መምህሩ ሥነ ጥበብ አልተማረም፡፡ የተመረቀበት ትምህርት ከሥነ ጥበብ ጋር ባይያያዝም ስሙን በማንጠቅሰው ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ሥዕል እንዲያስተምር ተመደበ፡፡ ወርኃዊ ዕቅድ ሲያዘጋጅ ለሳምንታት ተማሪዎችን አግድሞሽ መስመር ማስተማር በእቅዱ ይይዛል፡፡ ‹‹አጭር አግድሞሽ መስመር ማስተማር፤ ረዥም አግድሞሽ መስመር ማስተማር፤›› ከዚህ የዘለለ ትምህርት ለመስጠት አላቀደም፡፡ በዕቅዱ ‹‹ከላይ ወደ ታች ማስመር ማስተማር›› ማለት በሚገባው ቦታ በስህተት ‹‹አግድሞሽ›› ሲል ጠቅሷል፡፡ የመምህሩን እቅድ የተመለከተው ሠዓሊ አዲስ አፈወርቅ፣ ‹‹ተማሪዎች ማወቅ ከሚገባቸው በጣም ያነሰ መረጃ የሚሰጥ ዕቅድ ነው፡፡ ድግምግሞሽ ተማሪዎችን ያሰለቻል፡፡ ዕቅዱ ስህተትም ያዘለ ነው፤›› በማለት መምህሩ የሥነ ጥበብ ዕውቀት ሳይኖረው እንዲያስተምር መመደቡን ይተቻል፡፡
ብዙ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሥዕል ወይም የሙዚቃ መምህሮች በሙያው ባይካኑም በተለይ ለመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የሚመደቡበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡ ከሌሎቹ ትምህርቶች አንፃር በቂ ትኩረት ይቸራቸዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከመምህራን ብቃት ማነስ ባሻገር የግብዓት አለመሟላትም የትምህርቶቹ ፈተና ነው፡፡ ክፍለ ጊዜዎቹ ተማሪዎች ዕውቀት የሚቀስሙበት ሳይሆን ከሌሎች ትምህርቶች ዕረፍት የሚወስዱበት እንደሆነ የሚታይበት ጊዜም አለ፡፡ እነዚህ ዘርፎች ቦታ የሚሰጣቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ አልያም ሙያተኞች ስኬት ከጨበጡ በኋላ ብቻ ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ወደ ጥበባቱ ለሚያዘነብሉ ተማሪዎች መሠረት ማስያዝ እንዲሁም ለሌሎች ታዳጊዎች ስለጥበባት ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚጀመርበት ዕድሜ ላይ ምን ያህል ይሠራል? የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡ ለትምህርቶቹ የሚሰጠው ትኩረት ማነሱ በጥቂቱም ቢሆን በሙያው በሚገፉ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የሚናገሩ አሉ፡፡ የትምህርት አሰጣጡ ለውጥ እንደሚያስፈልገውም አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡
በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ሥዕል ያስተማረው አዲስ፣ ተመሳሳይ ሐሳብ ከሰጡን አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሽናሎችን የሚቀጥሩ ትምህርት ቤቶች ጥቂት ናቸው፡፡ በሙያ ብቃት የሚቀጥሩትም ለመምህራኑና ለሙያው የተዛባ አመለካከት እንዳላቸው መታዘቡን ይናገራል፡፡ በሙዚቃና በሥዕል ክፍለ ጊዜ ‹‹ተማሪዎች እንደፈለጉ እንዲሆኑ ነፃነት ስጧቸው›› የሚል መመሪያ የሚያስተላልፉ ትምህርት ቤቶች አጋጥመውታል፡፡ የሌላ ትምህርት መምህራን ክፍለ ጊዜያቸው አጥሮ ለማስተማር ያቀዱትን ካላጠናቀቁ የሙዚቃ ወይም የሥዕል ክፍለ ጊዜ ታጥፎ ይሰጣቸዋል፡፡
