Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉኮከቡ ያልሰመረው ትሪሊየን ጂዲፒ

ኮከቡ ያልሰመረው ትሪሊየን ጂዲፒ

ቀን:

ይድረስ ለአዲሶቹ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት

በጌታቸው አሰፋ

የፖለቲካ ሥልጣን ውድድሩ ተገባዶ አብዛኛው የምክር ቤት አባላት ውጤታቸውን አውቀው ወንበራቸውን ሊሠሩ ካለሙት ሥራ ጋር፣ ለሕዝብ ከገቡት ቃል ኪዳን ጋር፣ በዓይነ ህሊናቸው የሚያዩበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ሥልጣን ላይ መቀመጥም ሆነ ከተቀመጡበት መነሳት አዲስ አይደለም፡፡ ተመስግኖ መነሳትም አለ፣ ተንቋሾ መነሳትም አለ፡፡ አብርሃም ሊንከንም ከወንበሩ ጋር አልቆየም፣ ሂትለርም አልቆየም፣ ማንዴላም አልቆየም፣ የእኛ ነገሥታትም አልቆዩም፣ ደርጎችም አልቆዩም፣ ሁሉም አልፈዋል፡፡ ሥራቸውን ግን ትውልድና ታሪክ በደግና በክፉ ያነሱታል፣ ያወግዙታል፣ ይዘክሩታል፡፡

- Advertisement -

ሁሌም አዲሱ ነገር በያዙት ወንበር ሳይኩራሩ፣ ለግል ምቾት ሳይሳሱ፣ ለሕዝብ የሚጠቅም አዲስ ሥራ ለመሥራት ማሰብ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ሽጉጥ ለመጠጣት የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ሰው አይደሉም፡፡ ጀግና ያደረጋቸው ለሕዝብና ለአገር ክብር ሲሉ ሽጉጣቸውን ጠጥተው መሞታቸው ነው፡፡ ፖለቲከኞች ሕዝብን ለማክበር፣ ለሕዝብ ለመሥራት ቁርጠኛ አቋም ካላቸው ደግሞ፣ ሕዝብን ዓይንና ጆሮ ሊያደርጉ የሕዝብን ሐሳብ ሊሰሙ፣ ከሕዝብ አስተያየት ሊቀበሉ ይገባል፡፡ ከሕዝብ መካከልም ችግሩን በሆድ ይፍጀው አምቆ ከመያዝ ተናግሬ ለውጥ ላምጣ የሚል በጣም ጥቂት ስለሆነ ሰሚ ጆሮ ይሻል፡፡

የአስፈጻሚው የበላይና የበታች ባለሙያ ሹማምንት የግል ሥልጣን፣ ሀብትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ላለማጣት ሲሉ የሚያቀርቧቸውን በውብ ቃላትና ቁጥሮች የተሸፋፈኑ የውሸት ሪፖርቶችና መረጃዎች ሳይጠራጠሩ፣ ከገለልተኛ አካልና ከሕዝብ የተለየ ሐሳብን ሳይሰሙና ሳያነፃፅሩ እንደቀረበ መቀበል፣ የፖሊሲ መነሻ ሐሳብ ማድረግ የዚህን ዘመን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድም የመበደል ያህል ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ከሕዝብ አንዱ በመሆኔ በውድድሩ ወቅት ተፎካካሪዎች የበሰለ ክርክር እንዲያደርጉ በሙያዬ ያወቅሁትን ለማጋራት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በመጋቢትና በሚያዝያ መካከል በአንድ ወር ውስጥ ሦስት ጽሑፎች ለሪፖርተር ጋዜጣ አቅርቤ ሦስቱም ለንባብ በቅተውልኛል፡፡ ሪፖርተርን አመሰግናለሁ፡፡

አሁን ደግሞ ባለፉት ዓመታት የእኔን ሙያ (ኢኮኖሚክስ) በተመለከተ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ አስተውዬአቸዋለሁ የምላቸውን ጉዳዮች አዲሶቹ ባለወንበሮች ተረድተው በአዲስ ወኔ ሥራቸውን እንዲጀምሩና ለአምስቱ ዓመታት ጉዟቸው ስንቅ እንዲሆኗቸው፣ ከአንድ ወገን ብቻ በሚያዳምጧቸው መረጃዎች፣ ጥናቶችና ሪፖርቶች የተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ በሙያዬ የተገነዘብኳቸውንና ከመንግሥት የኢኮኖሚ አማካሪዎችና ባለሙያዎች ሪፖርቶች በተለየ ዓይን የማያቸውን ሐሳቦች ላካፍላቸው ወድድኩ፡፡ ምርት ሲያንስ በአምራቹ፣ ዋጋ ሲወደድ በነጋዴ፣ ወጣቶች ሲሰደዱ በደላላ ይሳበባል፡፡ የምርት እጥረት፣ የዋጋ መወደድና ሥራ ማጣት ሦስቱ የኢኮኖሚያዊ ኑሮ ነቀርሳዎች ናቸው፡፡ የኢኮኖሚያዊ ኑሮ መሐንዲስ የሆነው የመንግሥት የኢኮኖሚ አማካሪ ለችግሮቹ ኃላፊነት ሲወስድ አይታይም፣ አስቦትም አያውቅም፡፡ ሕዝቡም ተጠያቂ አድርጎት አያውቅም፡፡

ስለዚህም የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማና ትኩረት ኅብረተሰቡን ለሚያሰቃዩትና ለሚያስመርሩት ሦስቱ ነቀርሳዎች ተጠያቂው የኑሮ መሐንዲስና የኢኮኖሚ አማካሪው መሆኑን፣ በገሀድ በሚታይ ጭብጥና በሚያሳምን ሀቅ ማቅረብ ነው፡፡ በዓይን በሚታዩ ለሕዝብ በጋራ በሚሰጡ የመንግሥት መሠረተ ልማትና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ወይም የልማት እንቅስቃሴዎችን አደንቃለሁ፣ ምንም ትችትም የለኝም፡፡ በዚህ ጽሑፍ እንደ ጉድለት አይቼ ትክክለኛ ፖሊሲ ባለመነደፉ ሕዝብ ተሰቃይቶባቸዋል፣ ተማሮባቸዋል ብዬ የምገልጻቸው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ ለግለሰብ ገበያ ውስጥ በሽያጭ በሚቀርቡ ሸቀጦችና በገበያ ኢኮኖሚው ላይ ነው፡፡

ስለዚህም በዚህ ለየት ባለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስተሳሰብ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከልማት ኢኮኖሚ ጎን ለጎን ወደ ገበያ ኢኮኖሚም የምታመራበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገበያ ውስጥ በሚገጥሙን ዕለታዊ የምርት እጥረት፣ የዋጋ ውጣ ውረድ፣ የሥራ ማጣት፣ እንጀራ ፍለጋ እስከ መሰደድ መድረስ፣ የግል ኑሯችን መመሰቃቀል፣ የወረቀት ላይ የብሔራዊ ኢኮኖሚ መረጃ፣ ጥናትና ሪፖርት መካከል የተገነዘብኩትን ተቃርኖ በእንቆቅልሽ መልክ አቀርባለሁ፡፡

እንቆቅልሹ ምንድነው?

