Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የወጣቶች ጉዳይ ለምን ችላ ይባላል?

ወጣቱን ትውልድ ለቁም ነገር የማብቃት ኃላፊነት ያለበት ማን ነው? ወጣቱ በሥነ ምግባርና በሥነ ልቦና ብቁ ሆኖ የነገ አገር ተረካቢ እንዲሆን መሠረቱን መጣል ያለበት ማን ነው? ይህ ኃላፊነት የቤተሰብ፣ የኅብረተሰብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የቤተ ዕምነቶች፣ ለትርፍ የተቋቋሙ ድርጅቶችና አትራፊ ያልሆኑ ተቋማት፣ እንዲሁም አገርን የሚያስተዳድረው መንግሥት ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ባለድርሻ አካላት ምን እየሠሩ ነው? በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ወጣቱን ለማብቃት እየተደረገ ያለው ጥረት ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ስናነሳ የወጣቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡ ያስጨንቃል፡፡

ወጣቶችን ትምህርት ቤት መላክ ብቻውን እንደ ስኬት ተቆጥሮ ከሆነ ስህተት አለ፡፡ ወጣቶችን የከበቡዋቸው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ በሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም በችግሮች የተከበቡ ናቸው፡፡ ተምረው ሥራ ማግኘት ያልቻሉ ወይም የራሳቸውን ሥራ መፍጠር የተሳናቸው በርካቶች በችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ከትምህርት ገበታ ተፈናቅለው በአነስተኛና በጥቃቅን ሥራዎች ላይ የተሰማሩም ቢሆኑ ፈታኝ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ወጣቶች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጀምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚያጋጥሙዋቸውን ችግሮች ጠጋ ብሎ ማየት ካልተቻለና መፍትሔ መፈለግ ካልተጀመረ የወጣቶች ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ ዋና ዋና የሚባሉ ችግሮችን እንመልከት፡፡

  1. የስፖርትና የማንበቢያ ሥፍራዎች አለመኖር

በአሁኑ ጊዜ የበርካታ ወጣቶች ችግር የስፖርትና የማንበቢያ ሥፍራዎች አለመኖር ነው፡፡ በበርካታ ቦታዎች ለስፖርታዊ ተግባራት የሚያገለግሉ ሥፍራዎች ለተለያዩ ተግባራት በመዋላቸው ብዙዎቹ ወጣቶች ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተለያይተዋል፡፡ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ የጠረጴዛ ኳስ፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማድረግ አዳጋች በመሆኑ ወጣቶች አላስፈላጊ ቦታዎች እየዋሉ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን እንደ አሸን የፈሉት መጠጥ ቤቶች፣ ጫትና ሺሻ ቤቶች፣ የቁማር ቤቶችና የመሳሰሉት ወጣቶችን እያጠፉ ናቸው፡፡ በመኖሪያ፣ በመማሪያና በሥራ አካባቢዎች በብዛት የሚታዩት እነዚህ የወጣቶች ማኮላሻዎች የነገውን ብሩህ ተስፋ እያደበዘዙት ነው፡፡ በጣም ያሳስባል፡፡

ለወጣቶች ዕውቀት ማበልፀጊያ መሆን የሚገባቸው የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በብዛት አለመኖር የራሱን አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ወጣቶች ከሥራ ወይም ከትምህርት በኋላ የንባብ ባህላቸውን በማዳበር አገር ተረካቢ መሆን ሲገባቸው፣ ለእነሱ ተገቢ ያልሆኑ ሥፍራዎች በመዋላቸው የምትጎዳው አገር ናት፡፡ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በየደረጃው ባሉ መንግሥታዊ መዋቅሮችና በኅብረተሰቡ ትብብር እንደ አሸን መፍላት ሲገባቸው ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ባለመኖራቸው ምክንያትም ወጣቶች ለተለያዩ ሱሶች ተጋልጠዋል፡፡ ይህም በጣም አሳሳቢ ነው፡፡

  1. ለስደት የሚገፋፉ ችግሮች መበራከት

ወጣቶች በአገራቸው ተምረው የተሻለ ሕይወት መምራት ሲገባቸው በብዛት እየተሰደዱ ነው፡፡ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት በየብስና በባህር እየተንገላቱ የሚሰደዱ ወጣቶች በርካታ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ከችግሮቹ መካከል የከፍተኛ ትምህርት ዕድል አለማግኘት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ሥራ ማጣት፣ በቂ ምግብና የተመቻቸ ኑሮ አለመኖር፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ የማኅበራዊ ዋስትና አለመኖር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ወዘተ ናቸው፡፡

ወጣቶች ለኑሮ አመቺ ባልሆነ ከባቢ ውስጥ ሆነው አገራቸው ውስጥ መኖር ሳይችሉ ሲቀሩና አስፈሪውን ስደት ሲጋፈጡ ማየት ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ስደት የማያስፈልግ ተግባር ነው ብሎ መንገር ብቻ ሳይሆን፣ ስደትን አማራጭ እንዲያደርጉ የሚከላከል የፖሊሲ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ማሳጅ ቤት ውስጥ ተቀጥረው በአነስተኛ ደመወዝ ኑሮን መግፋት ያቃታቸውን ወጣቶች ከስደት የሚከላከል ፖሊሲና ተግባራዊ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡

በስደት ምክንያት በየበረሃውና በየባህሩ የሚያልቁ ወጣቶችን ዜና እየሰሙ የመጣው ይምጣ ብለው ወደ ስደት የሚጓዙ ሲበራከቱ፣ ችግሩ ምንድነው ብሎ መገምገም አስፈላጊ ነው፡፡ ወጣቶች በገዛ ፍላጎታቸው ወይም በአቻ ተፅዕኖ ምክንያት ችግር ውስጥ ሲገቡ ያላቸው አማራጭ ስደት ከሆነ እንደ አገር ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ስደት የተስፋ ቆራጭነት ምልክት በመሆኑ ወጣቶችን መታደግ ተገቢ ነው፡፡ ወጣቶች ከከተማም ሆነ ከገጠር በብዛት ሲሰደዱ፣ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ይህንን አስከፊ ተግባር የማስቆም ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡም ጭምር መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ይህ መፍትሔ አልባ ድርጊት ቀውስ ያመጣል፡፡

  1. ወጣቶች ላይ ኢንቨስት አለማድረግ

ወጣቶች ላይ ኢንቨስት መደረግ አለበት ሲባል፣ በሥነ ምግባርና በሥነ ልቦና ብቁ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ማለት ነው፡፡ ለዚህ በጎ ተግባር ደግሞ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ቢሆንም ቤተሰብ፣ ኅብረተሰቡና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማኅበራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወጣቶች የሚኖሩባቸው፣ የሚማሩባቸውና የሚሠሩባቸው አካባቢዎች ለእንቅስቃሴዎቻቸው የተመቻቹ እንዲሆኑ የስፖርትና የመዝናኛ ማዕከላት፣ ቤተ መጻሕፍትና የመሳሰሉትን ማቋቋም ተገቢ ነው፡፡ በአንፃሩ በእንቅፋትነት የሚጠቀሱት የሱስ ሥፍራዎች ደግሞ ከወጣቱ ጋር ቁርኝት እንዳይፈጥሩ ጥብቅ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡

ወጣቶች ከላይ በተጠቀሱት ባለድርሻ አካላት አማካይነት በጋራ ተጠቃሚ ሲሆኑና ባለድርሻ አካላቱም ድጋፋቸውን አጠናክረው ሲቀጥሉ ለአገር ተስፋ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለራሳቸውና ለማኅበረሰቡ ጠቃሚና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ወጣቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ደግሞ ማኅበራዊና ኮርፖሬት ኃላፊነት አለብን የሚሉ የፋይናንስ ተቋማት፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰቦችና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መንግሥትም እነዚህን ወገኖች የማስተባበር ኃላፊነት አለበት፡፡ እነሱም ወጣቶችን ለቁም ነገር በማብቃታቸውም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ወጣቶች በሥነ ምግባር እየታነፁና በሥነ ልቦና እየዳበሩ በየተሰማሩበት ሥፍራ ውጤታማ ሲሆኑ የምትጠቀመው አገር ናት፡፡ መብቱን የሚያውቅ ወጣት ግዴታውንም በሚገባ ይረዳል፡፡ የሚጠይቅ ወይም የሚመረምር ወጣት በስሜት አይነዳም፡፡ በጠየቀና በመረመረ ቁጥር የሚፈልገውን ያውቃል፡፡ ወጣቱን በለብለብ ትምህርትና ሥልጠና እያጣደፉ ለገበያ ከማውጣት ይልቅ፣ በተጓዳኝ ድጋፎች ጭምር ማብቃት ጥቅሙ ለአገር ነው፡፡ ወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚጠቅመው ለዚህ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ወጣቶች በትምህርት ላይ ሆነው የሚደግፋቸው ስለሌለ ተረጋግተው አይማሩም፡፡ በመከራ ጨርሰው የወጡትም ለኑሮ በቂ የሆነ ገቢ የላቸውም፡፡ የሥራ ፈጣሪነት ክህሎት ተላብሰው ስለማይወጡ ኑሮ አይመቻቸውም፡፡ ኑሮ ሳይመች ሲቀር ደግሞ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይኼንን በጥልቀት መፈተሽ አለባቸው፡፡ በቂ ምግብ በሌለበት፣ ለኑሮ ተስተማሚ ባልሆነ መኖሪያ ቤት እየተኖረ፣ ጠቀም ያለ ገቢ ሳይኖርና ዙሪያ ገባው በጨለመበት ወጣቱን ከተስፋ ቆራጭነትና ከስደት መከላከል አይቻልም፡፡ ወጣቶች በገዛ አገራቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲጓዙ፣ ስኬታማ እንዲሆኑ፣ የነገ አገር ተረካቢ መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ ወዘተ የሚፈለግ ከሆነ ኢንቨስት ይደረግባቸው፡፡ ወጣቶች ላይ ኢንቨስት አለማድረግ ፀፀቱ ከባድ ነው፡፡ የወጣቶችን ጉዳይ ችላ ማለት አይገባም፡፡ ለዚህም ነው የወጣቶች ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ሊያሳስበን ይገባል የሚባለው፡፡ የወጣቶች ጉዳይ ችላ አይባልም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...