Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርለኢትዮጵያ ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት የተሻለ ነው

ለኢትዮጵያ ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት የተሻለ ነው

ቀን:

በዶ/ር አደም ካሴ

የምርጫን ውጤት በእርግጠኝነት ከምርጫው በፊት ማወቅ ከሊበራልም ሆነ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መለያ ባህርያት ጋር የሚፃረር ነው፡፡ አዳም ፕርዜዎርስኪ በትክክል እንዳለው፣ ዴሞክራሲ የተለያዩ ፍላጎቶች ያላቸው አካላት በሥርዓቱና በአግባቡ እንዲወዳደሩ በማድረግ፣ እርግጠኛ አለመሆንን የሚያረጋግጥ ተቋማዊ አሠራር ይዘረጋል፡፡ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ሁሉንም ባያስደስትም ሁሉም የጠበቀው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የገዥው ፓርቲ ቃል አቀባዮች ይፋዊ በሆነና ባልሆነ መንገድ እንደገለጹት ከዚህ የተሻለ ውጤት ይመርጣሉ፡፡

ይህ የተለያየ ፍላጎት እንዳለ ሆኖ ከውጤቱ በኋላ በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሥርዓት ለተንጋደደው ውጤት ስላደረገው አስተዋጽኦ ክርክር እንዲደረግ አነሳስቷል፡፡ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታና የገንዘብ ችግር ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደሚጎዳቸው ይታወቃል፡፡ አሁን ጥያቄው ኢትዮጵያ የምትከተለው የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ውጤት እንዳያመጡ አድርጓል ወይ ነው፡፡

- Advertisement -

አንዳንዶች ሕጋዊ የሆኑና ከሕግ ውጪ የሚወሰዱ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ተቃዋሚዎች ላስመዘገቡት ውጤት ተጠያቂ የሚያደርጉ ሲሆን፣ የተሻለ ሁኔታ ከተፈጠረ የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ብዝኃነትን በማስተናገድና የተረጋጋ መንግሥት በመፍጠር ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የተመቸ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ይህ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በጻፏቸው ጽሑፎች ተንፀባርቋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው የምርጫ ሥርዓቱ በተፈጥሮው አግላይ በመሆኑ ኢሕአዴግ ለተጎናፀፈው ፍፁም የበላይነት አስተዋጽኦ አድርጓል በሚል ይከራከራሉ፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትን መከተል እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ይህ አቋም በቅርቡ አቶ ውብሸት ሙላት በዚሁ ጋዜጣ በጻፉት ጽሑፍ የተንፀባረቀ ሲሆን፣ ሳምንታዊው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ‘ፎርቹን’ም በርዕሰ አንቀጹ ይህንን ለውጥ እንደሚደግፍ አቋም ይዞ ጽፏል፡፡

ይህ ክርክር ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ነው፡፡ ምንም እንኳን የምርጫ ሥርዓቱ በመራጮች ባህርይና በምርጫ ውጤቱ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ጥልቀት ያለው አካዴሚያዊና ፖለቲካዊ ትንታኔን የሚሰጥ ጥናት ባይኖርም፣ ክርክሩ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ እስካሁን ያለው ክርክር የትኛው የምርጫ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የተሻለ ነው የሚል ነው፡፡ በሁለቱም የምርጫ ሥርዓቶች ላይ የተጻፉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የራሳቸው ጠቀሜታዎች አሉዋቸው፡፡ የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ዕጩ ተወዳዳሪው የትኛውንም ፓርቲ ቢወክል በዕጩ ተወዳዳሪውና በምርጫ ክልሉ መካከል ቀጥተኛና ግልጽ የሆነ ግንኙነት ይፈጥራል፡፡

ይህ ግንኙነት ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ የመራጩን ሕዝብ ግብረ መልስ በቀጣይነት ለማግኘትም የሚያስችል ነው፡፡ ይሁንና ይህ የምርጫ ሥርዓት የመራጮችን ድምፅ በማባከን ከዴሞክራሲ መሠረታዊ መርሆዎች አንዱ የሆነውን ‘አንድ ሰው፣ አንድ ድምፅ’ መርህ ይቃረናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ድምፆችን ወደ ወንበር በመቀየር የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን በፓርላማ አባላትና በምርጫ ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት ግልጽ ስላልሆነ ዕውቅና ለመስጠትም ሆነ ተጠያቂ ለማድረግ የሚመች አይደለም፡፡

