ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በሚደረገው ስደት በሽዎች ለሚቆጠሩት የሞት ምክንያት የሆነው የየብሱ ሐሩር ወይም የሜዴትራኒያን ባህር ማዕበል፣ ወይም ከልክ በላይ የጫኑ ጀልባዎች መስመጥ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በሕገወጥ ስደትና በሜዴትራኒያን ባህር ዙሪያ በተቀነባበረ መንገድ የሚካሄደው የማፊያ ወይም የሽፍቶች ወንጀል ጭምር ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ወደተለያዩ አገሮች ከተሰደዱ 350 ሺሕ ስደተኞች፣ 207 ሺሕ ያህሉ የሜዴትራኒያን ባህርን ማቋረጥ የቻሉት በባህሩ ዙሪያ ተደራጅተው ገንዘብ እያስከፈሉ ከሚያሻግሩ ሽፍቶች የተስማሙ ብቻ እንደሆኑ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ብቻ 1,850 የሚጠጉ ስደተኞች በሜዴትራኒያን ባህር ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ሲል ዘዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡
የጣሊያን ባህር ኃይል እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ወደ አውሮፓ ለመግባት፣ በተለይ ከአፍሪካ የሚሰደዱ ዜጐችን ለመታደግና ከገቡበት መከራ ለማውጣት እየሠሩ ቢሆንም፣ በሜዴትራኒያን ባህር አካባቢ የተደራጁትንና በስደተኞች ላይ ወንጀል የሚፈጽሙትን ለመግታት ለጊዜው አልተቻላቸውም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ብቻ እስከ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ከስደተኞች አግኝተዋል የሚባሉትን ሽፍቶች በቀላሉ ማስቆምም ቀላል አይሆንም፡፡ ሆኖም በተለያየ ጊዜ ሲያዙና ለፍርድ ሲቀርቡ ይሰማል፡፡
ሰሞኑን ኒውስዊክ ይዞት በወጣው ዘገባ፣ በሜዴትራኒያን ባህር የተደራጁትንና የአፍሪካን ስደተኞችን ለስቃይ፣ ለሞትና ሁሉንም ሴት ስደተኞች ለአስገድዶ መድፈር ሲዳርጉ የነበሩ 24 ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን የተመለከተ ነው፡፡ እነዚህ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ በየበረሃው ያስቀሩ፣ በቂ ክፍያ ያልከፈሉትን በየቦታው አጉረው ያስቀመጡ፣ ሰዎችን ለረሃብና ለእንግልት ብሎም ለሞት የዳረጉ ናቸው፡፡ ብዙዎቹም ተጠቂዎችም የሶሪያ፣ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ ዜጐች ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2013 በላምፔዱሳ የሰመጠውን ጀልባና በ366 ሰዎች ላይ የደረሰውን ሞት ተከትሎ ምርመራ ሲያካሂድ የነበረው ጣሊያናዊው ካሎጄሮ ፌሬራና ሌሎች ተባባሪዎቹ 526 ገጽ ያለውን፣ የ24 አፍሪካዊ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አቀናባሪዎች ወንጀልን የሚተነትነውን መዝገብ ጠቅሶ ኒውስዊክ በዋና አጀንዳነት ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ ከእነዚህ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› በማለት ኤርሚያስ ግርማይ ስለተባለ ሕገወጥ የስደት አቀነባባሪ አትቷል፡፡ ኒውስዊክ የወንጀለኞቹን ጉዳይ በዋናነት የያዙትን ፌሬራ ጠቅሶ፣ ኤርማያስ ግርማይን ‹‹ሰዎችን እንደ ቁሳቁስ በመቸብቸብ ገንዘብ የሚያጋብስ ጨካኝና ሩህሩህ ልብ የሌለው ወንጀለኛ፤›› ሲል ገልጾታል፡፡
የኤርሚያስ የሕገወጥ ዝውውር ሰንሰለት በቁጥጥር ሥር ከመዋል ሥጋት ነፃ የነበረ ነው፡፡ ከማዕከላዊ በተለይም ስደተኛ ከሚበዛበት ከምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞች ተነስተው ሊቢያ፣ ከዚያም ጣሊያን ከዚህ ሲያልፍም ወደ ሌሎች አገሮች ባደረጉት ጉዞ ሁሉ የተሟላ አገልግሎትን ያቀርባል፡፡ መጠለያ፣ ትራንስፖርትና ምግብም በሕገወጥ ዝውውሩ ተጠቃሚ ለመሆን ያላቸውን ጥሪት ለሚከፍሉ ሁሉ የሚሟላ ነው፡፡ ስማቸውንና የት እንደሚገኙ ማወቅ ግን ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ፌሬራ ይህንን ‹‹የተደራጀ የወንጀል መረብ›› ይሉታል፡፡ በቅብብል መረቡ የሚሸጋገሩ ቀድመው መክፈል አለባቸው፡፡ በጉዞ ላይ ባህር ወይም በረሃ በልቷቸው ቢቀሩም ኤርሚያስ የሚያጣው ነገር የለም፡፡ ገንዘቡ በእጁ አንዴ ገብቷልና፡፡
