Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልየስበት ኃይልን የፈተነው ምትሀተኛ

  የስበት ኃይልን የፈተነው ምትሀተኛ

  ቀን:

  ጐልማሳው ከወገቡ በታች በጥቁር ጨርቅ ተሸፍኖ ለሴኮንዶች ቆየ፡፡ ጨርቁ ሲገለጥ ከመሬት ጥቂት ሴንቲ ሜትሮች ከፍ ብሎ በአየር ላይ ቆሟል፡፡ ጥቂት ሰኮንዶችን አስቆጥሮ ወደ መሬት ተመለሰ፡፡ ታዳሚዎች ዓይናቸውን ለማመን ተቸገሩ፡፡ ከመሬት ወደ ላይ ከፍ እንዲል ያገዘው ቁስ ፍለጋ ወደ መድረኩ አማተሩ፡፡ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ በአግራሞት ከመቀመጫቸው ተነስተው አጨበጨቡ፡፡ ምትሀተኛው በአየር ላይ የመቆሙ ምስጢር ምንድን ነው? የመሬት ስበት ኃይልን አሸንፎ ይሆን ወይስ ሌላ ብለው እርስ በርስ የሚጠያየቁ ነበሩ፡፡

  ትዕይንቱ ፈረንሳዊው ምትሀተኛ ጉላውሜ ቫሌ ለዝግጅቱ መዝጊያ የመረጠው ነው፡፡ ሰኔ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ የተገኙ ታዳሚዎች አንድ ሰዓት ከ30 ደቂቃ የወሰደውን ትዕይንት በፅሞና ተከታትለዋል፡፡ በምሽቱ ላቀረባቸው አስገራሚ ትዕይንቶች መደምደሚያ ያደረገው ከመሬት መነሳት (ሌቪቴሽን) ብዙዎችን አስደንቋል፡፡

  ጉላውሜ ቴላፐቲ፣ ማግኔቲዝም፣ ሌቪቴሽን በሚባሉና ሌሎችም ትዕይንቶች ይታወቃል፡፡ ‹‹የምናውቃቸውን ቁሳቁሶች ባለመድነው መልኩ ያሳየናል›› በማለት የሚገልጹት ድረ ገጾች አሉ፡፡

  ካቀረባቸው ትዕይንቶች መካከል ውኃ የያዘ ብርጭቆን በአየር ላይ ለሰንኮንዶች ያቆመበት ይጠቀሳል፡፡ ለሌላው ትዕይንቱ ሻማ ለኮሰ፡፡ የእሳቱን ነበልባል ከሻማው ለይቶ በጥቁር ጨርቅ ላይ አሳርፎ ሲዘዋወር ታይቷል፡፡ ነበልባሉን ወደ ሻማው ከመለሰ በኋላ በወረቀት ቁርጥራጮች ከሻማው እሳት እየለኮሰ ጎረሳቸው፡፡ ቀጥሎም ነበልባሉን በክብ ፕላስቲክ አስገብቶ በመላ ሰውነቱ ላይ አንቀሳቅሶታል፡፡ በአፉ ገብቶ በጆሮው ሲወጣ እንዲሁም በጀርባውና በትከሻው ሲያዘዋውረውም ታይቷል፡፡

  ውኃ እጆቹ ላይ አፍስሶ አንዱን መዳፉን ከሌላው ጋር ለጥቂት ሰኮንዶች በማሻሸት ወደ መጠነኛ በረዶ ሲለውጥ ተስተውሏል፡፡ በዕለቱ የተገኘው አብዛኛው ታዳሚ ከእያንዳንዱ ትዕይንት ጀርባ ያለውን ምስጢር የሚመራመር ይመስላል፡፡ ምትሀተኛው ምስጢሩን ባያወጣም፣ የአዕምሮ በርን ስለመክፈትና ስለነገሮች በነፃነት የማሰብ ችሎታን ማዳበር በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡

  ከመድረክ ትዕይንቶቹ በበለጠ ከታዳሚው ጋር ያቀራረበው ሰዎች የሚያስቡትን ሳይገልጹለት ስለምን እያሰላሰሉ መሆኑን ማወቁ ነው፡፡ ሦስት ፈቃደኛ ታዳሚዎች ወደ መድረኩ ወጡ፡፡ ታዋቂ ሰው፣ አገርና የቅርብ ወዳጃቸውን እንዲያስቡ ጠየቃቸው፡፡ ያሰቡትን በወረቀት አስፍረው መድረኩ ላይ በሚገኝ ብርጭቆ ውስጥ ጨመሩ፡፡

