Saturday, January 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፕሬዚዳንት አል በሽር ከደቡብ አፍሪካ እስኪወጡ በሱዳን የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች በጦር...

ፕሬዚዳንት አል በሽር ከደቡብ አፍሪካ እስኪወጡ በሱዳን የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች በጦር ኃይል ተከበው ነበር

ቀን:

–  የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበረ ማብራሪያ ተጠየቀ

ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወደ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ያቀኑት የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር፣ የአገሪቱ ፍርድ ቤት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ቢሰጥም በሰላም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የሱዳን ጦር ኃይል በበኩሉ የደቡብ አፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላትን በቁጥጥር ሥር አውሎ እንደነበር ታወቀ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 እና በ2010 በዳርፉር በተፈጸመው ጅምላ ጭፍጨፋ ምክንያት በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ማዘዣ ዋራንት የተቆረጠባቸው የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ ከአይሲሲ ውሳኔ በኋላ የደቡብ አፍሪካን ምድር ሲረግጡ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡

የአይሲሲ ፈራሚ አገሮች አንድ የእስር ማዘዣ የተቆረጠበት ግለሰብ (መሪ) የመያዝና የማስረከብ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካም ከፈራሚዎቹ መካከል ነች፡፡ የኅብረቱን ስብሰባ ለመሳተፍ ወደ አካባቢው ያቀኑት ፕሬዚዳንቱ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ የአገሪቱ መንግሥት ግን ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በመፍቀድ አስመልጧቸዋል እየተባለ ነው፡፡

ተቀማጭነቱ ፕሪቶሪያ የሆነው አይዊትነስ ኒውስ የተባለ ሚዲያ እንደዘገበው ደግሞ፣ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አል በሽር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በዳርፉር አካባቢ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የደቡብ አፍሪካ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የሚገኙባቸው ሦስት ካምፖች በሱዳን ጦር ኃይል ተከበው ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት እንዳረጋገጡት፣ የሱዳን ጦር ኃይል በቁጥጥር ሥር አውሏቸው የነበሩ ካምፖችን የለቀቀው ፕሬዚዳንት አል በሽር ከአገሪቱ መውጣታቸው በተረጋገጠ ጊዜ ነበር፡፡

የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ኃይል ባለሥልጣናት በሱዳን የሚገኙት አባሎቻቸው ደኅንነትና የተባለውን ነገር እንዲጣራ፣ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን መጠየቃቸውን ዘገባው ያመለክታል፡፡  

ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በኋላ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አጀንዳ ሆነው የሰነበቱት ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ ከፕሪቶሪያ ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኘው አንድ የአየር ኃይል ሠፈር ተነስተው ነበር ሰኞ ጠዋት በራሳቸው አውሮፕላን ወደ አገራቸው የበረሩት፡፡ በካርቱም ኤርፖርትም በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ አቀባበል እንደተደረገላቸው ዘጋርድያን ከአካባቢው ዘግቧል፡፡

ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ድረስ ከደቡብ አፍሪካ ምድር እንዳይወጡ አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ያወጣው የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ለአይሲሲ ተላልፈው እንዲሰጡ ውሳኔ ያስተላለፈው ግን እሳቸው ወደ አገራቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ ሰኞ ጠዋት ነበር፡፡

የአገሪቱ ፍርድ ቤት መንግሥት ትዕዛዙን በመጣስ ሕገ መንግሥቱን የሚጋፉ ተግባር መፈጸሙን ጠቅሶ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ የጽሑፍ ማብራርያ ይዞ እንዲቀርብ አዟል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዲወጡ ያደረገበትን ምክንያት ማብራሪያ ይዞ እንዲቀርብ የተጠየቀው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፣ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የሚመጣ ማንኛውም የአገር መሪ ሙሉ ያለመከሰስ መብት (Immunity) የተሰጠው መሆኑን በመጥቀስ ራሱን እየተከላከለ ይገኛል፡፡ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ውድቅ ያደረገበትም ምክንያት ይኼው መብት እንደሆነ፣ ፕሬዚዳንት አል በሽር ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡት በመንግሥት ግብዣ መሆኑን የመንግሥት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት የዚምባብዌ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ስብሰባውን የመሩት ሲሆን፣ ቀደም ሲል የኅብረቱ አባላት ከአይሲሲ ፈራሚነት ራሳቸውን እንዲያገሉ ሲወተውቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት አይሲሲ እየነጠለ የአፍሪካ መሪዎችን ፍርድ ቤት የሚያቀርብ ተቋም መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ በማሰማቱ፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በኅብረቱና በፍርድ ቤቱ መካከል የነበረው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ አሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ግን ፕሬዚዳንቱን በቁጥጥር ሥር ባለማዋሉ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን እየወረፉ ይገኛሉ፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በጀኔቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አይሲሲ በፕሬዚዳንት አል በሽር ላይ ያወጣው የእስር ማዘዣ ትልቅ ትኩረት የምሰጠው ነው፡፡ የተቋሙ ትዕዛዝ መከበርና ተፈጻሚ መሆን ነበረበት፤›› ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ገዥ ፓርቲ ኤኤንሲ ግን የአይሲሲ ‹‹አግባብነትና ገለልተኝነት›› ወደፊት የሚከለስበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...