ኒውስዊክ ‹‹ኢትዮጵያዊ ነው›› ብሎ ወንጀለኛነቱን የተረከለትን ኤርሚያስ ለማነጋገር ባይችልም፣ የኤርሚያስ ደንበኞች የነበሩ ስደተኞችን ጠይቆ እንዳሰፈረው፣ ኤርሚያስ ውልደቱ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ ሥራውን ያቀነባብር የነበረው ደግሞ ሊቢያ ተቀምጦ ነው፡፡ 40 ዓመት የሚገመተው ኤርሚያስ አጠር ያለና ደንዳና ነው፡፡ የተማረ ባይመስልም አፈ ጮሌ ነው፡፡ አመለካከቱ የሰላና የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገርም ይችላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዓረብኛና በኤርትራና በትግራይ በስፋት የሚነገረውን ትግርኛ ያቀላጥፋል፡፡
በሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ከአሥር ዓመት ላላነሰ ጊዜ ሠርቷል፡፡ እንደ ሌሎች ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በሊቢያ ባህር ዳርቻ፣ በትሪፖሊና በምዕራብ ሊቢያ በምትገኘው ዙዋራህ ወደብ በማድረግ ሰዎችን በሜዴትራኒያን ባህር ወደ ጣሊያን ሲሲሊ፣ ሮምና ሚላን ያሸጋግራል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት በመርከብ የሚደረግ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መቆጣርና የሚመጡበትን መርከብ መከታተል ሲጀምሩ ደግሞ፣ ኤርሚያስ አዋጭ ሆኖ ያገኘውን ዘዴ ተጠቅሟል፡፡ ከእንጨት የተሠሩ የአሣ ማስገሪያ ጀልባዎችን በመግዛት ሰዎችን ሲያዘዋውር ከርሟል፡፡ ጀልባዎቹ አንድም በሜዴትራኒያን ባህር ሰምጠው የሚቀሩ ናቸው፡፡ ጀልባው ዕድል ቀንቶት ሲሲሊ ከደረሰ ደግሞ ከስደተኞች ጋር ሲሲሊ ይቀራል፡፡
ኤርሚያስ በሊቢያ ሆነው ወደ ጣሊያን ለመግባት የጓጉ ስደተኞች በሌላ ጀልባ እንዳይጓዙበት ሲልም በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የሚያጉርበት መጋዘን በዙዋራህ ተከራይቷል፡፡ በመጋዘኑ የሚታጐሩ ስደተኞች የእጅ ስልካቸውን በሙሉ የሚቀማ ሲሆን፣ ተቆልፎባቸውም ይከርማሉ፡፡ ጀልባ መጥቶ ዕድል የቀናቸው ከመጋዘኑ ሲወጡም የአንዱ ዜጋ ከአንዱ፣ ብዙ መክፈል የሚችለውና የማይችለው ተቀላቅሎ አይሄድም፡፡ ስደተኞች በዜግነታቸውና በሚከፍሉት መጠን የሚደራጁ ሲሆን፣ ብዙ መክፈል የሚችሉት ሶሪያውያን ቅድሚያውን የሚያገኙ ናቸው፡፡ ሶሪያውያን ጀልባው ላይ ሲጫኑም የላይኛው ክፍል ሲሆን፣ ቅናሽ ዋጋ የሚከፍሉት አፍሪካውያን ከጀልባው የታችኛው ክፍል ያለምግብና ውኃ የሚቆለፍባቸው ናቸው፡፡
በማዴትራኒያን ባህር ያሉ አብዛኞቹ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እርስ በርሳቸው ሰንሰለት አላቸው፡፡ የኤርሚያስ ግን ከዚህም የዘለለ ነው፡፡ ኤርሚያስ በሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በናይጄሪያና በኤርትራ ከሚገኙና ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ከባድ ተሽከርካሪ ከሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ጋር ሁሉ ግንኙነት አለው፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም በሲሲሊ፣ በሮምና በሚላን ከሚገኙ የስደተኞች ማዕከላት፣ በጀርመን በርሊን፣ በፈረንሳይ ፓሪስ፣ በስዊድን ስቶክሆልም እንዲሁም በእንግሊዝ ለንደን ግንኙነት አለው፡፡ በየአገሮቹ ካሉ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋርም ገንዘብና ሰዎች ይለዋወጣል፡፡
