Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክእልባት ያላገኘው የፕሮቪደንት ፈንድ ስንክሳር

እልባት ያላገኘው የፕሮቪደንት ፈንድ ስንክሳር

ቀን:

የፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓት ወደ ግል ድርጅቶች ጡረታ አዋጅ የሕግ ማዕቀፍ ሊገባ ነው መባሉ በዚህ ሳምንት አከራካሪ ከሆኑት ሰሞናዊ ዜናዎች አንዱ ነው፡፡ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚሠሩ ሠራተኞች ወቅታዊ አንገብጋቢ ነገር የፕሮቪደንት ፈንድ ወደ ጡረታ እንደሚለወጥ በመንግሥት ቁርጥ ሐሳብ መያዙ ነው፡፡ ይህ የታወቀው ሰሞኑን ተረቅቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የአዋጅ ቁጥር 715/2003 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ አሁን ሥራ ላይ ባለው አዋጅ (የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ) መሠረት አዋጁ ተግባራዊ መሆኑ ከመጀመሩ በፊት የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያላቸው የግል ድርጅቶች ሠራተኞች በነበራቸው የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነት ለመቀጠል እንዲወስኑ ወይም በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ ሊስማሙ እንደሚችሉ ደንግጓል፡፡ ይህንን ተከትሎ ብዙኃኑ የግል ድርጅት ሠራተኞች የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ መሆኑን የመረጡ ሲሆን፣ ከአዋጁ በኋላ ለተቀጠሩት ግን ይህ የምርጫ መብት በአዋጁ ስላልተጠበቀላቸው የግል ጡረታ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡ አሁን ፓርላማው እንዲያፀድቀው የቀረበው የአዋጁ ማሻሻያ ግን ለግል ሠራተኞች የተሰጠውን የምርጫ ነፃነት መልሶ ወስዶታል፡፡ በዚሁ መሠረት የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ የነበረ ሠራተኛ በሙሉ ወደ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ የሚገባ ሲሆን፣ ፈንዱና ሠራተኛው ያገለገለው ዘመን ግንዛቤ እየገባ ወደ ግል ጡረታ ኤጀንሲ ፈንዱ የሚዘዋወር ይሆናል፡፡ በአጭር ቃል ረቂቅ አዋጁ ከፀደቀ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ተፈጻሚነት የነበረው የፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓት ይቋረጣል፡፡ የፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓት ሊቀጥል የሚችለው የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ኢ-መደበኛ በሆኑ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ድርጅቶች በግል ጡረታ ዐቅድ ላለመሳተፍ ከወሰኑና ሠራተኞቻቸውን የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ ካደረጉ ነው፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ እነዚህ ተቋማት የግል ጡረታ ዐቅድ ተጠቃሚ ለመሆን ሊስማሙ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡

የፕሮቪደንት ፈንድን ወደ የግል ጡረታ ዐቅድ ለመለወጥ ምክንያት የተባሉት በአዋጁ ማብራሪያ መገለጻቸው በየመገናኛ ብዙኃኑ ተገልጿል፡፡ የረቂቅ አዋጁ ዋና ዓላማ በግል ጡረታ ዐቅድ መሠረት ችግሮችን በጋራ የማስቀረትና ጥቅሞቹን በጋራ የመጋራት ዓላማ ለሁሉም ሠራተኞች ተፈጻሚ ሊሆን ስለሚገባው ነው፡፡ እስካሁን ተፈጻሚ ይደረግ የነበረው የፕሮቪደንት ፈንድና የግል ጡረታ ዐቅድ አፈጻጸም በኅብረተሰቡ ውስጥ የመብትና የጥቅም ልዩነትን ያስከተለ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ ሁሉም ሠራተኞች የግል ጡረታ ዐቅድ ተፈጻሚ ስለሚሆኑ ልዩነቱን (Discrimination) የሚያስቀር ይሆናል፡፡ የረቂቅ አዋጁ ለፓርላማ መቅረቡን ተከትሎ በግል ድርጅቶች ዘንድ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ቀደም ብሎ የግል ጡረታ አዋጁ ሲረቀቅ ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሕግን እንደማስደንበሪያ

