በዘለዓለም ጉተማ
በአንድ አገር በሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ውስጥ እንደ ሕግ የበላይነት ያለ ቁልፍ ጉዳይ የለም፡፡ ሕግ ህሊናን ነፃ የሚያወጣ፣ ተበዳይን ብቻ የሚክስ፣ አጥፊን የሚቀጣ፣ የሚከበርና የማይደፈር የምድራዊው ዓለም ምሰሶ ነው፡፡ ሕግን ማንም የሚጥሰው፣ ዳኞችን በገንዘብ ወይም በሥልጣን ያሻው የሚያሽከረክረው ከሆነ፣ የሕግ የበላይነትም ሆነ የዳኝነት ነፃነት ህያው ሊሆን አይችልም፡፡
በአገራችን ያለፉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት ውስጥ ሕግም ሆነ ሥልጣን ከሕዝብ የሚመነጭ ሳይሆን፣ ከራሳቸው ከአገዛዞቹ ስለሆነ ፈላጭ ቆራጮቹ አፄዎቹ ወይም የደርጉ ቁንጮ ብቻ ነበሩ፡፡ ወደኋላ ላይ ‹‹የጦጣ ፍርድ ቤቶች›› በየቦታው መኮልኮላቸው ባይቀርም፡፡ የንፁኃን ደም በግፍ ከመፈሰስ አልዳነም ነበር፡፡ ደሃውንና ጭቁኑን የማይመለከቱ በርካታ ችሎቶችም የተዛባ ውሳኔ ተምሳሌቶች ነበር፡፡
አገራችን ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመዘርጋት የሞከረችው ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ ቢሆንም፣ አሁንም በሕግ የበላይነት ረገድ ያልተሟሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በእርግጥ በሕገ መንግሥቱ የዳኝነት አካላት ተቋማዊ ነፃነት መርህ፣ ከሕግ የበላይነት በተለይም የመንግሥት ሥልጣን መከፋፈልን ከሚመለከተው መርህ (The Principle of Separation of Powers) የመነጨ ነው፡፡ ስለዚህም ነው የመንግሥት ሥልጣን በሕግ አውጪ፣ በሕግ አስፈጻሚና በሕግ ተርጓሚው አካላት የተከፋፈለ ሲሆን አንዳቸው በሌላቸው ጣልቃ ሳይገቡ ነፃ ሆነው የኃይል ሚዛን ሰላማዊ መገዳደር እንዲገነባ የሚታሰበው፡፡
በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በብዙዎቹ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ያለው እውነት ግን፣ በተለይ ሥራ አስፈጻሚው ከሕግ አውጪውም ሆነ ከተርጓሚው በላይ ድምፅ ያለው፤ ቀስ በቀስ በፖለቲካ ምህዋሩ ውስጥ የጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭነት የሚንፀባረቅበት ሁኔታ ነው፡፡ በእነዚያ ጥቂቶች ጃንጥላ የተጠለለ ደግሞ ቢያጠፋም የማይከሰስ፣ ቢከሰስም የማይረታ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ የፍርድ ቤትም ሆነ የዳኝነት ነፃነት የሚባለው ገለጻም መርህ መሆኑ ይቀርና ወሬ ሆኖት ያርፈዋል፡፡
በአገራችን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደራዊ ነፃነት መሠረቱ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 79/6 እንዲሁም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 16(2) ድንጋጌዎች የፌዴራሉ የከፍተኛ ዳኝነት አካል የሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ይህም የፌዴራሉን መንግሥት የዳኝነት አካል የሚያስተዳድርበትን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ የሚያስወስን መሆኑንና ሲፈቀድም በጀትን የሚያስተዳድር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በሁለት አቅጣጫዎች ሊታይ ይችላል፡፡
