‹‹ጉዲፈቻ›› በ1999 ዓ.ም. ለዕይታ የበቃ ፊልም ነው፡፡ ወቅቱ እንዳሁኑ ፊልሞች የተበራከቱበት አልነበረም፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ የተለቀቀው የቴዎድሮስ ተሾመ ፊልም ‹‹ቀዝቃዛ ወላፈን›› እና ‹‹ጉዲፈቻ››ን ብዙዎች ተመልክተዋቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ የፊልም ቁጥር ጨምሮ ርዕስ ለማስታወስም ሊከብድ ይችላል፡፡ የ‹‹ጉዲፈቻ›› ደራሲ ደመረ ጽጌ እንደሚለው፣ ፊልሙ ጥሩ ምላሽ ያገኘበት ሥራው ነው፡፡ በወቅቱ የነበረውን የተመልካች ብዛትም ያስታውሳል፡፡
ፍቃዱ ተክለማርያም፣ መሠረት መብራቴና ተስፉ ብርሃኔ በመሪነት የተወኑበት ‹‹ጉዲፈቻ›› የደመረ ለመጀመሪያ ጊዜ በሲኒማ ቤት ስክሪን የቀረበ ፊልሙ ነው፡፡ ከዛ ቀደም የሠራቸው ሁለት ፊልሞች በቪኤችኤስ የቀረቡ ነበሩ፡፡ ቄራ አካባቢ የተወለደው ደመረ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ ነበር ጐን ለጐን የሥነ ጽሑፍ ችሎታውን ማዳበር የጀመረው፡፡ በታዳጊነቱ ብዙ የሥነ ጽሑፍ ውድድሮችን ተካፍሏል፡፡ መምህራኑም ያበረታቱት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ከፈረንሳይ መንግሥት በተገኘ ነፃ የትምህርት ዕድል ኤኮል ቴክኒክ የተባለ ትምህርት ቤት ገብቶ በምሕንድስና በ1984 ዓ.ም. ተመረቀ፡፡ ምርጫው መሐንዲስነት አልነበረም፡፡ ሳይውል ሳያድር ምሕንድስናን ተሰናብቶ የፊልም ጽሑፍ ማዘጋጀት ጀመረ፡፡
በ1985 ዓ.ም. ‹‹የነቀዘች ነፍስ›› የተሰኘውን የመጀመሪያ ፊልሙን ሠራ፡፡ አብዛኞቹ የፊልሙ ሠሪዎች ጀማሪ እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ የጠለቀ ዕውቀት ባይኖረውም ቶሎ ዘርፉን መቀላቀሉ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ በእጅጉ እንዳገዘው ይናገራል፡፡ ፊልሙ በቪኤችኤስ 100 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ በቪዲዮ ቤቶች ደግሞ አንድ ብር እየተከፈለ ይታያል፡፡ ፊልሙ ሲሠራ ብዙ ተመልካች ያገኛል ብሎ አልጠበቀም፡፡ ከግምቱ በተቃራኒው ፊልሙ በብዙዎች መታየቱ ለቀጣዩ ሥራው እንዳበረታታው ይገልጻል፡፡
ደመረ ከ‹‹የነቀዘች ነፍስ›› ፊልም በኋላ ‹‹ፍሬ ሕይወት›› የተሰኘ ቴአትር ጽፎ፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር ለሦስት ዓመታት ቀርቧል፡፡ በየክፍለ ሀገሩ ዞሮም ታይቷል፡፡ በቀጣይ ‹‹ሥጋ ያጣ መንፈስ›› የሚል ፊልም ጽፎ በቪኤችኤስ ቀርቧል፡፡ የፊልሙ አዘጋጅ ደበበ እሸቱ ሲሆን፣ ከሙሉዓለም ታደሰና ሌሎች ተዋንያን ጋር ደበበም ተውኖበታል፡፡ ፊልሙ አዲስ አበባ ሒልተን ሲመረቅ የክብር እንግዳ የነበሩት ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ስለፊልሙ አስተያየት ሲሰጡ፣ ‹‹ኅብረተሰቡ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ከሚሥልበት በተቃራኒው በማሳየት የማኅበረሰቡን ሕግ መጣስ ችላችኋል፤›› ማለታቸውን ያስታውሳል፡፡
