Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናሰማያዊ ፓርቲ በደብረ ማርቆስ ለምርጫ በዕጩነት ያቀረበው አባሉ ተገደለ

  ሰማያዊ ፓርቲ በደብረ ማርቆስ ለምርጫ በዕጩነት ያቀረበው አባሉ ተገደለ

  ቀን:

  –  ፓርቲው ክፍፍል ተፈጥሯል መባሉን አስተባበለ

  ሰማያዊ ፓርቲን በመወከል በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት በደብረ ማርቆስ ከተማ ተወዳዳሪ የነበረው አባሉ ወጣት ሳሙኤል አወቀ፣ ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 አካባቢ በስለት ተወግቶና ተደብድቦ ተገደለ፡፡ ፓርቲው አባሉ መገደሉን ለሪፖርተር በማረጋገጥ፣ ነገር ግን በማን እንደተገደለ ማጣራቱን አለማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

  ወጣት ሳሙኤል ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲያመራ በሁለት ሰዎች ተደብድቦ ጉዳት ስለደረሰበት ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደ ሕይወቱ ሊያልፍ መቻሉን፣   የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  ወጣት ሳሙኤል ከቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ጀምሮ በተቃውሞ ጎራ ሲታገል የቆየ መሆኑንና ፓርቲው ለሁለት ሲከፈል ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የፓርቲው ጸሐፊ ሆኖ መሥራቱን አቶ ዮናታን ጠቁመዋል፡፡ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድሮ ነበር፡፡

  ነገር ግን ከምርጫው በኋላ ሟች ወጣት ሳሙኤል ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርሰው እንደነበር አቶ ዮናታን ገልጸዋል፡፡ የሟቹ የፌስቡክ ግድግዳ ላይ በተጻፈ ማስታወሻም ይህንን የሚጠቁሙ መረጃዎች መስፈራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዮናታን ግን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ስለመገደሉ ለጊዜው ተጨባጭ ማስረጃ እንደሌላቸው፣ ፓርቲው ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

  ወጣት ሳሙኤል በፌስቡክ ግድግዳ ላይ ግንቦት 26 ቀን 2007 አሰፈረው በተባለው ማስታወሻ ላይ፣ ‹‹በስልኬ እየተደወደ ያለ ፍላጎቴ ደኅንነት እያስገደደኝ ይገኛል፡፡ ተገደልሁም፣ ታሰርሁም፣ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርምና ለማስረጃነት የደኅንነቶችን ስም፣ ፎቶግራፍና አድራሻ፣ እንዲሁም በሐሰት ምስክርነትና በከሳሽነት የተደራጁ አካላት ተወካዮች አስመዘግባለሁ፡፡ ማንኛውንም የምከፍለው ዋጋ ለአገሬና ለነፃነት ነው፡፡ ከታሰርኩም ህሊናዬ አይታሰርም፡፡ ከገደሉንም ትግሌን አደራ…›› የሚል ይነበባል፡፡ ይህንን ማስታወሻ በተመለከተ በመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት አስተያየት አልተሰጠም፡፡

  ይህ በዚህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ ከሰኔ 4 እስከ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. የምክር ቤት ስብሰባ ማድረጉን፣ በዋነኛነት በሚቀጥለው ወር ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት የቅድመ ሪፖርት ውይይት እንዳደረገ አቶ ዮናታን ገልጸዋል፡፡ ለግንቦቱ ምርጫ ማስፈጸሚያ በተደረጉ ወጪዎችና የበጀት አጠቃቀም ጉዳይና ፓርቲው ከተመሠረተ ጀምሮ ሲጠቀምበት በነበረው ሕገ ደንብ ጉዳይ፣ በከፍተኛ ክርክር የታጀበ ውይይት መደረጉንም አቶ ዮናታን አስረድተዋል፡፡

  በተለይ በበጀት ጉዳይ በአባላት መካከል የጋለ ክርክር ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም፣ በመግባባት ተጠናቋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በፓርቲ ውስጥ ‹‹ከፍተኛ ፍትጊያ ያለው›› ክርክር የተለመደ ቢሆንም፣ በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል እየተፈጠረ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ዝም ብለን ተሰብስበን አንበተንም፡፡ ከፍተኛ የሐሳብ ፍጭት የምናደርግ ስብስብ በመሆናችን ክርክራችን መከፋፈል የሚባል ነገር አያመጣም፤›› በማለት አስታውቀዋል፡፡

  ሰማያዊ ፓርቲ ከምርጫው በፊት 92 ሚሊዮን ብር ለምርጫ ማስፈጸሚያ መድቤያለሁ ብሎ ከገለጸ በኋላ፣ መንግሥት በፓርቲው የገንዘብ ምንጭ ላይ ምርመራ አደርጋለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን አቶ ዮናታን ፓርቲው እስካሁን ምንም ዓይነት ምርመራ እንዳልተደረገበት ጠቁመዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...