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ እንደሚወጣ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰማው 1997 ዓ.ም. አካባቢ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት አቋምና ፖሊሲ የታወቀው በ2003 ዓ.ም ረቂቅ አዋጁ ሲዘጋጅ ነው፡፡ በዚያን ወቅት በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የነበረው የአዋጁ እሳቤ አዎንታዊ አልነበረም፡፡ ረቂቅ አዋጁ ‹‹በግል ድርጅቶች የተጠራቀመውን የፕሮቪደንት ፈንድ መንግሥት ሊወስድ ነው፤ የፕሮቪደንት ፈንድ አስተዳደር በአስገዳጅ የጡረታ ዐቅድ ሊተካ ነው፤›› በሚል ብዥታ በኅብረተሰቡ ውስጥ በመፈጠሩ የአንድ ሰሞን ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ በጊዜው አብዛኛዎቹ የግል ድርጅቶች የተጠራቀመውን የፕሮቪደንት ፈንድ ለሠራተኞቻቸው ያከፋፈሉ ሲሆን፣ አንዳንዱም በግማሽ በመክፈል የመንግሥት ውሳኔን በመጠባበቅ ላይ ነበር፡፡

አዋጁ ሲመጣ ግን የተሠጋው ነገር አልነበረም፡፡ አዋጁ የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚዎች የሆኑ ሠራተኞች እንደማይገደዱ፣ ሠራተኛው በፈቃዱ የግል ጡረታ ዐቅድ ተጠቃሚ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ አስተዳደር ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ግልጽ አደረገ፡፡ የአገራችን የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ኅብረተሰቡን ያማከለ ቢሆን ኖሮ ሠራተኛው የተሳሳተ መረጃ በመያዝ ባንኮቹ የቁጠባ ድርቅ እስኪመታቸው ድረስ የፕሮቪደንት ፈንዱን ካስቀመጠበት ባላወጣ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ብርገጋ ባንኮች ደንበኞቻቸውን እንዲያውቁ በሚያስገድደው መመርያ አወጣጥ ጋር ተያይዞ መከሰቱ ይታወሳል፡፡ በጊዜው ብሔራዊ ባንክ ከ200,000 በላይ የሚደረጉ የባንክ ግብይቶች ሪፖርት እንዲደረጉ መመርያ ሲያስተላልፍ ሰው ገንዘቡ የሚወረስበት መስሎት በቤቱ ለማስቀመጥ ካዝና መግዛትን እንደተያያዘው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ሕግ መውጣት እንዳለበት፣ ዓላማው፣ ይዘቱ፣ ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖ ወዘተ. ኅብረተሰቡ ማወቅ ያለበት ረቂቁ ለፓርላማ ሲቀርብ ሳይሆን በረቂቁ ዝግጅት ወቅት ነው፡፡ በረቂቅ ዝግጅቱ ጊዜ ሕዝቡን ማሳተፍ ማስበርገግን ያስቀራል፣ አፈጻጸሙንም ያሳምራል፡፡ በዚህ ሰሞን ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅም ተመሳሳይ ውጤት ነው ያስከተለው፡፡ የግል ድርጅት ሠራተኞች የረቂቁን መዘጋጀት ተከትሎ መንግሥት የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘባችንን ለልማት ሊያውልብን ነው በማለት አሠሪው እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የተወሰኑት ለመፍቀድ ወይም ለመስጠት ወይም ወደ ብድር ለማዋል ወዘተ. በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ የግል ሠራተኛው መደናበር አሁን መቀጠሉን ልብ ይሏል፡፡ መነሻው ደግሞ የረቂቁ መዘጋጀት መሆኑን ላሰበ ሕግ ማስደንበሪያ ነውን? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፡፡

