[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተርን ሆቴል ቀጥረው እየጠበቁት ነው]
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር አረፈድኩኝ አይደል?
- አሥራ አምስት ደቂቃ እኮ አስቀመጥከኝ፡፡
- መንገድ ተዘጋግቶብኝ ነው፡፡
- በሌለኝ ሰዓት ከየት አመጣዋለሁ፡፡
- በጣም ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ ከውጭ እንግዶች መጥተውብኝ ነው፡፡
- የምን የውጭ እንግዳ?
- አገራችን ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉ ናቸዋ፡፡
- በዚህ ወቅት አገራችን ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች አሉ?
- አይ ያው ለረዥም ጊዜ ስንነጋገርበት የነበረና ሲጠና የነበረ ፕሮጀክት ነው፡፡
- አሁንም ኢንቨስተሮች በመንግሥታችን ላይ እምነት አላቸው ማለት ነው?
- በሚገርም ሁኔታ እኛም ይኼንኑ ነበር ስንወያይ የነበረው፡፡
- እና እዚህ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ?
- አሁን አሁን እንኳን እነሱን ማሳመን እየከበደኝ ነው፡፡
- ምኑ ነው የከበደህ?
- እዚህ ኢንቨስት ማድረግ አይፈልጉም፡፡
- ለምን?
- ይኸው ሦስት ዓመት ሙሉ ብጥብጥ ስለነበር እምነታቸውን አጥተዋል፡፡
- ለዚህች አገር እኮ ይኼ የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ዋነኛ ችግር እየሆነ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እነዚህ ሰዎች ለአገሪቱ ምን ያህል ጥቅም ያለው ፕሮጀክት ነበር ያሰቡት፡፡
- ምን ታደርገዋለህ?
- ባይገርምዎት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ከሁለት ኢንቨስተሮች ጋር ለመሥራት ተስማምተን እንደዚሁ ፈረሰብኝ፡፡
- ምን ትቀልዳለህ?
- በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ሥራ ሊጀምሩ አስበው በፀጥታው ሁኔታ ተደናግጠው ነው የሄዱት፡፡
- እነሱ እንኳን አይጠቅሙንም፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እኛ ቱሪስት ኢንቨስተር አንፈልግም፡፡
- ምን ማለት ነው?
- በየአገሩ እየዞሩ ይጠቅመኛል አይጠቅመኝም ብለው የሚሠሩትን ሳይሆን የምንፈልገው ከእኛው ጋር ሁሉን ነገር የሚጋፈጡትን ነው፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እንደዚህ ዓይነቶቹ ኢንቨስተሮች በየቀኑ ነው እኔ ጋ ቢመጡም ፊት አልሰጣቸውም፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- እነዚህ ወዲያው በልተው ወዲያው መጥፋት ነው የሚፈልጉት፡፡
- ታዲያ ምን ዓይነቶቹን ነው እኛ የምንፈልጋቸው?
- ከእኛ ጋር በችግሩም በደስታውም ጊዜ የሚሆኑትን ነዋ፡፡
- አሁን እኮ ደስታ የሚባል ነገር ጠፍቶ ይኸው ለሦስት ዓመት ችግር ነው የሰማነው፡፡
- አየህ ሊነጋ ሲል ይጨልማል ስለሚባል ለዚያ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎን በሚኒስትርነት አውቅዎታለሁ፣ በኢንቨስተርነት አውቅዎታለሁ፣ በነብይነት ግን አላውቅዎትም፡፡
- ከአንተም ጋር ተደፋፈርን ማለት ነው?
- ኧረ እኔ ለጨዋታ ነው፣ እኔ ለነገሩ ችግር የለብኝም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ዛሬ ከኢሕአዴግ ጋር እንደ ሠራሁት፣ ነገም ሌላ ከመጣ ከእሱም ጋር መሥራት አይከብደኝም፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት እንደዚህ ልታስብ ትችላለህ?
- ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ እኮ ነጋዴ ነኝ፡፡
- በዚህ ሥርዓት አይደለም እንዴ ከአፈር ተነስተህ እዚህ የደረስከው?
- እሱንማ አልክድም ክቡር ሚኒስትር፣ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡
- ታዲያ እንዴት ከሌላ መንግሥትም ጋር ቢሆን መሥራት እችላለሁ ትላለህ?
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ዝግጁ ነኝ ስላሉ እሱንም ማሰቡ አይከፋም ብዬ ነዋ፡፡
- እኔማ መቼ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን ተቃወምኩ?
- እና ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ዝግጁ ነዎት?
- በሚገባ እንጂ፣ እኔን ያስፈራኝ ሌላኛው ሽግግር አይኖርም ብዬ ነው፡፡
- ሌላኛው ሽግግር ምንድነው?
- ሰላማዊ የሀብት ሽግግር!
[አንድ በውጭ የሚኖር ተቃዋሚ ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የእኛ ኪራይ ሰብሳቢ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በቃ አበቃላችሁ እኮ፡፡
- ምኑ ነው ያበቃው?
- ተበላችሁ እኮ፡፡
- ምኑን ነው የተበላነው?
- ቁማሩን ተበላችሁ፡፡
- ምን እያወራህ እንደሆነ አልገባኝም?
- ይኸው ሕዝቡ እስረኛ አስፈታችሁ፣ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያስቀይራችሁ ነው፡፡
- እናንተ ለዚህ ነው ይህችን አገር ለመምራት ብቃቱም፣ አቅሙም የላችሁም የምንለው፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እኛ እኮ እስረኞቹንም ለመፍታት ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲወርዱ ከተስማማን ቆየን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እጃችሁን ተጠምዝዛችሁ እንጂ ተስማምታችሁ አይደለም፡፡
- ስነግርህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን መልቀቅ ከፈለጉ ቆይተዋል፤ እኛ እስክንተካቸው ነበር የቆዩት፡፡
- እናንተማ መቼም እንደማታምኑ አውቃለሁ፡፡
- ስማ ምንም ይፈጠራል ብለህ እንዳታስብ፡፡
- እሱንስ እንኳን ይተውት፡፡
- ማለት?
- እኔ አሁን ጮቤ እየረገጥኩ ነው፡፡
- ለምኑ?
- በቃ ክቡር ሚኒስትር አብቅቶላችኋል፣ እኔም ሻንጣዬን እያዘጋጀሁ ነው፡፡
- ምን ለማድረግ?
- አገሬ ለመግባት ነዋ፡፡
- እስቲ አታስቀኝ?
- ይኸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይኖራል እያሉ አይደል እንዴ?
- ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ፡፡
- አገሬ መግባቴ አይቀርም ስልዎት፡፡
- ለነገሩ ይኼንን ማሰቡ አይከፋም፡፡
- እንዴት?
- አንድ ቀን አገራችሁ ትገቡ ይሆናል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ውስጥዎት ያውቀዋል በቅርቡ መሆኑ አይቀርም፡፡
- በነገራችን ላይ አሜሪካ ጥሩ ቤት አለህ አሉ፡፡
- እሱንም ትቼው እምጣለሁ፡፡
- እኔም እዚህ ጥሩ ቤት ስላለኝ አንድ ነገር አስቤ ነበር፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ብንቀያየር ብዬ ነዋ፡፡
- ምኑን?
- ቤታችንን!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል]
- ክቡር ሚኒስትር ተቸገርን እኮ፡፡
- ምንድነው የተቸገርከው?
- ምንም ሥራ መሥራት አልተቻለም፡፡
- ምን ሆንክ ደግሞ?
- አንዴ መንገድ ተዘግቶ አገር ይታመሳል፡፡
- ምን ይኼ አዲስ ነገር ነው?
- ሰላም ነው ብለን ደግሞ ሥራ ስንጀምር በድጋሚ ይታመሳል፡፡
- ታዲያ ምን ይጠበስ?
- መንግሥት ምን እየሠራ ነው?
