያ ጊዜ በ1979 ዓ.ም. ሥራ ላይ እንዲውል ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ስለ በሽተኞች የምርመራ ሪፖርት አያያዝ በኪስ የሚያዝ መመርያ አዘጋጅተው በሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡ ይህን መመርያ የሕክምና ተማሪዎች አሁንም እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡

ክብሮች

ፕሮፌሰር እደማርያም የሚከተሉትን ክብሮችና ዕውቅናዎች አግኝተዋል፡፡ በአንደኛነት ማዕረግ ከለንደን ትሮፒካል ሜዲሲንና ኃይጂን ትምህርት ቤት ተመርቀዋል፣ የጎብኚ ሳይንቲስት የሚባል ሽልማት ከዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት፣ ጀኔቫ፣ ስዊትሰርላንድ አግኝተዋል፡፡ እጅግ የላቀ ሳይንቲስት ሽልማት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፣ የጥቁር ዓባይ ሜዳሊያ በሳይንስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ተሰጥቷቸዋል፣ እጅግ የላቀ አገልግሎት ለሰጠ ግለሰብ የሚሰጥ የፕሬዚዳንቶች ሽልማት በሚባል ስም የሚታወቅ ሽልማት ከሃሚልተን/ኦንታሪዮ የጤና ሳይንስ ማኅበር አግኝተዋል፣ በስማቸው የሚጠራ ሌክቸር በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

በአሜሪካ የሚገኘው የጎንደር ልማትና መረዳጃ ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት በማገልገላቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፣ በሕክምና ሙያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ከሐኪም ወርቅነህ መላኩ በያን የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ሐኪሞ ማኅበር ዕውቅና አግኝተዋል፣ በሕክምና ሙያ ፕሮፌሰር ከማክ ማስተር ዩኒቨርሲቲ፣ ሀሚልተን፣ ካናዳ የፕሮፌሰር ኤሜሪተስ ማዕረግ አግኝተዋል፣ በጤና አጠባበቅና በሕክምና ትምህርት ከፍተኛ አገልግሎት በኢትዮጵያና በካናዳ በማበርከታቸው የቢቂላ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡  

ፕሮፌሰር እደማርያም በአገልግሎት ዘመናቸው ብዙ ፈተናዎች አጋጥሟቸዋል፡፡ ይህንና ሀቀኛ፣ ትዕግሥተኛ፣ ትሁትና ከዓላማቸው ዝንፍ የማይሉ ሰው በመሆናቸው አብዛኛዎችን ፈተናዎች አሸንፈው አልፈዋል፡፡ እ.ኤአ. በ1994 ግን ባለሰቡት ሁኔታና ባልጠበቁት ጊዜ ወደ ጡረታ እንዲወጡ ተደርጎ ነበር፡፡

ሆኖም ፕሮፌሰሬ ሥራቸውንና አገልግሎታቸን ለማቋረጥ ዝግጁ አልነበሩም፡፡ ስለሆነም ከአገራቸው ወደ ካናዳ በማቅናት ለሰባት ዓመታት ኒው ፋውንድላንድ በምትገኘው ግራንድ ፎልስ ዊንዘር ከተማ በአስተማሪነትና በኢንርኒስትነት አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኒው ፋውንድላንድ ሳለሉ የሜሞሪያል ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፕሮፌሰር ነበሩ፡፡ ቀጥሎም ከ2001 ጀምሮ እስከ 2014 ድረስ ሃሚልተን ኦንታሪዮ በሚገኘው በማክማስተር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሆነው ሠርተዋል፡፡ በመጨረሻም በ2014 ጡረታ ወጥተዋል፡፡

ከ1999 እስከ 2004 እና ከ2006 እስከ 2008 የዕረፍት ጊዜያቸውን ወደ ጎንደር እየተመለሱ ለአንድ ወር ብቻ የሚዘልቅ ቆይታ በማድረግ በጎንደር የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ ከማስተማር በተጨማሪ ለምረቃ የተቃረቡ ተማሪዎች የሚሰጣቸውን የመጨረሻ ፈተና በውጭ ፈታኝነት ያገለግሉ ነበር፡ እንዲሁም ተማሪዎች በኢንዶስኮፒ እንዲሠለጥኑ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ጎንደር ውስጥ እንዲቋቋም ምክር ለግሰዋል፡፡

ጎንደር በሚቆዩበት ጊዜም ሆነ ከካናዳ ሆነው የሐኪም ቤቱ የመመርመርያ መሣሪያዎችና የጎንደር ኮሌጅ ሕንፃና ሆስፒታሉ የሚሻሻሉበትን ምክርና ዕርዳታ ይለግሱ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች አያሌ ግብዓቶችን እንደሚጎደሏቸው በመገንዘብ ለኒው ፋውድላንድ ሪጂናል የጤና ማዕከል የዕርዳታ ጥያቄ በማቅረብ ያገኟቸውን የአንስቲዚያ መሣሪያ፣ የልብ ትርታ መመርመርያ፣ የደም ትርታ መለኪያና የመማሪያ መጻሕትን ጨምሮ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችን ለጎንደር የሕክምና ኮሌጅ አድርሰዋል፡፡

ፕሮፌሰር በቅርቡ ስለአባታቸው ሕይወት ታሪክ አጭር መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ መጽሐፉ የአለቃ ፀጋን ቅኔዎች ያካተተ ሲሆን፣ መጽሐፉን ለኅትመት ለማብቃት የተለያዩ ምንጮችን ለረዥም ጊዜ ሲያሰባስቡ እንደነበር ያሳያል፡፡ መጽሐፉ መጀመርያ የታተመው በአማርኛ ቋንቋ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዕትም ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጎን ለጎን ተተርጉሟል፡፡

ምስክርነት

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ከበደ አሊ አያና በዕለቱ ለተገኙት ታዳሚዎች በሰጡት ምስክርነት ‹‹ፕሮፌሰር እደማርያም ፀጋ ታላቅ ሐኪም፣ ለታካሚዎች የቆሙና የሕክምና ምሳሌ ነበሩ፤››  ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡

ከአንደኛ ዓመት ሁለተኛ ሴሚስተር ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል ፐሮግራም በማዘጋጀት በቆዩበት ጊዜ የመማር ማስተማሩን ሥራ ሲያስተጓጉሉና ያለሪሰርች ፕሮጀክት አይተዋቸው እንደማያውቁ፣ በወቅታዊ ጉዳቶች ላይ ተመሥርተው እንደሚያስተምሩ፣ ሲያስተምሩ ደግሞ ተማሪው ይደክም እንደሆነ እንጂ እሳቸው እንደማይደክሙ፣ ወይም እንደማይሰለቻቸው፣ በአጠቃላይ ለተማሪው ዕውቀት እንዲሚጓጉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በዚያን ወቅት ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከመንግሥት የሚመደበው በጀት ለሠራተኛ ደመወዝ የሚውል ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሮፌሰር እደማርያም ባላቸው ኢንተርናሽናል ፓርትነርሺፕ ለምነው በሚያመጡት የገንዘብ ድጋፍ የሚያስገርም ደረጃ ያለው ሕክምና፣ የማስተማርያና ሪሰርች ፕሮጀክት ሲያካሂዱ ነበር፤›› ብለዋል ፕሮፌሰር ከበደ፡፡  

ፕሮጀክታቸውም ፋኩልቲውን የሚገነቡ ብዙ ነጥቦችን ያዘሉ እንደነበር፣ አስታውሰው ከተያዙትም ነጥቦች መካከል አዲስ አገልግሎት መጀመርና ያለውንም ማሻሻል ላይ ያተኮሩ እንደሚገኙባቸው አመልክተዋል፡፡      

 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ‹‹ከፕሮፌሰር እደማርያም ፀጋ የምንማረው ነገር ቢኖር በምንኖርበት ጊዜ ውስጥ ለትውልድ የሚተላለፈው ቋሚ ሥራ መሥራትን፣ ሕክምና ፍቅር፣ ትዕግሥትና የሰውን ልጆች መውደድ ወይም ለሰው ሕይወት ፍቅርና አክብሮት መስጠትንና ከፍቅር ውጪ የማይሆን መሆኑን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር እደማርያም በሕይወት ዘመናቸው ጠዋት ለሁለት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ሥራ ላይ ተሰማርተው እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት ድረስ ለታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት ከሰጡና ለተተኪው ሐኪም ሥራዎቻቸውን አንድ በአንድ ካስረከቡ በኋላ በአግባቡ እንደሚወጡ መረዳታቸውን አፈ ጉባዔ አባዱላ አመልክተው፣ ይህም የሙያ ግዴታቸውን በብቃት መወጣታቸውን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅር ሁሉ እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...