የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን አንዱ ሙስናና ብሽልሹ አሠራር ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ በሒደት ላይ ያሉ ጉዳዮች በተለይም ጎላ ጎላ ያሉ የግዥ ተግባራትን ግልጽነት በጎደለው፣ ሕግን ባልተከተለና በተሳሳተ መልኩ እየተፈጸመ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ሲደርሰው የሚያከናውነው የመከላከል ሥራ ነው፡፡
በዚህ የመከላከል ሥራው በ2007 ዓ.ም. አሥር ወራት ውስጥ ግልጽነት የሌላቸው፣ ከሕግና ሥርዓት ውጪ የሆኑ ግዥዎችን በማረም በግዥ ሒደቱ ሊበላ ይችል የነበረ 645 ሚሊዮን ብር የሕዝብ ሀብት ከብክነት ማዳኑን የኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል የመከላከል ተግባሩ ከተመለከታቸው የግዥ ሒደቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተለውን ይመስላሉ፡፡
የአዲስ አበባ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀምና ማስወገድ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለ2007 ዓ.ም. አገልግሎት የሚውሉ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችን ለመግዛት ባወጣው ግልጽ ጨረታ አስቸኳይ የመከላከል ሥራ ማከናወኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ በዚህ የግዥ ሒደት ላይ ከተለዩት ችግሮች መካከል የጨረታ ማስታወቂያ በጋዜጣ ሳይወጣ የጨረታ ሰነዱን ቀድሞ የሸጠ መሆኑ፣ የጨረታውን መሠረታዊ ሒደት የማይለወጡ መሥፈርቶችን በመጠቀም ጨረታ መሰረዝ፣ የጨረታ ሰነዱ የቴክኒክ ፍላጎት መግለጫዎች ተወዳዳሪዎች በግልጽ ሊረዱ የሚችሉት አለመሆን ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም የዕቃዎች የንግድ ምልክት (ብራንድ) መጥቀስ፣ የሚፈለገውን የቴክኒክ ፍላጎት መግለጫዎች ካሟሉ ዋጋ ያቀረበ እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ጥራት እየተባለ ከፍተኛ ዋጋ ያቀረቡ ተወዳዳሪዎች እንዲያሸንፉ መደረጉና በሌሎች ምክንያቶች ከ19.7 ሚሊዮን ብር በላይ ተደርጎ ሊፈጸም የነበረ ግዥ ግልጽነት የጎደለውና ፍትሐዊ የውድድር ሥርዓትን ያልተከተለ በመሆኑ፣ ጨረታው ተሰርዞ ድጋሚ ጨረታ እንዲወጣ መደረጉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን የ30,000 ሜትሪክ ቶን የነጭ ስኳር ግዥ ለመፈጸም የወጣው ውስን ጨረታ ላይ በተደረገው አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ፣ ተወዳዳሪዎችን በቂ ባልሆነ ምክንያት ከውድድር በማግለልና አንድ ተወዳዳሪን ለዋጋ ግምገማ በማሳለፍ ሊከናወን የነበረ ግዥ በነበረበት የአሠራር ክፍተት ምክንያት ተሰርዞ በድጋሚ እንዲወጣ በመደረጉ፣ ከግዥው ከ12 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ለማዳን መቻሉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ሌላው ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና መከላከል ተግባሩ ትኩረት ያደረገው በአገሪቱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል ደግሞ በዋናነት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ይገኝበታል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመስተንግዶ ቱሪዝም ኢንስቲትዩት ሕንፃ ግንባታ ግዥ ለመፈጸም ባወጣው የግልጽ ጨረታ ሒደት፣ የአንድ ሥራ ተቋራጭ የግንባታ መሣሪያዎች ምንጭ ኪራይ (ሊዝ) ወይም ባለቤትነት ሊሆን እንደሚችል እየታወቀ ዩኒቨርሲቲው ተጫራቾችን በውድድር ለመለየት ታወር ክሬንም ሆነ ሌሎች የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን በሚመለከት የባለቤትነት ማረጋገጫ ማቅረብ እንዳለባቸው ጨረታው ሰነዱ ላይ እንደመሥፈርትነት በማስቀመጡ፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ ማቅረብ ባለመቻላቸው ምክንያት ከውድድር እንዲወጡ የተደረገው የመከላከል ሥራ ተወዳዳሪዎቹ በጨረታው ሒደት እንዲሳተፉ ተደርጎ አሸናፊው እንዲለይ ለዩኒቨርሲቲው በተገለጸለት መሠረት ውድድሩ ተካሂዶ ከ372 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚያስገነባው የፎረም ሕንፃ ግንባታ ላይ በተከተለው ግልጽነት በጎደለው የመወዳደሪያ መሥፈርት ሊካሄድ በነበረ የግንባታ ግዥ ሒደት ላይ በተካሄደ አስቸኳይ የመከላከል ሥራ ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳኑን ከሪፖርቱ መረዳት ይቻላል፡፡
አምቦ ዩኒቨርሲቲ የተጋነነና መንግሥትን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ ግዥ ለመፈጸም ያደርግ የነበረውን ሒደትን በመከላከል 75 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉንና በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምግብ አቅርቦት ግዥ ሒደት ላይ በተደረገ የመከላከል ሥራ 16 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
በአጠቃላይ ግልጽነት የሌላቸውና ከሕግና ሥርዓት ውጪ የሆኑ ግዥዎችን በማረም ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ በመቻሉ፣ ሊባክን ይችል የነበረ 645 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ይገለጻል፡፡ ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀልን ከመከላከል በተጨማሪ የሙስና ወንጀሎችን በመመርመር ክስ እንደሚመሠርት ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በሙስና ወንጀልና ለሙስና ወንጀል የተጋለጠ አሠራር መካከል ያለው የልዩነት መስመር ብዥ ያለ ይመስላል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊ ይህንን የኮሚሽኑን ሪፖርት ለፓርላማ አቅርበው የነበሩት ኮሚሽነር አሊ ሱሌማንም ከምክር ቤቱ አባላት በሙስና ወንጀል መከላከልና ማዳን የተቻለው የሕዝብ ሀብት ሙስና አይደለም ብሎ ማመን እንዴት እንደሚቻል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
በሰጡት ምላሽም የሙስና ወንጀል መከላከል ክፍል ጥናት ለማካሄድ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የመንግሥት ተቋማት ክፍትና ፈቃደኛ ሆነው እንደሚጠብቁት ገልጸው፣ የኮሚሽኑ የወንጀል ምርምራ ክፍል በሚሄድበት ወቅት ግን ድብብቆሽ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሥራዎቹም ለየራሳቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ ወደ ወንጀል ለመሄድ ስህተቱ የተፈጸመው በዕውቀት ማነስ ነው ወይስ ባለማወቅ ነው? የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