ከእነዚህ የምርጫ ሥርዓቶቹ ተፈጥሯዊ መለያ ባህርያትና ውጤቶች ባሻገር፣ በተለያዩ አገሮች መራጮች እንዳላቸው ባህርያት፣ እንደሚቀርቡት ዕጩዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ሁኔታ የምርጫ ሥርዓቶቹ የተለያየ ውጤት አላቸው፡፡ አቶ ውብሸት እንደጠቆሙት የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ጥቂት ጠንካራ ፓርቲዎችን ለመፍጠር ያስችላል የሚል አካዴሚያዊ ስምምነት ያለ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ተቃራኒው ውጤት የተመዘገበውም ለዚሁ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን መፍላት በር ይከፍታል ቢባልም፣ እንደ ሩዋንዳ ባሉ አገሮች የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ፈጥሯል፡፡

ምንም እንኳን የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ያለውን ድክመት ለማስተካከል አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ላይ መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ እነዚህን ችግሮች ማቃለል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ምክንያታዊና ተቀባይነት ያለው ዝቅተኛ የድምፅ ብዛት በመወሰን ትንንሽና ፅንፈኛ ፓርቲዎችን ማግለል ወይም ጥምረት እንዲፈጥሩ ማስገደድ ይቻላል፡፡ ይሁንና ዝቅተኛው የድምፅ ብዛት ልክ ቱርክ እንዳደረገችው አሥር በመቶ ከፍተኛ ከሆነ፣ እንደ ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ሁሉ ድምፆችን ሊያባክን ይችላል፡፡

እንደ ጣሊያን ያሉ አገሮች ደግሞ ለየት ያለ የምርጫ ሥርዓት በመፍጠር የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት የአናሳና ያልተረጋጋ መንግሥት እንዳይፈጠር አድርገዋል፡፡ ጣሊያን በቅርቡ ባሻሻለችው የምርጫ ሥርዓት 40 በመቶውን የመራጮች ድምፅ ያገኘ ፓርቲ በፓርላማው አብላጫውን ወንበር ያገኛል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው ሥርዓት ፓርቲው ምንም ያህል ድምፅ ቢያገኝ፣ በአንፃራዊነት ከሌሎች ከተሻለ የፓርላማውን አብላጫ ወንበር እንዲቆጣጠር ያስችል ነበር፡፡ ይህ የምርጫ ሥርዓት ውድቅ የተደረገው በሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ነበር፡፡

ከእነዚህ ሁለት የምርጫ ሥርዓቶች አንዱን ከመምረጥ ባሻገር በርካታ አገሮች የአብላጫ ድምፅን ከተመጣጣኝ ውክልና ጋር በመቀላቀል፣ ለአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ የሚስማማ የምርጫ ሥርዓትን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ አብነት የምትሆነው ጀርመን ነች፡፡ ለታችኛው ምክር ቤት (የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቻ) አባላት የሚደረገው ምርጫ የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓትን ተግባራዊ ሲያደርግ፣ ለላይኛው ምክር ቤት (የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቻ) አባላት ደግሞ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

የመጀመሪያው ምርጫ የፓርቲ አባል ለሆነ ወይም ላልሆነ ዕጩ የግል ምርጫ የሚደረግበት ሲሆን፣ ሁለተኛው ግን በክልል ደረጃ ለፓርቲዎች በሚገኝ ድምፅ ይወሰናል፡፡ በተጨማሪም በተመጣጣኝ ውክልና የምክር ቤት ወንበር ድልድል ተሳታፊ ለመሆን፣ ከአጠቃላይ መራጩ አምስት በመቶ ድምፅ ማግኘትና በ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ቢያንስ ሦስት አባላትን ማስመረጥ ይጠይቃል፡፡ አንድ ፓርቲ በ‘አንደኛ አላፊ’ ምርጫ ያሸነፈው የወንበር ብዛት በተመጣጣኝ ውክልና ከሚያገኘው ከበለጠ፣ ሌሎቹ ፓርቲዎች ይህን ለማካካስ ተጨማሪ ወንበሮችን ያገኛሉ፡፡

