ባለፈው ግንቦት ወር መገባደጃ ላይ በአሜሪካኗ ዩጂን ከተማ ያሳካችውን የዳይመንድ ሊግ የ500 ሜትር ሩጫ ድሏን ባለፈው ሐሙስ (ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም.) በኖርዌይ ኦስሎ የደገመችው ገንዘቤ ዲባባ በታላቅ እህቷ ጥሩነሽ ዲባባ በ2000 ዓ.ም. በዚሁ ስታዲየም የተመዘገበውን የ14 ደቂቃ ከ11.15 ሰከንድ ሪከርድ ልታሻሽል አልቻለችም፡፡
ከ1,500 በላይ ኢትዮጵያውያን በኦስሎው ግዙፉ ስታዲየም ተገኝተው የ24 ዓመቷን ገንዘቤን ቢያበረታቱም ውድድሩን 14 ደቂቃ 21.19 ሰከንድ በአንደኝነት ከመፈጸም ባሻገር በውድድሩ ዋዜማ የታላቅ እህቷን ሪከርድ ልትሰብር የመሻቷን ግብ ግን ሳታሳካ ቀርታለች፡፡
በ10 ሰከንድ ዘግይታ የፈጸመችውን ገንዘቤን ተከትላ የገባችው የአገሯ ልጅ ሰንበሬ ተፈሪ ስትሆን ኬንያዊቷ ቪዮላ ኪቢዎት ሦስተኛ ሆናለች፡፡ ከዚህ ቀደም የቢዝሌት ጌምስ በመባል ይታወቅ የነበረውን ውድድር የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት ለማድመቅ በኦስሎ ስታዲየም የታደመው ተመልካች ቁጥር ከፍተኛ በነበረበት ዕለት ውድድሩን በአሸናፊነት የተወጡት አትሌቶች የላቀ የደስታ ስሜት እንደተሰማቸው ተዘግቧል፡፡
የኦስሎው ስታዲየም ከሰባት ዓመታት በፊት ገንዘቤን ከታላላቆቿ ጥሩነሽና እጅጋየሁ ጋር በአንድ የፉክክር መድረክ ያጋጠመ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ገንዘቤ በኦስሎው ስታዲየም የምታደርገውን ውድድር በተለየ መልኩ እንድትጠብቀው እንዳደረጋትም ተዘግቧል፡፡ በውድድሩ ዋዜማ በጥሩ ብቃት ላይ መገኘቷንና የኦስሎ የአየር ንብረትም ጥሩ መሆኑን ከግምት በማስገባት የእህቷን ሪከርድ ልታሻሽል እንደምትችል የገለጹ ቢሆንም ገንዘቤ አሁንም የጥሩነሽን የ5,000 ሜትር ርቀት ክብረወሰን ለመስበር ጊዜ እንደሚወስድባት ተገልጿል፡፡
ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠችው መግለጫ ‹‹ክብረወሰኑን ለመስበር ከፍተኛ ጥረት ባደርግም አሯሯጮቹ እንደምፈልገው አልሆኑልኝም፤›› ያለችው ገንዘቤ፣ ቅዝቃዜውና ነፋሱ የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም ውድድሩ ለኔ ጥሩ ነበር ብላለች፡፡
ዓምና በዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓመቱ ምርጥ ሽልማት ላይ በሞናኮ ከተማ ገንዘቤ እንደተናገረችው በ2015 ልታሳካው ያቀደችው ግብ ቢኖር የታላቋን ጥሩነሽ ዲባባን 5,000 ሜትር ክብረወሰን ማሻሻል እንደሆነ መናገሯ አይዘነጋም፡፡ ገንዘቤ በመጀመሪያው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ3,000 ሜትር ማሸነፏና በዩጂን በተከናወነው ሦስተኛ ውድድር በ5,000 ሜትር በ14 ደቂቃ 19.76 ሰከንድ በሆነ ጊዜ የራሷን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
ባለፈው ግንቦት በቻይናው ሻንጋይ ከተማ በተካሄደው ሁለተኛው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ5,000 ሜትር የዓለም ሦስተኛው ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና በኦሰሎው ውድድር አልተካፈለችም፡፡
ከጥሩነሽ ዲባባ (14፡11.15) እና መሠረት ደፋር (14፡12፡88) ቀጥሎ ለታሪክ ሦስተኛው የ5,000 ሜትር ፈጣን ሰዓት ግንቦት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በአስደናቂ ብቃት ያሸነፈችው አልማዝ የፈጸመችበት ጊዜ 14 ደቂቃ 14.32 ሰከንድ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በወንዶች ምድብ እስካሁን በተካሄዱት ውድድሮች ዮሚፍ ቀጀልቻ በ5,000 ሜትር፣ መሐመድ አማን በ800 ሜትር፣ ሐጎስ ገብረሕይወት በ3,000 ሜትር፣ በሴቶች ምድብ ዳዊት ሥዩም በ1,500 ሜትር ማሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡
የዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ በዶሃ ግንቦት 7 ቀን የተጀመረ ሲሆን እስከ ጳጉሜን 6 ቀን ድረስ በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳል፡፡ እስክ ሰኔ 6 ቀን ድረስ የተከናወኑት በዶሃ፣ ሻንጋይ፣ ዩጂን፣ ሮም፣ በርሚንግሃም፣ ኦስሎና ኒውዮርክ ሲሆን ስምንተኛው ውድድር በፓሪስ ሰኔ 27 ቀን እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
የምንጊዜም የሴቶች 5,000 ሜትር የዓለም ምርጥ ጊዜ
ተ.ቁ. |
አትሌት |
ጊዜ |
ከተማ |
ዓመት |
|
ጥሩነሽ ዲባባ |
14፡11.15 |
ኦስሎ |
29/09/2000 |
|
መሠረት ደፋር |
14፡12.88 |
ስቶክሆልም |
15/11/2000 |
|
አልማዝ አያና |
14፡14.32 |
ሻንጋይ |
09/09/2007 |
|
መሠረት ደፋር |
14፡16.63 |
ኦስሎ |
08/10/1999 |
|
ገንዘቤ ዲባባ |
14፡19.76 |
ዩጂን |
22/09/2007 |
|
ቪቪያን ቼሪዮት(ኬንያ) |
14፡20.87 |
ስቶክሆልም |
22/11/2003 |