- ሥራውን እየሠራ ነዋ፡፡
- ይኸው ንግዱም ቆሟል፣ ሁሉም እንቅስቃሴ ቆሟል፡፡
- ስማ እኔም ንግዱ ውስጥ ስላለሁ ሁሉን ነገር ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡
- ታዲያ ትንሽ አይቆጭዎትም?
- ለዚያ አይደል እንዴ መፍትሔ ለማምጣት ጠብ እርግፍ እያልን ያለነው፡፡
- ግን ምንም ዓይነት መሻሻል እያየን አይደለም፡፡
- እንቅልፍ አጥተን ነው እየሠራን ያለነው፡፡
- የሚመስለው ግን አውቃችሁ የተኛችሁ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ብትቀሰቀሱ አልሰማም አላችኋ?
- ሰውዬ ልትጨቀጭቀኝ ነው የደወልከው?
- እሱማ አንድ ጉዳይ ነበረኝ፡፡
- የምን ጉዳይ?
- በአካል ተገናኝተን ነው ማውራት ያለብን፡፡
- ጫፉን ንገረኛ?
- መሬት የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ፡፡
- በዚህ ጊዜም መሬት እየደለልክልኝ ነው?
- እንዲያውም ማጧጧፍ ያለብን በዚህ ወቅት ነው፡፡
- ለምን?
- ነገ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅማ፡፡
- በቃ ይኸው ነው ጉዳይህ?
- በዚያውም እንኳን አደረሰዎት ለማለት ነው?
- ፋሲካ ገና አይደል እንዴ?
- ኧረ ለዓመታዊው በዓላችን ነው፡፡
- ለምኑ?
- ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የፓርቲ ስብሰባ ውስጥ ናቸው]
- ክቡር ሚኒስትር በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቅ ምን ያስባሉ?
- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ትክክል ነው ባይ ነኝ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ሌሎቻችንም እንደ አርዓያ ልንከተለው የሚገባ ነዋ፡፡
- ይኼ ነው ሐሳብዎ?
- ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ሌላ ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የሚተካቸው ሰው ማን መሆን አለበት የሚለው ነዋ፡፡
- እርስዎ ማን ይተካቸው ይላሉ?
- ሕዝቡ እውነተኛ ለውጥ ነው የሚፈልገው፡፡
- እሱማ ትክክል ነው፡፡
- ስለዚህ በእኔ አስተያየት ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከእሳቸው የሚያጥር መሆን አለበት፡፡
- ምን?
- ከዚያም ባለፈ መነጽር የማያደርግ ቢሆን ይሻላል፡፡
- አበዱ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሕዝቡ እውነተኛ ለውጥ ነው የሚፈልገው ስላችሁ?
- እና ይኼ ነው እውነተኛ ለውጥ ለእርስዎ?
- ከቁመናው ባሻገር ራሰ በረሃ ሆኖ የደም ግባት ቢኖረው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
- ቀጥለው እኔን ምረጡኝ እንዳይሉ?
- ኧረ በፍጹም፡፡
- የሚመረጠው ሰው እኮ ለቁንጅና ውድድር አይደለም የሚፈለገው?
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- የሚመረጠው ሰው አገሪቷን ከገባችበት ቀውስ ሊያወጣት የሚችል መሪ መሆን አለበት፡፡
- ለዚያ ነው እኮ ሰውየው እነዚህን ነገሮች ማሟላት ያለበት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ስለጤነኝነትዎ እየተጠራጠርን ነው፡፡
- እንግዲህ መስማማት ካልቻልን አንድ አስታራቂ ሐሳብ ላቅርብ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የሚፈለገው መሪ ኢትዮጵያን ወደ አንድነት የሚያመጣ መሆን አለበት፡፡
- ለዚያ አይደል እንዴ እየተወያየን ያለነው፡፡
- ስለዚህ በጋዜጣ ማውጣት ነዋ፡፡
- ምንድነው የምናወጣው
- የሥራ ማስታወቂያ!