በልጅነቴ ካነበብኳቸው ጽሑፎች ውስጥ በአንዱ ግራ የሚያጋባ እንቆቅልሽ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ሚስቱ ምጥ የተያዘችበት ባል ከጎኗ ቁጭ ብሎ መጽሐፍ እየደገመ አንዴ ልጄ ተወለድ ይላል፣ ትንሽ ቆይቶ ልጄ አትወለድ ይላል፡፡ እነኚህን ቃላት እያፈራረቀ ሲል ቆይቶ ልጁ ተወለደና ድግምቱ አበቃ፡፡ እኔን ግራ ያጋባኝ እንቆቅልሽም ተፈታ፡፡ ለካስ ሰውየው ኮከብ ቆጣሪ ነው፡፡ የልጁን ኮከብ በከዋክብት ምልክት እያየ ኖሯል፣ ተወለድ አትወለድ ይል የነበረው፡፡ በቅርቡ የገጠመኝ ተመሳሳይ ግራ አጋቢ እንቆቅልሽ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ነው፡፡ ከ1981 እስከ 2006 ዓ.ም. በነበረው ሩብ ምዕተ ዓመት 25 (ዓመታት) ጂዲፒው የመነሻውን የ1981 ዓ.ም. አሥር ቢሊዮን አካባቢ ብር መቶ እጥፍ ሆኖ በ2006 ዓ.ም. ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህን የወረቀት ላይ የቁጥር መረጃ እንደ ኮከብ ቆጣሪው ወደ የገበያ ምልከታዊ መረጃ ብንተረጉመው፣ ከሌሎች የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ግቦች ጋር ብናገናዝበው፣ ከዝርዝር ገበያዎች ጋር ብናነፃፅረው ግራ የሚያጋባ እንቆቅልሽ ይገጥመናል፡፡

ሦስቱ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ (Macroeconomic Policy) የመጨሻ ግቦች የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ዕድገት፣ የዋጋ ግሽበት መቀነስና የሥራ አጥ ቁጥር መቀነስ ናቸው፡፡ ሦስቱም ይደጋገፋሉ፣ ይተሳሰራሉ፣ ወደ ክፍለ ኢኮኖሚያዊ (Sectoral Economy) ተዘርዝረውም ይተነተናሉ፣ ይጠናሉ፡፡ የጥቅሉና የዝርዝሩ መስተጋብርም ይመረመራል፡፡ በወረቀት ላይ በአሥራ አንድ በመቶ ዕድገት ቁጥሮች ታጅቦ ትሪሊዮን ውስጥ የገባው ጂዲፒ ኮከቡ አልሰመረም፡፡ በገበያ ውስጥ የሚታየው የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት ይቃረነዋል፡፡ አራት መቶ ብር የገባው የዘንድሮ ፋሲካ ዶሮ ዋጋ (እንደ አጠቃላይ የሸማቾች ዋጋ አመልካች መናር ምሳሌ ሲወሰድ) ይቃረነዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች የሎሌነት ሥራ ገበያ ፍለጋ ወደ በላቸው የበረሃ አሸዋ፣ ወደ ዋጣቸው ባህር፣ ወደ አቃጠላቸው እሳት፣ ወደ አራጅ አረመኔዎች መሰደድ በጥቅል አባባል ከኢትዮጵያ ኑሮ ሞትን መምረጥ (እንደ ሥራ አጥነት መጣኝ ምሳሌ ሲወሰድ) ይቃረነዋል፡፡

ትሪሊየን ጂዲፒው በሦስቱም የብሔራዊ ኢኮኖሚ የመጨረሻ ግቦች ውጤት አላመጣም፡፡ የጥቅል ኢኮኖሚውና ዝርዝር ኢኮኖሚው መስተጋብርም ባዶ ነው፡፡ ዝርዝር ገበያዎች በምርት አቅርቦት መጠን፣ በሸቀጥ ዋጋ፣ በሥራ ቅጥር አማካይነት የሚናገሩት ሌላ ስለብሔራዊ ኢኮኖሚው የሚጻፈው ሌላ፡፡ ምርት ሲያድግ የምርት አቅርቦት ይጨምራል፣ ምርት ሲያድግ የሸቀጥ ዋጋ ይቀንሳል፣ ምርት ሲጨምር ሥራ ቅጥር ይጨምራል የሚባሉት የገበያ ኢኮኖሚ ሕግጋት ምልክቶች በወረቀት ላይ በቁጥር በፍጥነት እያደገ ባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ አልሠሩም፡፡ በወረቀት ላይ ያየነውን ቁጥር በገበያው ውስጥ በምልክት አላየንም፡፡ ትሪሊዮን ጂዲፒው ‹የማትበላ ወፍ ተይዛ በጭራ ልቤን አደማችው ቦጫጭራ ቦጫጭራ› ነው የሆነብን፡፡

ከወረቀቱ ይልቅ የሚታመነው ገበያው ነው፡፡ በአጠገባችን ካለው ገበያ በላይ የሐበሻውም የፈረንጁም ጠቢባን በምናባዊ ዋጋ የተመኑትን ቁጥሮቻቸውንና መረጃዎቻቸውን እየተቀባበሉ፣ አንዳቸው የሌላኛው ምስክር ሆነው ሊነግሩን ቢሞክሩም ሊያሳምኑን አይችሉም፡፡ ከዓይናችን ጆሮአችንን አናምንም፡፡ የሥራ ገበያው ስለራሱ ይናገራል፡፡ የመሬት ገበያው ስለራሱ ይናገራል፡፡ የምርት ገበያው ስለራሱ ይናገራል፡፡ በዝርዝርም የአናጢነት ሥራ ገበያው፣ የወዛደር ገበያው፣ የሽንኩርት ገበያው፣ የዘይት ገበያው፣ እልፍ አዕላፍ ገበያዎች ስለየራሳቸው ይናገራሉ፡፡ የሚሰማ ይሰማል የማይሰማ አይሰማም፣ የሚያይ ያያል የማያይ አያይም፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተከናወኑትን የመንገድና የሕንፃ ግንባታዎች ሕዝቡ የሚያውቀው፣ የኢኮኖሚ አማካሪው ቁጥር ደርድሮለት ሳይሆን ገበያ ውስጥ በዓይኑ አይቶ አረጋግጦ ነው፡፡ የከርሰ ምድራችንን ብርቅ ማዕድን ወርቅ፣ የግብርና ምርቶች ምስር፣ አተር፣ ባቄላ፣ ሰሊጥ፣ ሥጋ፣ የቁም ከብት፣ ወዘተ ለውጭ ገበያ ተሽጦ ለሀብታሞች ከውጭ የሚገቡላቸውን የተቀናጡ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ዓይነት የሚያውቀው በገበያ ውስጥ በዓይኑ አይቶ ነው፡፡ ደሃው በሚገበያይባቸው የምግብና የመሠረታዊ የኑሮ ሸቀጦች ገበያ ውስጥ አቅርቦት ዝቅተኛ፣ ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆኑና ዋጋዎችም እንደናሩ የሚነግረንና የሚያሳየን ገበያው ነው፡፡ የእንቁላል፣ የወተት፣ የሥጋ፣ የጤፍ፣ የጥራጥሬ፣ የጎመን ዋጋ ከአሥር እጥፍ በላይ መጨመሩን ገበያው ይነግረናል፡፡

በሩብ ምዕተ ዓመቱ የአገር ውስጥ ምርት መቶ እጥፍ አደገ፣ የሕዝቡ ቁጥር ግን ያደገው በአንድ እጥፍ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ማን ነው መቶ እጥፍ ያደገውን ጉሮሯችን እንደደረቀ፣ ሆዳችን እንደጎደለ፣ ጠግቦ መብላት እንዳማረን፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ምግብ እንደናፈቀን፣ ወደ ኢንዱስትሪ ያሸጋግረናል የተባለውን የግብርና ምርት ገበያ ሳይወጣ ፀሐይ ሳይሞቀው በድብቅ በልቶ ጠጥቶ፣ ለብሶ፣ ተጫምቶ፣ ተጠቅሞ የጨረሰው? በበለፀጉት አገሮች ሁለት በመቶ ብቻ የሆነው ገበሬ ዘጠና ስምንት በመቶውን ገበሬ ያልሆነ ዜጋ አጥግቦ ይቀልባል፡፡ በእኛ አገር ግብርናው ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ ይዞ ለራሱም አልጠገበ፡፡ አሥራ አምስት በመቶ ብቻ የሆነውን በግብርና ያልተሰማራ ሕዝብም መመገብ አቅቶት ያስርበዋል፣ ያስጠማዋል፡፡ የሥጋና ቅባት ዘር ማዕድ ያለበት ድግስ ተጠርተን የብፌ ምግብ የማንሳት ተራችን ደርሶ ምግብ አንሱ ስንባል በደስታ ዓይናችን የሚበራ፣ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር የእንስሳት ተዋጽኦ ምግብ መመገብ ደስታችንን እጥፍ ድርብ የሚያደርግልን፣ ይህን ያህል የእንስሳት ተዋጽኦ ምግብ እንደ መንግሥተ ሰማያት የሚናፍቀን ሰዎች ነን፡፡ የችግራችንን መጠን የምንገልጸው ‹ተኖረና ተሞተ› በማለት ነው፡፡

ችግሩ የፖሊሲ ነው? ወይስ የፖሊሲ አፈጻጸም?

