Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምተስፋ የተጣለባቸው የደቡብ አፍሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፈተናዎች

ተስፋ የተጣለባቸው የደቡብ አፍሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፈተናዎች

ቀን:

ደቡብ አፍሪካ ጨቋኝና ዘረኛ ከነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ ከተላቀቀች 23 ዓመታት የሞላት ሲሆን፣ አገሪቱን ለመምራት ሲሪል ራማፎዛን አራተኛ ፕሬዚዳንቷ አድርጋ መርጣለች፡፡ ዓርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ራማፎዛ አገሪቱን ለመምራት ከኔልሰን ማንዴላ፣ ከታቦ ምቤኪና ሥልጣናቸውን በግፊት ከለቀቁት ከጃኮብ ዙማ በመቀጠል አራተኛ መሪ ይሆናሉ፡፡

በፓርቲያቸው ኤኤንሲ የበላይነት በተያዘው ፓርላማ ራማፎዛ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ ሲታወጅ፣ እርሳቸውን እጅ ያስነሳ የሙገሳ መዝሙር በፓርላማው ተሰምቶ ነበር፡፡

በጃኮብ ዙማ የሥልጣን ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የቆዩትና በቅርቡ በተደረገ ምርጫ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ራማፎዛ፣ ጃኮብ ዙማ ከሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ ሲገፋፉ ከነበሩ ግለሰቦች አንዱ ናቸው፡፡ ዙማም ሥልጣን መልቀቃቸውን ይፋ ካደረጉና እርሳቸውም የፕሬዚዳንትነታቸውን ዙፋን ከተቆናጠጡ በኋላ፣ ለዙማ የስንብት የራት ግብዣ ለማድረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተስፋ የተጣለባቸው የደቡብ አፍሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፈተናዎች

 

ፓርላማው በደስታና በጭብጨባ የእርሳቸውን ፕሬዚዳንትነት ይቀበለው እንጂ፣ ራማፎዛ የሚጠብቃቸው ወንበር ግን ከፍተኛ ፈተና ያለበት እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

የመጀመርያው ዕርምጃቸው የመንግሥትን መዋቅርና አደረጃጀት ማስተካከል እንደሆነ በፓርላማ የመጀመርያ ንግግራቸው ያስታወቁት ፕሬዚዳንት ራማፎዛ፣ የካቢኔ ምርጫ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ፍንጭ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

‹‹ያለፉ መቃቃሮችን ወደ ኋላ እንተዋቸው፤›› ያሉት ራማፎዛ፣ ‹‹አዲስ ቀን በደቡብ አፍሪካ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡ አዲሱ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት አዲስ ቀን መምጣቱን ቢያበስሩም እንኳን፣ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ተራራ ትልቅ ስለሆነ ፈተናቸው ከባድ ነው የሚሉ አልጠፉም፡፡

የመጀመርያውና ዋነኛው ፈተናቸው ሙስናን መዋጋት ነው፡፡ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ዙማ በእጅጉ በሙስና የሚታሙ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥትን ሀብት ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ እንደሆኑ በተከታታይ የቀረቡባቸውና ፍርድ ቤት የደረሱ ክሶቻቸው ያመለክታሉ፡፡

ተስፋ የተጣለባቸው የደቡብ አፍሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፈተናዎች

 

ይሁንና ይኼንን የጎደፈ ወንበር ማፅዳት የአዲሱ ፕሬዚዳንት ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

‹‹በመንግሥት ተቋማት የሚታየውን የሙስና መንሰራፋት ጠራርገን ለማጥፋት ቆርጠን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ይኼንንም በዚህ ዓመት ነው ማድረግ ያለብን፤›› ብለዋል፡፡

ሆኖም እንዴት የሚለው ጥያቄ መልስ አላገኘም፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ እጅግ ከፍተኛ ሀብት ያላቸውና የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ የሆኑ ግለሰቦች የሙስናው ተሳታፊዎች በመሆናቸውና የሙስና ደላሎች በመንሰራፋታቸው፣ የሙስና ትግሉን ከባድ ያደርግባቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

