Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሣር እጥረት የሚፈተነው የወተት ምርት

በሣር እጥረት የሚፈተነው የወተት ምርት

ቀን:

‹‹ሻሎ›› የበልግ ዝናብን ተከትሎ የሚበቅል የሣር ዓይነት ነው፡፡ ሣሩ ከሌላው የሣር ዓይነት በተለየ መልኩ እርጥብ ነው፡፡ ውኃ የመያዝ አቅሙም ከሌሎቹ ይለያል፡፡ በብዛት ለከብቶች ግጦሽነት ይውላል፡፡ ሻሎን የተመገቡ ከብቶች በቀን የሚሰጡት የወተት መጠን ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ‹‹ሻሎ የበልግ ዝናብ ከጣለ በኋላ እስከ ሰኔ ይደርስልናል፡፡ ሣሩ እርጥብ ስለሆነ የከብቶቹን ወተት መጠን ይጨምራል፡፡ በዚህ ጊዜ ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለሽያጭ የምናቀርበው ወተትም ይበዛል፤›› ያሉት አቶ ዮሴፍ ተኩ በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ደገም ወረዳ ሀምቢሶ 01 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡

አቶ ዮሴፍ አምስት የሚታለቡ የሐበሻ ላሞች አሏቸው፡፡ በቀን ከ38 እስከ 40 ሊትር ወተትም ከላሞቹ ያገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት በተለመደው መጠን ወተት ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶች ይጠብቋቸዋል፡፡ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የሣር እጥረት አጋጥሟቸዋል፡፡ ከብቶቹ የሚግጡት ለምለም ሣር የለም፡፡ በዚህ ወቅት ደርሶ ለከብቶቻቸው መኖ ይሆን የነበረው ሻሎ ሣርም የበልግ ዝናብ ጊዜውን ጠብቆ ባለመጣሉ ሊበቅል አልቻለም፡፡ ለወራት ያህልም ሣር አልተገኘም፡፡ ‹‹ዘንድሮ እስከ ጥር ድረስ ሣር ነበረን፡፡ አሁን ደረቅ ወቅት ነው፡፡ ከመጋቢት እስከ ሰኔ መጀመርያ ግን ሣር አልበቀለልንም፤›› ይላሉ፡፡

በዚህም የከብቶቹ ወተት የመስጠት አቅም ቀንሷል፡፡ ይህንን ለማካካስም በርካታ መኖ ማቅረብ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ አቶ ዮሴፍ ለወራት ያህል ለከብቶቻቸው ብዙ የመኖ ዓይነቶችን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በአንዴ ጣሪያ የነካው የመኖ ዋጋ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ የመኖ ዋጋ በእጥፍና ከዚያም በላይ አሻቅቧል፡፡

‹‹በቅርቡ ያስተዋወቁን ሣር ነበር፡፡ ይህንን ሣር በኪሎ ከ35 እስከ 39 ብር እንገዛለን፡፡ በመኖ ብቻ መንቀሳቀስ ከባድ ነው፡፡ አንዲት ላም በቀን ከስድስት እስከ ሰባት ኪሎ ግራም ያስፈልጋታል፡፡ የተመጣጠነ መኖ ፋጉሎ እንዲሁ ከሦስት እስከ አምስት ኪሎ ግራም በቀን ትመገባለች፡፡ ከወተት ሽያጭ መኖ ገዝቶ የሚተርፈን ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤›› በማለት የሣር መጥፋት ያደረሰባቸውን ችግር ይናገራሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሰው ልጅ ወተትን እንደ አንድ የምግብ ዓይነት መጠቀም የጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ9000 – 7000 በኒዮሎቲክ ሪቮሉሽን ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሰዎች በእርሻ ሥራ በመሰማራት ራሳቸውን የቻሉበት ወቅት ነበር፡፡

ሁኔታው በበርካታ አካባቢዎች ላይ የተፈጠረ ሲሆን፣ በተለይም በደቡብ ምዕራብ እስያ አካባቢ ጐልቶ ታይቶ ነበር፡፡ ፍየል፣ በግና ላሞች በወቅቱ ለማዳ ከሆኑና ወተታቸው ጥቅም ላይ ከዋሉ እንስሳት ግንባር ቀደም ናቸው፡፡

ወተት ከእስያ በመቀጠልም ወደ አውሮፓ፣ እንግሊዝ፣ ስካንዲኔቪያና በሌሎች አገሮች ጥቅም ላይ እንደዋለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከያዘው ንጥረ ነገር ማለትም ካልሲየም፣ ፎስፎረስ፣ ፖታሲየም፣ ሴሌኒየምና ዚንክ አንፃርም ዛሬ በስፋት ለምግብነት እየዋለ ይገኛል፡፡