መጋቢት 16፣ ሚያዝያ 7 እና ሚያዝያ 21 በወጡ የሪፖርተር ጋዜጣ ዕትሞች በጻፍኳቸው ጽሑፎች የነፃ ገበያ ሥርዓት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሁለት ዓቢይ ጎራዎች እንደሚከፈሉ ገልጬ፣ አንዱ የፍላጎት ጎን ጎራ (የሸማቹን አቅም መገንባት) እና ሁለተኛው የአቅርቦት ጎን ጎራ (የአምራቹን አቅም መገንባት) እንደሆኑ አመልክቼአለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በአብዛኛው በሸማቹ እጅ የገባውን ጥሬ ገንዘብ መጠን የሚያበዛ የፍላጎት ጎን ፖሊሲ እንደተገበረችም ተናግሬአለሁ፡፡ ሸማቹ እጅ የገባው ጥሬ ገንዘብ በሸቀጥ ሸመታ ወቅት ወደ አምራቹ ይተላለፋል፡፡ በኢትዮጵያ በሸማቹ እጅ የገባው ከፍተኛ ጥሬ ገንዘብ የሸቀጥ ዋጋን ከማናሩም በላይ፣ ወደ ቁሳዊ ሸቀጥ አምራቹ ሳይሆን ወደ አገልግሎት ሸቀጥ አምራቹና በውጭ ምንዛሪ ተመንዝሮ ወደ የውጭ አገር በተለይም ለቻይና ቁሳዊ ሸቀጥ አምራች ነው የተላለፈው፡፡ የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ጠንሳሽ ኢኮኖሚስት ጆን ሜናርድ ኬንስ አስፋፊ የገንዘብ ፖሊሲ (Expansionary Monetary Policy) መጠቀም የሚያስፈልገው፣ ጥቅል የምርት ፍላጎት ከጥቅል የምርት አቅርቦት ሲያንስ ነው ይላል፡፡

ኢትዮጵያ አስፋፊ የገንዘብ ፖሊሲ በተጠቀመችባቸው ባለፉት ዓመታት በእያንዳንዱ ዓመት ጥቅል የምርት ፍላጎት (የግል ፍጆታ፣ የመንግሥት ፍጆታ፣ የግልና የመንግሥት መዋዕለ ነዋይ) ከጥቅል የምርት አቅርቦት (የአገር ውስጥ ምርት [ጂዲፒ] እንደሚበልጥ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው የብሔራዊ ገቢ ሰንጠረዥ (National Income Accounting) ይታያል፡፡ ኢምፖርትና ኤክስፖርትን ካሰብንም የፍላጎት ከአቅርቦት መብለጥ የባሰ ይሰፋል፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ወግና ሥርዓት ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ የአምራቹን አቅም የሚገነባ (ድጋፍ) የአቅርቦት ጎን ፖሊሲም ተግብራለች፡፡ ከፍላጎት ጎን ፖሊሲው በላይም ተጋኖ የሚወራለት የአቅርቦት ጎን ፖሊሲው ነው፡፡ ይህ በገበያ ምልከታዊ መረጃ ዳኝነት መሠረት ለወሬና ለጥቂቶች ትርፍ እንጂ፣ ለሰፊው ሕዝብ ብልፅግና ያልበቃው ድጋፍ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ውድድርንና አገሪቱ ያወጀችውን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ድንጋጌን የሚቃረንም ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ በኒዮሊበራሊስቶች ግፊት ገበሬን እንኳ አልደጉምም የሚል አቋም ይዞ ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን ለጥቃቅንና ለአነስተኛ አንቀሳቃሾች ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለጥቂት ሲራራ ነጋዴዎች በአገር ውስጥ መሬትና ብድር ከመስጠት፣ በአገር ውስጥ ከመንግሥታዊ ዕቃ ግዢ ጋር በገበያ ከማስተሳሰር ድጋፍ አልፎ፣ መንግሥት በውጭ ገበያ ሊያፈላልግላቸው አዝሏቸው ዞሯል፡፡ ከወገቡ ሊወርዱም አልቻሉም፡፡ ራሳቸው በለፀጉ፣ የሕዝብን ሕይወት አልቀየሩም፣ የሕዝብን ረሃብ እንኳ አላስታገሱም፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አቅርቦት ጎን ፖሊሲ ውድድርን የሚጋብዝና ለሁሉም አምራቾች እኩል መድረክ የሚፈጥር ሲሆን፣ የኢትዮጵያው ድጋፍ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ግን ውድድርን የሚቃረን፣ ምርታማነትን የሚቀንስ፣ አድሎአዊ፣ የኪራይ መሰብሰቢያ መድረክ፣ የሙስና ሜዳ ነው፡፡

ሆኖም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትን ሳታውቅ ከዜሮ ለተነሳችዋ ኢትዮጵያ፣ ለአምራቾቿ ወደ ምርት የመግባት መጀመርያ ምዕራፍ ድጋፍ መስጠት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ስለነበረ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ለአገር ውስጥ አምራቾች የሚቻላትን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ለአገር ውስጥ አምራቹ የሚሰጠው ድጋፍ ውጤት አልባ ሆኖ ተስፋው ተሟጦ በማለቁም ይሆናል፣ የመንግሥት እጅ ከውጭ ለሚመጡ ባለሀብቶች ተዘርግቷል፡፡ ፀረ ድጋፍ አቋም የነበራቸው ኒዮሊበራሊስቶች በተራቸው መዋዕለ ነዋይ ይዘን ብንመጣ ምን ድጋፍ ትሰጡናላችሁ የመጀመሪያው ጥያቄአቸው ሆኗል፡፡ ከድጋፉም ሌላ በነፃ ገበያ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ጋር የሚጋጩ ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀምጣሉ፡፡ አገሪቱ ልታቀርብ የምትችላቸው ድጋፎች ከሁለት ምንጮች የሚገኙ ናቸው፡፡ አንዱ ከከርሰ ምድሯና ከገጸ ምድሯ ሲሆን፣ ሁለተኛው ርካሽ የሚባለው የሰው ጉልበት ነው፡፡ አማራጭ የሌላት አገር በእነርሱ ቅድመ ሁኔታ እያስተናገደቻቸው ነው፡፡ ከርሰ ምድሯን ያሟጥጣሉ፣ የሰው ጉልበት በርካሽ ይገዛሉ፡፡

የፖሊሲዎቹ ውጤቶች በባለሙያ እንዴት ይታያሉ?

የሸማቹን አቅም ለመገንባት ገበያ ውስጥ የገባው በርካታ የጥሬ ገንዘብ መጠን ሥርጭት የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ወደኋላ እየተኮሰ፣ ዘንድሮ የፋሲካ ዶሮን አራት መቶ ብር አስገባ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አንድ ኪሎ ግራም ምስር ከሰላሳ ስምንት ብር ወደ ሃምሳ ብር ገብቷል፡፡ የሌሎች በርካታ ሸቀጦች ዋጋም በፍጥነት እያሻቀበ ነው፡፡ ገቢን አሳድጎ የሸመታ ፍላጎትን ለመፍጠር ሲባል በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በአንድ ሰው ሊሠራ የሚችልን ሥራ ሁለትና ሦስት ሰዎች በመመደብ፣ ፊስካል ፖሊሲ ከገንዘብ ሥርጭቱ ፖሊሲ (ሁለቱም የፍላጎት ጎን ፖሊሲዎች) ጋር በመተጋገዝ፣ በተፈጠረው ተጨማሪ ገቢ ምክንያት የሸማችነት አቅም አድጎ ዋጋን አናረ፡፡

በዚህ ፖሊሲ ግልጽ ሥራ አጥነት በስውር ሥራ አጥነት (ከአቅም በታች መሥራት) ተደብቆ ምርታማነት ቀነሰ፡፡ አሁን በትምህርት ገበታ ላይ ለሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች በመንግሥት መዋቅር በዚሁ ፍጥነት ሥራ ሊፈጠር ስለማይችል፣ የቀጣዩ ትውልድ ከርታታነት ከአሁኑ ይከፋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ወደ ማኅበራዊ ቀውስም ያዘግማል፡፡ ከነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ውጪ የሆነው የጥቂት አምራቾችን ብቻ አቅም የመገንባት ድጋፍ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲም ጥቂቶች ከበሩበት እንጂ፣ በገበያ ውስጥ ለሕዝብ በቂ ምርት አላቀረበም፡፡