ትምህርቶቹ ራሳቸውን ችለው የሚቆሙና ጠቀሜታ ያላቸው ሳይሆኑ እንደ ተቀጥላ ይወሰዳሉ፡፡ ሠዓሊ ወይም ሙዚቀኛ የመሆን ፍላጎት ያላቸውን ልጆች የሚያበረታታ ቤተሰብ ጥቂት መሆኑ ችግሩን ያጎላዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው አልፎበታል በሚባል መልኩ ችግሩ ለዓመታት ቢዘልቅም፣ ለውጡ አዝጋሚ ይመስላል፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሙዚቃና የሥዕል ትምህርት መሣሪያ ተሟልቶ፣ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓት ውጪ ተጨማሪ ትምህርት የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል፡፡ የተማሪዎች የሥዕል ዐውደ ርዕይና የሙዚቃ ዝግጅት የሚያሰናዱም አሉ፡፡ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከነጭራሹ ትምህርቶቹ አይሰጡም፡፡
ሙዚቀኛ በሱፍቃድ አብርሃም በአዲስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ሙዚቃ ያስተምራል፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ ለጥቂት ጊዜ በተለያዩ ክለቦች ፒያኖ ይጫወት ነበር፡፡ ታዳጊዎችን ወደ ማስተማር የገባው እሱ ካለፈበት የተሻለ መንገድ ለመፍጠር ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቀኛ የመሆን ፍላጎት ቢኖረውም፣ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ያገኘው ነገር የለም፡፡ አጎቱ ሙዚቀኛ ስለነበር ፒያኖ አጨዋወት ቢማርም በትምህርት ቤት ቆይታው ሙያውን የማዳበር ዕድል ቢያገኝ የተሻለ ደረጃ መድረስ ይችል እንደነበር ያምናል፡፡
እሱ እንደተማረበት ጊዜ ሁሉ አሁንም የሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ተራ መዝናኛ የሚመስላቸው እንዳሉ በሐዘኔታ ይናገራል፡፡ ይህም ታዳጊዎች ለጥበብ ያላቸውን አመለካከት እንደሚያዛባ፣ አንዳንዶች በቀላሉ ውጤት የሚገኝበት ትምህርት አድርገው እንደሚወስዱት ይገልጻል፡፡ በዚህ ረገድ ገጠመኙን አካፍሎናል፡፡ በሁሉም ትምህርቶቹ ከ100ው100 የሚያመጣ ተማሪ ነው፡፡ በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ግን ምንም ጥረት አያደርግም፡፡ በሙዚቃ ከ100/75 ይሰጠዋል፡፡ በውጤቱ ያልተደሰተው የልጁ አባት ‹‹እንዴት ለሙዚቃ 75 ይሰጠዋል፤›› ሲል እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስታውሳል፡፡
በኤስተቲክስ ዘርፍ ሙዚቃ፣ ሥዕልና ስፖርት በአንድነት ይሰጣሉ፡፡ ስፖርት እስከ 12ኛ ክፍል ሲቀጥል ሙዚቃና ሥዕል ስድስተኛ ክፍል ላይ ይቋረጣሉ፡፡ በሱፍቃድ እንደሚናገረው፣ ትምህርቶቹ እስከ መሰናዶ መሰጠት አለባቸው፡፡ ‹‹ሁሉም ተማሪ ሙዚቀኛ ወይም ሠዓሊ መሆን አይችልም፡፡ ትምህርቶቹ መሰጠታቸው ለሌሎች ትምህርቶችም አስተዋጽኦ አለው፡፡ ተማሪዎች በየትኛውም ሙያ ቢሰማሩ፣ ጥበባት የሰው ልጅን አዕምሮ የማጎልበት ሚና ስላላቸው መማር አለባቸው፤›› ይላል፡፡
ትምህርት ቤቶች ለሳይንስና ለሌሎችም ትምህርቶች መርጃ መሣሪያ ለመግዛት ወጪ እንደሚመድቡ ሁሉ ለሙዚቃና ሥዕልም መመደብ እንዳለባቸው፣ ስለ ትምህርት ጥራት ሲነገር እያንዳንዱ ትምህርት እኩል መካተት እንዳለበት ይናገራል፡፡ ከሌሎች አገሮች አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ለኪነ ጥበብ ትምህርቶች ተገቢው ቦታ አለመሰጠቱንና መማርያ መጻሕፍትም ንድፈ ሐሳብና የተግባር ሥራን ያጣመሩ አለመሆናቸውን ይተቻል፡፡
በሱፍቃድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ካሉ 18 ተማሪዎች ጋር የሙዚቃ ዝግጅት አሰናድቶ ነበር፡፡ ታዳጊዎቹ የዕድሜ እኩዮቻቸውን፣ መምህሮቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጋብዘው ነበር፡፡ በፒያኖ ሙዚቃ ካስደመጡት መካከል የስድስተኛ ክፍል ተማሪዋ ፍቅር ነገሠና የአምስተኛ ክፍል ተማሪው ልዑል ታዘበው ይገኙበታል፡፡
ሁለቱም ታዳጊዎች ለሙዚቃ ፍቅር አላቸው፡፡ ፍቅር ሙዚቀኛ መሆን ትፈልጋለች፡፡ ልዑል ደግሞ የሕክምና ባለሙያ የመሆን ምኞት አለው፡፡ ፒያኖ መጫወት ማቆምም አይፈልግም፡፡ ፍቅር ‹‹ፒያኖ መጫወት ያስደስተኛል፤›› ትላለች፡፡ ተማሪዎቹ የሙዚቃ ክፍለ ጊዜን በጉጉት ከሚጠብቁት መካከል ናቸው፡፡ ሁለቱም ከቤተሰቦቻቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ይናገራሉ፡፡ ልዑል እንደሚለው፣ በትምህርት ቤታቸው የሙዚቃ መሣሪያ ስለሚያገኝ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ለማጥናት ዕድሉን አግኝቷል፡፡ ‹‹ስጨነቅ ወይም የመረበሽ ስሜት ሲሰማኝ ሙዚቃ ዕፎይታ ይሰጠኛል፤›› የሚለው ልዑል፣ የሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ቀጣይ እንዲሆን ይመኛል፡፡
ፍቅርም የልዑልን ሐሳብ ትጋራለች፡፡ ‹‹ሙዚቃ መጫወት ለኔ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ደስታ እንድፈጥር አስችሎኛል፤›› ትላለች፡፡ ሙዚቃ በሳምንት ሁለት ክፍለ ጊዜ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ክፍላቸው እየጨመረ ሲሄድ በሳምንት አንድ ጊዜ መደረጉን በቅሬታ ትናገራለች፡፡
ሁለተኛው ዓመታዊ የሥነ ጥበብ ፌስቲቫል በቅርቡ ተካሂዷል፡፡ ‹‹ጥበብ ለሁሉም›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ፌስቲቫል ወደ 25 ከሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሥዕል መምህራን ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ አሠልጣኞቹ ሴቶች የሠዓሊያት ማኅበር አባላት ናቸው፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሠዓሊት ስናፍቅሽ ዘለቀ ሥልጠናውን ለመስጠት ያነሳሳቸውን ታስረዳለች፡፡ የማኅበሩ አባላት ስለልጅነት ተሞክሯቸው ሲወያዩ አብዛኞቹ ከመምህራቸው ድጋፍ እንዳላገኙ ይገነዘባሉ፡፡ ይህ ባለሙያዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡ ለሥነ ጥበብ ለሚሰጠው አነስተኛ ግምት አንድ ምክንያት እንደሆነ ስናፍቅሽ ትናገራለች፡፡
ሥልጠና ከሰጧቸው መምህራን መካከል አንድም ፕሮፌሽናል አለመኖሩንና ሥልጠናው አስፈላጊውን ዕውቀት ባጠቃላይ ለመስጠት ባያስችልም መሠረታዊ ነገሮችን እንዳስተማሩበት ገልጻለች፡፡ ‹‹የሥነ ጥበብ ዐውደ ርዕዮችን የመጎብኘት ልማድ አነስተኛ የሆነው እንዲሁም ሥዕል አይገባኝም የሚል ሐሳብ የሚደመጠው አንድም የሥነ ጥበብ ትምህርት በደንብ ስለማይሰጥ ነው፤›› የምትለው ሠዓሊቷ፣ ሥነ ጥበብ በሌላው ትምህርት ዘርፍ የደከሙ ተማሪዎች ምርጫ ተደርጐ እንደሚታሰብ ተናግራለች፡፡
እንደ ስናፍቅሽ፣ ጥበብ የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ፍላጎቱ ያላቸው በዘርፉ ሲቀጥሉ ሌሎች ታዳጊዎች ደግሞ ግንዛቤው ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ትምህርቱ ቀላል ተደርጎ መወሰድም የለበትም፡፡ መንግሥት ለትምህርቶቹ የሚሰጠው ትኩረትም መጠናከር አለበት፡፡
አቶ እንዳልካቸው ባጫ (ስማቸው ተቀይሯል) ወደ 35 ዓመታት በመንግሥት፣ በሕዝብና በግል ትምህርት ቤቶች አስተምረዋል፡፡ ያጠኑት ቋንቋ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ያስተማሩት ሙዚቃ ነው፡፡ በክፍለ ጊዜያቸውም የተለያዩ ዘፈኖችን ተማሪዎችን ያዘፍኑ ነበር፡፡ ስለሙዚቃ መሣሪያዎች ወይም የሙዚቃ ምት የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን ጨምሮ ሌሎችም ዘፈኖች እየዘፈኑ ይፈተናሉ፡፡ በዓመቱ አጋማሽና መጨረሻ ብዙዎቹ ከ95 እስከ 100 ይሰጣቸዋል፡፡ የሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ፈተና ሲቃረብ ማጥኛና ማረፊያም ይሆናል፡፡ ተማሪዎች ስለሙዚቃ አንዳች ትምህርት ሳይሰጣቸው ዓመታት ያልፋሉ፡፡