አንደኛው የፌዴራሉ መንግሥት ፍርድ ቤቶች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ሥር የሚተዳደሩ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ከመታወጁ አስቀድሞ በነበሩ የተለያዩ ሥርዓቶችም ሆነ ሕገ መንግሥት፣ ሌሎች ሕጎች የዳኝነት ነፃነት የታወጀ ቢሆንም እንኳ የዳኝነት አካሉ አስተዳደር የሚይዘው በራሱ በዳኝነት አካሉ ሳይሆን፣ እንደየወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ በአስፈጻሚው አካል ነበር፡፡
በዚህ ረገድ አሁን የዳኝነት ነፃነቱ ከበጀት ነፃነትም ሆነ ከአሠራር ተፅዕኖ አንፃር ከቀደሙት ጊዜያት እጅግ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የፍርድ ቤቶች ነፃነት በግልጽ አሠራር የተደገፈ መሆን ሌላኛው የዳኝነት ነፃነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1998 ፍርድ ቤቶች ከሕዝብ ምክር ቤቶችም ሆነ ከአስፈፃሚ አካላት በመረጃ ልውውጥ፣ በሪፖርትና ጥናታዊ ዘገባን በማቅረብና በመገምገም፣ እንዲሁም በአሠራርና በአደረጃጀት ነፃነታቸውን የሚያረጋግጥ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡
የዘርፉ ምሁራን ግን ለዳኝነት ነፃነት መረጋገጥ በሕግና በመመርያ ብቻ ድንጋጌ መውጣቱን እንደ ግብ አይቆጥሩም፡፡ ይልቁንም በቀዳሚነት የፍርድ ቤቶችም ሆነ የዳኝነት ነፃነት ከስፈጻሚው ጠንካራ ክንድና ፖለቲካዊ ጫና ነፃ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ውስጥ አንድ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛና የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይም አስተዳዳሪው አንድ ዓይነት ግዴታ ያለባቸው የአንድ ዓለም ሰዎች ናቸው በማለት ይናገራሉ፡፡
‹‹ሦስቱም የመንግሥት ክንፎች በተመሳሳይ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ማመናቸው በየትኛውም ዓለም ያለና የሚኖር ቢሆንም፣ የሚሾምና የሚሽራቸው አስፈጻሚው (የፓርቲ መሪው) ብቻ ከሆነ ሁሉም የፖለቲከኛነት ካባው ይጫናቸዋል፤›› ይላል አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት፡፡ ይህን አባባል ዕውን የሚያደርገው ብዙዎቹ የሕግ ተሿሚዎች የገዢው ፓርቲ አባላትና የአስፈጻሚው አካል የነበሩ በመሆናቸው ነው፡፡ በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የሕግ ትምህርት የሚማሩ ብዙዎቹ ምሩቃን የኢሕአዴግ ካድሬዎች፣ የወረዳና የዞን አመራር አባላት ሲሆኑ በሕግ ተመርቀው ዳኛ ቢሆኑም፣ የሚያድርባቸው ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን የሚተቹ አሉ፡፡
አንድ አስተያየት ሰጪ እንደገለጹልኝ ለምሳሌ በ2006 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ሹመት የተሰጣቸው 78 የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ውስጥ 28ቱ ሴቶች መሆናቸው መልካም ነው፡፡ ሚያዝያ 12 ቀን 2006 እና ሰኔ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በተካሄደው ሹመት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹በሕገ መንግሥት የሠለጠኑና በቂ የሆነ የሕግ ዕውቀት ያላቸው፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆኑ እንዲሁም በታታሪነታቸው፣ በፍትሐዊነታቸውና በሥነ ምግባራቸው መልካም ስም የተረፉ ናቸው ፡፡››