አንዳንዶች የፕሮቪደንት ፈንድን የግል ጡረታ ዐቅድ አካል ማድረግ ሐሳቡ በመንግሥት ከነበር ያኔውኑ (አዋጅ ቁጥር 715/2003 ሲወጣ) ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ አጀንዳውን በየጊዜው እያነሱ እያመነቱ መተው የመንግሥትን ቁርጥ አቋም ለመረዳት ማስቸገሩን ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች የፕሮቪደንት ፈንድን የግል ጡረታ ዐቅድ አካል ማድረግ ድሮውንም የነበረ ሐሳብ ሲሆን፣ አዋጁ ሲወጣ ስለግል ጡረታ ዐቅድ ይነሱ የነበሩ ሥጋቶችን ለማስቀረት እንዲዘገይ ተደርጎ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ መሠረት በ2003 ዓ.ም. አዋጁ ሲወጣ ፕሮቪደንት ፈንድ የግል ጡረታ ዐቅድ አካል ቢሆን ኖሮ ‘መንግሥት የፕሮቪደንት ፈንዱን ሊወስደው ነው፤’ ሲባል የነበረውን ሀሜት አያስቀርለትም ነበር ይላሉ፡፡ ጸሐፊው የችግሩ ምንጭ ከሕጉ የረቂቅ ዝግጅት፣ ኅብረተሰቡ ሊኖረው የሚገባውን ተሳትፎ ካለማረጋገጥ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናል፡፡ ሕጉ ሲወጣ በጎ ዓላማ እንደነበረው ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ዓላማው የዜጎችን የማኅበራዊ ዋስትና መብት ያለ አድልኦ ጥበቃ መስጠት ነው፡፡ ይህንን ዓላማ በጊዜው ለኅብረተሰቡ በተለይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ለግል ድርጅቶች አሠሪዎችና ሠራተኞች ማስገንዘብ የሕጉን ይዘት በዘለቄታው መደንገግ በተቻለ ነበር፡፡ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ስለተቃወመ በአዋጁ የታሰበውን በጎ ዓላማ ሙሉ ለሙሉ አለማስተግበርም ሆነ በጊዜው የተነሱ አሳማኝ የሠራተኛውን ጥያቄዎች አለመመለስ አግባብ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው አሁን እንደገና ጥያቄውን ለማንሳት መንግሥት የተገደደው፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ መክረውበት አዋጁ በምልዓት ቢፀድቅ ኖሮ አዋጁን አራት ዓመት ሳይሞላው ለማሻሻል መጣደፍ ባልኖረ ነበር፡፡

መንግሥት የነበሩት አማራጮች

የፕሮቪደንት ፈንድ ምንነት፣ ዓላማና አፈጻጸሙን በተመለከተ በአገራችን ባለፉት ዓመታት የተለያዩ አቋሞች ተይዘዋል፡፡ በተግባር በግል ድርጅቶች ካለው አሠራር የፕሮቪደንት ፈንድ አሠሪውና ሠራተኛው በሚያደርጉት ስምምነት የሚቋቋም ሲሆን፣ አሠሪውና ሠራተኛው የየራሳቸውን አስተዋጾኦ በማድረግ በስምምነቱ በተገለጹት ቅድመ ሁኔታዎች መሠረት የሠራተኛው የሥራ ውል ሲቋረጥ/አልፎ አልፎም የሥራ ውሉ በጸናበት ወቅት በአንድ ጊዜ ክፍያ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ የፕሮቪደንት ፈንድ በመዋጮውና በዓላማው ከጡረታ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ሠራተኛው በመዋጮው ዕድገት ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆኑ፣ ክፍያው የሥራ ውል ሲቋረጥ በአንድ ጊዜ መከፈሉ፣ እንዲሁም የገበያን ግሽበት ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ ከጡረታ ይለያል፡፡

