Monday, October 2, 2023

የ2008 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት ዝርዝር ዕይታና ፖለቲካዊ አንድምታው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በኋላ ያሉት ሳምንታት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠንካራና አወዛጋቢ ሪፖርቶችና ሕጐች የቀረቡበት ነበር፡፡

ጠቅላላ ምርጫ እሑድ ተካሂዶ ማክሰኞ ዕለት ለምክር ቤቱ በአጀንዳነት ቀርበው ከነበሩት አዋጆች መካከል የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ በፕሮቪደንት ፈንድ ታቅፈው የነበሩ የግል ድርጅት ሠራተኞችን ወደ የግል ድርጅቶች ጡረታ እንዲገቡ የሚያስገድድ ነው፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ድርጅት ሠራተኞችን ተቃውሞ የቀሰቀሰ ነበር፡፡ የተያዘው የሰኔ ወር የመጨረሻ የሥልጣን ዘመኑ የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በዚሁ ከላይ በተጠቀሰው ሳምንት ያዳመጠው ሌላው ሪፖርት የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በ2006 ዓ.ም. በጀት አፈጻጸም ላይ ያደረገው የሒሳብ ኦዲት ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ በርካታ ቢሊዮን ብሮች በዚህም ሪፖርት የኦዲት ችግሮች ወይም አስተያየቶች የተሰጡባቸው ነበሩ፡፡ በመሆኑም በፓርላማ አባላት ዘንድም ሆነ በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች ዘንድ ትኩረትን ያገኘ ነበር፡፡

በመቀጠልም በቀጣዩ ሳምንት ምክር ቤቱ ያዳመጠው የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርትን ነው፡፡ ይህ ሪፖርትም በምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ትኩረትን ያገኘ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፓርላማው ለፌዴራሉ መንግሥት በየዓመቱ የሚመድበው በጀት በየዓመቱ ለሙስና ተጋላጭ በመሆኑ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ሊባክን የነበረ ገንዘብ ማዳኑን፣ እንዲሁም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የተመዘበረ የመንግሥት ሀብት ላይ የወንጀል ምርመራና ክስ መመሥረቱን ገልጿል፡፡

በተጠናቀቀው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ደግሞ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ለረዥም ዓመታት እየመሩ የሚገኙት ብቸኛው አቶ ሱፊያን አህመድ፣ የ2008 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡

አቶ ሱፊያን በጠቅላላው ከ223 ቢሊዮን ብር በላይ የተደገፈ በጀት ለ2008 ዓ.ም. እንዲሆን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ሚኒስትሩ በጀቱን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፣ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸሞች ላይ ላዩን ለመመልከት ሞክረዋል፡፡

ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም. በነበሩት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕድገት ትግበራ ዓመታት ኢኮኖሚው በየዓመቱ በአማካይ 10.1 በመቶ እንዳደገ ገልጸዋል፡፡ ለተመዘገበው ዕድገት የግብርናው ዘርፍ በአማካይ በየዓመቱ 6.6 በመቶ በማደግ ዋና የዕድገት ምንጭ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት ታቅዶ ከነበረው የ11 በመቶ ግብ በመጠኑ ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ ከብዙ መመዘኛዎች አንፃር ሲታይ እጅግ ፈጣን የሚባል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አራት ተከታታይ ዓመታት ሦስቱም ክፍላተ ኢኮኖሚዎች ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) በነበራቸው ድርሻ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ በመጠኑም ቢሆን መዋቅራዊ ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል፡፡ ይኸውም በ2003 በጀት ዓመት ግብርናው ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 44.7 በመቶ ይሸፍን የነበረ ሲሆን፣ በ2006 ዓ.ም. ወደ 40.2 በመቶ መውረዱን ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፉም በአንፃሩ መጠነኛ ለውጥ በማምጣት በ2003 ዓ.ም. ከነበረበት 10.5 በመቶ ድርሻ፣ በ2006 ዓ.ም. ወደ 14.3 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ ዕድገት እንዲያመጣ ቢጠበቅም፡፡

ሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ አገልግሎት ሲሆን፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት የሌለው በመሆኑ እንዲወርድ ቢፈለግም በተቃራኒው በ2003 ዓ.ም. ከነበረበት 45.5 በመቶ ወደ 46.2 በመቶ ማደጉን አስረድተዋል፡፡

ለ2008 ዓ.ም. የተዘጋጀው በጀት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሚጠበቁ ዋና ዋና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ግቦችን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል፣ አሁን የተገኘውን የልማት ውጤት በአስተማማኝ መሠረት ላይ በመጣል የዕድገቱን ቀጣይነት በማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ልማትና ኤክስፖርትን ወደ ሚያስፋፋ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያሸጋግር ነው ብለውታል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ የተያዘው 50.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ለካፒታል ወጪ ደግሞ 84.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 76.8 ቢሊዮን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 12 ቢሊዮን ብር ተደግፎ መቅረቡን የሚኒስትሩ የበጀት መግለጫ ያስረዳል፡፡ በዚህም መሠረት አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት በጀት 223.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከ2007 ዓ.ም. በጀት በ36.8 ቢሊዮን ብር ማለትም የ19.7 በመቶ ብልጫ ያሳያል፡፡

ለመደበኛ ወጪ የተያዘው 50.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለደመወዝ፣ ለአበልና ለልዩ ልዩ ወጪዎች የተደገፈው 17.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ወጪ በ2007 ዓ.ም. የተደረገውንም የደመወዝ ጭማሪ ታሳቢ ያደረገ ከመሆኑም ባሻገር፣ ከ2007 ዓ.ም. የ3.2 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያሳያል፡፡

ለካፒታል በጀት የተመደበው 84.3 ቢሊዮን ብር በ2007 በጀት ዓመት ከነበረው የካፒታል በጀት በ17.3 ቢሊዮን ብር ይበልጣል፡፡ በካፒታል በጀት ውስጥ ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከል የዋና ዋና መንገዶች ማጠናከሪያና ማሻሻያ ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከውጭ ብድር 5.3 ቢሊዮን ብር፣ ለአገናኝ መንገዶች ግንባታና ማሻሻያ ደግሞ 24.6 ቢሊዮን ብር መያዙን የበጀት መግለጫው ያስረዳል፡፡

ሌላው ትልቁን የካፒታል በጀት የያዘው የነባር ዩኒቨርሲቲዎችን ማጠናከሪያና የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ነው፡፡ ለዚህም 17 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡

ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ደግሞ ሦስት ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ በተጨማሪም ለመስኖ ልማትና ግድብ ሥራዎች፣ ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ለተፋሰስ ጥናትና ልማት፣ ለከርሰ ምድር ውኃ ጥናትና ለኢነርጂ ጥናት በድምሩ 6.5 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡

ከመስኖ ልማት ትኩረት ያገኙት ከሰም ተንዳሆ መስኖ ልማትና ግድብ፣ ርብ ግድብና መስኖ ልማት፣ መገጭ ግድብና መስኖ ልማት ይገኙበታል፡፡

መንግሥት ለሚመድበው ዓመታዊ በጀት መሸፈኛ ምንጩ ምንድነው የሚለው፣ በአብዛኛው ጊዜ አወዛጋቢና አከራካሪ እንዲሁም ፖለቲካዊ ይዘት አለው፡፡

የ2008 በጀት ዓመት በጀት ታሳቢ ያደረጋቸው መሸፈኛዎች የአገር ውስጥና የውጭ ምንጮችን ነው፡፡ በአጠቃላይ 195.7 ቢሊዮን ብር እንደሚሰበስብ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 157.06 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች ይገኛል ተብሎ ታቅዷል፡፡ ቀሪው መጠን ደግሞ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ የሚገኝ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በገቢው 195.7 ቢሊዮን ብር እና በጠቅላላ ወጪው ብር 223.3 ቢሊዮን ብር መካከል የ27.6 ቢሊዮን ብር ልዩነት ይታያል፡፡