ኢትዮጵያውያን የሕግ ባለሙያዎች ሁሉ መነሻና መድረሻቸው የሕግ የበላይነት፣ ህሊናና የሕዝብ ጥቅም ሊሆን የግድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሕግ ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን ዳኞች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ዜጋ ለእርሱ መታመን ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ታዲያ ‹‹በሕገ መንግሥት መታመን›› ስም ለኢሕአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮት ብቻ ዘብ የሚቆሙ፣ በሌላ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተሠለፉን በጠላትነት ፈርጀው ከሕግና ከህሊና ዳኝነት ያፈነገጡ ‹‹የፖለቲካ ዳኞች›› እንዳይኖሩ ምን ይደረግ የሚሉም አጋጥመውኛል፡፡
የዳኝነት ነፃነት ሲነሳ የአስፈጻሚውና የገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ብቻ አይደለም የሚታሰበው፡፡ ይልቁንም የሌላ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ አልያም የግል ባለሀብቱ ሕገወጥ መዳፍም የዳኝነት አካሉን እንዳይደፈጥጠው ያሳስባል፡፡ ዛሬ በተለይ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ያሉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የወረዳና ዞን የፍርድ ቤት አካላት ሀብትና አኗኗር ይታወቃልን? ማለት ጠቃሚ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በዘርፉ በተካሄደ አንድ ዓውደ ጥናት ላይ የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ዋነኛ ተግዳሮት ‹‹ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው›› ሲል መንግሥት ራሱ ገልጿል፡፡ በተለይ በብዙዎቹ ዳኞችና የከሳች/ተከሳሽ ጉዳይ የሚይዙ ጠበቆች መካከል እየተፈጠረ ያለው ሕገወጥ ግንኙነት (በዘር ሐረግ፣ በትምህርትና በሥልጠና ጓደኝነት፣ በቅጥር ባልደረባነት ተመሥርቶ በገንዘብ መደራደር) በጥብቅ ዲሲፒሊንና አሠራር ካልተፈተሸ ከፍትሕ የራቀ ሕዝብና በገንዘባቸው የፈለጉትን ‹‹ፍርድ›› የሚገዙ ሕገወጦች አገሩን መሙላታቸው አይቀርም ተብሏል፡፡
በአገራችን በሕገወጥ መረጃና በተጭበረበረ ፍትሕ ደሃ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥትን ጭምር እየረቱ ያሉ ‹‹ቱባ›› ባለሀብቶችና ባለሥልጣናት አሉ፡፡ እምብዛም በማያሳምን ምክንያት ለዘመናት የኖርንበትን ይዞታ ተነጠቅን (አንዳንዱ በጉልበተኛና ባለጊዜ ቀሚን ሕዝቡም ይፈርድበታል)፣ በተፈጸመብን ግፍ አቤት ማለት አልቻልንም፣ ጠበቃ አቁመን መከራከር ተቸገርን፣ ‹‹እሱን›› እንዴት ልረታው የሚሉ ተስፋ ቆራጮች እንዳይበዙ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳይኖሩ መሥራት የወቅቱ ጥያቄ ሆኗል፡፡
መንግሥት በርካታ ዳኞችን እያሠለጠነ መሾሙ መልካም ነው፡፡ የፍርድ ቤቶች አዳዲስ የጥሪ ማዕከላት፣ በቪዲዮ ፍትሕ መስጠት መጀመርና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ የመረጃ ቅብብልም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ በፍርድ ተደራሽነት እንደተዘዋዋሪ ችሎት ባሉ አሠራሮች ለሕዝቡ ፍትሕን ማቅረብ መጎልበት ያለበት ነው፡፡
