የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስና ወንጀል የተገኙ የመሬት ይዞታዎችን ያለምንም ዕውቀት የገዙ የከተማ ነዋሪዎች የመሬት ባለቤትነት ዕጣ ፈንታ ሊወስን ነው፡፡
ምንጮች እንደገለጹት፣ የከተማው አስተዳደር በመሬት ይዞታዎቹ ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመወሰን ያስችለው ዘንድ በይዞዎቹ ላይ ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡
ኮሚቴው ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለሙያዎች ጋር በመሆን ምን ያህል ነዋሪዎች የመሬት ይዞታቸው በሙስና የተገኘ መሆኑን እየተገነዘቡ ግዥ ፈጽመዋል? ምን ያህሉስ ባለማወቅ ግዥ ፈጽመዋል? የሚለውን የመለየት ሥራ በማከናወን ለአስተዳደሩ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌማን፣ የሙስና ወንጀል ፍሬ የሆኑ የመሬት ይዞታዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች የመጨረሻ እልባት ለምን እንዳልተሰጠው ተጠይቀው ነበር፡፡
በመኖሪያ ማኅበራት ስም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ይዞታዎችን በሙስና በሕገወጥ መንገድ የያዙትን ኮሚሽኑ እንዲቀጡ ማድረጉን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ በሕገወጥ መንገድ የተያዙትን የመሬት ይዞታዎችም የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕጋዊ ሥርዓት እንዲያስይዘው ከፍርድ ቤት ጭምር ትዕዛዝ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡
‹‹በዚህ ጉዳይ ውስጥ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ በትክክል በሕገወጥ መንገድ የተያዘ መሬት መሆኑን እያወቁ ተሳትፎ ያደረጉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ወንጀለኞች በማኅበር ውስጥ የተያዙ ቦታዎችን በሙሉ አልያዙትም፣ ለንፁኃን ሸጠውታል፡፡ ምናልባትም ትክክለኛ ነው በማለት የየክፍላተ ከተማ ማኅበራት ማደራጃዎች አረጋግጠውላቸው ገዝተውታል፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ለይቶ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ፀረ ሙስና ኮሚሽን ወንጀለኞችን የወንጀል ፍሬያቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጉን የተናገሩት ኮሚሽነር ዓሊ፣ በቅን ልቦና የገዙና የመስተዳደር አካላት ሕጋዊ ነው ብለዋቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋቸው የገዙ ሰዎች ደግሞ እንዴት ሊስተናገዱ እንደሚገባ አስተዳደሩ የሚወስነው ይሆናል ብለዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አፀደ ዓባይ መረጃ እንዲሰጡ ቢጠየቁም፣ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
በ1997 ዓ.ም. የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት በመጠቀም፣ ከ500 በላይ የመኖሪያ ቤት ማኅበራት በሕገወጥ መንገድ ከሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መያዛቸውና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ተከታትሎ መሬቱን ማስመለሱ ይታወቃል፡፡