ከአንዲት ላም በቂ ወተት ለማግኘት ተመጣጣኝ መኖ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ በአገር ውስጥ ካለው የተለመደ አካሄድም ከብቶች በዋና ምግብነት የሚጠቀሙት ከግጦሽ መሬት የሚገኝ ሣርን ነው፡፡ በቂ ሣር ለማግኘትም የዝናብ መኖር ወሳኝ ነው፡፡ የዝናብ ሁኔታን ተከትሎም የወተት ምርት ከፍ ዝቅ ሲል ይስተዋላል፡፡ በአሁን ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ዝናብ ጊዜውን ጠብቆ ባለመጣሉም ለከብቶች ግጦሽ የሚሆን ሣር ማግኘት ከባድ ሆኗል፡፡ ይህም በወተት አቅርቦት ላይ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል፡፡

በመጀመሪያው የበልግ ወቅት በቂ ዝናብ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ መረጃ መሠረት፣ በበልግ ወቅት 36 ሚሊ ሜትርና 90 ሚሊ ሜትር ዝናብ ተጠብቆ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በመጋቢት ወር ላይ 80 ሚሊ ሜትር ዝናብ የተጠበቀ ቢሆንም ከ23 ሚሊ ሜትር በላይ አልተመዘገበም፡፡ እንዲሁም በግንቦት ወር 80 ሚሊ ሊትር እንደሚዘንብ ቢጠበቅም እስከ ወሩ አጋማሽ ከአሥር ሚሊ ሊትር የዘለለ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ዘጠኝ ከብቶች እንዳላቸው የሚናገሩት የደገም ወረዳ ነዋሪ አቶ መኰንን ኮርሜ ናቸው፡፡ አቶ መኰንን እንደሚሉት፣ ከዘጠኙ ከብቶች አራቱ የሚታለቡ የአሜሪካ ላሞች ናቸው፡፡ አቶ መኰንን እንደሚሉት የበልግ ዝናብ ጊዜውን ጠብቆ አልዘነበም፡፡ በአካባቢውም ለከብቶች የሚሆን ሣር ጠፍቷል፡፡ ከመኖሪያ ቤታቸው በትንሽ ርቀት ላይ የሚገኘው የግጦሽ መሬት ከዚህ ቀደም የአካባቢው ከብቶች ተሰማርተው ሲግጡት ይውሉ ነበር፡፡ ይደርቃል የሚል ሥጋት አድሮባቸውም አያውቅም፡፡ ነገር ግን ያልጠበቁት ተከስቷል፡፡ ‹‹የግጦሽ መሬቱ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየት አይችልም፡፡ በፊት የነበረው በቂ ሣር ዛሬ የለም፡፡ ከቀናት በኋላ ይደርቃል፤›› ብለዋል፡፡

በቀን እስከ 51 ሊትር ያገኙ እንደነበር የሚናገሩት አቶ መኰንን፣ በአሁኑ ወቅት በተለመደው መጠን ለማግኘት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለከብቶቹ የሚሆን መኖ በውድ ዋጋ መግዛት ከጀመሩም ውለው አድረዋል፡፡ ቀድሞ በ300 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ፋጉሎ ዛሬ 800 ብር ገብቷል፡፡ ፉሩሽካም እንዲሁ 280 ብር የነበረው 520 ከገባ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ወተት በሊትር ስድስት ብር ይሸጡ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወተት አቀነባብረው ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች መፈጠር፣ ለአካባቢው አርብቶ አደሮች መልካም አጋጣሚ ፈጥረውላቸዋል፡፡ በሊትር እስከ አሥር ብር ይገዟቸዋል፡፡ ነገር ግን ከወራት በፊት በተከሰተ የሣር እጥረት የሚያገኙት ገንዘብ ለመኖ መግዣነት ስለሚውል ከምርቱ መጠቀም አልቻሉም፡፡

የሣሩ እጥረት በመኖ ዋጋ መናርና በምርት ውስንነት ብቻ አልተገደበም፡፡ ጥቂት የማይባሉ አርብቶ አደሮች ጥራት ያለው ወተት ማቅረብ አቅቷቸዋል፡፡ በተከሰተው የሣር መጥፋት ቀድሞ ያስረክቡት ከነበረው የወተት መጠን እኩል ማግኘት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ውኃ በማቀላቀል ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህም በወተት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል ሲሆን በውስጡ የያዛቸውን ንጥረ ነገሮች ይዘትም ያሳሳል፡፡

በዝናብ እጥረት ከሚፈጠረው የወተት እጥረት ባሻገር የክርስትና እምነት ተከታዮች ጾም በሚፈታበት ጊዜም ካለው ሰፊ ፍላጐት አንፃር አቅርቦቱ ሳይመጣጠን ይቀራል፡፡ ይህ የተለመደ ቢሆንም ከመቼውም ለየት ባለ መልኩ ባለፈው የሁዳዴ ጾም እንደተፈታ የወተት ምርት እጥረት አጋጥሟል፡፡ ምንም እንኳ ካለው ሰፊ ፍላጐት አንፃር አቅርቦቱ ያልተመጣጠነ ቢሆንም የዝናብ እጥረትም ከፍተኛ ድርሻ ነበረው፡፡ ይህንንም ተከተሎ የዋጋ ጭማሪዎች ተደርገዋል፡፡