በተወሰኑ ጠባብ የሥራ መስኮች ድጋፍ ፈላጊው እየበዛ መምጣት፣ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚም በአንድ ሰው ሊሠራ የሚችልን ሥራ ብዙ ሆኖ በመሥራት ግልጽ ሥራ አጥነት በስውር ሥራ አጥነት ተደብቆ ምርታማነት ቀነሰ፡፡ ከተቋቋሙት በቀር የፈረሱትና የሚንገዳገዱት ስለማይመዘገብ እንጂ የአብዛኛዎቹ ሥራዎች ባህሪይ ጊዜያዊ በመሆኑ፣ ስውር ሥራ አጥነቱ እንደገና ወደ ግልጽ ሥራ አጥነትም እየተመለሰ ነው፡፡ ድጋፍ ሊያገኙ ያልቻሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችንም የሥራ ገበያ ፍለጋ አስኮበለለ፡፡ በዚህ ፖሊሲም ተመሳሳይ ድጋፍ ለሚቀጥለው ትውልድና ታዳጊ ወጣቶች ሊሰጥ ስለማይችል፣ የተፈጠሩት ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችም በራሳቸው ጊዜ ስለሚታጠፉ የወደፊቱ መንከራተት፣ መሰቃየት፣ ሁለትና ሦስት የሚሸጡ ሳልቫጅ ሸሚዞች ይዞ መንገድ ዳር ገዥ ፍለጋ መጮህ ከአሁኑ ይብሳል፡፡ ወጣቶች ከመኪና ጭነት ለማውረድ ይፈነካከታሉ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ወደ ማኅበራዊ ቀውስም ያዘግማል፡፡

ከዚህ አረንቋ ለመውጣት መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት የድጋፍ አሰጣጡን ከአገር ውስጥ አምራቾች ወደ የውጭ አገር ባለሀብቶች ማዞር ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሽሚያ ገበያው አብኩተው ያልጋገሩትን እንጀራ የውጭ ባለሀብቶች እንደገና በሽሚያ ገበያ ሊያቦኩት እየተረከቡ ነው፡፡ ባዕዶቹ በነፃ ገበያ መርህ ጋግረው ያበሉን ይሆን? ወይስ የእኛ ኢኮኖሚ በሽሚያ ገበያ ከመቡካት የሚያልፍ ገና በሙከራ ላይ ያለ ነገር ነው? ሌሎች አገሮች ቢያንስ ዜጎቻቸውን የሚቀጥሩበትን ዝቅተኛ የሰዓት ክፍያ ወለል ይወስኑባቸዋል፡፡ እኛስ እንዴት ነው የተቀበልናቸው? የሕዝብ ምኞት ከውስጥ ጩልሌዎች ለውጭ ጩልሌዎች መስጠትን ሳይሆን በልቶ ማደር ነውና እንደ የውስጥ ባለሀብቶቹ ባዕዶቹም በሕይወታችን እንዳይቀልዱ አዲሶቹ ፖለቲከኞች አስቡበት፡፡

ከአምራችነትና ከሸማችነት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የኢኮኖሚ አማካሪዎቹ እያጨበጨቡ ያሉት በአንዱ በአምራችነት እጅ ብቻ ነው፡፡ የሸማችነቱን እጅ ኪሳቸው ውስጥ ደብቀውታል፡፡ የሸማችነትን አቅም ለመገንባት ገንዘብ ገበያ ውስጥ ከመበተን ሌላ፣ የቁሳዊ ሸቀጥ ምርትን እንዲያበረታታ ለማመጣጠን የታሰበም፣ የተተገበረም ፖሊሲ የለም፡፡ አምራቹ ከቁሳዊ ምርት ይልቅ ወደ አገልግሎት ምርት አደላ ብለው በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ ለመሆኑ አምራቹ የምርት ትዕዛዝ የሚቀበለው ከሸማቹ እንደሆነ አይታወቅምን? የአንድ የዓመት በዓል ዋዜማ የሁለት ሦስት ሰዓት ኮንሰርት መግቢያ ትኬት ዋጋ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ብር ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የወር ደመወዝ ጋር እኩል ሲሆን፣ አምራቹ ወደ አገልግሎት ዘርፍ ቢያደላ ምን ይገርማል?

ኒዮሊበራሊስቶቹ እንኳ የሚያከብሩትን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሕግ ጥሰው ለሠራተኛው ዝቅተኛ የሥራ ሰዓት ክፍያ ወለል ሲደነግጉ፣ ለደሃው ቆመናል የሚሉት የእኛ ኢኮኖሚ አማካሪዎች የቢጤያቸው የኮንሰርትና መሰል መዝናኛ አገልግሎቶች አሳዳጁ ገቢ እንዲያድግ ነው የሚተጉት፡፡ የ2007 ዓ.ም. ፋሲካ ሰሞን በሐዘን አሳለፍነው፡፡ በፋሲካ ዶሮ ዋጋ ያረረው አንጀታችን ሳይሽር ሥራ ፍለጋ የተሰደዱ ወጣቶች መስዋዕትነት ዓይናችንን በእንባ አረጠበው፡፡ ሁኔታዎች ካልተለወጡ የተማመንባቸው የውጭ ባለሀብቶች በሽሚያ ገበያ የተቦካውን በነፃ ገበያ ካልጋገሩ ገና ብዙ እንሞታለን፡፡ ገና ብዙ እናለቅሳለን፡፡ በጠራራ ፀሐይ በገጠርና በከተማ ሥራ ፈትቶ መንገድ ላይ የሚንከላወሰው ወጣት ብዛት፣ በጊዜያዊ የንግድ ሥራ ለዕለት ጉርሷ ጉልት የምትቸረችረዋ፣ የጀበና ቡና የምታፈላዋ ኮረዳ ቁጥር አስደንጋጭ ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን የባህርና የበረሃ አጥሮች ከመሰደድ እንደማይገቷቸው አመልካች ነው፡፡

በእነኚህ ምክንያቶችም ነው ትሪሊየን የገባው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) መጠን ኮከቡ አልሰመረለትም የሚባለው፡፡ ስለመጠኑ በቁጥር ብቻ ከማሰብ፣ በምናባዊ ዕቅድና ክንውን ፈረስ ከመጋለብ፣ እንደ ኮከብ ቆጣሪው ልጅ ምርቱ በገበያ ውስጥ ከመታየቱ ጋር፣ ከዋጋ ንረትና ከሥራ አጥነት ጋር ሊገናዘብ ይገባው ነበር፡፡ ቁጥር ቢቆለል የአብዛኛውን ሕዝብ ችግር ካልፈታ ምን ፋይዳ አለው? በጭንቅላታችን ላይ ጎፈሬ ቢከመር ወይ አናታችንን ከፀሐይ ቃጠሎና ከብርድ ይከላከልልናል? ወይስ የቅጫምና ቅማል ማርቢያ ይሆንብናል? ትሪሊየን ጂዲፒው ከረሃብ ላይከላከለን ቅጫምና ቅማል አረባብን፡፡ ምርትን ለማገበያየት የቀረበው የገንዘብ መጠን በገበያ ዋጋ ካልተለካው ምርት ጋር ሊመጣጠን ባለመቻሉ በዋጋ ግሽበት የሰደድ እሳት ተጠቃን፡፡