ይህ ሁሉ ግን የፍርድ ቤቶችን ዕቅድ አፈጻጸም ሊያሳድግ ይችል ወይም ጉዳዮችን በፍጥነትና በቅርበት ለማየት ፍርድ እንደሆነ እንጂ፣ ነፃና ትክክለኛ ፍትሕን ለማረጋገጥ በቂ አይደለም፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያሉ ዜጎች (ልክ እንደሠለጠነው የምዕራቡ ዓለም) ከሁሉም ሥልጣን በላይ ሕግ አለ የሚል እምነት መፈጠር አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት አለ ማለት ዜጎች ሁሉ እከሌ ከእከሌ ሳይለዩ በሕግ ፊት እኩል ናቸው ማለት ነው፡፡ አድልኦ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ተጠያቂነት በመኖሩ ሕገወጥነት ሥፍራ አይኖረውም፡፡
የመስኩ ምሁራን፣ ‹‹የዳኝነት ነፃነት መኖሩ ለሕዝብ ግልጽ ሆኖ ካልታዩ ሕዝብ በፍርድ ቤቶች ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ዳኝነት እንደሚያገኝ ያለውን አመኔታ ማጎልበት አይቻልም፤›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡ በእርግጥም እውነት ነው፡፡
በመሠረቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች የዳኝነት አካላት በራዕያቸው ያስቀመጡትን ቁልፍ ጉዳይ በጥልቀት ማጤን አለባቸው፡፡ ከተደራሽነትም ሆነ ከፍጥነት በላይ ለሕግ የበላይነትና ለዳኝነት ነፃነት የሰጡት ትኩረት አለ፡፡ ‹‹በ2015 ዓ.ም. የተሟላ የሕዝብ አመኔታ የተቸረው ፍርድ ቤት ሆና መገኘት›› የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቶች ምንም ያህል ቢያሸበርቁና በምሁራን ቢሞሉ የሚመጣ እርካታ አይደለም፡፡ በአንፃራዊነት እንኳ ሀቀኝነት፣ ሚዛናዊነት፣ ከሙስናና መድልኦ የፀዳ ፍትሕ ሰጪ የሚል ሕዝባዊ አመኔታን የማትረፉ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካ ውዝግብና በተገዳዳሪነት በዜጎች ላይ በሀቅ ላይ ሳይመሠረት የሚፈጸም ክስም ሆነ የተዛባ ፍርድ እንዳይበረክት ትኩረት መስጠት ያሻል፡፡
‹‹ፍርድ መስጠት›› ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ ዕውቀትና ዕድሜ ብቻ ሳይሆን የሞራልና የሥነ ምግባር ጠንካራ ሰብዕናን ይሻል፡፡ ወላዋይነት፣ አድርባይነትና ግላዊ ጥቅምን ማባረር ፍትሕን የሚዘነጥሉ ጎራዴዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ገንዘብና ሥልጣን ያለው ዳኞችና ፍርድ ቤቶችን እንደፈለገና እንደ ጉልቻ እንዳያሽከረክራቸው ጠንካራ ጥበቃ ያሻል የሚባለው፡፡
ዛሬ ዛሬ ፍርድ ቤቶች ሕግ ሊያዛቡ የሚችሉት በዳኞች ነፃነት ማጣት ወይም መጠምዘዝ ብቻ አይደለም፡፡ በመጭበርበርና በመሳሳትም ነው፡፡ እንደ በጋ ገበያ የደራው የሐሰት ምስክርነት፣ የተጭበረበረ ሰነድና በአንዳንድ የአስፈጻሚ አካላት (በተለይ መሬት) የሚፈጸም አሻጥርም ፍርድ ቤቶች የተዛባ ፍርድ እንዲወስኑ እያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ በሥነ ምግባር፣ በጥብቅ አሠራርም ሆነ በቴክኖሎጂ ሐሰተኛ ፍርድን መቀነስ ይገባል፡፡ ብዙ ድካምና ስኬት ባለበት አገር ውስጥ ‹‹የጦጣ ፍርድ ቤቶች›› እንዳይበዙ ትውልዳዊ አደራ አለብን፡፡
በአገራችን የዳኝነት ሥርዓትም ሆነ የፍርድ ሒደት የተጀመረው ‹‹ገዢዎች›› በመንግሥትነት ቁመና አገር (ግዛት) ማስተዳደር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ልማት ያከናውናል ከመባሉ ከሺሕ ዓመታት በፊት ፍትሕን ይላበስ አይላበስም ዳኝነት ነበር፡፡ በ‹‹በላ ልበልሃ›› እሰጥ አገባ በፍርድ ፊት ተከራክሮ መርታትም ሆነ መረታት ያለና የነበረ ነው፡፡