  ታዋቂ ሰው ያሰበው ወጣት በጭንቅላቱ የሚመላለሰው ሙዚቀኛ እንደሆነ ምትሀተኛው ከገመተ በኋላ ‹‹አንድ ዘፈኑን በልብህ አዚም፤›› አለው፡፡ ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ ‹‹ማይክል ጃክሰን ይሆን?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ልክ ነበረ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አገር ያሰላሰለው ግለሰብ አሜሪካ፣ ኮሎራዶን በወረቀቱ እንዳሰፈረ ገለጸ፡፡ ታዳሚው በምስጢር ያሠፈረውን አገር ስም ምትሀተኛው እንዴት እንደደረሰበት ግራ እየተጋባ ወደ መቀመጫው ተመለሰ፡፡ የቅርብ ጓደኛዋን ታሰላስል የነበረችው ታዳጊም ያሰበቻት ጓደኛዋን ስም ተናገረ፡፡ ታዳጊዋ እንደመደናገጥ አለች፡፡ ታዳሚዎቹ ዳግም ማጨብጨብ ቀጠሉ፡፡

  ቀድመው ይተዋወቁ ይሆን? እውነት በሰዎች ጭንቅላት የሚመላለሰውን ማወቅ ይቻላል? ሲሉ የጠየቁ ተስተውለዋል፡፡ ምናልባት ፊታቸው ላይ ከሚነበበውና ከሰውነታቸው እንቅስቃሴ በመነሳት ይሆናል ያሰቡትን የደረሰበት ያሉም ነበሩ፡፡

  ሦስት ግለሰቦች የተለያየ ቁጥር እንዲጠሩ አደረገ፡፡ ሦስቱም ከጠሩ በኋላ ከታዳሚው መካከል በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሐፍ የያዘ ሰው ጠየቀ፡፡ ከተጠሩት ቁጥሮች አንዱ የመጽሐፉን ገፅ ቁጥር፣ ሌላው በዛ ገፅ ያለ መስመርና የተቀረው ዓረፍተ ነገር ይወክላሉ አለ፡፡ ለደቂቃዎች ዓይኑን ጨፍኖ ካሰላሰለ በኋላ መጽሐፉ (ሀሪ ፖተር የተሰኘው ልቦለድ) ላይ የሰፈረውን ዓረፍተ ነገር ገመተ፡፡ ከአንድ ቃል በስተቀር ትክክል መሆኑ ብዙዎችን አስገርሞ፣ ምትሀተኛውም ልክ በመሆኑ መፈንጠዙ የበለጠ አስደንቋል፡፡

  ከጉላውሜ ጋር የሚቀራረቡ አንዳንዴም የተመልካችን ዓይን የሚያጠራጥሩ ትዕይንቶችን የሚያቀርቡ ምትሀተኞች ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይ አውሮፓውያኑ የምትሀት ትዕይንቶች የሚቀርቡባቸው የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች ሳይቀር አሏቸው፡፡ በየአገሮቹ የተሰጥኦ ውድድሮች ላይም የብዙዎችን ትኩረት ያገኛሉ፡፡ ምትሀት የብዙዎችን ቀልብ የሚስብና ‹‹እንዴት?›› የሚል ጥያቄ ያለማቋረጥ የሚያጠይቅ መሆኑም እሙን ነው፡፡

  በተለያዩ ማኅበረሰቦች ልዩ ልዩ ትርጓሜዎች ያለው ምትሀት፣ ለሳይንቲስቶችም የምርምር በር የከፈተ ነው፡፡ ምትሀተኞች ከረዥም ጊዜ ልምምድ በኋላ ለትዕይንቱ የሚጠቅሟቸው ቁሳቁሶች እንዳሉ ይገለጻል፡፡ አንዳንድ ተመራማሪዎች ምትሀት ከተመልካች እይታ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ የሰው ልጅን ሥነ ልቦና በጥልቀት አጥንቶ የሚተገበር ነው የሚል ማብራሪያ ያላቸው እንዳሉ ሁሉ፣ ምትሀትን ከመንፈሳዊ እምነት ጋር የሚያስተሳስሩም አይታጡም፡፡

  ምትሀተኛና ኮሜዲያን ጉላውሜ ወደ ሙያው የገባው በ24 ዓመቱ ሲሆን፣ በዘርፉ በዓለም ዝናን ካተረፉ መካከል አንዱ ነው፡፡ ትዕይንቱን በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትና በድሬዳዋ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝም አቅርቧል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...