አገር በመርህ የምትመራው ከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነት ሲኖር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳል፡፡ የሕግ የበላይነት አለ ሲባል ዜጎች በነፃነት የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ሕገወጦችና ግብረ አበሮቻቸው ደግሞ አደብ ይገዛሉ ማለት ነው፡፡ በሕግ ፊት ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው ማለት ከሕግ በላይ ማንም የለም ማለት ነው፡፡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ራሳቸው ሕግ መሆን ሲጀምሩ ግን አደጋ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አዝማሚያ ሲኖር በሕግ ማለት ተገቢ ነው፡፡
የሕግ የበላይነት እንዲከበር የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ዜጎች ቢሆንም፣ ከማንም በበለጠ ግን መንግሥትን ይመለከተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ ሁሉም ሕጎች በአግባቡ ሥራ ላይ መዋላቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ በተለይ ዜጎች በሕገወጦችና በሥርዓተ አልበኞች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከመከላከል ጀምሮ፣ በአጥቂዎች ላይ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ ድረስ ተጠያቂነት አለበት፡፡ ዜጎችም መብታቸው ሲጣስ ቅሬታ የሚያቀርቡበትና አፋጣኝ ምላሽ የሚያገኙበት ሁኔታም መመቻቸት ይኖርበታል፡፡
በአገሪቱ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ዜጎች ቅሬታ ሲያቀርቡ አፋጣኝ ምላሽ ስለማያገኙ በደሉ የተደራረበ ይሆንባቸዋል፡፡ ፍትሕ ሲፈልጉ በተቃራኒው ሲገጥማቸው ብሶት ይበረታባቸዋል፡፡ በዳተኛና በሙሰኛ ሹማምንት ምክንያት ሥራቸው ሲጓተትባቸውና አላስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች ሲዳረጉ ምሬቱ ጣሪያ ይነካል፡፡ በዜጎች ላይ ተደራራቢ በደሎችን የሚፈጽሙ ግለሰቦች ጥሩ እንደሠሩ ተቆጥረው በሹመት ላይ ሹመት ሲደረብላቸው ዜጎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ በሙስና የሚታሙ ሹማምንት በማናለብኝነት የፈለጉትን ሲፈጽሙ የሚቆጣጠርና የሚገስፅ ከሌለ መንግሥት እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው ችግር ይህንን በስፋት ያሳያል፡፡ ለዜጎች ምሬት ምክንያት የሆኑ ችግሮችና ግለሰቦች እንደፈለጉ ሲፈነጩ ጠያቂ የለባቸውም፡፡
በበርካታ መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ሙስና እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ በየደረሰበት የሚያጋጥመው አምጣ የሚል ብቻ ሆኗል፡፡ ሙስናው እየከፋ ከመምጣቱ የተነሳ ለሚከፈለው ጉቦ ደረሰኝ አምጡ ቢባሉ ከመስጠት ወደኋላ የማይሉ አሉ፡፡ በየተቋማቱ የተገልጋዩን ሕዝብ ቅሬታ የሚሰማ ባለመኖሩ ዜጎች ሳይወዱ በግድ የሕገወጦች ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ሙስና ለምን ተስፋፋ ተብሎ ሲጠየቅ፣ በዝቅተኛ ደመወዝ ተቀጣሪ የሆኑ ግለሰቦች ገንዘብ በብዛት የሚንቀሳቀስበት ቦታ ላይ ሆነው እንዴት ይተዋሉ የሚል ምላሽ ይሰማል፡፡ የኑሮን ጫና ለመቋቋም አማራጩ መንገድ ጉቦ መቀበል ነው፡፡ በዚህም የሕዝቡን ቅሬታ ማባባስ ውስጥ ይገባል፡፡ መፍትሔ ካልተፈለገለት አደጋ ነው፡፡
ሕጋዊውን የግዥና የጨረታ አሠራር በማፋለስ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሀብት ይዘረፋል፡፡ በነፃ የገበያ ሥርዓት ውስጥ በጤናማ ውድድር መሥፈርቱን በማሟላት ለሥራው ብቁ የሆኑ እያሉ፣ በሙስና ኔትወርክ የተሳሰሩ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ፕሮጀክቶችን ይረከባሉ፡፡ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ወደ ጎን እየተገፉ በሕገወጥ መንገድ የሚከብሩ ኃይሎች ገበያውን ይወሩታል፡፡ በበርካታ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች አሁንም ወጪና ገቢን በሥርዓቱ የማወራረድ ችግር እንደሚታይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት እያሳየ ነው፡፡ ብዙዎቹ ሒሳብ በአግባቡ የማወራረድ ችግራቸው ምንድነው ተብሎ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም አሁንም መልስ የለም፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱን ጠብቀው ሠርተዋል ቢባል እንኳ፣ ለምን በአግባቡ ሒሳባቸውን አወራርደው ንፅህናቸውን አያሳዩም? ይኼ የግልጽነትና