በየአካባቢው ከሚገኙ አርሶ አደሮች ምርት ሰብስበው ለገበያ ከሚያቀርቡ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኤሌምቱ ኢንተግሬትድ የወተት ኢንዱስትሪ ገበያውን ከተቀላቀለ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማቅረብ የድርጅቱ ዓላማ ነው የሚሉት የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በላቸው ሁሪሳ ናቸው፡፡

አቶ በላቸው እንደሚሉት፣ ድርጅቱ በቀን እስከ 10,000 ሊትር ወተት በማቀነባበር በከተማ ውስጥ ለሚገኙ ሱፐር ማርኬቶች፣ አነስተኛ ሱቆች፣ አከፋፋይ ነጋዴዎች፣ ሆቴሎችና ለመሳሰሉት ያሰራጫሉ፡፡ ከገበሬው በሊትር 11 ብር የሚገዙ ሲሆን፣ ተቀነባብሮ 18 ብር ይሸጡታል፡፡

‹‹የወተት አቅርቦቱን የሚፈታተን የዝናብ እጥረት ተከስቷል፡፡ በመሆኑም ምርቶቻቸውን ለድርጅቱ ለሚያስረክቡ አርብቶ አደሮች አማራጭ መኖ እያቀረብን እንገኛለን›› በማለት ለሚያቀርቡት ድርቆሽ ሣር መጠነኛ ክፍያ እንደሚያስከፍሉ ገልጸዋል፡፡

በጾም ወቅት እስከ 500 ሊትር ወተት ተረክቦ የሚቸረችረው መገናኛ አካባቢ የሚገኘው ሸዋ ሱፐር ማርኬት ነው፡፡ በሸዋ ሱፐር ማርኬት ሐርሜ፣ እቴቴ፣ ማማ እና ሾላ የተባሉ የወተት ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ ጾም በሚፈታበት ጊዜ በቀን እስከ አንድ ሺሕ ሊትር ወተት እንደሚረከቡ የሚናገሩት ማናጀሩ በገበያው የተወሰኑ የወተት ዓይነቶች እጥረት እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እስከ አንድ ሺሕ ሊትር ስናስገባ ካሉት የወተት ዓይነቶች መካከል እጅግ ተፈላጊ የሆኑትን በብዛት መውሰድ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን አናገኝም፡፡ ስለዚህም ሌሎቹን ጨምረን ለመውሰድ እንገደዳለን፤›› ብለዋል፡፡ ጾም እስኪገባ ድረስም ከፍተኛ እጥረት የነበረ ሲሆን በሊትር ሁለት ብርና ከዚያ በላይ መጨመሩን ይጠቁማሉ፡፡

የሚፈልጉትን የወተት ዓይነት አጥተው የተቸገሩ ተጠቃሚዎችም አሉ፡፡ አራስ ነች፡፡ ልጇን ከተገላገለች ሁለት ወር አልሞላትም፡፡ ልጇም ተጨማሪ ምግብ መብላት አልጀመረም፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አንድ ሕፃን ተወልዶ ስድስት ወር እስኪሆነው ከእናት ጡት ወተት በስተቀር ምንም መሰጠት የለበት ቢልም ልጇን የላም  ወተት ልታጠጣው ፍለጋ ነበር፡፡ ሆኖም ገበያ ላይ የሚገኘውን ወተት ስለማታምነውና ብዙ ጊዜም ውኃ እንደሚጨምሩበት ስለሰማች የዱቄት ወተቶችን መስጠት መርጣለች፡፡ ለራሷ በቀን ግማሽ ሊትር ተከራይታ ጀምራ ነበር፡፡ ‹‹በወር 300 ብር ከፍዬ በየቀኑ ግማሽ ሊትር ወተት ይመጣልኝ ነበር፡፡ የጀመርኩ አካባቢም ይመጣልኝ የነበረው ወተት ቃና ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ከቀናት በኋላ ተለወጠብኝ፤›› የምትለው ወጣቷ፣ ወተቱን እንዳልወደደችው በመግለጽ ለምን እንደቀየሩት ጠይቃቸው ነበር፡፡ የሰጧት ምላሽም ሣር በመጥፋቱ ከብቶቹ ከሚሰጣቸው መኖ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት በአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ከዓለም ደግሞ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ትመደባለች፡፡ ነገር ግን በአማካይ የወተት ፍጆታ በዓለም በዝቅተኛ ደረጃ ከሚመደቡት ተርታ ትሰለፋለች፡፡ በመሆኑም በዓመት አንድ ሰው 19 ሊትር በአማካይ የሚጠቀም ሲሆን አጐራባች በሆነችው በኬንያ አንድ ሰው በአማካይ 100 ሊትር ወተት ይጠጣል፡፡ ለዚህም ዋነኛው መንስኤ ከሚጠቀሱት መካከል መኖ በብዛትና በጥራት አለመገኘት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...