Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፍቅርና የመተሳሰብ የመከባበርና የመቻቻል ወር

የፍቅርና የመተሳሰብ የመከባበርና የመቻቻል ወር

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በመላው ዓለም በጾም የሚከበረው የ2007 (1436 ዓመተ ሒጅራ) የረመዳን ወር በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ 11 ቀን ተጀምሯል፡፡

ረመዳን በዓረብ የወራት ቀመር መሠረት ዘጠነኛው ወር ሲሆን በዚህ ወር በመጨረሻው የወር ሲሶ (በሃያኛው ቀን) ፈጣሪ ለነቢዩ ሙሐመድ ቁርዓን ያወረደበት ነው፡፡ ረመዳን የመጀመሪያው የቁርዓን አንቀጽ የወረደበት ወር በመሆኑም በዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ትንሽ ቀደም ብሎ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ ባለው ጊዜ በጾም፣ በጸሎት ጥሩ ነገር በመሥራት፣ በምግባራቸው አርአያ ሆነው በመገኘት ያከብሩታል፡፡

የረመዳን ወር የሚጾምበት የሚጸለይበትና ፈጣሪ ጸንቶ የሚዘከርበት ወር ብቻ ሳይሆን ሰዎች ተዋደው፣ ተፋቅረው፣ ተሳስበውና ተከባብረው እንዲኖሩ በፈጣሪ መታዘዛቸውን ለማስመስከር እጅግ በጣም ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ኢስላም ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ሃይማኖት ሳይለይ የሰላም ሃይማኖት፣ የመከባበርና የመቻቻል ሃይማኖት መሆኑን ከቤተሰብና ከጎረቤት ጀምሮ ያለው ሰው ሁሉ መልካም ምሳሌ ሆኖ በመገኘት የበለጠ የሚረጋገጥበት ነው፡፡

ፈትሑላህ ጉለን የተባሉ ቱርካዊ የሃይማኖት አባት ‹‹የመንፈሳችን ሐውልት››፣ ‹‹ፍቅርና መቻቻል›› በተሰኙት መጽሐፎቻቸውና በሌሎችም ሥራዎቻቸው እንደሚያስተምሩት እስልምና ፍቅር ነው፡፡ እስልምና መከባበር ነው፡፡ እስልምና በአንድ አምላክ ለሚያምኑ ሁሉ ታላቅ አክብሮት የሚሰጥ ሃይማኖት ነው፡፡ እኒህ ምሑር ታላቁ ሙስሊም መምህር መውላና ጀላሉዲን ሩሚን (1207 እስከ 1273) ጠቅሰው እንደሚያብራሩትም ‹‹በምክንያቶች ላይ የተመሠረቱ አስተምህሮቶችን ሳንተው፣ ሐሳብ የሌሽ ሆነን የፈጣሪን ፈቃድ (ከዛሬ ነገ ይፈጸማል ብለን) መጠበቅ ሲገባን ማለትም ጊዜውን በዋዛ ፈዛዛ ሳናሳልፍ፣ ይህችን በመታመስ ላይ ያለች ዓለም ሰላምና ፍትሕ፣ ለሁሉም የምትመች አድርገን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማሸጋገር ያለመታከት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል›› በማለት ያስተላለፈው አስተሳሰብ ያስተጋባሉ፡፡

ጀላሉዲን ሩሚ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹(ሙስሊሞች) ለፈጣሪ ፍላጎት እራሳችንን ለማስገዛት ፈቃደኞች ሆነን ስንገኝ ብቻ እውነተኛ ነፃነት እንደሚገኝ፣ እራስን ለፈጣሪ ማስገዛት ማለት ከአጥፊ ፍላጎትና አምሮት፣ ከትርጉም አልባ ባዶ ስሜት፣ ከንቱ ከሆነ አስተሳሰብ፣ ከነሆለለ ሕይወት፣ ከፈተናና ከባርነት ነፃ ያወጣናል፤›› በማለት ያስገነዝበናል፡፡ 

በመሠረቱ፣ በመቻቻልና በሰላም አብሮ ለመኖር በፍቅር መኖርን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር የሚጀምረው ደግሞ ከአዕምሯችን ነው፡፡ ስለፍቅር ስንጨነቅና ስለፍቅር ተግተን ስንሠራ አፍቃሪ እንሆናለን፡፡ አፍቃሪ ስንሆን ስለራሳችንና ስለሌሎች የነበረን አመለካከት ይቀየራል፡፡ ሌሎችን ስናፈቅር ከሌሎች ፍቅርንና መፈቀርን እናገኛለን፡፡ የምንሰጠው ፍቅር ከፍ እያለ በሄደ መጠን የምንቀበለው ፍቅርም እያደገ ይሄዳል፡፡