ወቅቱ የደጃዝማች በላይ ዘለቀን ሕይወት የሚያሳይ ፊልም ለመሥራት ጥናት የጀመረበትም ነው፡፡ የበላይ ዘለቀን ቤተሰቦችና ዘመዶች አግኝቶ ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ ካነጋገራቸው መካከል ልጁ የሻሽወርቅ በላይና የልጅ ልጁ ዘለቀ መታፈሪያ ይጠቀሳሉ፡፡ ለፊልሙ ግብዓት የሚሆኑ አስፈላጊ መረጃዎች ቢሟሉም ስፖንሰር ስላልተገኘ እስከዛሬ (ለ20 ዓመታት) አልተሠራም፡፡ ደመረ እንደሚለው፣ ገንዘብ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ ጐን ለጐን ሌሎች ፊልሞችን መጻፉን ቀጥሏል፡፡
በተፈሪ ዓለሙ የተዘጋጀው ‹‹ስውር ችሎት›› እና በግርማ ዘለቀ አኒሜሽኑ የተሠራለት ‹‹ንጉሥ ናሁሰናይ›› ከሥራዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡ ከጽሑፍ በተጨማሪ የፊልም ዝግጅት የጀመረው በ2002 ዓ.ም. በሠራው ‹‹ስደት›› ፊልም ነው፡፡ ሠርግ ከሚቀረጽበት ካሜራ ወደ ዘመን አመጣሽ መሣሪያዎች መሸጋገር በዘርፉ ያስተዋለው ትልቁ ለውጥ እንደሆነ ይናገራል፡፡
የደመረ ሰባተኛ ፊልም ‹‹አብስትራክት›› ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዶት ሲኒማ ተመርቋል፡፡ ‹‹ዓለማችን በማይታዩ ግን አብረውን በሚኖሩ ምስጢሮች የተሞላች ነች›› የሚል ኃይለቃል የያዘውና በዘመነ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው ልብ አንጠልጣይ ፊልሙ ኤልሳቤጥ መላኩ፣ ቃልኪዳን ጥበቡና ኃይለማርያም ሰይፉ በዋናነት ተውነውበታል፡፡ ባለሙያው ብዙ ጊዜ በአንድ ፊልም ካስት ካደረጋቸው ተዋንያን ጋር ደግሞ ይሠራል፡፡
ሙሉዓለም ታደሰ በሦስት ፊልሞቹ፣ መሠረት መብራቴ በሁለት ፊልሞቹ፣ በላይነሽ አመዴ በሦስት ፊልሞቹና ደበበ እሸቱ በሁለት ፊልሞቹ ተውነዋል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ተዋንያኑ በአንድ ፊልም ሲተውኑ ያሳዩትን ብቃት ተመርኩዞ ለሌላ ያጫቸዋል፡፡
ደመረ በኢትዮጵያ ሲኒማ በዋነኛነት የሚስተዋሉት ችግሮች የታሪክ አወቃቀርና የበጀት እጥረት እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ፊልሞች ወጥነት ስለማጣታቸው የሚሰማው ትችት ባለሙያዎች ለጽሑፍ ጊዜ ሰጥተው ካለማዘጋጀት የመነጨ ነው ይላል፡፡ ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ለፊልም ሥራ በቂ በጀት ማግኘት ፈታኝ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
በቅርቡ የፊልም ፖሊሲ መረቀቁ ለዘርፉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይናገራል፡፡ በተለያዩ ተቋሞች የሚማሩ ባለሙያዎች መበራከታቸው ለውጥ እንደሚያመጣም ያምናል፡፡ ባለሀብቶች ወደ ሲኒማው ዘርፍ ፊታቸውን ማዞር እንዳለባቸውም ይገልጻል፡፡ ይህ የበጀት ችግርን እንደሚቀርፈው ተስፋ ያደርጋል፡፡
አዲሱ ፊልሙ አብስትራክት ዛሬ ሰኔ 13 እና ነገ ሰኔ 14 በየሲኒማ ቤቱ መታየት ይጀምራል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሠራው አንፃር በታሪክ አወቃቀርና በቴክኒክ ለውጥ የታየበት መሆኑን በመግለጽ ‹‹ጥሩ ምላሽ እጠብቃለሁ፤›› ይላል፡፡