Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርየኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን እየለበለበው ነው

የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን እየለበለበው ነው

ቀን:

የሪፖርተርን ርዕሰ አንቀጽ ሳነብ ብዕሬን እንዳነሳ ገፋፋኝ፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት በርካታ ጠንካራ ጎኖች አሉት፡፡ ለምሳሌ የፀጥታ አጠባበቁ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታው ወዘተ. ሊጠቀስለት ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በዕለት ኑሮው የሚያጋጥመውን አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጥ ችግር መንግሥት ሙሉ በሙሉ ባይፈታውም ማቃለል ይችላል፡፡ ዝም ብሎ ማየቱ ግን ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡

ለምሳሌ ግለሰቦች ያለአግባብ የሚጨምሩትን የቤት ኪራይ መከታተልና ሥርዓት ማስያዝ ወይም እንደ መንግሥት ቤት አግባብ የሆነ ተመን መንግሥት አውጥቶ ቀበሌ እንዲከታተለው ማድረግ ይቻላል፡፡

አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለባት ለአገር የማይጠቅሙ እንደ ውስኪ ያሉ ሸቀጦችና የመሳሰሉት ወደ አገር እንዳይገቡ ለጊዜው በመከልከል፣ በአንፃሩ በቂ የምግብ ዘይትና ሌላም ጠቃሚ የፍጆታ ዕቃ ማስገባት ይችላል፡፡

- Advertisement -

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጀት እንዳይቃጠል በማለት የሚፈጽሙት አላስፈላጊ ግዥ የውጭ ምንዛሪን የሚጎዳ በመሆኑ ማስቆም ቢቻልና ከአገር ውስጥ አምራቾች የሚገዛው ቢገዛ፣ የውጭ ምንዛሪን ማዳን ብቻም ሳይሆን ሥራ አጥነትንም ይቀንሳል፡፡

ሕዝቡ በተለይም ብዙ ቤተሰብ የሚያስተዳድረው ክፍል እንደ እሳት እየተለበለበ መንግሥት ነገሮችን ማርገብና መቆጣጠር ካልቻለ፣ አማራሪውም ከበዛ መጨረሻው አብዮት መፈንዳት ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ የ1953ቱና የ1966ቱ የባለሥልጣናት እልቂት እንዳይመጣ እሰጋለሁ፡፡

(ዳንኤል ወልዱ፣ ከአዲስ አበባ)

*********

አሽከርካሪዎችን ለክፍያ የሚያስገድድ ደንብ አልወጣም

እሑድ ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር አማርኛ ጋዜጣ ‹‹አሽከርካሪዎች ለሚጠቀሙበት መንገድ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ አዋጅ ወጣ፤›› በሚል ርዕስ በአገሪቱ በሥራ ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎች ለሚጠቀሙበት መንገድ ማደሻ የሚውል ክፍያ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ መፈጸም እንዳለባቸው ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠቱን በማተት መዘገቡ ይታወቃል፡፡

ጋዜጣው ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው ዕትሙ ለዘገባው የመረጠው ርዕስ አሽከርካሪዎች ለሚጠቀሙበት መንገድ ክፍያ እንደሚፈጽሙ የሚያስገድድ ደንብ በመንግሥት እንደወጣ የሚያሳይ ነው፡፡

በመሠረቱ በክብደት ላይ የተመሠረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ደንብ ቁጥር 340/2007 አስመልክቶ፣ ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም.  በግዮን ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ፣ በአገሪቱ የነበሩና በአዲስ መልክ የሚገነቡ መንገዶች በየጊዜው እየጨመሩ በመሄዳቸው የተነሳ፣ ተሽከርካሪዎች ጉዳት የሚደርስባቸው በመሆኑ መንገዶችን በአግባቡ ለመንከባከብና ለመጠገን የሚያስችል አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ለመፍጠር፤ ዋነኛ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ መፈጸም ይኖርባቸዋል የሚል ነው፡፡ ክፍያውም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በትራንስፖርት ባለሥልጣን አማካይነት መኪኖች ዓመታዊ የተሽከርካሪ ብቃት ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት እንደሚገለጽም ተገልጿል፡፡

ስለሆነም መንግሥት ባወጣው በክብደት ላይ የተመሠረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ ደንብ ቁጥር 340/2007 ላይ፣ አሽከርካሪዎችን ለክፍያ የሚያስገድድ ምንም አንቀጽ ያልተካተተበት መሆኑ ታውቆ በደንቡ የተቀመጡ ክፍያዎችን የሚመለከተው ዋነኛ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑትን የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ስለሆነ በርዕሱ ላይ ተገቢው የዕርማት ማስተካከያ እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

(የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን)

********

የአዳማ ችግሮች በአፋጣኝ ይወገዱ

 በአገራችን አሉ ከሚባሉ ከተሞች አዳማ አንዷ ናት፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኦሮሚያ  ክልላዊ መንግሥት ለኦሮሚያ ከተሞች ዕድገት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አዳማ ከተማም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆና  ዛሬ  የኮንፈረንስና የአስተዳደር ማዕከል ሆና እያደገችና እየተዋበች፣ የስምጥ ሸለቆዋ እንቁ እስከመባል ደርሳለች፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ለነዋሪዎቿ ያልተመቻቹ አንዳንድ ችግሮች ይታያሉ፡፡ የውኃና የኤሌክትሪክ መብራት መቆራረጥ አንደኛው ችግር ነው፡፡ በክረምት ወቅት ከንብረት መውደም እስከ ሕይወት መጥፋት የሚያደርስ የጎርፍ አደጋ ሌላው አሳሳቢ ችግር ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የከተማው ችግሮች በመንግሥት ደረጃ የታወቁና መፍትሔ ለመስጠትም መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ በተለያየ ጊዜ ከከተማው አመራሮች ሲነገር ቀይቷል፡፡

እኔ ግን እንደ ነዋርነቴ ለመጠየቅ የምፈልገው የኅብረተሰቡን ጤና በተመለከተ ነው፡፡ ዛሬ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንኳ ተግባራዊ እየሆነ ያለው  በሽታን ቀድሞ የመከላከል ፖሊሲ፣ በአዳማ ከተማ ተግባራዊ ያለመሆኑን ሲሆን፣ የከተማው አመራሮችም ሆኑ የክልሉ መንግሥት ይህን ያውቁ ይሆን?

እኔን በጣም ያሳሰበኝ ሌላው ጉዳይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዳርቻው ላይ የሚታየው ክምር ደረቅ ቆሻሻ፣ በየጊዜው በየመንገዶች ዳር እየተጣለ ከነሽታቸው መንገድ የሚዘጋ ሲሆን፣ ለጉንፋንና ለአስም በሽታ የሚዳርግ የቤት እንስሳት ቆሻሻ ይጥላል፡፡ ምሽት ከሁለት ሰዓት በኋላ በማጅራት መችዎች የሚደረስብን አደጋም ቀላል አይደለም፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች ጋር ስሜቴ፣ ዓይኔና አፍንጫዬ ተላምዷል፡፡

እኔን የሚያሳስበኝ ሌላው ነገር በአዳማ ከተማ በየጎዳናው የሚርመሰመሱት ባለቤት የሌላችው የውሾች መንጋ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ውሻ ታማኝ እንስሳ ነው፡፡ በጥንቃቄና በአንክብካቤ ከያዙት የሰው ሕይወትን ጨምሮ ንብረትን ከአደጋ ይጠብቃል፡፡ በዚህ አያያዛቸው በርካታ ነዋሪዎች ውሾቻቸውን በየግቢያቸዉ አሳድገዉ በአግባቡ ሲጠቀሙባቸው እናያለን፡፡ ይሁን እንጂ ከየት እንደመጡ የማይታወቁ የውሻ መንጋዎች በየጎዳናው እየተሸኮለኮሉ  በእብድ ውሻ በሽታ በየጊዜው ነዋሪውን  እያጠቁ ይገኛል፡፡

በአዳማ ከተማ  አንድ የመንግሥት፣ ሁለት የግል ትልልቅ ሆስፒታሎች፣ በርካታ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁምና የግል ክሊኒኮች ቢኖሩም ፣ ሰው ታሞ ሲሄድ ቢሮክራሲ ከማብዛት በዘለለ ለዚህና ለመሳሰሉት የነዋሪው የጤና ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሠሩት ተጨባጭ ሥራ የለም፡፡

መንግሥት የሚከተለው የጤና ፖሊሲ ያመጣው ችግር ሳይሆን፣ በከተማው ሕዝቡን እንዲያገለግሉ፣ ከተማውን  በዕድገት ጎዳና እንዲመሩ የሕዝብና የመንግሥት አደራ ተቀብለው ነገር ግን አደራውን በበሉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ያጋጠመን የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡

ስለዚህ የሰው  ልጅ በዚህ አሰቃቂ የእብድ ውሻ በሽታ ከሚሰቃይ ሌላው  ቢያቅታችሁ እንኳ ባለቤት የሌላቸው ውሾች ከከተማችን  አስወግዱልን፡፡

                                                                           (ጫላ ቦካ፣ ከአዳማ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...