ቅልቅል የምርጫ ሥርዓቶች በአጠቃላይ በጀርመን ደግሞ በተለይ ከሁለቱ የምርጫ ሥርዓቶች የሚገኘውን ጥቅም በመያዝ ያሉባቸውን ችግሮች ለማስወገድ ይጥራሉ፡፡ በተቻለ መጠን ድምፆች ወደ ወንበሮች እንዲቀየሩ ያደርጋል፡፡ ይህ የድብልቅ አሠራር ፖለቲካ ፓርቲዎች ወንበር እንዲያገኙና አማራጮቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ በመፍጠርና በመራጮችና በተመራጮች መካከል ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግ ተመራጭ ነው፡፡ በተጨማሪም መራጮች ድምፃቸውን ከፋፍለው በጥንቃቄ እንዲሰጡም አጋጣሚውን ይፈጥራል፡፡ ይህ የጀርመን አሠራር ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ልምድ ሊሆን ይችላል፡፡ ኔፓልም በቅርቡ የፌዴራላዊ የመንግሥት መዋቅርን ስትቀበል ይህንኑ የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ ይህ የድብልቅ አሠራር በምርጫ 2002 እና 2007 ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ ገዥው ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ቢያገኝ እንኳን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውክልና እንዲኖራቸው በማድረግ የተረጋጋ መንግሥት ለመፍጠር ያስችል ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ሌላው የሚነሳው ጉዳይ በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ የሚደረገው የምርጫ ሥርዓት ሰፊ የሆነ ማኅበራዊ፣ ሥነ ሕዝባዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልዩነት ባላቸው ክልሎችም ተግባራዊ መደረጉ ነው፡፡ የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት በፌዴራል ደረጃ ነገሮችን ለማስታረቅ ጠቃሚ ነው ተብሎ እንኳን ቢታሰብ፣ ሁሉንም ክልሎች በእኩልነት ያገለግላል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ክልሎች በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የተቀመጠውን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ማክበርን ጨምሮ ዝቅተኛ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦላቸው የራሳቸውን የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጋቸው ጠቃሚ ስለመሆን አለመሆኑ ውይይት መክፈት አለብን፡፡ በበርካታ የፌዴራል የመንግሥት አወቃቀር የሚከተሉ አገሮች ክልላዊ ምርጫዎች በራሳቸው በክልሎቹ ይካሄዳል፡፡ ለአብነት ጀርመንንና አሜሪካን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ ክልሎች እርስ በርስ እንዲማማሩና በፌዴራል ደረጃ ለውጥ እንደሚመጣም ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ክልላዊ መንግሥታት የዴሞክራሲ ላብራቶሪ በመሆንም እንዲያገለግሉ ማድረግ ይቻላል፡፡

በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ተስማሚ በሆነው የምርጫ ሥርዓት ዙሪያ ክርክር መፈጠሩ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ከሁለቱ ዋነኛ የምርጫ ሥርዓቶችን አንዱን ከመምረጥ ወጥተን ለእኛ የሚስማማውን ድብልቅ አሠራር ብንፈጥር የተሻለ ነው ብሎ አስባለሁ፡፡ ይህ ዓይነት ንቁ ክርክርና ውይይት በሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችም ሊቀጥል ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲ በእነዚህ ውይይቶች ውስጥ ተሳታፊ እንደሚሆንና ሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ እንደሚያስብ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በተግባር ሥር የሰደደው ሕገ መንግሥቱ እንደ ቅዱስ መጽሐፍ የማይቀር አድርጎ የማየት ፖሊሲ ጠቃሚ አይደለም፡፡ ለውጥ የጥንካሬ እንጂ የድክመት ምልክት አይደለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ዶ/ር አደም ካሴ መቀመጫቸውን ጀርመን ያደረጉ የሰብዓዊ መብትና የሕገ መንግሥት ተማራማሪ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...