በ1997 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) ዕርዳታ በተዘጋጀው ጉባዔ የግል ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድና ፕሮቪደንት ፈንድ በተመለከተ ሦስት ዓይነት አቋም ተንፀባርቋል፡፡ እስካሁን ተፈጻሚ የነበረውን የፕሮቪደንት ፈንድን አሠራር አቁሞ በጡረታ ዐቅድ መተካት የመጀመሪያው አቋም ነው፡፡ ይህ አቋም በ1997 ዓ.ም. አካባቢና አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ  ከመዘጋጀቱ በፊትና ረቂቁ ሲዘጋጅ ባሉት ጊዜያት ሠራተኞች የፕሮቪደንት ፈንዳቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ያነሳሳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው አቋም የፕሮቪደንት ፈንድን ወደ ማኅበራዊ ዋስትና ዐቅድ (Scheme) መቀየር ነው፡፡ ሦስተኛው አቋም ደግሞ የፕሮቪደንት ፈንድንና የግል ድርጅት ሠራተኞችን የጡረታ ዐቅድ ጎን ለጎን ማስኬድ ነው፡፡ ይህ አቋም ሠራተኞች በአንድ ጊዜ ሁለት መዋጮ እንዲያወጡ የሚጠይቅ በመሆኑ ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የሁለተኛውን አቋም የሚያንፀባርቅና ተፈጻሚነቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ አሠሪውና ሠራተኛው ተስማምተው በፕሮቪደንት ፈንድ አሠራር ከቀጠሉ ድርጅቱ የፕሮቪደንት ፈንድ አሠራርን የሚተገብር ሲሆን፣ በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ መተዳደር የፈለገ ደግሞ በአዋጁ መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ አዋጁ የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን በሌለባቸው ድርጅቶች ላይ የግዴታ ተፈጻሚ መሆኑ የዜጎችን የማኅበራዊ መብት ዋስትና የሚጠብቅ ሲሆን፣ ፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ባላቸውም ድርጅቶች ዘንድ በፍላጎት እንደሚፈጸም መደንገጉ መብትን መሠረት ያደረገ አካሄድ ነው፡፡ አሁን ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን የመንግሥት አቋም ወደ መጀመሪያው አማራጭ መቀየሩን የሚያመላክት ነው፡፡ የአቋሙን መቀየርም ተከትሎ በአዋጁ ደጋፊና ተቀዋሚ መካከል የከረረ ሙግት ተከፍቷል፡፡

ግራ ቀኝ ሙግቶች

የፕሮቪደንት ፈንድ በአስገዳጅ የግል ጡረታ ዐቅድ መካተቱን በተመለከተ ሕጉን ያረቀቀው አካልና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የተስማሙ አይመስልም፡፡ በመገናኛ ብዙኃኑ እንደተዘገበው የግል ድርጅት ሠራተኞቹ ተቃውመውታል፡፡ የመንግሥት አመክንዮ (Justification) ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በረቂቁ ማብራሪያም እንደተገለጸው አዋጁ መሻሻል ያለበት መንግሥት የዜጎቹን የማኅበራዊ ዋስትና የማረጋገጥ ግዴታ ስላለበትና አሁን እየተተገበረ ያለው የፕሮቪደንት ፈንድ ይህንን ዓላማ በእኩልነት ለሁሉም ለማረጋገጥ ስለማያስችለው ነው፡፡ በአገራችን ዐውድ የጡረታ ዐቅድ ዋና ዓላማ ሠራተኞች በዕድሜ ወይም በጤና ምክንያት በማይሠሩበት የሕይወት ዘመን ባጠራቀሙት ወይም አሠሪያቸውም ባጠራቀመላቸው ገንዘብ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ የማኅበራዊ ዋስትና ከጤና መድን፣ ከሥራ ማጣት፣ ከአካል ጉዳተኝነት፣ ከሕመም ወዘተ. ጋር የሚያያዝ ቢሆንም የግል የጡረታ ዕቅድ ዋና ዓላማው በስተርጅና የሚኖረውን ችግር መቀነስ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ዓላማ አንፃር የፕሮቪደንት ፈንድን ሥርዓት ከቃኘነው ሠራተኛው የሥራ ውሉ በፀናበት በተወሰነ ጊዜ ወይም ሲቋረጥ ጠቅልሎ የሚወስደው እንጂ እስከ እርጅናው የሚጠብቀው ባለመሆኑ የመንግሥት ሐሳብ ጋር አንድ ላይሆን ይችላል፡፡ ሠራተኛው ገንዘቡን አሁን ምርታማ በሆንኩበት ዘመን እፈልገዋለሁ ሲል መንግሥት ግን በስተርጅናህ እንዳታስቸግረኝ ላንተ ከአንተ በላይ አስባለሁ ነገር ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ሐሳብ በረቂቁ ማብራሪያ ላይ ‹‹ሠራተኛው በነበረው የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነት እንዲቀጥል ማድረጉ የሠራተኛውን ተተኪዎች (ልጆችና ቤተሰቦች) የዘለቄታ የማኅበራዊ ዋስትና መብትና ጥቅም ያሳጣል፤›› ሲል የተገለጸው ነው፡፡

