Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ በምታዘጋጀው ግዙፉ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በርካታ የአገር መሪዎች ይጠበቃሉ

ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው ግዙፉ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በርካታ የአገር መሪዎች ይጠበቃሉ

ቀን:

ኢትዮጵያ በታሪኳ ካዘጋጀቻቸው ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ሁሉ ትልቁ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ጉባዔ፣ ብዛት ያላቸው የዓለም መሪዎች እንደሚጠበቁ መንግሥት ገለጹ፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይጠበቃሉ፡፡

የዘንድሮው ጉባዔ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2015 ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብን ይተካል ለተባለለት ዘላቂ የልማት ግቦች ለመተግበር የሚያስችሉ የፋይናንስ ምንጮች ላይ ለመምከር የአገር መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የግል ተቋማትና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች አዲስ አበባ እንደሚመጡ ታውቋል፡፡

ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የ2008 ዓ.ም. ረቂቅ በጀትን ያቀረቡት የፋይናንስንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ዓይታችሁት የማታውቁትን የመሪዎች ብዛት ታያላችሁ፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ለምክር ቤቱ ረቂቅ በጀቱን ባቀረቡበት ወቅት ለዘላቂ ልማት ግቦች 12 ቢሊዮን ብር መያዙን ሲገልጹ፣ ከአባላት የፋይናንስ ምንጩን አስመልክቶ በተጠየቁበት ወቅት ሲያስረዱ ነበር በሚቀጥለው ወር ስለሚዘጋጀው ጉባዔ እግረ መንገዳቸውን ያወሱት፡፡ ነገር ግን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ውስጥ ምን ያህል መሪዎች እንደሚመጡ ሚኒስትሩ በቁጥር አልገለጹም፡፡ ሆኖም ከ5,000 በላይ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የዜና ምንጮች የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ የታላላቅ አገሮች መሪዎች በአዲስ አበባው ኮንፈረንስ ሊሳተፉ እንደሚችሉ እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የአሜሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እስካሁን ምንም አልተናገሩም፡፡

በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ በአዲስ አበባ የተገኙት የፕሬዚዳንት ኦባማ ልዩ ተወካይ ጆን ፓዴስታ፣ ፕሬዚዳንቱ ጉባዔው በአዲስ አበባ መዘጋጀቱን አገራቸው እንደምትደግፍ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱም ልዩ ተወካዩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ጉባዔውን በተመለከተ ተወያይተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሐምሌ 5 እስከ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚካሄደው ጉባዔ በስኬት ለማስተናገድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ በጉባዔው እንደሚሳተፉ ከሚጠበቁት 5,000 የተለያዩ አገሮች ዜጎች በተጨማሪ ከ200 በላይ ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ ተገኝተው ለመላው ዓለም ዘገባቸውን እንደሚያቀርቡ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባው የዓለም መሪዎች ጉባዔ ለጋሾችና የተለያዩ ተቋማት እ.ኤ.አ. እስከ 2025 ድረስ ለሚቆየው የዘላቂ የልማት ግቦች በቢሊዮኖች ዶላሮች የሚገመት ገቢ ማስገኘት በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚመክሩ ሲሆን፣ በመስከረም ወር ስምምነት እንደሚደረግበት ለሚጠበቀው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ መንደርደሪያ ነው በማለት አዘጋጆቹ እየገለጹ ነው፡፡

ጉባዔውን አስመልክቶ የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ባለፈው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንቱ ጂም ዮንግ ኪም፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋር፣ የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሮበርት አዜቬደንና ሌሎች የተመድ ተወካዮች ‹‹ኢትዮጵያ ተገናኝተን ዓለማችንንና ሕዝባችን እንታደግ፤›› በማለት የሁለት ደቂቃ ቆይታ ያለው የቪዲዮ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...