Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአላና ፖታሽ ሽያጭና ዝውውር እንዲፈጸም ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የማዕድን ሚኒስቴር ስለኩባንያው ሽያጭና ዝውውር የቀረበልኝ ጥያቄ የለም ብሏል

ላለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖታሽ ማዕድን ፍለጋና ማምረት ሥራ ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አላና ፖታሽ ኩባንያ፣ እስራኤል ኬሚካልስ ለተባለ የእስራአል ኩባንያ በመሸጡ ምክንያት ሽያጭና ዝውውሩ ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡፡ ማዕድን ሚኒስቴርን ስለኩባንያው ዝውውር እስካሁን በይፋ የደረሰኝ መረጃ የለም ብሏል፡፡

አላና ፖታሽ ለኩባንያው ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት ባስተላለፈው መልዕክት፣  ለእስራኤሉ ኩባንያ ዝውውር ተፈጻሚ እንዲሆን ከሁሉም የአላና ፖታሽ ባለአክሲዮኖች ድጋፍ በማግኘቱ የኩባንያው ዝውውር በይፋ ይካሄዳል ብሏል፡፡ የእስራኤሉ ኩባንያ  ከሰኞ ጀምሮ በይፋ ሥራ የሚጀመር መሆኑን በማረጋገጥ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙት የአላና ፖታሽ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች አብረውት እንዲሠሩም የተላለፈው መልዕክት አመልክቷል፡፡

የኩባንያው ዝውውር ለአላና ፖታሽ ስኬታማነትን የሚያረጋግጥና ለድርጅቱ ሠራተኞችም መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥር መሆኑን የሚጠቁመው መልዕክት፣ እስካሁን ያሉት ሠራተኞች ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጦላቸዋል፡፡ አላና ፖታሽ 120 ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡

የእስራኤሉ ኩባንያ አላና ፖታሽ ኩባንያ ያሉትን 300 ሚሊዮን አክሲዮኖች እያንዳንዳቸው በ0.50 የካናዳ ዶላር ዋጋ እንደገቸዛው ታውቋል፡፡ ይህም ከ150 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ አላና ፖታሽ የተሸጠበት ይህ ዋጋ አላና ፖታሽ እስካሁን ለፕሮጀክቱ ካወጣው ወጪ አንፃር ሲታይ አትራፊ የሆነበትን የሽያጭ ገቢ እንዳገኘ የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡

የአላና ፖታሽ በአፋር ክልል በዳሎል ጠቅላላ የኢንቨስትመንት ወጪው ከ750 እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል ተብሎ ይገመት ነበር፡፡ ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር የሽያጭ ስምምነቱ እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ አላና ፖታሽ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ነጅብ አባቢያ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የእስራኤል ኩባንያ አላና ፖታሽን ሙሉ በሙሉ ከመግዛቱ ቀደም ብሎ፣ የ16 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለመውሰድ የሚያስችለውን ከ85 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ግዥ ለመፈጸም ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ እስራኤል ኬሚካልስ ኩባንያ ከ85 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለአላና ፖታሽ ገቢ ሳያደርግ በመቆየቱ ስምምነታቸው ሳይፈርስ እንዳልቀረ ተነግሮ ነበር፡፡ በመሀል ግን አላና ፖታሽ ለፕሮጀክቱ ኢንቨስትመንት የሚውል ካፒታል ለማሰባሰብ በሽርክና ሊሠሩ የሚችሉ ሌሎች አማራጮችን ወደማፈላለግ ገብቶ፣ ከሦስት ኩባንያዎች ጋር ድርድር በማድረግ በመጨረሻ ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ በመደረስ ግዥውን ሊፈጽም ችሏል፡፡ ይህም ስምምነት መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈጽሟል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ግን የአላና ፖታሽን ሽያጭና ዝውውር የሚመለከት ምንም ዓይነት ይፋዊ የሆነ መረጃ ያልደረሰው መሆኑን ይገልጻል፡፡ የሚኒስቴሩ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አላና ኩባንያውን ሸጫለሁ ስለማለቱ መረጃ ቢኖርም እስካሁን በሕጋዊ መንገድ ጥያቄ አለመቅረቡን ነው፡፡