ይህ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) አንፃር ማለትም ከ1.3 ትሪሊዮን የሚገመት ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ድርሻ 1.8 በመቶ ብቻ በመሆኑ፣ የዋጋ ግሽበትን የማያስከትል እንደሆነ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የ2008 በጀት በባለሙያዎች ዕይታ

የአገሪቱ ፓርላማ በኢሕአዴግ የበላይነት የተሞላ በመሆኑ በፓርላማ የፀደቁ ሥራዎችና የተያዘላቸው በጀት በበጀት አዋጁ ለማይታወቁ ሥራዎች ሊውሉ እንደሚችሉ፣ ይኼውም ኢሕአዴግ በምክር ቤቱ ከፍተኛ አብላጫ የያዘ በመሆኑ ተለዋዋጭ (Flexible) ውሳኔ ለመወሰን ያስችለዋል የሚሉት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ናቸው፡፡

‹‹በጀት ማለት የመንግሥት ፍላጐት መግለጫ ሰነድ ማለት ነው፡፡ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ቢሆንም መተግበር ያለበት ሰነድ ሊሆን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ከአጠቃላይ የበጀት አመዳደብ ውስጥ የመደበኛ በጀቱ ማለትም ለደመወዝና ለአስተዳደር የተመደበው 50.2 ቢሊዮን ብር፣ የአገሪቱን ሁኔታ መግለጽ መቻል አለበት ይላሉ፡፡

በተለይ በኃላፊነት ላይ የተቀመጡ የመንግሥት ሠራተኞችን ፍላጐት በአሁኑ ወቅት ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር መመለስ የሚችል አይደለም በማለትም ያስረዳሉ፡፡

ሌላው እጅግ አከራካሪ መሆኑን ወይም ተዓማኒነት እንደሚጐድለው የሚያምኑት፣ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን በአገር ውስጥ ብድር ብቻ እንደሚሸፍንና የዋጋ ግሽበት እንደማያስከትል መግለጹን ነው፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን የበጀት ጉድለቱን መንግሥት ከአገር ውስጥ ብድር እንደሚሸፍን፣ ይህ ማለት ግን ከብሔራዊ ባንክ ይበደራል ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ የግምጃ ቤት ሰነዶችን በመሸጥ ከባንኮች፣ ከግለሰቦች እንዲሁም ከጡረታ ፈንዶች የሚጐድለውን 27.6 ቢሊዮን ብር ማግኘት እንደሚቻል ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ግን ይህንን የበጀት ጉድለት በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ መሙላት ይቻላል ብለው አያምኑም፡፡

የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ገበያ የሚያስገኘው ትርፍ እጅግ በጣም ትንሽ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ በዚህ ላይ በየዓመቱ የማይታይ የብር የመግዛት አቅም መቀነስ (Devaluation) መኖሩን በተጨማሪም በነጠላ አኃዝ ላይ ቢሆንም የዋጋ ግሽበትም በኢኮኖሚው የሚታይ በመሆኑ በግምጃ ቤት ሰነድ ላይ የመሳተፍ ፍላጐት ይኖራል ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡

ከአጠቃላይ 223.3 ቢሊዮን ብር 34.4 ቢሊዮን ብር ድርሻ የያዘው ለክልል መንግሥታት በየዓመቱ የሚሰጠው የበጀት ድጋፍ ነው፡፡ ይህም በ2008 በጀት ዓመት 76.8 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የተደገፈ ሲሆን፣ በ2007 ዓ.ም. ለክልሎች ከተደጐመው 51.8 ቢሊዮን ጋር ሲወዳደር 25 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን ባቀረቡት ሪፖርት ግን በ2007 በጀት ዓመት ለክልል መንግሥታት የተደረገው ድጋፍ በተከለሰው የበጀት አዋጅ መሠረት 62.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ማለት የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ያደረገውን 11 ቢሊዮን ብር የደመወዝ ጭማሪ እንደ በጀት ድጐማ አስልተውታል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማው ከወራት በፊት ያፀደቀው የበጀት ጭማሪ እንጂ ለክልሎች የሚደረግ የበጀት ድጋፍ እንዳልሆነ የሚከራከሩ አሉ፡፡

ለክልሎች በሚሰጥ የበጀት ድጋፍ ላይ ሁለት አከራካሪ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው ክልሎች ከፌዴራሉ መንግሥት ሊያገኙት የሚገባው የበጀት ድጐማ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ እስከሆነ ድረስ፣ የድጐማ ሥሌቱ ግልጽ ሊሆን ይገባል የሚለው ይገኝበታል፡፡

አንዳንድ አገሮች ከአገራቸው ጠቅላላ ምርት ውስጥ የክልሎች ድርሻ አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው የሚለውን በማሥላት ለክልሎች የሚመደበውን ጥቅል ገንዘብ እንደሚወስኑ፣ የፊስካል ፌዴራሊዝም ባለሙያው ዶ/ር ሰለሞን ንጉሤ ይገልጻሉ፡፡ ሌላኛው አሠራር ደግሞ አጠቃላይ የፌዴራል በጀት ካለፈው በጀት በምን ያህል እንደጨመረ በመቶኛ ተሠልቶ ለክልሎች ድጐማ እዲውል የሚያደርጉ አገሮች ስለመኖራቸው ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ግን የሚመደበው ጥቅል ገንዘብ ማለትም በ2008 በጀት ዓመት የተደገፈው 76.8 ቢሊዮን ብር በምን መመዘኛ ስለመሆኑ ግልጽ አሠራር አለመኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡

ሌላው ክርክር ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች እያደረገ ያለው ድጐማ በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረ ቁጥር፣ የክልሎችን የሥልጣን ነፃነት የሚጋፋ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ዶ/ር ሰለሞንም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አሁን ያለው ከፍተኛ የበጀት ድጐማ አሠራር የክልሎችን ጥገኝነት ነው እያበረታታ ያለው ይላሉ፡፡ በመሆኑም ክልሎች የበለጠ ነፃ እየሆኑ እንዲሄዱና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተጠያቂ እንዲሆኑ የራሳቸውን ታክስ በመሰብሰብ እንዲያስተዳድሩ የሚደረግበት አሠራር ቢኖርም፣ የበለጠ ተጠናክሮ ቀዳሚ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በበጀት ረቂቁ ላይ የመጀመሪያ ውይይት ያደረጉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አብዛኞቹ ዝርዝር ጥያቄዎችን፣ ማለትም የተመረጡበትን አካባቢ ኅብረተሰብ መሠረት በማድረግ ጥያቄዎችን ለመሰንዘር ከፍተኛ ፍላጐት ቢኖራቸውም፣ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ፍላጐታቸውን ለጊዜው ገድበውታል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የሚደረግ ውይይት በበጀት ረቂቅ አዋጁ የዝግጅት ሥርዓትና ታሳቢዎችን የተመለከተ አጠቃላይ ውይይት ብቻ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የተወሰኑ አባላት የመንግሥት በጀት ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ነው ወይ ወደሚል ጥያቄ አድልተዋል፡፡ ቀደም ባሉት ሳምንታት ለፓርላማው ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የፌዴራሉ ዋና ኦዲተርና የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ያቀረቧቸው ሪፖርቶች፣ ለመንግሥት የሚመደበው በጀት እየባከነ መሆኑን መጠቆማቸውን በመግለጽ የሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የተለያዩ ችግሮች አሉብን፡፡ በፀረ ሙስና ኮሚሽንና በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚቀርቡ ሪፖርቶች የሚያሳዩት እነዚህን ችግሮች ነው፡፡ ችግሮቹ በስኬት ውስጥ የሚታዩ ስለሆነ ሥርዓቱ እየሠራ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዋናው በኤክስፖርት ዘርፍ ያለብንን ችግር የማንቀርፈው ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ ኢኮኖሚ መቀጠል የምንችል አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም የ2008 በጀት ዓመት የመንግሥት ትኩረት ኢኮኖሚው እንዳይቆም ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡            

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -