Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት እሑድ ከሰዓት በኋላ ከሁለት ታዳጊ ልጆቼ ጋር ሆኜ የቴሌቪዥን ‹‹የመዝናኛ ፕሮግራም›› እየተከታተልኩ ሳለሁ፣ እጅግ በጣም ከልቤ የምወደው የትዝታው ንጉሥ የመሐሙድ አህመድ ሥራዎችን የሚዘክር ዝግጅት ቀረበ፡፡ መሐሙድን ለመሰሉ ምርጥ ድምፃውያን ያለኝ ፍቅርና አክብሮት እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ለመሐሙድ ደግሞ የተለየ ትዝታ አለኝ፡፡ ተወልጄ ያደግኩት ጃንሜዳ አካባቢ ስለሆነ የዝነኛውን የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ፈርጦች ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ተፈራ ካሳ፣ ተዘራ ኃይለ ሚካኤልና ሌሎችን ጭምር በቅርበት አውቃቸው ነበር፡፡ በተለይ መድፈኛ ግቢ የሚባለው የክብር ዘበኛ ካምፕ ውስጥ በየአሥራ አምስት ቀናት ይቀርብ በነበረው የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ለምን እንደሆነ አላውቅም መሐሙድ የበለጠ ይመቸኝ ነበር፡፡ ከዚያም ከሮሃ ባንድ ጋር የተጫወታቸው ዘመን አይሽሬ ዘፈኖቹ አሁንም እንዳሸበረቁ አሉ፡፡ ሥራዎቹን የሚዘክር ፕሮግራም ሲቀርብ እንዴት አልደሰት? እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡

ደስታዬ ግን ብዙም አልቆየም፡፡ መሐሙድ ሊገዘፍበት የነበረው ዝግጅት የሌሎች መወዳደሻና መፎለያ ሆነ፡፡ መድረኩን ይመራ የነበረው ግለሰብ (ስሙን መጥራት በፍፁም አስፈላጊ ባለመሆኑና ስለማይመጥን) ስለመሐሙድ ትዝታቸውንና አድናቆታቸውን የተናገሩትን የተለያዩ ሰዎች ካስተናገደ በኋላ፣ መሐሙድን በቀጥታ ዘፈን እንዲዘፍን ጋበዘው፡፡ ይኼኔ አንጀቴ አረረ፡፡ በዕድሜም ሆነ በሕይወት ተሞክሮው የበሰለው ውድ ወንድማችን መሐሙድ ግን ቅሬታውን ገለጸ፡፡ ስለሱ ሰዎች ተናግረው እሱ የምሥጋና ንግግር ማቅረብ ሲገባው ዝፈን መባሉን በሐዘን ሲገልጽ እኔም ተናድጄ ስለነበር በሐሳቤ ደገፍኩት፡፡ እኔማ ለመሆኑ ይህንን የሚያህል የአገር አድባር የሆነ ታላቅ ድምፃዊ እንደ ጠጅ ቤት ‹አዝማሪ› ዝፈን የሚለው ፍጡር ከየት ነው የበቀለው አልኩ፡፡ በአቋራጭ የሚገኝ ሀብትና ዝና ስንቱን ከነባራዊው ዓለም ጋር እያለያየው መሆኑ ሲታሰበኝ ደግሞ አዘንኩ፡፡ ዕድሜ፣ ዕውቀት፣ ልምድና ማስተዋል የጎደሉት ሀብትና ዝና በዜሮ የተባዛ ሕይወት መሰለኝ፡፡ በዚህም ማዘን የሚገባን ሁላችንም ሳንሆን አንቀርም፡፡

የቴሌቪዥኑ ዝግጅት ቀጥሏል፡፡ ለመሐሙድ ሥራዎች መዘከር አስተዋጽኦ ያደረጉት ባለሀብት በአድራጎታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ነገር ግን እሳቸውም ቢሆኑ  አማካሪ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ካሜራ ፊት ሆነው ‹እከሌ ና፣ የት ትደበቃለህ? እከሌን አይቼው አልነበር? የታለ? ና ወደዚህ …!› በማለት ተዋናይ መሆን ሲቃጣቸው ማየት ደስ አይልም፡፡ ይኼ ወግ አጥባቂ ኅብረተሰብ ዕድሜን እንደ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ስለሚቆጥር፣ ከዚያ ጋር የሚመጣጠን ድርጊት ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ አለበለዚያ ‹እሳቸውም እንዲህ ናቸው እንዴ? በስተርጅና የምን ጎረምሳነት ነው?› እየተባሉ ይነቀፋሉ፡፡ ቴሌቪዥን ጣቢያው ግን ራሱ የቀረፀው ይሁን ወይም ተቀርፆ የተሰጠው አላውቅም አሰሱን ገሰሱን ይዞ ነበር የቀረበው፡፡ ጉዱ ይቀጥላል፡፡

እየቆየ ሲሄድ ሰውየው ‹ዘ ሞስት አክቲቭ ያንግ ሌዲ› ያሉዋትን ተዋናይ ጠርተው ለዳንስ ሲጋብዙ ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ደስ አላለኝም፡፡ ይኼኔ የዘጠኝ ዓመቱ ትንሽ ልጄ ‹‹ዋው! ለካ ኮንፎርምድ ሆኗል?›› ብሎ ወደ 12 ዓመቱ ልጄ ጥያቄ ሲሰነዝር፣ ‹‹ዓይንህን ማመን ነው እንግዲህ …›› ሲለው ጣልቃ ገባሁ፡፡ ‹‹ምንድነው የምታወሩት?›› በማለት ትልቁን ስጠይቀው፣ ‹‹ዳድ ምን መሰለህ? ትምህርት ቤት በተለይ ሴቶቹ ተማሪዎች የሁለቱን ‹ካፕሎች› ጉዳይ በስፋት ሲያወሩ ሰምተን ስለነበር ነው…›› አለኝ፡፡ ወገኖቼ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ መደንገጥ ብቻ ሳይሆን በጣምም ተናደድኩ፡፡ ‹‹እናንተ ትምህርት ነው የምትማሩት? ወይስ ወሬ ነው የምትቃርሙት?›› በማለት ሳፈጥባቸው ትንሹ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ዳድ ዶንት ቢ ሲርየስ! ጓደኞቻችን እኮ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ መዓት ጊዜ አውርተዋል …›› ሲለኝ፣ ‹‹በቃህ ዝም በል…›› ብዬ ጮህኩኝ፡፡ በሌላው የምጠላው ቤቴ ድረስ ሲመጣ አሳበደኝ፡፡

ልጆቼ በሁኔታዬ ተደናግጠው የተቀመጥኩበት ጥለውኝ ወደ ጥናት ክፍላቸው ገቡ፡፡ ቁጭ ብዬ ለበርካታ ደቂቃዎች ተከዝኩ፡፡ የመጀመርያው በማያገባን ጉዳይ ከልጆቼ ጋር ስንቀያየም፡፡ ግድየለም ሁሌም በብዙ ጉዳዮች በግልጽ ስለምንነጋገር ከንዴቴ በኋላ ይስተካከላል፡፡ ሁለተኛው የማይመለከተንን ጉዳይ ቤታችን ድረስ ባመጣብን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ብሽቀት ያዘኝ፡፡ አፌን እስኪመረኝ ድረስ ተናደድኩ፡፡ ማንም ከማንም ጋር የመጎዳኘት ወይም የመደነስ መብቱ የተከበረ ነው፡፡ ያለኔ ፍላጎት ግን ግብር የምከፍልበት ጣቢያ በልጆቼ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነገር ሲያቀርብ እበሳጫለሁ፡፡ ባለጉዳዮቹ እንደፈለጉ የመሆን መብታቸውን አከብራለሁ፡፡ የእነሱ ጉዳይ እኔንና ቤተሰቤን አይመለከትም፡፡ ነገር ግን ጥሬውንና ብስሉን መለየት ያቃተው የቴሌቪዥን ጣቢያ መረን ከተለቀቀ ተግባር መውጣት አለበት፡፡ በየቦታው የሚፈተፈተውን ሐሜት በአደባባይ ዘርግፎ እኔንና ልጆቼን ማጣላት የለበትም፡፡

ላባችንን ጠብ አድርገን ወገብ በሚሰብር ክፍያ ልጆቻችንን ያስተምራሉ የተባሉ ትምህርት ቤቶቻችንን ተማሪዎቻቸውን መቆጣጠር እንዳቃታቸው አንዱ ይኼ ማሳያ ነው፡፡ ተማሪዎች የሚጠቅማቸውንና የማይጠቅማቸውን ለይተው እንዲያውቁ መርዳት ሲገባቸው፣ በልጅነታቸው የእከሌንና የእከሊትን ጉዳይ አጀንዳ ሲያደርጉ የት ናቸው? የእያንዳንዱን ተማሪ ውሎ በሚገባ እየተከታተሉ ማረቅ ሲገባቸው፣ ልጆቹ ሐሜት ሲሰልቁ ዝም ካሉ አገሪቱ ውስጥ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ እኔ ልጆቼን ትምህርት ቤት የምልከው በዕውቀትና በሥነ ምግባር እንዲኮተኮቱ ነው፡፡ የበኩሌንም ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የሚያስገድዳቸው ችግር እንዳይፈጠርም እሟሟታለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ካላገዘኝ ግን ምን ዋጋ አለው? እቤቴ የሚደርሰው ቴሌቪዥን ካልደገፈኝ ምን ይረባኛል? የእሑድ ዕለት ብሶቴ ነው ይህንን ሁሉ እንድዘከዝክ ያደረገኝ፡፡ እግጅ በጣም የምወደው መሐሙድ አህመድ ሥራዎቹ ሲዘከሩ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ባይፈጠር ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ያለፈው አልፏል፡፡ ወደፊት ግን እንዲህ ዓይነቱ ተግባር እንዳይከሰት ይታሰብበት፡፡ ቴሌቪዥን ጣቢያውም ኃላፊነት ይሰማው፡፡ ኃላፊነት በጎደለን መጠን በሕዝብና በአገር ላይ ጉዳት እናደርሳለን፡፡

(ክብሩ ገብረ ጊዮርጊስ፣ ከጎተራ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...