Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርባቡሩንና ከተማችንን ከቆሻሻ እንታደጋቸው!

ባቡሩንና ከተማችንን ከቆሻሻ እንታደጋቸው!

ቀን:

በአዲስ አበባችን የውስጥ ለውስጥና አዲስ አበባን ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚያገናኙ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ከተሞችን እርስ በርስ የሚያገናኙ የባቡር መስመሮች መዘርጋት መጀመራቸውና በተለይም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡ ይህ በአዲስ አባባችን እንደ ጠዋት ፀሐይ ጨረሩ ፈንጠቅጠቅ ብሎ እያንፀባረቀ የሚታየው መስመር እንኳን ነዋሪዎችን የሌሎች አጐራባች አገሮችንም ምራቅ ያስዋጠ መሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያስማማል፡፡ ታዲያ ይህ ነፀብራቅ እየደመቀ እንዲሄድ ጐን ለጐን መሠራት ያለባቸው ቁልፍ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን ነው፡፡ በከተማችን የደረቅም ሆነ የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ወጥነት ባለው ሁኔታ አልተመቻቸም፡፡ በመሆኑም የባቡሩ ሐዲድ በተዘረጋባቸው መስመሮች ውስጥ በርካታ ደረቅ ቆሻሻዎች ተጠራቅመው ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ባቡሩ ሥራ በጀመረ ጊዜም መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ከቀጠለ ደግሞ ሐዲዱ በደረቅ ቆሻሻ መበከል ከፍተኛ አደጋ እንደሚሆን ለመገመት የዘርፉ ባለሙያ ወይም አዋቂ መሆን አይጠበቅም፡፡

በሌላ በኩል ከመሬት በላይ ባቡሩ የሚጓዝባቸውን መስመሮች ተሸካሚ የሆኑ ድልድዮች በአቀማመጣቸውና በቅርፃቸው አሁን ባለበት ሁኔታም ለዓይን ማራኪ ቢሆንም ወደፊት የአገራችንን ባህል ታሪክ ብርቅዬ ቅርሶች አመላካች የሆኑ ሥዕሎችና ቅቦች ቢደረግባቸው ተጨማሪ ውበት እንደሚሆኑ የሚታመን ነው፡፡ ነገር ግን ከአሁኑ ከሥር ከቅርበት አፈርና አስፋልት እየተጋጨ በሚነሳ ፈሳሽ ቆሻሻ ቀለማቸው እየተለወጠ ይገኛል፡፡ በአካባቢው በሚፈጥሩት ጥላ ከፀሐይ እየተከለለ ሊጓዝ የሚሞክረውን እግረኛ በመጥፎ ጠረን መገፍተር ጀምረዋል፡፡

የባቡሩ መስመር ጐን ለጐን የተዘረጉ የመኪና መንገዶች ዳር ዳር አደባባዮች ለአረንጓዴ ዕፅዋት እየተመቻቹ ያሉት ቦታዎች የታሰበላቸውን ዓላማ ሲፈጽም ምን ያህል ከተማችንን ሊያስውቡና ጤናማ የአየር ፀባይ ሊፈጥሩ የሚችሉ ቦታዎች በቆሻሻ ክምር እየሞሉ ማየታችን እጅግ አሳሳቢና ወዴት እየተጓዝን ነው የሚያስብል ነው፡፡  በአንድ በኩል የዘመናዊነት መገለጫ የሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ግንባታዎችና የከተማ ፕላኖች ይራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ ሥርዓትና ባህል እየዳበረ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ እያየን ያለነው የዘመናዊነት ጮራ ነፀብራቅ እንዳይደበዝዝ ቢያንስ የሚከተሉት ጉዳዩች መከናወን አለባቸው፡፡

  1. ዋና ዋና በባቡሩ መዳረሻ ጣቢያዎች ለምሳሌ መገናኛ፣ ሳሪስ፣ መስቀል አደባባይ፣ አውቶብስ ተራ፣ ጐተራ በመሳሰሉት ቢያንስ ሁለት ቀዳዳ ያለው ከምድር ጋር የታሰረ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ/ማከማቻ ቢዘጋጅ፣ ከላይ እንደተገለጸው ባቡሩ የሚሄድባቸው መነሻና መድረሻ መሀል ሰፊ የሚባል ርቀት ስላለ በዚህ መስመር ተጓዡ  በዓይነትም በብዛትም ከፍተኛ የሆነ ደረቅ ቆሻሻ ሊጥል ይችላል፡፡ ስለዚህ ጠርሙስና ፕላስቲክ የሆኑ በአንድ ኮንቴነር፣ ወረቀትና በቀላሉ መወገድ የሚችሉ የምግብ ትርፍራፊም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንድ ኮንቴነር እንዲከተት                                          አመላካች ቅርጽ ያለው ለዓይን ማራኪ የሆነና የመንገዶችንም ገጽታ የማያበላሽ እንዲሁም በቀላሉ በሰዎች ወይም በእንስሳ የማይጐዳ ሆኖ መሠራት ይችላል፡፡

 

  1. ደረጃቸውን የጠበቁ ውበት ያላቸው በአንድ ጊዜ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ሊያስተናግዱ የሚችሉ በውኃ የሚታገዙ መፀዳጃ ቤቶች መገንባት አለባቸው፡፡ ባቡሩ ረጅም ርቀትና በአንድ ጊዜ የሚያጓጉዘው ሰው በርካታ ከመሆኑ አንፃር በእነዚህ ትልልቅ መዳረሻ ጣቢያዎች ይህን አገልግሎት የሚፈልግ ሰው በርካታ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ስለዚህ ይህ በአስቸኳይ በሚመለከታቸው አካላት በጣምራም ሆነ በተናጠል መከናወን የሚገባው  ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከሆነ የባቡር ተጓዥ እንዲሁም እግረኛ በእነዚህ ቦታዎች በአግባቡ ደረቅም ሆነ ፈሳሽ ቆሻሻን የማስወገድ የውዴታ ግዴታ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ አደባባይና ደሴቶችም የዓይን ማረፊያ ከተማችንም ፅዱ ነዋሪዎች ጤነኞች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
  2. Anchorበርካታ ሕንፃዎች በተገነቡባቸው ዋና ዋና የአዲስ አበባ ወረዳና ቀበሌዎች የመኪና ማቆሚያዎችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ሥራው አረንጓዴ መናፈሻን ጨምሮ ወይም ለመኪና ማቆሚያ ብቻ ሊደረግ ይችላል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት ትልልቅ ማማ/ቁመት ያላቸው በርካታ ሕንፃዎች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ሕንፃዎች የሚገኙ ለቢሮ፣ ለንግድ ማዕከላት የሚውሉ ክፍሎች የሚያስተናገዱት ሠራተኞችና ደንበኞች መጠቀሚያ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች፣ በቂ  ማቆሚያ ቦታዎች ከሌላቸው የመኪና መንገዶችን፣ የእግረኛ መሄጃ መንገዶችን በማጥበብ የትራፊክ ፍሰትን በማስተጓጐል፣ እግረኛን ለአደጋ ሊያጋልጥ በሚችልበት ሁኔታ ማለትም ተሽከርካሪ በፍጥነት የሚሄድባቸው መንገዶች ላይ እየተጓዙ ለአደጋ እየተጋለጡ ያሉበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡  ስለዚህ ቢያንስ በተወሰኑ ርቀቶች ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎችን ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡  ዛሬ አገራችን ይልቁንም ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ የሆነች ከታዋቂ አየር መንገዷ የተነሳ አጐራባች አገሮች ተደራሽ የሆኑ መንገደኞች እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሙባት ከመሆኗ የተነሳ ደረጃውን የጠበቀ የቆሻሻ አወጋገድና ጤናማ የሆነ የትራፊክ ፍሰት ሊኖራት ይገባል፡፡

ይህ ሥራ በምን በጀት በማን ይከናወን ለሚለው ባለድርሻ አካላት ዋና ዋና የሚባሉትን በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፡

  • የመንገዶች ባለሥልጣን (ፌደራል አዲስ አበባ)
  • የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን
  • የአዲስ አበባ አስተዳድር (አዲስ አበባ ፅዳትና ውበት)
  • የትምህርት ሚኒስቴር (በትምህርት ግንዛቤ መፍጠር)
  • የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር (ለጤና አጠባበቅና የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር)
  • የፖሊስና ትራፊክ ደኅንነት /የትራፊክና የመንገድ ደኅንነት ከመጠበቅ አንፃር/