አቶ እንዳልካቸው ከጊዜ በኋላ ‹‹የማስተምርበት መንገድ ተለውጧል፤›› ይላሉ፡፡ የሙዚቃ መጻሕፍት ማንበብና ጥናቶች ማገላበጥ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ ተማሪዎች ስለሙዚቃ መሣሪያዎች እንዲያውቁ ማስታወሻ ያጽፏቸዋል፡፡ ስለ ሙዚቀኞች የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸው እንዲጽፉም ያደርጋሉ፡፡ አካሄዳቸው ግን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አንዳንድ ተማሪዎችና የትምህርት ቤቱ አመራሮች ‹‹ለሙዚቃ በዚህ መጠን ተማሪዎችን መጫን ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋቸዋል፡፡ የተማሪዎች ቤተሰቦችም ደስተኛ አልሆኑም፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ ዋነኛ ችግሩ ፕሮፌሽናሎች አለመቀጠራቸው ነው፡፡ የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ባለሙያ ስላልቀጠረ ራሳቸውን እያስተማሩ ዛሬም ሙዚቃ ያስተምራሉ፡፡ ‹‹ተማሪዎች ዴስክ በእንጨት እየመቱ ሪትም ማጥናት ይችላሉ፡፡ ሥዕል በእርሳስ፣ በካርቶንና በጭቃም መሥራት ይችላሉ፡፡ መምህሮቻቸው ዕውቀት ከሌላቸው ግን ይህ ሁሉ አይሆንም፤›› ይላሉ፡፡ በተጨማሪ የትምህርት ቤቶችና የቤተሰብ አመለካከት መለወጥ እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
‹‹መክሊትን ፍለጋ›› 12 ተማሪዎች የተሳተፉበት የሥዕል ዐውደ ርዕይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጋለሪ የተከፈተው ዐውደ ርዕዩ እስከ ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ይሆናል፡፡ የሙለተ ሀዩ አካዳሚና የተስፋ ለሕፃናት የተራድኦ ድርጅት ተማሪዎች ያዘጋጁት ነው፡፡ ተማሪዎቹ ከሰል፣ አፈር፣ ሸንበቆ፣ አበባ፣ እሾህ፣ መስታወት፣ ሳማ፣ ሳር፣ ቅጠልና ሌሎችም ቁሶችን ተጠቅመው ሥዕሎች አዘጋጅተዋል፡፡ ስፕሬይ፣ ከለርና ቀለም በመጠቀም በወረቀትና በካርቶን ላይ ሥዕሎች የሣሉም አሉ፡፡
ሠዓሊ ብሩክ ኃይሌና ሠዓሊ ዮሴፍ ሰቦቅሳ መምህራኑ ናቸው፡፡ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች አሰባስበው ካሠለጠኑ በኋላ ያዘጋጁት ነው፡፡ ብሩክ እንደሚለው፣ ዐውደ ርዕዩን ማዘጋጀት ከባድ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ስፖንሰር ማግኘት ፈታኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል የቤተሰቦቻቸውን ጫና ሰብሮ መውጣት ቀላል አልነበረም፡፡ ቢሆንም የዐውደ ርዕዩ መክፈቻ ቀን የተገኙት ቤተሰቦች በልጆቻቸው ሥራ መገረማቸውን ይገልጻል፡፡ ‹‹ወላጆች ልጆቻቸው ያላቸውን ተሰጥኦ እንኳን አያውቁም፤›› ይላል፡፡
ለታዳጊዎች የሥነ ጥበብ ትምህርት የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ መሆኑ በእሱና በሌሎች ሙያተኞች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይናገራል፡፡ በመሰል ሥርዓት ተምረውና ሰብረው የወጡ ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያምናል፡፡ አብዛኞቹ የተሳካላቸው ባለሙያዎች ልጆችን የማስተማር ፍላጎት አይታይባቸውም፡፡ ‹‹እኛ ካለፍንበት በተሻለ መንገድ እንዲሄዱ የበኩላችንን መወጣት አለብን፤›› ይላል፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት ትልቅ ሚና የሚጫወቱ የጥበባት ትምህርቶች በአግባቡ ቢሰጡና ታዳጊዎች ቢበረታቱ አገሪቷ ምን ያህል ሙያተኞች ባገኘች ነበር ሲል አስተያየት ይሰጣል፡፡