የተጠያቂነት ችግር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በርካታ ችግሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የሕግ የበላይነት ሲከበር ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ተቋማትና የመንግሥት መዋቅሮች በሙሉ ሥራቸውን በአግባቡ ይሠራሉ፡፡ ሕገወጦች የሕግ የበላይነትን ሲጋፉ ዝም ከተባለ ግን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓቱ ይናጋል፡፡ አንዱ ሌላውን ሲሸፍንና ሲከላከል ለጊዜው ሕግ የተከበረ ቢመስልም፣ እየቆየ ግን ሥሩ የማይነቀል ደዌ ይተክላል፡፡ ሕጋዊና ሕገወጡ እየተጣቀሱ መኖር ስለማይችሉ በአገርና በሕዝብ ላይ መጠኑን ለመገመት የሚያዳግት ጉዳት ይደርሳል፡፡ በዚህ ዘመን ድንገት ሳይታሰብ ሚሊየነር የሆኑ ሰዎች ሲፈጠሩ ለምን ካልተባለ፣ የሚወቀሱት ሰዎቹ ሳይሆኑ መንግሥት ነው፡፡ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢምፖርት ኤክስፖርትና በመሳሰሉት የሥራ መስኮች ሳይሳተፉ፣ ወይም የረባ ቢሮ ሳይኖራቸው በጉዳይ አስፈጻሚነት ወይም በደላላነት የሚከብሩ ሰዎች እየበዙ ነው፡፡ የአየር በአየር ሥራ አገርን እንደማያሳድግ፣ ይልቁንም መቀመቅ እንደሚከት መታወቅ አለበት፡፡ ሕገወጥ ተግባር ስለሆነ፡፡ በሙስና እየተቀባበሉ መክበር ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን አገርንም ያሳፍራል፡፡
ሕግ ይከበር ሲባል የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው በነፃነት አመለካከቱን የማራመድ፣ የመሰለውን የመምረጥ፣ የመደራጀትና ዓላማውን የማስተዋወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ይህንን መብት መጋፋት ማለት ሕገ መንግሥቱን መጋፋት ነው፡፡ በአመለካከቱ ምክንያቱ መሠረታዊ መብቶቹን ለመጋፋት የሚሞክሩ ወገኖች ሕገወጥ ናቸው፡፡ ሕግ ጥሰው የሰው መብት ሲጋፉ ዝም ሲባል መንግሥት አለ ወይ ነው የሚባለው፡፡ ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በዋና ዋና በብሔራዊ ጉዳዮች መስማማት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በማያግባቡ ጉዳዮች ላይ መከራከር ሊደገፍ ይገባዋል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ዓላማውን የሚያራምድ ዜጋ የሕግ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ይህንን ዜጋ ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጋፋት ሕገወጥነት ነው፡፡ ሕግ ይከበር፡፡
ዜጎች የሕግ የበላይነት አለ ብለው እንዲተማመኑ ከሚያደርጋቸው መካከል አንዱ የመንግሥት ጥበቃ ነው፡፡ መንግሥት ዜጎችን ከተለያዩ አጥቂዎች የመጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለምሳሌ ዜጎች ካቅማቸው በላይ የሆኑ የኑሮ ጫና ሲገጥማቸው፣ በገበያው ውስጥ የሚከናወኑ አሻጥሮችንና ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ማስቆም አለበት፡፡ በተለይ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ያለምክንያት ሲንሩ ችግሩን ከምንጩ መርምሮ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ሸቀጦች ገበያ ውስጥ እንዳይገቡ ይደረጋሉ? የአቅርቦት መስመሩ ይስተጓጎላል? ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረቶች እንዲፈጠሩ ይደረጋል? በሸማቾች፣ በነጋዴዎችና በመንግሥት መካከል ያለው መስተጋብር ምን ይመስላል? ክፍተቶች ካሉ ለሕገወጦች ተመቻችተዋል ወይ? ወዘተ መመርመር አለበት፡፡ ሕገወጦች የዜጎችን ሕይወት እያመሰቃቀሉት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ተሿሚዎች እጅ አለበት፡፡
ብዙ ጊዜ በጥፋት ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ሰዎች ለፍርድ ሲቀርቡ አይታይም፡፡ ይልቁንም ለጥቂት ጊዜ ገለል ከተደረጉ በኋላ ሌላ ቦታ ይሾማሉ፡፡ ከጥፋታቸው ይልቅ ውለታቸው አመዝኖ ከሆነ ይሁን፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ሲከሰሱ ከሚታዩ ግለሰቦች ጋር ሲወዳደሩ አገርና ሕዝብ ያስመረሩ ግለሰቦችን ማንም አይነካቸውም፡፡ ይኼ ደግሞ ሌሎች ጥጋበኛ ሕገወጦችን ያበረታታል፡፡ የሕግ የበላይነት የሚያስፈልገው ጠንካራና አንድነቷ የተጠበቀ አገር እንድትኖር ነው፡፡ ሕወጦች ደግሞ ከራሳቸው በላይ የአገር ጉዳይ ስለማያሳስባቸው ደንታቸው አይደለም፡፡ የእነሱ ዋና ዓላማ የጥቅም ሸሪኮቻቸውንና ቢጤዎቻቸውን በማበልፀግ ሕጋዊነትን ማጥፋት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሕገወጥነት አደብ ይግዛ የሚባለው!