በጣምራ ወይም እንደ ቡድን ሥራ ተከፋፍለው መንቀሳቀስ የሚችሉ ይሆናል፡፡ በጀትን በተመለከተ እንደ ዜጋ ወይም እንደ ተቋም ከሚከፈለው ግብር የሚመደብ በጀት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ከልማት ድርጅቶች (ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ባንኮች፣ ከማኅበራት)፣ ከተሽከርካሪ ማኅበራት (የታክሲ፣ የመለስተኛ አውቶብሶች፣ ከፍተኛ አገር አቋራጭ የሕዝብ የጭነት ተሽከርካሪ ማኅበራት) ሌሎችም የትራፊክ መንገዶች ዋና ዋና ተጠቃሚ እስከሆኑ ድረስ በዓመት የተወሰነ መጠነኛ በጀት ቢመደብ በቀላሉ ይህን ማስኬድ ይቻላል፡፡ እንደ መጀመሪያ እንቅስቃሴ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የግል ተቋማትን በማሳተፍ የመጀመሪያውን ግንባታ ማከናወን ይቻላል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ማንም የአገሩ ገጽታ እንዳይበላሽ የሚፈልግ ሁሉ በፈቃደኝነት ተሳታፊ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡

ሌላው በጣም አሳዛኝና ምናልባትም አስጊ የሚሆነው ጉዳይ በከተማዋ ፅዳት ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ጠዋት ጠዋት የከተማችንን መንገዶች ሲያፀዱ የተመለከተ አሽከርካሪ ለበርካታ ጊዜያት እነዚህ ሰዎች ላይ አደጋ እንዳይደርስ ያልተጨነቀ ያልደነገጠ አሽከርካሪ ይኖራል ማለት አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፅዳቱን የሚያከናውኑት ሠራተኞች ወጥነትና ተመሳሳይነት ያለው አለባበስና መጫሚያ ስለማይጠቀሙ በቀላሉ በፅዳት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች መሆናቸው የሚለይበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህም ባለመሆኑ ተለይተው ሊታወቁ የሚችሉባቸው የቦታ መከለያ ካለመኖሩም በላይ ተሽከርካሪ በፍጥነት የሚጓዝበት መንገድ ውስጥ ገብተው ስለሚያፀዱ  ለአደጋ በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው፡፡

በተጨማሪም አልፎ አልፎም ቢሆን ትራንስፖርት እየጠበቀ ከሚቆመው እግረኛ ጋር መጋጨታቸውም እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ አብዛኛው ትራንስፖርት ጥበቃ በየመጠበቂያው የሚቆመው እግረኛ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች የሚሠራ በመሆኑ አለባበሱን አስተካክሎ አስፈላጊውን የሰውነት ፅዳት         አከናውኖ የሚወጣ ስለሆነ መንገዶች ሲጠረጉ በሚነሳው አቧራ ወይም ሌላ ቆሻሻ ልብሱ እየተበላሸ የሰውነቱም ፅዳት እንደነበር ስለማይመስለው ወደ መደበኛ ሥራው ሲደርስ በጥሩ ስሜት ውስጥ ላናገኘው እንችላለን፡፡

ስለዚህ የፅዳት አገልግሎት ሠራተኞች ቢቻል ወጥነት ባለው መልኩ (ዩኒፎርም) መገልገያ ቁሳቁስ እንደ ቱታ፣ ባርኔጣ፣ መጫሚያ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደማንኛውም የፋብሪካ ሠራተኛ እንደሚደረግለት የሥራ መሥሪያ ቁሳቁስ ማሟላትና የአደጋ መከላከያም እንዲሁ ለእነዚህ የፅዳት ሠራተኞች ማሟላት ግድ ይላል፡፡ ለሥራ የሚሰማሩበት የመንገድ ክፍልም በመስመር ቢለይ፣ ለፅዳት የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶችም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ቢደረግ፡፡

(ውቢት ኢትዮጵያ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...