በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና በቀለመወርቅ ትምህርት ቤት በስተጀርባ (ሰሜን ማዘጋጃ) የሚገኘው፣ በተለምዶ ዶሮ ተራ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም በደረሰ የእሳት ቃጠሎ የንግድ መደብሮች ወደሙ፡፡ የአደጋው መንስዔና እሳቱ ያደረሰው የንብረት ውድመት ግምት አለመታወቁን፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠርና መከላከል ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከሰዓት በኋላ በግምት አሥር ሰዓት አካባቢ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ በ11፡30 ሰዓት ላይ መቆጣጠር መቻሉንም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ እሳቱ በተከሰተበት በግምት 200 ካሬ ሜትር ስፋት ይኖረዋል በተባለው ቦታ ላይ የተለያዩ ግብይቶች የሚደረጉ ሲሆን፣ በተለይ በበዓላት ወቅት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መዳረሻ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ባለሥልጣኑ ሰባት የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎች በማሰማራት፣ በሁለት ቦቴዎች ውኃ በማቅረብና 48 ሠራተኞች በማሰማራት እሳቱ ወደ ሌላ እንዳይዛመት መደረጉንም አቶ ንጋቱ ገልጸዋል፡፡