ኤርሚያስ በአብዛኛው የገንዘብ ዝውውሩን የሚያካሂደው በኢትዮጵያ፣ በእስራኤል፣ በስዊዘርላንድ እንዲሁም አሜሪካ በሚገኙ ሕጋዊ የገንዘብ ዝውውር መስመሮች መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡ ስደተኞቹ ከሊቢያ ወጥተው ኤርሚያስ ግንኙነት በፈጠረባቸው አገሮች ሲደርሱም፣ ተቀባዮቻቸው ሌላ ገንዘብ ተቀብለው መሄድ ወደሚፈልጉበት አገር ለማድረስ አዋጭ የሆነውን መንገድ ያመቻቻሉ፡፡ ኤርሚያስ ብዙ መክፈል ለሚችሉት ስደተኞች ሕገወጥ ፓስፖርት፣ ሐሰተኛ የጋብቻ ማስረጃ፣ አንዳንዴም አምባሳደሮችን በገንዘብ በመያዝ ሕጋዊ ፓስፖርትና ቪዛ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ወንጀል መርማሪው ፌሬራ ያስረዳሉ፡፡ ጠቀም ያለ ለሚከፍሉት ደግሞ የአውሮፕላን ጉዞን ያመቻቻል፡፡
ፌሬራ እንደሚሉት፣ ኤርሚያስ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመክበር በአንድ ቦታ ሁሉም አገልግሎት የሚሰጥበት ዓለም አቀፍ መረብ ዘርግቷል፡፡ በተለያዩ አገሮች የሚገኙት ተወካዮቹም ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ለማዘዋወር አቅሙና ዕውቀቱ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ በዓለም በየትኛውም ቦታ የማይገኝ የኤርሚያስና የግብረ አበሮቹ ግዛት ነው፡፡ ‹‹ተቀያያሪና አዳዲስ ክስተቶች በተፈጠሩ ቁጥር በዚያው ልክ የሚተጣጠፍ፣ አዳዲስ ችግሮችን የሚቋቋም አራት ጥንድ እግሮች ያሉት የባህር ፍጥረት ነው፤›› ሲሉ በጣሊያን ፓሌርሞ የክስ መዝገቡን ያዩት ዳኛ ይናገራሉ፡፡ ኤርሚያስ በሕገወጥ ሥራ ውስጥ ሆኖ ታዋቂ የሆነው ስደተኞችንና የስደተኛ ቤተሰቦችን በማሳመን ኃይሉ ነው፡፡ አብዛኛውን ቀኑን የሚያሳልፈው ከስደተኞች ቤተሰቦች ጋር በስልክ ሲያወራ ነው፡፡ የላኳቸው ቤተሰቦች ያለምንም ጉዳት ከሚፈለገው አገር እንደሚደርሱ ያሳምናል፡፡ ገንዘቡንም ይቀበላል፡፡
በኢትዮጵያ በሚገኙ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ከሚወጡት አብዛኞቹ ኤርትራውያን ታዳጊ ሕፃናት ይበዛሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብቻውን ለተገኘ ሕፃን ማንኛውም የአውሮፓ አገር ነፃ ጥገኝነት ስለሚሰጥ ነው፡፡ ሕፃኑ ኢትዮጵያ ከሚገኘው የስደተኞች ካምፕ ከሄደ በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር የሚገናኝበት መንገድ በአዘዋዋሪዎች ይመቻቻል፡፡ ቤተሰቦች ከልጃቸው ለመቀላቀል ለትራንስፖርት እስከ ማዴትራኒያን ባህር ላለው ጉዞ 1,800 ዶላር፣ ባህሩን ለማቋረጥ ደግሞ ተጨማሪ 1,800 ዶላር ይከፍላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ቀድሞ የወጣው ሕፃን በሊቢያ በሚገኘው የኤርሚያስ መጋዘን ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ኤርሚያስ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድና ክትትል በበዛበት ሥራ፣ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት ሥራው የተሳካለት በማግባባት ችሎታው ነው ይላል ዘገባው፡፡ ለኒውስዊክ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የፖሌርሞ ፖሊስ፣ ‹‹ይህ ዝርፊያ አይደለም፡፡ ይህ ከሰዎች ጋር መደራደርና ተዓማኒነት ማግኘት ነው፡፡ ኤርሚያስ የበለጠ ታማኝ በሆነ ቁጥር ብዙ ሰዎች እሱ ጋ ይሄዳሉ፤›› ብሏል፡፡
የጣሊያን ወንጀል መርማሪዎች እ.ኤ.አ. በ2014 በሮም 36 ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን ወንጀል 1,200 ገጽ ባለው መዝገብ አቅርበው ነበር፡፡ በሰኔ 2015 ደግሞ 44 ሰዎችን ለተመሳሳይ ምርመራ በቁጥጥር ሥር አውለዋል፡፡ በጣሊያን ሮም እንዲሁም ሲሲሊና ሚላን ተቀምጠው ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ ዜጐችን የሚያዘዋውሩ ሕገወጦች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዝተዋል፡፡ የጣሊያን መንግሥትም በአዘዋዋሪዎቹ ላይ አደን ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ የተዘረጋውን ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መረብ ለመበጣጠስ ጣሊያን ከአውሮፓ ኅብረት ጋር እየሠራች መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