የግላዊ ኢኮኖሚውና የብሔራዊ ኢኮኖሚው ተዛምዶ

የግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚው ተዛምዶ መገለጫ ሰዎች በተፈጥሮ ባህሪያቸው ምንጊዜም በሚያወጡት ወጪ ልክ ጥቅማቸውን ከፍ ለማድረግ የሚበጃቸውን በመምረጥ አዋቂዎች ናቸው (People are Rational) በሚለው የግላዊ ኢኮኖሚ እሳቤ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት የአዳም ስሚዝና የሌሎች ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች ዋናው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ጥናት መስክ የነበረ ሲሆን፣ ይህም በተሃድሶ ጥንታውያን በቀጣይ ጠቀሜታ (Marginal Utility) እና በቀጣይ ምርታማነት (Marginal Productivity) አለካክ፣ የሸቀጥ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓቶች ዳብሮ የግላዊ ኢኮኖሚ (Microeconomy) ጥናት ድንጸ ሐሳብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምንጊዜም ሸማቾች በሚሸምቱት ሸቀጥ ዋጋ ልክ የሚያገኙትን ጠቀሜታ ከፍተኛ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አምራቾችም በሚያመርቱት ምርት ወጪ ልክ የሚያገኙትን ትርፍ ከፍተኛ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ይህ ጥረትም ሰውን ኢኮኖሚያዊ ሰው (Economic Man) ያደርገዋል፡፡

ይህንን ነው እንግዲህ የዘመኑ የኖቤል ተሸላሚዎችን ጨምሮ ብዙ የፍላጎት ጎንና የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚስቶች፣ ለብሔራዊ ኢኮኖሚው ዕድገት የግሉ ኢኮኖሚ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ነው የሚሉት፡፡ ለብሔራዊ ኢኮኖሚው ዕድገት የግሉ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ መሠረትነት (Microeconomic Fundation of the Macroeconomy) ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡ የግለሰቦች በሸማችነትና በአምራችነት የሚበጃቸውን በመምረጥ አዋቂ ሆነው የገበያ ዋጋ አወሳሰን ላይ ተፅዕኖ ማሳደር፣ ከመንግሥታዊ የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ጋር በጥምረት ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ያሳድጋል፡፡ ይህን የሚለው ኢኮኖሚክስ ነው እኔ አይደለሁም፡፡ ኢኮኖሚክስ ተምሮ ይህን የማያውቅ ካለ በዲግሪ ላይ ዲግሪ ቢጭንም ማስትሬት ዶክትሬት ቢኖረውም ገና ኢኮኖሚስት አልሆነም፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1965 ዓ.ም. ጂማ ከተማ መጥተው አንድ ቀን እንኳ ጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን አፈጮሌ ሰዎች ግራ አዝማች ቀኝ አዝማች ብለው ሾመው ተመለሱ፡፡ ማስትሬት ዶክትሬት ካልተናገረ፣ ካልጻፈ፣ ካላስተማረ፣ ካልሠራበት፣ ሙያዊ ውጤት ካላሳየ የንጉሡ ግራ አዝማችነትና ቀኝ አዝማችነት ነው፡፡

የግላዊና የብሔራዊ ኢኮኖሚው ተዛምዶ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ምን ይመስላል? በግልና በጋራ እያደግን ነው? ወይስ እየተሻማን ነው? ከየሽሚያ ሰውነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ሰውነት እየተቀየርን ነው? ወይስ ከኢኮኖሚያዊ ሰውነት ወደ የሽሚያ ሰውነት እየተቀየርን ነው? ራሳቸውን የሚቃረኑት የእኛ ኢኮኖሚ አማካሪዎች ግላዊ ኢኮኖሚው በኪራይ ሰብሳቢነት የተጨማለቀ ነው ይላሉ፡፡ አፍታም ሳይቆዩ ብሔራዊ ኢኮኖሚው በፍጥነት እያደገ ነው፡፡ ወደፊትም በዚሁ ፍጥነት ያድጋል ይላሉ፡፡ መሠረቱ የተበላሸ ቤት መጨረሻው ምን እንደሆነ አላወቁምን? ይህ ነው ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚው በአንድነት፣ በተደጋጋፊነትና አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ አድራጊ መሆናቸውን፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግም የሁለቱ ጥምረትና ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን ለማየት ያልቻሉ የሚያደርጋቸው፡፡ የሸማቹ ጠቀሜታ ከፍተኛ የሚሆነው በጤናማ አስተሳሰብና ሥነ ምግባር ሸቀጥን ከሸቀጥ ማማረጥ ሲችልና የሚመረጥ የሸቀጥ ዓይነትም በብዛት ሲኖር ነው፡፡ ከምግብ፣ ከልብስና ከመጠለያ ይልቅ ከሱሶች የሚገኘው ጠቀሜታ የሚበልጥበት ሰው ጤናማ አስተሳሰብ የለውም፡፡

የአምራቹ ትርፍም ከፍተኛ የሚሆነው በውድድር ላይ ተመርኩዞ ምርታማነቱን ሲያሳድግ እንጂ፣ በሕዝብ ወጪ ተደጋግፎ በሰው ትከሻ ተሻግሮ ወይም አታሎ በአቋራጭ ለመክበር ሥነ ምግባር ሲያጎድል አይደለም፡፡ የሸማቹ ግብይይት መጣመም የአምራቹን ምርት ያጣምመዋል፡፡ የአምራቹ ምርት መጣመም የሸማቹን ግብይይት ያጣምመዋል፡፡ የግለሰቦች (ሸማቾችና አምራቾች) ጤናማ የሸማችነት አስተሳሰብና የአምራችነት ሥነ ምግባር ማጣት፣ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ክፉኛ ይጎዳዋል፡፡ የእምቧይ ካብ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት በርካታ ዓመታት ኅብረተሰባችን ቀድሞ የነበረውን መልካም የሸማችነትና የአምራችነት ባህሪይና አዋቂነቱን አጥቷል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ሰውነት ወደ የሽሚያ ሰውነት ተቀይሯል፡፡ ገበያዎቻችን ከመጥራት ወደ አለመጥራት፣ የሸቀጥ ዋጋን አውቆ ያለጭቅጭቅ ከመክፈል ወደ አለማወቅና ንትርክ ተጉዘናል፡፡ ዋጋዎች በቀናትና በሳምንታት ይለዋወጡብናል፡፡ ለዚህም ምክንያቶቹ በአንድ በኩል በግላዊ ኢኮኖሚው የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት መዛባት፣ በሌላ በኩል በብሔራዊ ኢኮኖሚው ደረጃ ሁለቱ የፍላጎት ጎንና የአቅርቦት ጎን ፖሊሲዎች ተደጋግፈውና ተቀናጅተው አለመሄዳቸው ነው፡፡ በገበያ ውስጥ ከመጠን ያለፈ ጥሬ ገንዘብና ከልክ በላይ የመንግሥት ሥራ ቅጥር ፊስካል (ሁለቱም የፍላጎት ጎን ፖሊሲዎች) ምክንያት፣ ገንዘቡም ዋጋ አጣ፣ የሠራተኛው ምርታማነትም ቀነሰ፡፡

ገንዘቡ ዋጋ ያጣው ገቢ አሁንም ቢሆን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ የገቢ ዕድገት ከምታማነት ዕድገት በላይ ስለሆነ ነው፡፡ ምርታማነት የቀነሰው የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ዕድገት፣ የሥልጠና ዕድል፣ ሙያዊ ክህሎትን መገንባት፣ ወዘተ የሚቻለው አለቃን በማምለክ እንጂ ችሎታን አዳብሮ ውድድር ውስጥ በመግባት ስላልሆነ ነው፡፡ በጭፍን ድጋፍ መስጠት የአቅርቦት ጎን ፖሊሲም ግልጽ ሥራ አጥነት በስውር ሥራ አጥነት ተተክቶ ምርታማነትን ቀነሰ፡፡ ቀድሞ የተደራጁት ወጣቶች በሙሉ አቅማቸው ሳይሠሩ በፊት በእነርሱ ላይ ሌሎች ማደራጀት፣ የቀድሞዎቹንም አዲሶቹንም በሙሉ አቅማቸው እንዳይሠሩና ምርታማ እንዳይሆኑ አደረገ፡፡ ሥራ ፈጠራ በብሎኬት ምርት፣ መስኮትና በር መግጠም፣ አልባሳት፣ ቦርሳና ቀበቶን የመሳሰሉ የግል መጠቀሚያዎችን ማምረት ጀምሮ አሁን ወደ ጀበና ቡና፣ ቦርዴ (ሻሜታ) ጠመቃ፣ የዓረብ ሱቅ፣ በቆርቆሮ ግድግዳ ደሳሳ ጎጆ የሆቴል ኪዮስክ ወርዷል፡፡ ከዚህ በታች ወዴት እንደሚወርድ አይታወቅም፡፡

