Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርናስ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ኃላፊነታቸውን ለቀቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ተቋማት የመልካም አስተዳደር እንዲገነቡ ለማስቻል የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት የቀድሞው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ዘገየ ኃላፊነታቸውን ለቀቁ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት አቶ አያሌው ኃላፊነታቸውን የለቀቁት ከንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ጋር ባለመግባባታቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኃላፊነቱን እንዲለቁ ግፊት ተደርጎባቸዋል የሚል ቢሆንም አቶ አያሌው ግን ይህንን አስተያየት አልተቀበሉም፡፡ ‹‹ከተቋሙ ፕሬዚዳንትነቴ የለቀቅሁት በፈቃዴ ነው፤›› ያሉት አቶ አያሌው፣ ከተቋሙ ፕሬዚዳንትነት የለቀቁበት ዋናው ምክንያታቸው በኃላፊነት የተመደቡት ሥራ ከግል ሥራቸው ጋር ባለመጣጣሙ ነው፡፡ ተቋሙ አዲስ እንደመሆኑ መጠን የተሻለ ጊዜ ወስዶ ሊሠራ በሚችል ሰው እንዲመራ ለማድረግ በግል ፍላጎታቸው የለቀቁ መሆኑንም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በግፊት ወጥተዋል የተባለውን አስተያየትም በፍጹም የማይቀበሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እስካሁንም ባለባቸው የጊዜ ጥበት ለተቋሙ መሥራት ያለባቸውን ያህል አለመሥራታቸውንም በመግለጽ፣ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን የሚያመለክተውን ደብዳቤ በአቶ ኤልያስ ገነቴ ለሚመራው የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቦርዱ ለደብዳቤው ምን ምላሽ እንደሰጠ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እኔ መልቀቂያዬን አስገብቻለሁ፡፡ የተቋሙን ሠራተኞች ሰብስቤ ኃላፊነቴን መልቀቄን ገልጫለሁ፤›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ በንግድ ኅብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር እንዲሰርፅ በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ የሚሠራ ነው፡፡ ኩባንያዎች በራስ ተነሳሽነት የንግድ ሥራ ሥነ ምግባር ደንብ በመቅረፅና በዚሁ ደንብ መሠረት እንዲሠሩ ማድረግ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የንግድ ድርጅቶች ለአገሪቱ ሕጎች ተገዢ እንደሆኑ፣ ኩባንያዎች መልካም የንግድ ውድድር እንዲኖራቸውና ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ለማድረግ ጭምር የተቋቋመ ነው፡፡ ተቋሙ በእስካሁኑ ቆይታው ይኼነው የሚባል ሥራ እንዳልሠራም ይነገራል፡፡ አቶ አያሌውም ተቋሙ አዲስ በመሆኑ የቢሮ ማደራጀት ሥራው ጊዜ መውሰዱን ገልጸው፣ ይህም ቢሆን ግን አንዳንድ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ ማድረጋቸውንና በተመሳሳይ ዓላማ የተሰማራው አፍሪካዊ ተቋም አባል መሆን መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በቂ ሥራ አለመሠራቱን ግን ይስማሙበታል፡፡

አቶ አያሌው ይህንን ተቋም በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተሰየሙት ለሁለት የምርጫ ዘመን ነው፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ በኋላ ወዲያው የተቋሙ ፕሬዚዳንት ሆነው መሥራት ጀምረዋል፡፡ በወቅቱ አቶ አያሌው የንግድ ምክር ቤቱን ፕሬዚዳንትነት ካስረከቡ በኋላ ወደ ተቋሙ ፕሬዚዳንትነት መሸጋገራቸው አግባብ አልነበረም የሚል ትችት የሰነዘሩ ነበር፡፡ በተለይ እርሳቸው በፕሬዚዳንትነት ይመሩት የነበረው ንግድ ምክር ቤት ውስጥ ከተፈጠረው ውዝግብ ጋር ተያይዞ ስማቸው ይነሳ ስለነበር፣ የመልካም አስተዳደርን የሚመለከተውን ተቋም መምራት አልነበረባቸውም ነበር የሚሉም አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ ለዚህም ንግድ ምክር ቤቱ በፍርድ ቤት ተከሶ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲታገድ የተደረገበትንና የቀድሞ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይገቡ የተላለፈውን ውሳኔ ያስተላለፉ መሆናቸውን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡

አቶ አያሌው ከንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትነታቸው ከመልቀቃቸው ቀደም ብሎ ወደ አራት ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ወጪ ይጠይቃል የተባለውንና በንግድ ምክር ቤቱና በአዲስ አበባ አስተዳደር የበላይ ባለቤትነት የተቋቋመው የአዲስ አፍሪካ ዓለም ኮንቬንሽን ማዕከል አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር በመሆንም ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

ሆኖም የአክሲዮን ማኅበሩን የቦርድ ሊቀመንበርነታቸውን ማስረከባቸው ይታወሳል፡፡ አቶ አያሌው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከተቀላቀሉ በኋላ ለአሥራ አንድ ዓመታት የቦርድ አባልና ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርተዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ኢንስቲትዩቱን ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር፣ አክሲዮን ማኅበሩን ደግሞ ለሦስት ዓመት በፕሬዚዳንትነትና በቦርድ ሰብሳቢነት መርተዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመው በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች