Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየድሬዳዋ ምድር ባቡር የቀድሞ ሠራተኞች እንዲለቁ የተደረገባቸውን ቤቶቻቸውን ተረከቡ

የድሬዳዋ ምድር ባቡር የቀድሞ ሠራተኞች እንዲለቁ የተደረገባቸውን ቤቶቻቸውን ተረከቡ

ቀን:

በድሬዳዋ ከተማ በቀድሞው ኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ጣቢያ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ሠራተኞች በአገልግሎታቸው ወቅት ተሰጥተዋቸው ከነበሩት መኖሪያ ቤቶች እንዲለቁ ሲደረጉ፣ የከተማው ከንቲባ ጣልቃ በመግባት የተፈናቀሉት ሠራተኞች ቤቶቻቸውን መልሰው ማግኘታቸው ታወቀ፡፡

ከ2,000 በላይ ቤተሰቦችን እንደሚያስተዳድሩ የተነገረላቸው ቁጥራቸው 240 ገደማ የሚሆኑ የምድር ባቡር ሠራተኞች፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጣቢያው ኃላፊዎች ቤቶቹን ለድርጅቱ አስረክበው እንዲለቁ ታዘው ነበር፡፡ በተፈጠረው ውዝግብ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ የድሬዳዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለድርጅቱ የፍርድ ውሳኔ ሲሰጥ፣ ሠራተኞች መበተናቸውንና ለችግር ተዳርገው እንደበር ሠራተኞቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ተፈናቃዮቹ ያለመጠለያ መቅረታቸውን ያወቀው የከንቲባው ጽሕፈት ቤት፣ ከጣቢያው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ሠራተኞችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት አድርጎ እንደነበር የቀድሞ ሠራተኞች ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም  የጽሕፈት ቤቱ ጥረት ውጤት ማስገኘት ባለመቻሉ የከተማው ከንቲባ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለጂቡቲ መንግሥት አቅርበው እንደነበር፣ የቀድሞ ሠራተኞች መሠረታዊ ማኅበር ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሽመልስ እሸቱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በፌዴራል ደረጃ ያሉ ተቋማት በተለይም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ምድር በቡር ኮርፖሬሽን፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጋር ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ በኮሚቴው አባላት በዝርዝር ምርመራ ከተደረገ በኋላ የተፈናቀሉ ሁሉም የቀድሞ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤታቸውን እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡ በውሳኔው ምክንያት ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለሳቸውንና ፍትሕ መገኘቱን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአገራችን እኛን ያጋጠሙን ዓይነት መሰል ችግሮች በተለያዩ ጊዜያት ይከሰታሉ፡፡ ከአንድ ተቋም ጋር በሚፈጠሩ ችግሮች ዜጎች በአብዛኛው ፍትሕ አጥተው ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ ለእኛ የተወሰነው ውሳኔ ለዜጎች ተቆርቋሪነትን ያሳየና ፍትሕ ወይም መልካም አስተዳዳርን ያስፈነ በመሆኑ፣ እንደ አርዓያ መታየት ያለበት ይመስለኛል፤›› ሲሉ አቶ ሽመልስ በከተማው ከንቲባ የተደረገላቸውን ፍትሐዊ ዕርዳታ አወድሰዋል፡፡

ችግሩ ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ በመረዳት የተቻለውን ጥረት በማድረግ ዜጎችን ከችግር ለማዳን የተደረገው ጥረት ውጤት በማስገኘቱ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተደደር የነዋሪዎችን ደስታ መካፈሉ እንዳስደሰተው የአስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በየነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 03 ወይም ከዚራ በሚባለው አካባቢ የኢትዮና የጂቡቲ ምድር ባቡር ኩባንያ ከ30 ዓመታት በፊት ለሠራተኞቹ ቤቶቹን መገንባቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን በድርጅቱና በሠራተኞቹ መካከል በቤቶቹ ጉዳይ ውዝግቡ ከደርግ ዘመን ጀምሮ እንደነበረ፣ የሠራተኞቹ ጡረተኞች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አብዱሰላም ሁሴን ይናገራሉ፡፡ እሳቸውም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ላደረገላቸው እገዛ ምሥጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...