‹‹እስካሁን ለእኛ የቀረበልን ነገር የለም፤›› ያሉት እኚሁ ኃላፊ፣ “አላና ፖታሽ ለእስራኤሉ ኩባንያ ሊተላለፍ መሆኑን የሚያመለክት ጥያቄ አላቀረበም፤” ብለዋል፡፡ በጆይንት ቬንቸር ለመሥራት ከሆነ በራሳቸው ስምምነት ሊፈራረሙ የሚችሉ ቢሆንም፣ ኩባንያውን ለሌላ ኩባንያ አስተላልፋለሁ ካለ ግን ጉዳዩ ለማዕድን ሚኒስቴር መቅረብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

የዝውውሩ ጥያቄም ተቀባይነት የሚኖረው መጀመሪያ አላና ፖታሽ ግዴታውን የተወጣ መሆኑ ከተረጋገጠ ነው፡፡ ኩባንያው የሚተላለፍለት ድርጅት ሕጋዊ፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ብቃት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ብለዋል፡፡ ኩባንያዎቹ በግላቸው የሚደርሱበት ስምምነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኩባንያው ዝውውር የሚፈቀደው ማዕድን ሚኒስቴር ማረጋገጫ ሲሰጥ ብቻ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

አላና ፖታሽ ላከ በተባለው መልዕክት ላይ ኩባንያዎቹ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደራደሩ መሆናቸው ጠቅሷል፡፡ የመጨረሻ የሽያጭ ርክክቡ በካናዳ ይካሄዳል የተባለ ሲሆን፣ መንግሥት የሚጠይቃቸውን ፎርማሊቲዎች ከርክክቡ በኋላ ሊከናውኑ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ የእስራኤሉ ኩባንያ በዳሎል የሚገኘውን ፕሮጀክት ለረጅም ጊዜ እንደ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት የሚመለከተው መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የአላና ፖታሽ ቡድን ጋር በመሆን የፕሮጀክቱን ሥራ  እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በኩባንያው ይፋ በሆነው መረጃ መሠረት የእስራኤሉ ኩባንያ አላና ፖታሽን ሙሉ ለሙሉ ለመግዛት የወሰነው በቀጣይ በአፍሪካ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ገበያ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው  ተብሏል፡፡ ከኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የፖታሽ ማዕድን ምርት በዋነኝነት ለግብርና ማዳበሪያ ማምረቻ የሚጠቅም ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለሚገነቡ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ ጥሩ ገበያ አለው ተብሎ ስለሚታመን ጭምር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ማምረት ሲጀምር ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ መሆኑን የሚገልጸው በኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፣ አሁን ባለው ገበያ በዓመት የፖታሽ ወጪ ንግድ ገቢው ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይጠቁማል፡፡

የአላና ፖታሽ ፕሮጀክት ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በመገንዘብ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይ የፖታሽ ምርትን በዓለም ገበያ ለማቅረብ ይረዳሉ የተባሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እያካሄደ ነው፡፡ ከደንከል-ጂቡቲ ታጁራ ወደብ ድረስ በመገንባት ላይ ያለው መንገድ ይጠቀሳል፡፡  

