Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕልመኛው አውሮፕላን ሠሪ

ሕልመኛው አውሮፕላን ሠሪ

ቀን:

ከ19 ወራት ያላነሰ ጊዜ የፈጀችውና በሰንዳፋ ዳቢ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ተንደርድራ ልትበር የነበረችው አነስተኛ አውሮፕላን ባጋጠማት ብልሽት ሳትበር ቀረች፡፡ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለበረራ ዝግጁ ትሆናለች ተብሏል፡፡

ትውልዱ ትግራይ ክልል ዋጅራት አካባቢ ነው፡፡ ያደገው ሐዋሳ ሲሆን የተማረው በአለማያ (ሐሮማያ) ዩኒቨርሲቲ የጤና መኮንንነት ነበር፡፡ ይህን የተማረው አማራጭ ስላጣ እንጂ የልጅነት ሕልሙ አውሮፕላን አብራሪ መሆን እንደነበረ ይናገራል፡፡

የ35 ዓመቱ አስመላሽ ዘፈሩ ከ14 ዓመታት በፊት የጤና መኮንን ለመሆን ያስገደደውን አጋጣሚ ለሪፖርተር የገለጸው፣ ለመሥራት አንድ ዓመት ከሰባት ወራት የፈጀችበትን አውሮፕላን ለማብረር እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ አስመላሽ  አውሮፕላን ለማብረር ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኝ ኖሯል፡፡ በትምህርቱ አጥጋቢ ውጤት አምጥቶ ዩኒቨርሲቲ ቢገባም፣ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የበረራ ትምህርት የማይሰጥ በመሆኑ የጤና መኮንንነትን ለማጥናት ተገዷል፡፡ ይህም ሆኖ በድሬዳዋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ምልመላ ሲያካሂድ ተመዝገቦ ቢቀርብም፣ ቁመትህ በሚፈለገው ልክ አይደለም ተብሎ ሳይመረጥ መቅረቱን ይናገራል፡፡

‹‹ቁመትህ አንድ ሳንቲ ሜትር አጥሯል ተብዬ የአብራሪነት ሕልሜ ሳይሳካ ቀረ፤›› የሚለው አስመላሽ፣ ከ21 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ የራሱን አውሮፕላን ሠርቶ የማብረር ፍላጎት እንዳደረበት ተናግሯል፡፡ በዚህ አኳኋን ከጤና መኮንንነት ሙያው ባሻገር የምህንድስና ትምህርት በማታው ክፍለ ጊዜ በመከታተልና ስለአውሮፕላን አሠራር በማጥናት በመጨረሻም ‹‹K-570A›› የሚል ስያሜ የሰጣትንና ሁለት ሰው ማሳፈር የምትችል የድሮ ሞዴል አውሮፕላን ሠርቶ ለማብረር ተቃርቦ ነበር፡፡ ከእናቱ ወይዘሮ ኪሮስ ስም የመጀመርያ የእንግሊዝኛ ፊደል በመውሰድና አውሮፕላኑን ለመሥራት የፈጁበትን 570 ቀናት፣ እንዲሁም ‹‹ኤርክራፍት›› ከሚለው ፊደል የመጀርያውን ተጠቅሞ ለአውሮፕላኑ ስያሜ ሰጥቷል፡፡

ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አውሮፕላኗን ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሰንዳፋ ከተማ፣ ዳቢ ጊዮርጊስ በተባለ ሜዳ ላይ አንደርድሮ ለማብረር ዝግጅት በማድረግ ላይ ሳለ፣ ሁለት ጊዜ በተሰበሩበት የአየር መቅዘፊያዎች ምክንያት በረራውን ሳያካሄድ ቀርቷል፡፡ አየር መቅዘፊያውን በጥቂት ቀናት ውስጥ በመሥራት ለሞት አደጋ ሊያጋልጠው የሚችለውን አስፈሪ በረራ በድጋሚ ለመሞከር መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የመትረፍ ዕድሉ ግማሽ በግማሽ እንደሆነ የሚገልጸው አስመላሽ፣ እስካሁን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ማድረጉንና ያለውን ነገር ሁሉ አሟጦ በአቅሙ መሥራት የቻለውን አውሮፕላን ዕውን ማድረጉን በመግለጽ ከማብረር እንደማይመለስ ይፋ አድርጓል፡፡ ለሠራው አውሮፕላን 160 ሺሕ ብር ማውጣቱን፣ ከዚህ አውሮፕላን ውጪ ምንም ነገር እንደሌለው፣ ሙሉ ጊዜውን አውሮፕላን ለመሥራት ሲል ከሥራ ገበታው ራሱን ማግለሉን አስመላሽ ይናገራል፡፡ ከወዳደቁ ቁሳቁሶች፣ 40 የፈረስ ጉልበት ካለው የቮልስ ዋገን ሞተር፣ ከእንጨት፣ ከብረት፣ ከሱዙኪ ሞተር ብስክሌት ጎማዎች፣ ከአልሙኒየምና ከመሳሰሉት ቁሳቁሶች የሠራት አውሮፕላን አንዴ ከበረረች በኋላ ዳግመኛ ስለማትበር ሙዚየም የምትገባ መሆኗን ገልጿል፡፡ የቅርብ ጊዜ ህልሙ ናይጄሪያዊው ወጣት ከውድቅዳቂዎች የሠራትንና በአራት ሜትር ከፍታ ላይ ያበረራትን አውሮፕላን በመብለጥ፣ ተጨማሪ ሜትሮችን ወደ ሰማይ በመንሳፈፍ ለማብረር አቅዷል፡፡

እጁን ካፍታታባትና ሙሉ በሙሉ ሜካኒካል በሆነ መንገድ ከምትሠራው አውሮፕላን በተጨማሪ፣ ዲጂታል የሆነና አራት ሰዎችን ማሳፈር የሚችል ዘመናዊ አውሮፕላን የመሥራት ሕልም የሰነቀው አስመላሽ፣ በሰንዳፋ የሠራትን አውሮፕላን ለማበረር ሲሰናዳ የሕይወት አድን ጃኬትም ሆነ ከአየር መዝለያ ፓራሹት አልታጠቀም ነበር፡፡ የሞተር ብስክሌት ሔልሜት በአናቱ ላይ ከማጥለቁ በቀር ለአውሮፕላን አብራሪ የሚመጥን ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት አይታይበትም፡፡ ይህ ሁሉ አቅም ስለሌለው እንጂ ሳያስፈልገው ቀርቶ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የሠራት አውሮፕላን በርካታ ማሟላት የሚገባት መሠረታዊ ነገሮች እንደሚቀረም ያምናል፡፡ ይህም ሆኖ አሥር ሜትር ያህል አብርሮ ለማሳረፍ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎባት ነበር፡፡

የአስመላሽ አባት አቶ ዘፈሩ፣ ከ90 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸውና የ11 ልጆች አባት ሲሆኑ፣ አሥረኛው ልጃቸው አስመላሽ ራሱ በሠራው አውሮፕላን እየሩሳሌም እንደሚወስዳቸው ከልጅነቱ ጀምሮ ይነግራቸው እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አስመላሽን ጨምሮ አብዛኞቹ ልጆቻቸው በሰማይ ላይ መብረርን አጥብቀው የሚመኙ፣ የራሳቸውን መኪና ለመሥራት ሲጥሩ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ አንድ ቀን እየሩሳሌምን የመጎብኘት ሕልማቸው በልጃቸው እንደሚሳካ ተስፋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ልጃቸው በሠራት አውሮፕላንም ከመደሰት በላይ ለአገሩ የሚያኮራ ሥራ መሥራቱን እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...