የፕሮቪደንት ፈንድ የግል ጡረታ ዐቅድ አካል መሆኑን የሚቃወሙት የተለያዩ መነሻ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ መንግሥት የራሱን ገቢ በመጨመር የጀመራቸውን ግዙፍ  ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ገንዘብ አጥሮት፣ ገንዘብ ለማግኘት እንጂ ለሠራተኛው የሚጠቅመውን ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም ይላሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ማብራሪያ ላይ የግል ጡረታ አዋጁ ‘የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት’ እንዲረዳው ታስቦ የነበረ መሆኑን ለተረዳ ሰው መንግሥት ከግል ጡረታ ዐቅድ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለልማቱ ለማዋል፣ ለሁለተኛውም ዐቅድ ለመጠቀም የፈለገ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከአሁኑም ረቂቅ ጋር ተያይዘው የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የወጣው መረጃ መንግሥት በጡረታ መልክ በዓመት 340 ሚሊዮን የማሰባሰብና ለልማት የማዋል ዕቅድ አለው፡፡ እንዲህ ዓይነት ምክንያቶች መንግሥት ለሠራተኛው ዘለቄታዊ የማኅበራዊ ዋስትና ከማሰብ ይልቅ ለትላልቅ የልማት ግንባታዎቹ የተጨነቀ ያስመስለዋል፡፡ አንዳንዶች ይህን ሐሳብ በማጠናከር የግል ባለሀብቶቹ በርካታ የማኅበራዊ ዋስትና አማራጮች እንዳሏቸው (የጡረታ ኢንሹራንስ መግባት፣ በዘለቄታው ሕይወትን በሚለውጥ ሀብት መተካት ወዘተ.) በመግለጽ መንግሥት የግል ጡረታን አስገዳጅ ማድረጉን ይቃወማሉ፡፡ 