ተቀማጭነቱን ካናዳ ያደረገው አላና ፖታሽ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖታሽ ለማምረት በአፋር ክልል በደንከል ዝቅተኛ አካባቢ የፖታሽ ፍለጋውን በስኬት በማጠናቀቁ፣ ከማዕድን ሚኒስቴር የፖታሽ ማዕድን የማውጣት ፈቃድ አግኝቶ ነበር፡፡ የፖታሽ ምርቱንም በዚህ ዓመት አውጥቶ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ የነበረው ሲሆን፣ ይህንን ሳያሳካ ኢንቨስትመንቱን ሸጧል፡፡ አላና ፖታሽ ይዞት የነበረው ዕቅድ ሳያሳካ ወደ ሽያጭ የገባው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወጪ ማሟላት ባለመቻሉ ነው፡፡ በተለይ የእስራኤሉ ኩባንያ እገዛዋለሁ ላለው የ16 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ይከፍላል ተብሎ የነበረውን ገንዘብ በወቅቱ ባለመክፈሉ ሌላ አማራጭ ፍለጋ ሊገባ እንደቻለም ይነገራል፡፡ አላና ፖታሽ በበኩሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖታሽ ዋጋ ማሽቆልቆል ኩባንያውን ለመሸጥ እንዳስገደደው ይገልጻል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዓመታት በፊት አንድ ቶን ፖታሽ ከ570 ዶላር በላይ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 280 ዶላር ወርዷል፡፡ በካናዳ ባለው የፖታሽ ስቶክ ገበያም ከአራት ዓመት በፊት 2.8 ዶላር ይሸጥ የነበረው የአላና የአንድ አክሲዮን ዋጋ፣ አሁን ከ0.40 የካናዳ ዶላር በታች በመውረዱ አላና ፖታሽን ለመሸጥ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ እንዳደረገው ተነግሯል፡፡ አቶ ነጅብ እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖታሽ ዋጋ ዝቅ እያለ በመምጣቱ አላና ፖታሽ ሊሸጥ ችሏል፡፡ የእስራኤል ኩባንያ የሽያጩ ሒደት ስምምነት መፅደቁን ተከትሎ በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባትና የቅድመ ግንባታ ጥናት በመጀመር፣ የፕሮጀክቱን የኢንጂነሪግ ዲዛይንና የቦታ መረጣ፣ የውኃ አቅርቦትና የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሥራዎችን ተፈጻሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ተፈጻሚ የሚሆንበትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንደሚመክርበት የኩባንያው መረጃ ያመላክታል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የአላና ፖታሽ የማኔጅመንት ቡድን የእስራኤሉ ኩባንያ  ሲረከብ ዓላማውንና የሥራ ድርሻውን በመግለጽ፣ ለአዲሱ ኩባንያ የሚያስረዳበትን ዝግጅት እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

የእስራኤሉ ኩባንያ በንግድ ድርጅትነት በኒውዮርክ የአክሲዮን ገበያና በቴልአቪቭ አክሲዮን ገበያ የተመዘገበ ነው፡፡ የኩባንያውን የቅድመ ታሪክና ወቅታዊ አቋሙን በሚመለከት ባለፈው ሳምንት ለአላና ፖታሽ ሠራተኞች በተሠራጨው መልዕክት ላይ፣ እስራኤል ኬሚካልስ እ.ኤ.አ. በ2014 አጠቃላይ ገቢው ወደ 6.1 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ኩባንያው በዋናነት በምግብ፣ በምህንድስና መገልገያ መሣሪያዎች ምርትና ሥርጭት ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በቀዳሚነት በፖታሽ፣ በፎስፌትና በብሮሚን ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ በመላው ዓለም ከ30 በላይ በሚሆኑ አገሮች ይንቀሳቀሳል፡፡ 12,500 ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡ የኩባንያው ጠቅላላ ሀብትም 12 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የፖታሽ ምርትን በዓለም ገበያ ለማቅረብ በቅድሚያ ተነሳሽነቱን ያሳዩት የአላና ፖታሽ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጅብ አባቢያ፣ ወደ ኢንቨስትመንቱ ሲገቡ ተሰማርተው የነበሩት በወርቅ ማዕድን ፍላጋ ላይ ነበረ፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ በአገሪቱ ያለውን የፖታሽ ማዕድን ዕምቅ ሀብት መኖሩን በጥናት በማረጋገጥ፣ ወደ ዘርፉ ፊታቸውን ሊያዞሩ መቻላቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ ነጅብ ኢትዮጵያ ውስጥ በጂኦተርሚል ኃይል ማመንጨት ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች