Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልእንዴት ነው ነገሩ?

እንዴት ነው ነገሩ?

ቀን:

ዘንድሮም የፓርላማው ጳጉሜን 6 የት ደረሰ?

ዛሬ እሑድ ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ላይ እንገኛለን፡፡ የዓመቱ 284ኛ ቀን፡፡ በመደበኛው አቈጣጠራችን በባሕረ ሐሳባችን ከመስከረም 1 ቀን ተነሥተን ስንቈጥር ማለት ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ግን 349ኛ ቀን ላይ እንገኛለን፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ተነሥተን ማለት ነው፡፡ የበጀት ዓመቱን ልናጠናቅቅ 16 ቀኖች ብቻ ይቀሩናል፡፡ በመደበኛው አቈጣጠር ዓመቱ ሊያበቃስ ስንት ቀን ይቀረዋል? ባሕረ ሐሳቡን የቀን መቁጠሪያውን ጠንቅቀው የሚያውቁቱ፣ በየአራት ዓመቱ ጳጉሜን 6 እንደምትሆን የሚገነዘቡቱ 83 ቀን እንደሚቀር ያውቁታል፡፡ በተንጠልጣይ፣ በጠረጴዛ ላይ እና በአጀንዳ ባዘጋጇቸው የ2007 ዓ.ም. ቀን መቁጠርያቸው ላይ በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡

አንዳንድ ተቋማት መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዘንድሮ ሠግር ዓመት (Leap year) መሆኗን ያላስተዋሉቱ ‹‹ዓመታቸው›› የሚያበቃው ከ82 ቀን በኋላ ጳጉሜን 5 ቀን ነው፡፡

እንዴት ነው ነገሩ?

የዘንድሮው 2007 ዓ.ም. ካለፉት ሦስት ዓመታት (2004፣ 2005፣ 2006) ለየት ያለ ዓመት ነው፡፡ እንዳለፉት ዓመታት ዓመቱን የሚፈጽመው በ365ኛው ቀን አይደለም፡፡ አንድ ዓመት የሚባለው መሬት ፀሓይን ዞራ የሚፈጅባት የ365 ¼ኛ ቀን በአራት ዓመት ሩቡ አንድ ሙሉ ቀን ስለሚሆን በ366ኛው ቀን ላይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ይህንን አጋጣሚ ያላስተዋሉ ጥቂት አይደሉም፡፡

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ልዩ ልዩ ተቋማት ለዓመት ጉዟቸው እንዲረዳቸው በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ (ካሌንደር) ላይ የተመሠረተ አጀንዳ፣ ተንጠልጣይና የጠረጴዛ መቁጠሪያዎች ያዘጋጃሉ፡፡ በዚሁ መሠረት አጀንዳ ካዘጋጁት መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት አውራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ግንባር ቀደሙ ነው፡፡

እጅግ በሚያምር ጥራዝ በወርቃማ ቀለም ከምቾት ጋር የተላበሰው ‹‹የኢፌዴሪ የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ፳፻፯ House of peoples’ Representatives of The FDRE 2014/15›› አጀንዳ የዘንድሮውን 2007 ዓ.ም. ማብቂያ ጳጉሜን 5 ላይ አስቀምጦታል፡፡ ጳጉሜን 6 ፈጽሞ በአጀንዳው ውስጥ የለችም፡፡ ፓርላማው ጳጉሜን 6ን የመርሳት አባዜ ያልተላቀቀው ዘንድሮ ብቻ አይደለም፡፡ ከአራት ዓመት በፊትም ባሳተመው አጀንዳ ከጳጉሜን 6 ጋር ሳይገናኝ አልፏል፡፡

እንዴት ነው ነገሩ?

ዘንድሮም ተደገመ!

የካሌንደር ቃፊር ፓርላማው የለውም እንዴ?

በ1999 ዓ.ም. ጳጉሜን 6 ቀን መንፈቀ ሌሊት ላይ ያልገባውን ሦስተኛውን ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) ‹‹በተሰጠኝ ሥልጣን መሠረት›› ገብቷል ተብሎ እንደታወጀው ሁሉ የሕግ አውጪውን ፓርላማ አጀንዳ ተከትለን በጳጉሜን 5 ሐሙስ ማግስት የሚመጣውን ዓርብ (ጳጉሜን 6 ቀንን) የ2008 ዓ.ም. መስከረም 1 ቀን ይገባል ይባልልን ይሆን?

እንደ ፓርላማው ሁሉ ዓመቱን ጳጉሜን 5 ላይ የዘጋው ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ (በአጀንዳውም በጠረጴዛ ካሌንደሩም) ሐሙስ ጳጉሜን 5 ዓመቱ አብቅቶ በማግስቱ ዓርብ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲሱ ዓመት እንደሚውል በግልጽ አስፍሯል፡፡

እንዴት ነው ነገሩ? የካሌንደር፣ የዘመን መቁጠሪያ፣ የባሕረ ሐሳብ ጉዳይ ቸል ተባለሳ?

ለነገሩ ፓርላማው ብቻ አይደለም ‹‹ሁሌም የሚተማመኑበት ባንክ›› እያለ የሚያስነግረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበታ ካሌንደሩ ጳጉሜን 6 አላመለከታትም፡፡ አላወቃትም፡፡ ዘንድሮ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጳጉሜን 6ትን የመጣል አባዜ የተፈጠረበት፤ ከአራት ዓመት በፊት ባንኩ ያሳተመው የጠረጴዛ ቀን መቁጠርያ ዓመቱን በጳጉሜን 5 ነው ያጠረው፡፡ ጎርጎርዮሳዊውን ቀመር የሚከተለው ባንኩ የአገርኛው ቀመር ቃፊር የለውም እንዴ? በንዋይ የሚተማመኑበት ባንክ ለካሌንደሩስ ምን ቅፅል ይሰጠው ይሆን?

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም በተመሳሳይ ዓመቱን ጳጉሜን 5 ላይ ከርችሞታል፡፡ ሸገር ሬዲዮም፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ፡፡

እንዴት ነው ነገሩ?

ጳጉሜን 6 የረሱ አጀንዳዎችና ካሌንደሮች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ የካሌንደር ጉዳይ በተለይ በቅርበት የሚመለከታቸው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ትምህርት ሚኒስቴርና የመሳሰሉት በየአራት ዓመቱ እየተፈጠረ ያለውን መፋለስ እንዳይደገም ጥንቃቄ የሚያደርጉት መቼ ነው?

ቱሪስቶችን የሚያስመጡት አስጎብኚዎቹ ቱር ኦፕሬተሮች ካሌንደሩን በቅጡ ካልመዘገቡት መፋለስ እንደሚመጣ ልብ ይሏል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት ጳጉሜን 6 የረሳ አንድ ቱር ኦፕሬተር የ2004 ዓ.ም. ደመራና መስቀል የሚውሉበትን መስከረም 16 እና 17፣ በጎርጎርዮሳዊው (አውሮፓ) ቀመር ‹‹ሴፕቴምበር 27 እና 28 ይከበራሉ›› ብሎ ከመግለጽ ይልቅ እንዳለፉት ሦስት ዓመታት ሴፕተምበር 26 እና 27 ብሎ ቡክ በማድረጉ ቱሪስቶቹ መስተጓጐላቸው ይነገራል፡፡

እንዴት ነው ነገሩ?

ለአገሪቱ የገጽታ ግንባታ ሁነኛ ስፍራ ያለው ቱሪዝም ከጊዜ ጋር ያለው ቁርኝነት ይበልጥ ዘልቆ የሚሰማቸው ካሌንደር ሕይወታቸው ለሆነው የባሕር ማዶ ቱሪስቶች ነው፡፡ እነርሱን በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻል ትልቅ መፋለስን ይፈጥራልና ሃይ የሚል የለም እንዴ? እንዴት ነው ነገሩ?

ከአራት ዓመት በፊት የጳጉሜን 6 ሰለባ የነበሩት ቱሪስቶች ብቻ አልነበሩም፡፡ የ2004 ዓ.ም. የሰንደቅ ዓላማ ቀን ክብረ በዓል ጭምር እንጂ፡፡

2003 ዓ.ም. ቅዳሜ ጳጉሜን 5 ያበቃል የሚለውን የፓርላማውንና የራሱን አጀንዳ በመከተል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነሐሴ 14 ቀን (ኢዜአ እንደዘገበው) በወጣው መግለጫ፣ ‹‹መስከረም 9 ቀን 2004 ዓ.ም. የሚከበረውን በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበር›› ተብሎ ዝርዝሩ መቅረቡ በዓሉ ከሰኞ ወደ ማክሰኞ ተቀየረ ወይ አስብሎ ነበር፡፡

እንደ 2003ቱ አጀንዳ ጳጉሜን 5 ቅዳሜ አብቅቶ የ2004 መስከረም 1 እሑድ ሆነ፡፡ መስከረም 2 ሰኞ ብሎ በማስላት ሁለተኛውን ሰኞ መስከረም 9 ላይ አመለከተ፡፡ ይሁን እንጂ ጉዱ የታወቀው ቆይቶ ነው፡፡ ‹‹ኧረ ጳጉሜ 6 ነች፣ መስከረም 1ም ሰኞ ነው የሚለው ተሰምቶ ማስተካከያ የተደረገው በዓሉን ከአዋጅ ውጭ ወደ ሦስተኛ ሰኞ በመውሰድ መከበሩ ነበር፡፡ ሰበብ የተደረገውም፣ ‹‹የቀኑ መተላለፍም በቂ ዝግጅት [ለ] ማድረግ›› በሚል ነበር፡፡

እንዴት ነው ነገሩ?

ጊዜን ቀመርን በአግባቡ መጠቀም መሠረታዊ ነገር መሆኑ አይሳትም፡፡ አራት ነገሮችን የያዘ አንድ ቀዋሚ ጥንታዊ አገላለጽ አለ፡፡ ንግግር ለማድረግ ሐሳብን በጽሑፍ ለማስፈር ሰዋስው (ግራመር) የቋንቋ ሥርዓት አስፈላጊ ነው፡፡ ለአምልኮትም ይሁን ለክብረ በዓል ሙዚቃ ከነሥርዓቱ ያስፈልጋል፡፡

አገር ከነጓዙ ለመምራት ሕግና ቀኖና መሠረታዊው ነገር ነው፡፡

በዓላትና የዘመን መለወጫን በፀሐይም ሆነ በጨረቃ መንገድ ለማወቅ ካለንደር መሠረታዊ ነገር ነው፡፡

ከእነዚህ አራት ምሰሶዎች በኢትዮጵያችን ክፍተት ያለው የዘመን አቈጣጠር፣ ባሕረ ሐሳብ ላይ ነው፡፡ መንጋደዱ ጳጉሜን 6ን የመርሳቱ ነገርን ለማረቅ አራተኛው ምሰሶ ላይ አገሪቱ ትኩረት የምትሰጠውስ መቼ ነው?

እንዴት ነው ነገሩ?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...