ሌሎች ለሙስሊም ወንድሞቻቸው ሊያደርጉት የሚገባ

በሌሎች አገሮች ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በታላቋ ብሪታኒያ፣ በአውስትራሊያና በካናዳ የአገሮቹ ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች የእንኳን ደህና ደረሳችሁ መልዕክት ከማስተላለፋቸውም በላይ በቤተ መንግሥቶቻቸው በመጋበዝ የሰላምና የመተሳሰብ ወር ሆኖ እንዲያልፍ መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ለሰላም፣ ለመቻቻልና ለፍቅር አጥብቀው የሚሠሩ አብያተ ክርስቲያናትም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ከማስተላለፋቸውም በተጨማሪ የማታ ግብዣ በማዘጋጀት የወንድማማችነት ስሜታቸውን ይገልጣሉ፡፡  ግለሰብ የክርስትናና የሌሎች እምነት ተከታዮችም እንደዚሁ፡፡

የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖቶች ተከታዮች የአንድ አገር ሕዝቦች ናቸውና ከመሬቷ የበቀለውን ይመገባሉ፡፡ ለልብስ የሚሆነውንም በሥራቸው ለውጠው ይለብሳሉ፡፡ በአገራቸው ተወልዶ ያደገውንና ለመብል የታዘዘውን እንስሳ የፈጣሪን ስም አንስተው በማረድ ይመገባሉ፡፡ አንድ አየር ይተነፍሳሉ፡፡ አንድ ብርሃን ይጋራሉ፡፡ በአንድ ምድር ቤታቸውን ሠርተው ይኖራሉ፡፡ በአንድ መንግሥት ይተዳደራሉ፡፡ ባህላቸው፣ ቋንቋቸው ቢለያይ እንኳን በኢትዮጵያዊነታቸው አንድ ናቸው፡፡ ይህንን ሁሉ በጋራ ሲያደርጉ የሚለያዩት (እምብዛም የተለያዩ ባይሆኑም) በአንድ ሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የአይሁድ እምነት የሚከተለውንም ሆነ የበሃኡላህን፣ ካለም የዞሮአስተሩን፣ የታኦውን፣ የሂዱስታኑን የሚመለከት ነው፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም ሙስሊም ሃይማኖትን እንደዘር፣ እንደቀለም፣ እንደጎሳ ወዘተ የተለያየ ያደረገው ራሱ ፈጣሪ ስለሆነ ሌሎች የፈለጉትን እንዳይከተሉ ሊከለክላቸው እንደማይገባ በተለያዩ አንቀጾች አዟል፡፡ ስለዚህም አንድ ሙስሊም፣ ሰዎች የተለያየ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የተለያየ አመለካከት እንዳላቸውና በያዙት ሃይማኖትና የመቀጠሉ ጉዳይ የራሳቸው ምርጫ መሆኑን፣ የሚጸድቀውንና የማይጸድቀውን የሚለየው ራሱ ፈጣሪ እንደሆነ ግልጽ በቁርአን አስፍሯል፡፡

መሠረታዊ ሐቁ ይህ ከሆነ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችም ሙስሊም ወንድማቸው ነውና በሰላም በመጾም ፈጣሪውን ማወደስና ማክበር ይችል ዘንድ በልዩ ልዩ መንገዶች መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሃይማኖታቸው ለሰው ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባ ጥሩ ነገር ሁሉ የማድረግ ሃይማኖታዊ ግዴታ አለባቸውና፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የረመዳን ወር ማስታወስ ያለባቸው ሌላው ዋነኛው  ቁም ነገር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብና ክልል ኩሩ የመሆናቸውን ያህል ከሌሎች አገሮች በሚነሳ ማዕበል የማይናጡ ጠንካራ ሕዝቦች መሆናቸውን ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል የእምነት ልዩነት ቢኖርም ሰብአዊ ፍጡር መሆናቸውን፣ ተመሳሳይ ባህል፣ ተመሳሳይ ታሪክ፣ ተመሳሳይ ልምድና ተመሳሳይ ሥነ አእምሮ የሚጋሩ መሆናቸውም የበለጠ ቢያዳብር እንጂ አያቀጭጭም፡፡ 

በመሠረቱ በአገራችን ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ክፍሎች የሚኖሩት አብረው ነው፡፡ በአንድ ግቢ ብቻ ሳይሆን በአንድ ቤት ውስጥ ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች አብረው የመኖራቸው ጉዳይ እንግዳ አይደለም፡፡ በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ መስክ አንዱ የሌላው ጓደኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ አንዱ ሌላውን ከእምነቱ ተከታይ የበለጠ ያምነዋል፡፡ ያከብረዋል፡፡ ይህ ጾታን፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብን፣ ዘርንና ክልልን የሚለይ አይደለም፡፡ ሐዘን ወይም ደስታ ቢኖር ሙስሊሙ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ የሐዘን ተካፋይ ወይም የደስታ ተካፋይ ቢሆን፤ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ጎን መስጊድ ቢሠራ፤ የአንዱን ጸሎት ሌላው ቢያዳምጥ የሚሰማው የከፋ ስሜት የለም፡፡ ከሚያለያዩት ነገሮች ይልቅ የሚያገናኙት ነገሮች እንደሚበዙ ስለሚገነዘብም ተቻችሎ ይኖራል፡፡ ስለዚህም፣ ‹‹ኢትዮጵያ፣ ሕዝቦቿ በሰላም፣ በመከባበር፣ በመፋቀር፣ በመተባበር፣ የሚኖሩባት የተቀደሰች ስፍራ ናት፤» ተብሎ የሚነገርላትም ለዚህ ነው፡፡ ከሠላሳና ከአርባ ዓመታት በፊት በፖለቲካ መሪዎች አነሳሽነት አልፎ አልፎ ሁከት ሲፈጠር በቀላሉ ይቀዘቅዝና ይረሳ የነበረውም ለዚህ እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡ 