ቀጣዩ ለራማፎዛ ፈተና ይሆንባቸዋል የሚባለው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከውድቀት ማዳን ነው፡፡ ብዙዎቹ በተለይም እንደ አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ኤስኮም ያሉ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት በገንዘብ ዕጥረት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ እንደ ኤስኮም ያሉ ተቋማትን አዲስ ቦርድ በመሰየም መታደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሌላው የፕሬዚዳንቱ ፈተና እንደ አፍሪካ ሪዘርቭ ባንክ መረጃ ከ150 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆነው የአገሪቱ የውጭ ዕዳና ከ20 ቢሊዮን ዶላር የዘለለው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር ነው፡፡ ለዚህም ፕሬዚዳንቱ የበጀት ማስተካከያ በማድረግና የበጀት ጉድለቱን በማስተካከል ይኼንን ችግር ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሆኖም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 4.3 በመቶ የደረሰው የአገሪቱ የበጀት ጉድለት ከፍተኛ ፈተና ጋርጦባቸዋል ይባላል፡፡

ተስፋ የተጣለባቸው የደቡብ አፍሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፈተናዎች

 

የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ የቁልቁለት ጉዞ ሌላው የአዲሱ ፕሬዚዳንት ፈተና እንደሚሆን እየተገለጸ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ምንም እንኳን መነቃቃት እያሳየ ቢሆንም፣ የምንዛሪ መጠን በእጅጉ አናሳ በመሆኑ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ይነገራል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2017 26.7 በመቶ የደረሰው የአገሪቱ የሥራ አጥነት ምጣኔ መፍትሔ የሚያሻውና የማዕድን ዘርፉን በመደገፍና በማነቃቃት የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚያስፈልግ ለዚህም ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ ያለባቸው ራማፎዛ እንደሆኑ እየተነገረላቸው ነው፡፡ የውጭ አገር ባለሀብቶችም በደቡብ አፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ እያስተላለፉ ያሉት ራማፎዛ፣ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የወጣቶች የሥራ አጥነት ምጣኔ ደግሞ 68 በመቶ መድረሱም የሚጠብቃቸው ፈተና በእጅጉ ከባድ እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡

ከእነዚህ ሁሉ በልጦ ግን የፕሬዚዳንቱን ቆይታ ፈታኝ ያደርገዋል የሚባልለት ጉዳይ የፓርቲያቸውን አንድነት መጠበቅና የወጣት ፖለቲከኞችን እምነት ማግኘት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ወጣት ፖለቲከኞች ተስፈኞችና ለውጥ ፈላጊዎች እንደሆኑና ጥፋትንና ቂመኝነትን ታግሰው እንደማይቆዩ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው የድጋፍ መሠረት ሳይናወጥ እንዲቆይ ማድረግ አንዱ ከፍተኛ ፈተና ነው፡፡ ፓርቲው እስካሁን በተቃዋሚዎች የመሸነፍ ፈተና ባይገጥመውም እንኳን፣ ለወደፊት በምርጫ ውጤቶች የተነሳ የጥምር መንግሥት ለመፍጠር ሊገደድ ይችላል የሚሉም አሉ፡፡

ተስፋ የተጣለባቸው የደቡብ አፍሪካ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፈተናዎች

 

ጃኮብ ዙማ ሥልጣናቸውን ከመልቀቃቸው በፊት ቃል ገቡትን የሦስተኛ ደረጃ ትምህርትን ነፃ የማድረግ ጫናም አለባቸው፡፡ ራማፎዛ ይህን ለማድረግ የቁርጠኝነት ችግር ሳይሆን የሚገጥማቸው፣ የበጀት ችግር ዋነኛ መሰናክል ይሆንባቸዋል ነው የሚባለው፡፡

‹‹የበጀት ጉድለቱን ለማስተካከል፣ ዕዳችንን ለማቃለልና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ጤናማ እንዲሆኑ ለማስቻል ጠንካራ ውሳኔዎች መወሰን ይገባናል፤›› ሲሉም ራማፎዛ የሚጠብቋቸውን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የአዲሱን ፕሬዚዳንት ስኬት ጊዜ የሚፈታው ሆኖ ሳለ በርካታ ባለሀብቶች፣ ፖለቲከኞችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ፕሬዚዳንቱን ለውጥ ያመጣሉ በማለት ተስፋ ጥለውባቸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...