ምርታማ ሆኖ ገንዘብ ማግኘት ካልተቻለ አጭበርብሮም፣ ቀምቶም፣ ሰርቆም፣ የሰው አካልንም ቢሆን ደልሎ ገንዘብ ለማግኘት ይሞከራል፡፡ ውድድር ሳይሆን ሽሚያ ይፈጠራል፡፡ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው ይህ አጉል የመስገብገብ፣ የመሻማት፣ የመሻሻጥ ባህሪይ ነው፡፡ ሁላችንም በባህሪይ፣ በአስተሳሰብና መስሎ በመታየት ደላላ እየሆን ነው፡፡ በመንግሥት ድጋፍ በሦስት ሺሕ ብር የፈጠራ ሥራ ጀምሮ በዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገብ፣ መቶ ሺሕ ብር ለደላላ ከፍሎ ወደ ሞት ለመሄድ መደራደር፣ ለጥቂት ደቂቃዎች መዝናኛ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣት፣ ቅጥ ላጣ የውጭ አገር ጉዞ የቅንጦት ወጪ ማድረግ፣ ምልክት የጥሬ ገንዘብ ከጓሮ የሚሸመጠጥ ቅጠል መምሰል ነው፡፡

አምና በመቶ ሺሕ ብር መነሻ ካፒታል የከተማ ሥራ ጀምሬ ዘንድሮ ሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ በግማሽ ሔክታር መሬት የግብርና ሥራ አሥር ሚሊዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ የወጣቱን ሥነ ልቦና ሰለበ፡፡ የሥራ ባህል ጠፋ፡፡ ገንዘብ ተሠርቶ የሚገኝ ሳይሆን ከሜዳ የሚታፈስ ወይም ጓሮ ከበቀለ ዛፍ የሚሸመጠጥ መሰለ፡፡ መቶ ሺሕ በትኖ ሚሊዮን ለማፈስ የተሰናዳ ትውልድ ተፈጠረ፡፡ ከሠርቶ በሌው አውርቶ በሌውና ዘሎ በሌው በዛ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን አቋርጦ ጊታር ማንሳት ተለመደ፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ በተመሳሳይ ቁሳዊ ሸቀጦችና የአገልግሎት ምርቶች ጠባብ ምኅዳር እየተጨናነቁ ካሉት ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ባሻገር፣ አዳዲስ ከፍተኛ ድርጅቶች ሲከፈቱና ተጨማሪ ሠራተኞች ሥራ ሲቀጠሩ በዓይናችን እናያለን፡፡ ይህ አያጠራጥርም፡፡ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችም ተቋቁመዋል፣ ተጠንስሰዋልም፡፡

ሆኖም ይህ የጥቂቶች በጠባብ ሜዳ እንቅስቃሴ ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ዓባይን በጭልፋ ነው፡፡ በሺዎች ተሠርቶ ሚሊዮኖች አይጠግቡም፡፡ ይህም ሆኖ ግማሽ ያህሉን የአገር ውስጥ ምርት በያዘው ጠቃሚም አሰስ ገሰስም በሆነው የአገልግሎት ምርት ምክንያት፣ የሸማቹ ገቢ ከምርታማነቱ በላይ በፍጥነት አድጓል፡፡ በሌላ በኩል በምርት እጥረት በሚከሰት የዋጋ ግሽበት ትርፍ ማግኘት ላይ ያተኮረው የቁሳዊ ሸቀጥና አገልግሎት ምርት አምራቹ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በጠባብ የኢኮኖሚው ምኅዳርና በጥቂት የምርት ዓይነቶች የገበያ ሽሚያና መጨናነቅ ተፈጥሯል፡፡ በአንዳንድ ድርጅቶችና በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ምርታማነት ሊጨምር ቢችልም እንኳ፣ በአገር ደረጃ ግን ምርታማነት ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አጠቃላዩ የአካላቶቹ ድምር ብቻ አይደለም የራሱ የሆነ ባህሪይም አለው፡፡ ለዚህም ነው የድርጅቶች የተናጠል ምርታማነት የአገር ምርታማነት ሊሆን የማይችለው፡፡ እንኳንስ ብዙ ሚሊየነሮች ብዙ ቢሊየነሮችም ቢፈጠሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ግላዊ ኢኮኖሚው በሸማችነት የጠቀሜታ ምርጫና በአምራችነት የምርታማነት ሥሌት ዋጋን እንዲወስኑ በማድረግ፣ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲው ከብሔራዊ ኢኮኖሚው መንግሥታዊ የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ጋር ተጣምሮና ተቀናጅቶ ካልተጓዘ አገር በዘላቂነት ልታድግ አትችልም፡፡ የኢኮኖሚክስ ሕግ ነው፡፡

በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ የሕዝቡን ምርታማነት ሊጨምሩ የሚችሉ የመጠን ለውጦችና መሻሻያዎች ባለፉት ዓመታት ታይተዋል፡፡ ቢሆንም ሰውን ማልማት ስንት ባለዲግሪ እንዳለ ለመቁጠር ከሆነ ቁጥር አምላኪዎች እንሆናለን፡፡ በዚህም ላይ የምናፈራቸው ወጣቶች ፌርማታ ለባዕድ አገር ሎሌነት ሥራ መሆኑ ከቀጠለ፣ አገር አቀፉ ምርታማነት ሊያድግ አይችልም፡፡

በመሠረተ ልማትና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ባለፉት ዓመታት የተሰሩት ሥራዎች የሕዝቡ የተጠቃሚነት ደረጃ እንደ የሀብት መደቡ፣ የሚኖርበት አካባቢ፣ የዕድሜው ክልል፣ ቢለያይም በጥቅሉ ለሁሉም ሰው ለኢኮኖሚ ዕድገትም ለልማትም ስለሚጠቅም መልካም ነው፡፡ ሆኖም ግን ለግለሰብ ሊሸጥ የሚችል፣ በግለሰብ ሊለማና የገበያ ዋጋ ሊኖረውም ይገባ የነበረን የጋራ ልማት ሥራ አድርጎ በመንግሥት እጅ አፍኖ ይዞ የገበያ ዋጋ እንዳይኖረው ማድረግ ምርቱን ትክክለኛ ዋጋ ያሳጣዋል፡፡

የጋራ በሆነ መሬት ላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ መሥራት የሚቻለው በጋራ ብቻ ነው፡፡ የጋራ የሆነም የግል አይደለም፡፡ የግል ያልሆነም ገበያ አይወጣም፡፡ ገበያ ያልወጣም የገበያ ዋጋ የለውም፡፡ የገበያ ዋጋ የሌለውም በገበያ ዋጋ በገንዘብ አይተመንም፡፡ ስለዚህም በሪፖርት ከምናየውና ከሚነገረን የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) መጠን ገሚሱ የገበያ ዋጋ የሌለው ምናባዊ ስሌት ነው፡፡ የኑሮ መሐንዲሱ ኢኮኖሚያዊ ኑሮን ወደ ምናባዊ ሥሌት ከወሰደው የሕዝብ ገቢ መጠንና ኑሮም በገበያ ተለክቶ እውነቱ የሚታወቅ ሳይሆን ምናባዊ ይሆናል፡፡ አመለካከቱና አስተሳሰቡም የኑሮው ነፀብራቅ ነውና ኑሮውን ተከትሎ ምናባዊ ይሆናል፡፡ ሲያገኝም ሲያወጣም በምናባዊ ሥሌት ነው፡፡ ሳይበላ የበላ መስሎ፣ ሳይጠጣ የጠጣ መስሎ፣ ሳይደላው የደላው መስሎ፣ ያላመነውን ያመነ መስሎ፣ ያልተቀበለውን የተቀበለ መስሎ፣ የናቀውን ያከበረ መስሎ፣ የጠላውን የወደደ መስሎ በመታየት በምናባዊ ዓለም ውስጥ ይኖራል፡፡

ሕዝቡ ከምናባዊ ዓለም ወጥቶ ገሃዱን ዓለም እንዲቀላቀል የኑሮ መሐንዲሱ ኢኮኖሚስት አለ ብሎ በወረቀት ላይ የሚጽፈውን የምርት መጠን ለሽያጭ ወደ ገበያ አውጥቶ፣ በበያ ዋጋ አስተምኖ እውነተኛውን በገበያ ዋጋ የተለካ የምርት መጠን ያሳየን፡፡ ያለበለዚያም የገንዘብ አቅርቦቱ ለገበያ በቀረበው ምርት መጠን ልክ ሆኖ በዋጋ ግሽበት ስቃይ እንዳን፡፡ እኔ እንኳ በሩቁ ከማውቀው ወደ ገበያ ከማይቀርቡና ማገበያያ ገንዘብ ከማያስፈልጋቸው ምርቶች ውስጥ ከጠቅላላ ጂዲፒው አንድ ሦስተኛው የሚሆነው፣ ገበሬው ከራሱ እንደገዛ ተቆጥሮ በምናባዊ ሥሌት በገንዘብ የሚለካው የግብርና ምርት ይገኝበታል፡፡ በወረቀት ላይ የሚመለከቱ የአገር ውስጥ ምርት መጠን ቁጥርና ለፕሮፓጋንዳ የሚያገለግሉ ጥንስስ ፕሮጀክቶች ስም ጋጋታ ሳይሆን፣ የአጠቃላዩ ሕዝብ ምርታማነት ብቻ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ነው፡፡

አንጀት ላይ ጠብ የሚለው ሺዎች ለሚሊዮኖች አስበውና ተደራጅተው ሲሠሩ ሳይሆን፣ የአጠቃላዩ ሕዝብ ሚሊዮኖች ለራሳቸው አስበው በገበያ ውስጥ ተወዳድረው እንዲሠሩ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሲመቻችላቸው ነው፡፡ ‹‹ጧት ጧት ዳቦአችንን ጠረጴዛችን ላይ የምናገኘው በዳቦ ጋጋሪው የፅድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ለራሱ ገንዘብ ለማግኘት ሲል በሚሠራው ሥራ ነው›› አዳም ስሚዝ፡- ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጠንሳሽ፡፡ ‹‹ልማት ማለት አንድ ሰው ሊሆንና ሊያደርግ የሚፈልገውን ሕጋዊ ነገሮች የመሆንና የማድረግ ነፃነትና አቅም ሲያገኝ ነው›› አማርተያ ሴን፡- በ1998 በልማት ኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ፡፡

መፍትሔው ምንድነው?

ይህን ዓይቶ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንደገና ካልመረመረ፣ የኢኮኖሚ አማካሪዎቹን ችሎታ ካልተጠራጠረ፣ የወረቀት ላይ ቁጥርን ብቻ ሳይሆን ገበያዎችን ተንትናችሁ ተርጉሙልኝ ካላላቸው ተያይዘን ገደል መግባታችን ነው፡፡ በፖለቲካው የተፈለገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓይነት ማዕከላዊ ዕቅድንና ነፃ ገበያውን ማቀላቀል ቢሆንም፣ የቅልቅሉን ዓይነት በብልኃት መምረጥ፣ ምናባዊ የዕቅድ ክንውኑን ብቻ ሳይሆን በገሃድ በዓይን የሚታየውን የገበያውን ሁኔታ መከታተል፣ ተነጣጥለው ለየራስ እየሄዱ ያሉትን ማዕከላዊ ዕቅድና ገበያውን ማቀናጀት ያስፈልጋል፡፡ ጌትነት እንየው በግጥሙ እኛው ገዳዮች እኛው ሟቾች እኛው አልቃሾች ብሎ የሞቱ ልጆችን ያሰደዳቸው ኑሮ መሆኑን ልብ በሚነካ ነገር ነግሮናል፡፡ ለእኔ ጌትነት ገጣሚ ብቻ ሳይሆን ዝም ካለ ኢኮኖሚስት (የኑሮ መሐንዲስ) የሚበልጥ ኢኮኖሚስት ነው፡፡

የገበያውን ምልክትና ቋንቋ ያልተረዱ፣ ይህ ከዚያ ይበልጣል ያ ከዚህ ያንሳል እያሉ ምናባዊ ቁጥር ገጣጥመው ማማለል የለመዱ፣ በምናባቸው አቅደው በምናባቸው የፈጸሙትን ማነፃፀር ብቻ የሚችሉ፣ ወደ ገበያ ወረድ ብለው ተግባርን ያላዩ ቁጥር አምላኪ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ገበያው በሽሚያ እርሾ እየቦካ መሆኑን ማየት ተስኗቸዋል፡፡ ሙያቸው ሰው እያስራበ፣ ሰው እያስኮበለለ፣ ሰው እያስገደለ እንደሆነ አልተሰማቸውም፣ ልባቸው ደንድኗል፡፡  ጂዲፒው አሥር ቢሊዮን ብር በነበረ ጊዜ አራት ብር ብቻ የነበረ የፋሲካ ዶሮ ዋጋ፣ ጂዲፒው ትሪሊዮን ብር ሲሆን አራት መቶ ብር የገባበትን ምክንያት የምርት አቅርቦትና የምርት ዋጋ ተዛምዶ የሚጽፉት የወረቀት ላይ ቁጥር አይነግረንም፡፡ በምርጫ 2002 ፋሲካ ሰሞን አርባ ብር የነበረ የዶሮ ዋጋ በምርጫ 2007 ፋሲካ ሰሞን አራት መቶ ብር ከገባ፣ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል፣ በምርጫ 2007 ሚሊዮኖች ከተሰደዱ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሰደዱ እንደሚችሉ አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት ሊያስቡበት ይገባል፡፡

ያሰቃየን ካይዘንን፣ ውጤት ተኮርን፣ ቢፒአርን፣ ቢኤስሲን አለማወቅ አይደለም፡፡ ያሰቃየን ደላላው አይደለም፣ ነጋዴውም አይደለም፡፡ ያሰቃየን የእነኚህ ሁሉ ገዢ ቃል የሆነው ገበያው የሚነግረንን አለመስማት ነው፡፡ እኛው ከነፃ ውድድራዊ ገበያነት ወደ የሽሚያ ገበያነት የለወጥነውን ገበያውን አለማዳመጥ ነው፡፡ የበላን የበረሃ አሸዋ አይደለም፣ ባህርም አይደለም፣ ያረደንም ሰው አይደለም፡፡ የበላን ያረደን፣ ለስደት፣ ለስቃይ፣ ለሞት፣ ለዋይታ የዳረገን ገበያ ነው፡፡ ሰው አገር ሞልቶና ተርፎ እኛ አገር የጠበበውና የተኮማተረው፣ መኮማተሩንም ራሱን ሳይደብቅ የሚነግረን የሥራና የእንጀራ ገበያ ነው፡፡ ገበያን እንደ ካይዘኑ፣ እንደ ውጤት ተኮሩ፣ እንደ ቢፒአሩ፣ እንደ በኤስሲው የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓቱ ቁልፍና ገዥ ቃል አድርገን ልናውቅ፣ ልናጠናና ልናስጠና በተገባን ነበር፡፡

እንደ መርህ በአዋጅና በሕግ ስለተደነገገው ነፃ ገበያ ሥርዓት ምን ያህል እናውቃለን? አዋጁንና ሕጉን አለማወቅም ሆነ አለመተግበር በሕግ ድንጋጌ ባያስቀጣም በኑሮ ያስቀጣል፣ እየተቀጣንም ነው፡፡ ገበያው ያሰድደናል ያስገድለናል፣ ጥቂቶችንም ገበያው ሰማይ ይሰቅለናል፣ ጥቂቶችንም ገበያው ያንቀባርራል፣ ያንደላቅቃል፣ ያመፃድቃል፡፡ የሚጻፉትን ቁጥሮችና የገበያውን ምልክት በማያገናዝቡ፣ የእኛን የምርትና የሸመታ ምርጫ ሥነ ልቦና በማያውቁ፣ እኛ በገበያዎቻችን ውስጥ ልናገኛቸው የምንፈልጋቸውን የሸቀጦች ዓይነት በማይረዱ ባዕዳን አማካሪዎች እገዛ፣ ምክርና ትዕዛዝ ገበያውን ማየትና የገበያውን ቋንቋ መስማት በተሳናቸው የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጓዳ ውስጥ፣ በማዕከል ታቅዶ የሚተገበር ፖሊሲ ጎዶሎ ነው፡፡ የውጭውን አገር ጽንሰ ሐሳብና ልምድ ብቻ ይዞ ምድሩ ሳይታወቅ ሰማይ መቧጠጥ ነው፡፡ በሰው አገር ዕድገት ሞዴል ጉጉት፣ ናፍቶትና ምኞት ራስን መደለል የልማትን ትርጉም ሳያውቁ ልማታዊ ነኝ ማለት የሕዝብ ሕይወትና ኑሮን የሙከራ ጊዜ ማድረግ ነው፡፡ ለአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታና ለሕዝቡ ሥነ ልቦና በቂ ትኩረት አለመስጠት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በልማታዊ መንግሥትነት ተምሳሌት የምታደርጋቸው የጃፓን፣ የደቡብ ኮሪያና የቻይና ኢኮኖሚ ፖሊሲ ህዳሴ ዘመነ ንግድ (Neo-Merecantalism) ሲሆን፣ ስትራቴጂው ኤክስፖርትን ከኢምፖርት አስበልጦ በውጭ ኢኮኖሚ ንግድ አትራፊ መሆን ነው፡፡ ራሷ በምትከተለው አስፋፊ የገንዘብ ሥርጭት የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ግን፣ በአገር ውስጥ የምርት ፍላጎት ከምርት አቅርቦት ስለሚበልጥ ምንጊዜም በውጭ ንግድ ሰፊ ጉድለት ይታይባታል እንጂ አትራፊ ልትሆን አትችልም፡፡ ቁጥር ብቻ እየታየ የሸማቹን አቅም ለመገንባት የሚረጨው የጥሬ ገንዘብ መጠን ወደኋላ ተኩሶ ዋጋን በማናር ጀርባችንን አቁስሎታል፡፡ የአምራቹን አቅም ለማሳደግ ለጥቂቶች የሚሰጥ ያዝ ለቀቅ ድጋፍ ግብታዊ ዕርምጃም ነቀዝ ፈልፍሏል፡፡ ከቁጥር ቁማርና ከግብታዊ ዕርምጃ ወጥተን ከፈጠርነው አርቲፊሻል የሽሚያ ገበያ ተላቀን፣ ወደ አወጅነው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ካልገባን ላንነሳ ተሰናክለን እስከምንወድቅ ኑሯችን የአቦ ሰጥ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ በአቦ ሰጥ ይገኛል በአቦ ሰጥ ይታጣል፡፡

የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አወቃቀርና አካሄድ በውስጣዊ ኃይሎች እንቅስቃሴ የሚመራ ሥርዓት (System) ነው፡፡ ላለመሰቃየት፣ ላለመሰደድ፣ ላለመሞት፣ ላለማልቀስ በአቦ ሰጥ ላለመኖር ከሽሚያ ገበያ ወጥተን የነፃ ገበያ ሥርዓትን መዘርጋትና የሥርዓቱን ውስጣዊ ኃይሎች እንቅስቃሴ ማወቅና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ሰዎች ገበያ ውስጥ የሚያዩት ከኢኮኖሚ አማካሪዎቹ ሪፖርት ጋር አልጣጣም ብሏቸው የአገር ውስጥ ምርትን አሥር አንድ በመቶ ማደግ ሊጠራጠሩና ሐሰት ነው ሊሉም ይችላሉ፡፡ እኔ ግን በራሴ መንገድ ለክቼ ያወቅሁት ነገር ስለሌለ ለመጠራጠርም አልቻልኩም፡፡ ሐሰት ነውም አልልም፡፡ ህሊና ያለው የብሔራዊ ገቢ ሒሳብ ባለሙያ ዓለም አቀፍ የአለካክ ዘዴ ተጠቅሞ በምናባዊ ሒሳብም ቢሆን ለክቶታል ብዬ አምኜ እቀበላለሁ፡፡ እኔ እርግጠኛ ሆኜ የማውቀው በዓይኔ የማየውና የምለው ሎሚና እምቧይ ተቀላቅለው እየተቆጠሩ ስለሆነ የእምቧዩ መብዛት የአገር ውስጥ ምርቱን ማሳበጡን ነው፡፡ ይህ ግን የአገር ውስጥ ምርቱን ከሚያሳብጡት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው፡፡ ሌሎችም በዚህ ጽሑፍ የማልገልጻቸው በባለሙያ ደረጃ ብቻ ለክርክር ሊቀርቡ የሚችሉ ረቀቅ ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡

የአገር ውስጥ ምርት በግሳንግስ ምርቶች ማበጡ የምርታማነት ማደግ አይደለም፡፡ ያበጠ ነገርም ይፈርጣል፡፡ ኢኮኖሚ ሲፈርጥ ደግሞ ማኅበራዊ ቀውስ ያመጣል፡፡ ‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል› ተረት እንዳይተረትብን፡፡ የብሔራዊ ገቢ ሒሳብ ባለሙያው በተቀመጠለት የማዕከላዊ ዕቅድ የጊዜ ገደብ አገሪቱን በእጁም በእግሩም ገፍቶ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማድረስ አስቦ፣ በነፃና በጋራ የሚሠራውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በምናባዊ ሒሳብ የአገር ውስጥ ምርት ሥሌት ውስጥ አካቶ ሊሆንም ይችላል ምርቱን ያሳበጠው፡፡ ኢኮኖሚ ከቁጥር ሌላ ሥነ ልቦናዊ ጉዳይም ነው፡፡ የኑሮ ጉዳይም ነው፡፡ የጉሮሮ ጉዳይም ነው፡፡ በቁጥር ብቻ አይለካም፡፡ እንደ ዶሚኖ ጨዋታ ቁጥር በመገጣጠም ብቻም የሚገነባ አይደለም፡፡ የሕንፃ መሐንዲስ ቢሳሳት ሕንፃ ይደረመሳል፡፡ የሰው ኑሮ መሐንዲስ ሲሳሳት ግን ሕይወት ይጠፋል፣ ሕዝብ ያልቃል፣ ትውልድ ይረግፋል፣ አገር ይበጠበጣል፡፡ በዓይናችን እያየነው ነው፡፡

የፍላጎት ጎን ብሔራዊ ፖሊሲውም ሆነ የአቅርቦት ጎን ብሔራዊ ፖሊሲው በቁጥር መጠን ብቻ ሳይሆን፣ በገበያ ምልክት መረጃም መለካትና መቃኘት አለባቸው፡፡ ለአምራቹ ያልተገባ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ የሸማቹን የገቢ ሥርጭት በማመጣጠን ንጉሥ የሆነው ሸማቹ በሸመት ምርጫውና በዋጋ አወሳሰን አቅሙ እንዲያዘው፣ እንዲሸልመውና እንዲቀጣው ማድረግ ይበጃል፡፡ ከአምራቹ ይልቅ በሸማቹ ላይ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በብዙ አገሮች ለመዋዕለ ንዋይ ውሳኔ የሰነድ (የቦንድና የአክሲዮን) ገበያዎች ዋጋ ወደ ላይ መውጣትና ወደ ታች መውረድ ምልክቶች፣ ለምርት መጠን ውሳኔ የሸማቾች ዋጋ አመልካቾች፣ ለሥራ ገበያ ምንዳ ውሳኔ የሥራ አጥ መጣኝ ምልክቶች፣ በየቀኑ በየሳምንቱ፣ በየወሩና በየዓመቱ ይለካሉ፡፡ የፖሊሲ መቃኛ መረጃዎች ሆነውም ያገለግላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገበያይባቸውን ገበያዎች አይተው የማያውቁ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ውጤቶቻቸውን የሚለኩት ጓዳቸው ውስጥ ተቀምጠው በወረቀት ላይ ዕቅድ ክንውን ብለው በምናባቸው ያሰፈሯቸውን ቁጥሮች በማነፃፀር ነው፡፡ ከድህነትና ከችግር ለመውጣት መፍትሔው አጭር ነው፡፡ በአምራቹ ላይ ሸማቹን ለማንገሥ፣ ፍጆታንና ምርትን ለማመጣጠን የሚያስችል ሙያዊ ችሎታ ያላቸውን ኢኮኖሚስቶች በመጠቀም ከገበያው ሁኔታ ጋር የሚስማማ ፖሊሲ መንደፍ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...