ፈትሑላህ ጉለን በጥልቅ ዕውቀታቸውና በተባ ብዕራቸው ስለረመዳን ካሉት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

በአንድ ኢፍጣር ቀን (ማታ የሚበላበት ሰዓት) ስለተደረገው ግብዣ ፈትሑላህ ጉለን ሲገልጡ «የደራስያንና የጋዜጠኞች ፋውዴሽን በኮንራድ ሆቴል እራት ግብዣ ሥነ ሥርዓት፣ የተለያዩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች ተከታዮች ተገናኝተው ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ፣ የቱርክ አይሁዶች መሪ (ራባይ)፣ የአሜሪካ ፓትሪያርኬት ጳጳስ ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ተመሳሳይ ቋንቋና ቀለም›› በሚል ርእስ የተዘጋጀው ፊልምና የእውቅ ገጣሚያን ቅኔዎች ቀርበዋል፡፡ በነዚህም ፊልሞችና ግጥሞች የሰላምና የመቻቻል አስፈላጊነት ተንፀባርቀዋል፡፡ የደራስያኑና የጋዜጠኞች ፋውዴሽኑ ፕሬዚዳንት ‹‹የያንዳንዱ ሰው የጋራ አካፋይ ሰው መሆኑ በቂ ሆኖ እያለ ሰዎች ይህንን በኃይል ለመለያየት ሲደክሙ ይታያሉ›› ያሉ ሲሆን ሌላው ተጋባዥም ‹‹ለመሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት የሃይማኖትም ሆነ የአመለካከት ልዩነት ይኑራቸው አብሮ ከመኖር የተሻለ ነገር አለን?» በማለት ያቀረቡትን በጽሑፋቸው ገልጸዋል፡፡ ለፈትሑላህ ጉለን ሃይማኖት የግል ጉዳይ ሲሆን የተለያዩ እምነት ያላቸው ሰዎች አብረው ለመኖር የሚያስችሏቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ በተለያዩ ሥራዎቻቸው ይገልጻሉ፡፡ 

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም በተያዘው የረመዳን ወር ልዩ ትኩረት ቢሰጠው ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ሕዝብ ይጠቅማል፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታ ጋር ይመሳሰላል ብሎ ያሰበውን ፈትሑላህ ጉለን «የነፍሳችን ሐውልት» በሚል ካዘጋጁት መጽሐፍ ያገኘውን እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡  

«መጾም ለመክሳት ሲባል ወይም ከምግብና ከመጠጥ ራስን ለተወሰነ ጊዜ ለመከልከል ሲባል የሚደረግ በፍጹም አይደለም፡፡ በየዕለቱ የሚደረጉ ጸሎቶች ለመቀመጥና ለማጎንበስ ታስበው የተዘጋጁ የአካል ማሠልጠኛ ስፖርቶች አይደሉም፡፡ ምጽዋት መስጠት ካለው ገቢ ትንሽ ግብር መክፈል ወይም በማያውቁት አገር የሚገኙ ለማያውቋቸው ችግረኛ ሰዎች ከችግራቸው ፋታ እንዲያገኙ ሲባልና፣ ለማይታወቅ ዓላማ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሐጅ መሄድ ሲባል ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመጓዝ ያጠራቀሙትን የአገር ውስጥ ገንዘብ ወደ ውጭ ምንዛሪ ለውጦ ማጥፋት አይደለም፡፡ ወይም ወደ ሐጅ ለጸሎት የሚሄዱበትን መሠረታዊ ምክንያት አውቀው ካልሄዱ በስተቀር «ሐጅ» የሚለውን ስምና ከዚያ ጋር የሚገኘውን ዝና ለማግኘት ከመሆን አይዘልም፡፡ እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች በምሕዋራቸው ዙሪያና በተዘረጋላቸው መስመርና መንፈስ በተግባር ካልዋሉ በስተቀር ከሌላው የዕለት ተዕለት ተመሳሳይ ሥራ እንደምን ተለይተው ሊታዩ ይችላሉ? በአምልኮ ተግባር ውስጥ ቁጥርን ለማብዛት መንቀሳቀስ ከልጅነት ጨዋታ ጋር የሚመላለስ ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥያቄ ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር በከንቱ መጮህና ማንቧረቅ የድምፅ ሳጥንን ከማለማመድ/ከማሠልጠን የተለየ ሊሆን አይችልም፤» በማለት ያስረዳሉ፡፡

ረመዳን ሙባረክ – የተቀደሰና የተባረከ ረመዳን

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]ማግኘት ይቻላል፡፡  

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...