Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየሊዝ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢገባም እስካሁን ውይይት አልተደረገበትም

የሊዝ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢገባም እስካሁን ውይይት አልተደረገበትም

ቀን:

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገውን አዋጅ ቁጥር 721/2004 በድጋሚ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ ከወራት በፊት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢቀርብም፣ ምክር ቤቱ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመጠመዱ እስካሁን እንዳልመከረበት ምንጮች ገለጹ፡፡

በኅዳር 2004 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ፣ በመላ አገሪቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው ይህ የሊዝ አዋጅ፣ በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአዋጁ ላይ የሚያነሱትን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ባለሙያዎች አሰማርቶ አዋጁን መርምሯል፡፡ ሚኒስቴሩ በተጨማሪ የኦዲት ምርመራ ያካሄደ ሲሆን፣ በዚህም በአፈጻጸም ወቅት ክፍተቶች መኖሯቸውንና ሊካተቱ ይገባቸው የነበሩ አንቀጾች መኖራቸው በመረጋገጡ አዋጁ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡

- Advertisement -

በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብዙዓለም አድማሱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ከሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ጠቃሚ አስተያየቶች ተካተው አዋጁን እንዲያፀድቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል፡፡

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢቀርብም፣ እስካሁን ውይይት ተደርጎበት ባለመፅደቁ ምክንያት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊመራ አልቻለም፡፡

‹‹በወረፋ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ገና አልተወያየበትም፤›› ሲሉ አቶ ብዙዓለም ገልጸዋል፡፡

በተሻሻለው ሊዝ አዋጅ ከተካተቱ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚጠብቃቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል፣ በአንድ ግቢ የግልና የቀበሌ ቤት ተካተው በሚገኙበት ወቅት መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑ፣ ዋጋ የሚያንሩ የመሬት ሊዝ ተጫራቾችን ለመቆጣጠር መፍትሔ ያበጀ መሆኑ፣ ለተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የማያስፋፊያ መሬት የሚፈቅድ መሆኑ፣ እስካሁን ግልጽ ባይሆንም አገልግሎት መስጫ ተቋማት መሬት በድርድር ማግኘት የሚችሉበት ተስፋ መያዙ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት በአንድ ግቢ ውስጥ የቀበሌ ወይም የመንግሥት ቤቶች ሲገኙ፣ ለማናቸውም ማልማት የሚያስችል መፍትሔ አልተቀመጠም ነበር፡፡ በማሻሻያው ግን የግለሰቡ ወይም የቀበሌ ይዞታ አብላጫው መሬት የያዘ ከሆነ ወደ አንዱ እንዲጠቃለል ተደርጓል፡፡

የሊዝ ጨረታ በሚወጣበት ወቅት ማልማት አለማልማታቸው የማይታወቅ ግለሰቦች፣ የመሬቱን ዋጋው ከሚገባው በላይ በማናር በርካታ ቦታዎችን ሲይዙ ቆይተዋል፡፡ በአዲሱ ማሻሻያ አንድ ተጫራች ሁለት ቦታዎች አሸንፎ ሙሉ ግንባታውን ሳያጠናቅቅ ለሦስተኛ ወገን ካስተላለፈ፣ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በጨረታ እንዳይሳተፍ ይከለክላል፡፡ ከዚሁ ጋርም በምደባ (ድርድር) የሚሰጡ ቦታዎች ላይ ደግሞ ፕሮጀክቱን ለማካሄድ ከሚያስፈልገው በጀት ውስጥ 25 በመቶ በባንክ ዝግ ሒሳብ እንዲገባ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩልም አንድ የተጠናቀቀ ፕሮጀክት የሚያስፈልገው ቦታ በሚጠይቅበት ወቅት በሊዝ አዋጅ እንዳይስተናገድ ተደንግጎ ነበር፡፡ በአሁኑ ማሻሻያ ግን የማስፋፊያ ቦታ ተፈቅዷል፡፡ ይኼ ማሻሻያ እናለማለን ብለው በሚጠብቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ ቢሆንም፣ መንግሥት በገጠመው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በዚህ ጉዳይ ላይ ለመምከር ጊዜ እንዳጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...