በተለይ በዘመነ መሳፍንትና በቀደሙት የአፄዎቹ አገዛዞች ተከናውነው እስከዛሬ ትውልድ በታሪክ ድርሳናትና በአፈ ታሪክ የሚነገሩ የፍርድ ሒደቶችን ለመረመረ ‹‹ድንቅ›› የሚባሉበት መገለጫ አላቸው፡፡ ይኼውም የችሎቱ ፍጥነትና ተደራሽነት አይደለም፡፡ ያ ቢሆንም ዜጎች ስንቅ ቋጥረው፣ ለቀናት በእግርና በጋማ ከብት ተጉዘው በገዢው ፊት ፍርድን አይጠይቁም ነበር፡፡ ዋናው መሣሪያ ግን የሕግ ትምህርት የሌላቸው፣ በልበ ብርሃንነት ህሊናና ሞራልን ከእምነትና ከፈሪኃ እግዚአብሔር ጋር አስተሳስረው በሚሰጡት ርትዕ ፍትሕ ነው፡፡ በሁለት ምስክርና አጭበርባሪነት ሊያሳስት የሞከረውን ሳይቀር አጋልጠው ፍትሕን በነፃነት የሰጡ ብዙ ተጠቃሾች አሉ፡፡
ዛሬና ትናንትን የሚያነፃፅር ምንም መሠረት ባይኖርም፣ አሁን እየተገነባ ካለው የዴሞክራሲ ሥርዓት አንፃር የፍርድ ቤቶችና የዳኞችን ነፃነትም ሆነ ገለልተኝነት፣ እንዲሁም ለሕግ የቆሙና ታማኝ መሆን ጉዳይ ሊጤንና ሊጠናከር የግድ ነው፡፡ በፍትሕ ዘርፉ በርካታ መልካም ተግባሮች እንደተሠሩ አያጠራጥርም፡፡ አሁንም ግን የሕግ የበላይነትና የዳኝነት ነፃነት ጉዳይ ወደኋላ ይቀራል፡፡
እንደማንኛውም ነገሮችን በሚዛኑ የሚለካበት ዜጋ የፍርድ ቤቶች ነፃነት ጉዳይም ቢሆን፣ ልክ እንደ ዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የሚወስደው ጊዜ አለ፡፡ ያ ጊዜና ወቅት ግን ቆመን ስለጠበቅነው አይመጣም፡፡ ‹‹ከቀስ በቀስ›› ዘልማድ በወጣ መንገድ በምሁራዊ ምክክር እያሻሻልንና እየገነባን መሄድ አለብን፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንድ ፀረ ዴሞክራሲያዊና ፊውዳላዊ አስተሳሰብ የቀረፃቸው የፍርድ ቤት ገጽታዎች ሊታዩ ይገባል፡፡
አንደኛው በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ያሉ ፍርድ ቤቶች አስፈሪና አስደንጋጭ ተደርገው የተሳሉበት አካሄድ ነው፡፡ ብዙዎቹ ዳኞችም በሥነ ምግባር አርዓያነታቸው ወይም በፍትሐዊነታቸው ከሚጠቀሱ ይልቅ ‹‹እርሱ አይምርም፣ ኃይለኛ ነው›› በሚል ሙገሳ ሲታነፁ ይታያል፡፡ በተለያዩ የችሎት መድረኮች ‹‹ችሎት ተደፈረ፣ ዘንግ ይዘሃል፣ ባርኔጣ አድርገሃል…›› እያሉ ዜጎች ‹‹ምስክርም፣ ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ መሆን አልፈልግም›› የሚል ሽሽት ውስጥ እንዲገቡ መደረግ የለበትም፡፡
የፍርድ ቤቶች ችሎትም ሆኑ የዳኝነት አካሉ መከበር፣ መወደድና መተማመኛ ነው መሆን ያለባቸው፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ የሕግ ዋስትና አለን ሲባል መነሻና መድረሻው ይኼው ነው እንጂ በአቀማመጡ፣ በመጋረጃውና የወንበሩ የገዢና የተገዢነት ካባ የለበሰ የፍርድ ቤት አደረጃጀትና አሠራር በመጠኑም ቢሆን እየተከለሰ መሄድ አለበት የሚሉ ሙያተኞች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡
ዜጎች ፍርድ ቤቶችን ከመፍራትና ከመጠራጠር (በሙስና ወይም በፖለቲካ መድልኦ ይፈርዱብኛል ብለው ከመሥጋት) እንዲወጡ ትልቁ ሥራ በሕግ የበላይነትና በዳኝነት አካሉ ነፃነት ላይ የሚሠራው ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ በዳኝነት የሚሾሙ ሰዎች በብሔር፣ በሃይማኖትና በሠለጠኑበት ዩኒቨርሲቲ ቢሰባጠሩ መልካም ነው፡፡
በመስኩ ለውይይት በር ይከፍታሉ ያልናቸው ነጥቦች በተለይ ከዳኝነትና ከፍርድ ቤቶች ነፃነት አንፃር አነሳን እንጂ ዝርዝር ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም በመጪው ጊዜ ለሕግ ያለበላይነት በዳኞች ነፃነትና ዜጎች በፍርድ ቤቶች እንዲተማመኑ ማድረግ ላይ መንግሥት፣ ራሱ ሕዝቡ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ራሳቸው የመስኩ ሙያተኞች ኃላፊነታቸውን በንቃት ሊወጡ ይገባል በማለት አሰናብታችኋለሁ፡፡