Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊስምንት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዕርምጃ ተወሰደባቸው

ስምንት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዕርምጃ ተወሰደባቸው

ቀን:

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልል ከተሞች የሚገኙና የሕግ ጥሰቶች ፈጽመዋል ባላቸው ስምንት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ፕሮግራም መዝጋት የሚያደርስ ዕርምጃ ወሰደ፡፡ ከዚህ በፊት የታዩባቸውን ችግሮች አስተካክለዋል ያላቸው ሌሎች ሁለት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ ተማሪዎችን እንዲቀበሉ መፍቀዱ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ገረሱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው ይህንኑ አስመልክተው በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በተቋማቱ ላይ ዕርምጃ የተወሰደባቸው በኅብረተሰቡ ተጨባጭ ጥቆማና በባለሙያ በተደረገው ድንገተኛ ግምገማ ነው፡፡ በጥቆማውና በግምገማው መሠረት ከቅበላ መሥፈርት ውጪ፣ ባልተፈቀደላቸው የትምህርት መስክና ካምፓሶች ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማራቸውና ሌሎች የሕግ ጥሰቶችን መፈጸማቸው በተጨባጭ ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

ውሳኔው ከሰኔ ወር መጀመሪያ አንስቶ ለየተቋማቱ በደብዳቤ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ፕሮግራሞቻቸውን እንዲዘጉ ከተወሰነባቸውም መካከል ሚሽክን ኮሌጅ ይገኝበታል፡፡ ኮሌጁ ከቅበላ መሥፈርት ውጪ የተቀበላቸውን ተማሪዎች እንዲያሰናብት ቀደም ሲል የተሰጠውን ውሳኔ ተፈጻሚ አላደረገም፡፡ በዚህም መሠረት በመማር ላይ ያሉ ሕጋዊ የሆኑ ተማሪዎችን ብቻ አስጨርሶ ሁሉንም ፕሮግራሞች እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡

ሐያት ሜዲካል ኮሌጅ፣ ቤቴል ሜዲካል ኮሌጅ፣ አፍሪካ የጤና ሳይንስ ኮሌጅና አትላስ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከኤጀንሲው ከተፈቀደላቸው የተማሪ ቁጥር በላይ ተቀብለው በማስተማራቸው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ተማሪ እንዳይቀበሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ መቐለ የሚገኘው ናይል ኮሌጅም የቅበላ መስፈርቱን ያላሟሉ ተማሪዎችን በመቀበሉ፣ በመስፈርቱ መሠረት ቋሚ መምህራን የሌለው በመሆኑና በኤጀንሲው የተሰጡ የእርምት ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ባለማድረጉ የእውቅና ፈቃዱ ከመስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲሰረዝ ሆኗል፡፡

ይኼው ኮሌጅ ከሕግ ውጪ የተቀበላቸውን ተማሪዎች እንዲያሰናብት፣ በመማር ላይ ያሉ ሕጋዊ የሆኑ ተማሪዎችም እውቅና ወዳላቸው ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ፣ እስከ 2007 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መጨረሻ ድረስ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ሕጋዊ ተማሪዎችን ብቻ እንዲያስመርቅ ተወስኖበታል፡፡

አዳማ የሚገኘው ሐራምቤ ኮሌጅ የታዩበትን የሕግ ጥሰቶች ማስተካከሉ እስኪረጋገጥ ድረስ በርቀት ትምህርት አዲስ ተማሪዎችን እንዳይቀበል ተደርጓል፡፡ ከሕግ ውጪ የተቀበላቸውን፣ እንዲሁም ባልተፈቀደላቸው ቅርንጫፍ ማዕከላትና የትምህርት መስኮች ተቀብሎ የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች እንዲያሰናብት፣ እንዲሁም በመደበኛ መርሐ ግብር ለሚሰጠው ሥልጠና በመመርያው መሠረት በየፕሮግራሙ የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን ቋሚ መምህራን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በማሟላት እንዲያስገመግም ተወስኖበታል፡፡

በኮሌጁ ላይ ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ሊተላለፍበት የቻለው መስፈርቱን የማያሟሉ ተማሪዎችን በመቀበሉ፣ ባልተፈቀደለት ቅርንጫፍ ማዕከላት የርቀት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማሩ፣ ያልተፈቀደለትን የትምህርት መስኮች የተፈቀደለት በማስመሰል በማስታወቂያ በማውጣቱ፣ ባልተፈቀደለት የደረጃ ስያሜ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› በሚል እየተጠቀመ በመሆኑ፣ ለደረጃው የተቀመጠውን መስፈርት በማያሟሉ መምህራን ተጠቅሞ ሲያስተምር በመገኘቱ ነው፡፡

ሻሸመኔ ከተማ የተቋቋመውም ፓራዳይዝ ኮሌጅ መስፈርቱን የማያሟሉ ተማሪዎችን መቀበሉና ባልተፈቀደለት የደረጃ ስያሜ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› በሚል እየተጠቀመ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ በዚህም የሕግ መሠረት የታየበትን የሕግ ጥሰቶች መስተካከላቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በርቀት ትምህርት አዲስ ተማሪዎችን እንዳይቀበል ተደርጓል፡፡

ከዚህ በፊት ከመስፈርት ውጪ የተቀበሏቸውን ተማሪዎች እስኪያሰናብቱ ድረስ የርቀት ትምህርት እንዳይሰጡ የተወሰነባቸው ዩኤስ ኮሌጅና ያርድስቲክ የርቀት ትምህርት ኮሌጅ ውሳኔውን ተቀብለው ማስተካከያ በማድረጋቸው አዲስ የርቀት ተማሪዎችን እንዲቀበሉ ኤጀንሲው የፈቀደላቸው መሆኑን ከአቶ ታረቀኝ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...