ያልተቋጩ ነጥቦች

አዋጁ በረቂቅነት የፈጠረውን መደናገር ድርጅቶች እንደየራሳቸው ዓውድ መፍትሔ ይሰጡታል፡፡ አንዳንዶቹ ድርጅቶች ፕሮቪደንት ፈንዱን አከፋፍለዋል ይባላል፤ አንዳንዶችም ለብድር መክፈያ ሊያውሉት አስበዋል፤ ሌሎቹም በየስድስት ወሩም ሆነ በየዓመቱ ለሠራተኛው የመስጠት ልምድ ስላላቸው በዚሁ አሠራር መስመር ያስይዙታል የሚል መላ ምት አለ፡፡ ቀሪዎቹ ግን መንግሥት እስከዛሬ ለዘመናት ያጠራቀማችሁት ገንዘብ የታለ? በየአንዳንዱ ሠራተኛ ስም ከመረጃዎቹ ጋርና በአዋጁ አስገዳጅ በሆነው የመዋጮ ስሌት መሠረት የማስተላለፍ ግዴታ አለባችሁ ብንባልስ? በሚል ዝምታን መርጠዋል፡፡ የኋለኞቹ ድርጅቶች ሥጋት የሕግ ባለሙያ ምክር ቢያገኝ በቀላሉ መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ከመንግሥት/ከፍርድ ቤት የፕሮቪደንት ፈንዱ እንዲታገድ፣ እንዳይሰጥ፣ እንዳይተላለፍ ወይም በማናቸውም መልኩ እንዳይወጣ የተሰጠ እግድ ከሌለ ማከፋፈልም፣ መስጠትም፣ለብድርም ማዋል በሕግ አልተከለከለም፡፡ ረቂቅ አዋጅ እስካልፀደቀ ድረስ ሕግ የሚኖረው አስገዳጅ ባህርይ አይኖረውም፡፡ በሌላ በኩል ግን የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ መንግሥት የተጠራቀመው የፕሮቪደንት ፈንድ ከግል ተቋማቱ ቋት ወደ የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ ኤጀንሲ ቋት እንዲተላለፍ የሚፈልግ ያስመስለዋል፡፡ በረቂቁ በፕሮቪደንት ፈንድ ሲቆጥቡ የነበሩ ሠራተኞች ፈንድ ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ እንደሚዘዋወር፤ በሚዘዋወርበት ጊዜ በፕሮቪደንት ፈንድ የተቀመጠው ከሚገባው መጠን በላይ የተከፈለ ከሆነ ልዩነቱ ለሠራተኞች ተመላሽ እንደሚደረግ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ የሚያሳየው የፕሮቪደንት ፈንዱ አዋጁ እስከሚፀድቅበት ግን ተጠራቅሞ እንደሚጠብቅ ይመስላል፡፡ አስገዳጅ ሕግ ወይም የፍርድ ቤት እግድ ወይም እንደተለመደው የመንግሥት መመርያ ከሌለ በቀር የረቂቁን መንፈስ መፈጸም አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ ለፍርድ ቤት እግድ መነሻ የሚሆን ጭብጥ ባለመኖሩ፣ መመርያዎቹም ከአዋጅ ይልቅ ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው፣ መብት ለመንጠቅም ወደኋላ የሚሠራ ሕግ ማውጣትም ፍትሐዊ ስለማይሆን የመንግሥት ዕቅድ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሚሰበሰበውን የሚመለከት እንደሚሆን መገመት አሳማኝ ነው፡፡ የዚህ ውጤቱም ለረጅም ጊዜ በግል ድርጅት ሲሠሩ የነበሩና በሚወጣው አዋጅ የሚታቀፉት ሠራተኞች ሰፊ የጡረታ መጠን ላይኖራቸው እንደሚችል ነው፡፡

የረቂቅ አዋጁ ፕሮቪደንት ፈንድን በግል ጡረታ ዐቅድ ከማጠቃለል ባለፈ የያዛቸውም ድንጋጌዎች ፍተሻ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ቀደም ባለው ሕግ ‹‹ቢያንስ 10 ዓመት ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜው በመድረሱ ከሥራ ሲሰናበት የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ ልኩ ይከፈለዋል፤›› የሚለው የመሻሩ ጉዳይ ነው፡፡ የድንጋጌው ወሰንና አፈጻጸሙ ቀድሞም ግልጽነት ያልነበረው ሲሆን፣ አንዳንድ ሠራተኞች መብትን የሚቀንስ ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ሲወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያጋጠሙት ክፍተቶች ወይም ተግዳሮቶች ካሉ አሁኑኑ በጥንቃቄ መርምሮ ማሻሻል ተገቢ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የአዋጁን ይዘት፣ ዓላማና አፈጻጸም በተመለከተ ጥናት በመሥራት ባለድርሻ አካላት እንዲመክሩበት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰፊ ጊዜ ወስዶ፣ ጥናትን መሠረት አድርጎ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተጨባጭ በማሳተፍ ረቂቁ ካልዳበረ ሕጉ በወጣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የመሻሻል ሥጋት ይደቀንበታል፡፡ ሕግን አውጥቶ በፍጥነት የማሻሻል አባዜ የሕግ ሥርዓቱ ድካም፣ ለዘመናት እንዲወጡ ተስፋ የተጣለባቸውን ሕግጋት የማሰበያ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡          

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...