Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ትልቁ ፈተና በኦዲት ግኝት ላይ ዕርምጃ አለመውሰድ ነው›› አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ዋና ኦዲተር

ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከስኮትላንድ ግላስኮ ካልዶኒያን ዩኒቨርሲቲ በፋይናንስ ማኔጅመንት አግኝተዋል፡፡ አቶ ገመቹ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ሆነው ተሹመዋል፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት በመከታተልና በመመርመር ረገድ እየተወጣ ስላለው ኃላፊነትና በችግሮቹ ዙሪያ ዮሐንስ አንበርብርና ዮናስ ዓብይ አነጋግረዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በ2006 በጀት ዓመት የኦዲት አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ ሲያቀርቡ፣ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር ሠራተኞች ተገቢ የደመወዝ ማስተካከያ ማድረግ ባለመቻሉ የተቋሙ ሠራተኞች እየለቀቁና አዲስ ሠራተኞችንም ማቆየት እንዳልተቻለ ገልጸው ነበር፡፡ ይህም የተቋሙን የኦዲት ሥራ ጥልቀትና ጥራት ሊጐዳው እንደሚችል አስታውቀው ነበር፡፡ ይህንን የገለጹትን ችግርና አጠቃላይ ኃላፊነታችሁን መወጣት የሚያስችላችሁ አቅምና አደረጃጀታችሁን እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ገመቹ፡- የተሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልግ የሰው ኃይልን በተመለከተ በመዋቅር ደረጃ ምንም ችግር የለም፡፡ በማቋቋሚያ አዋጃችን ላይ እንደተጠቀሰው ዋና ኦዲተሩ መሥሪያ ቤቱን እንደሚያደራጅና መዋቅር አዘጋጅቶ ለፓርላማ እንደሚያቀርብ ይደነግጋል፡፡ የደመወዝ ስኬል አዘጋጅቶ ለፓርላማው እንደሚያቀርብ፣ ለሥራው የሚያስፈልገውን አጠቃላይ በጀት አዘጋጅቶ ለምክር ቤት በቀጥታ እንደሚያቀርብ፣ ሲፈቀድለትም የተሰጠውን ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት ኦዲት የማድረግ ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት በአዋጁ ላይ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም በመዋቅር ረገድ ምንም ችግር የለብንም፡፡ መዋቅራችንን አዘጋጅተን ለምክር ቤት አቅርበናል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ መዋቅር የሚያጠናለት ባለሙያ ወይም አደረጃጀት ከሌለው ብዙ ጊዜ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ምክር ይጠይቃል፡፡ በዚያው መሠረት መዋቅሩ ተፈቅዶልናል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ይህንን መዋቅር ብቃት ባለው የሰው ኃይል የመሙላት ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ሁለት ጉዳዮች ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ አንደኛው የሚፈለገው የባለሙያ ዓይነት በብዛት በገበያ ውስጥ የመገኘቱ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለሰው ኃይል የሚከፈለው ክፍያና የጥቅማ ጥቅም ፓኬጅ ባለሙያውን ከገበያ ለመሳብ የሚያስችል ነው ወይ የሚሉት ናቸው፡፡ ምቹ የሥራ አካባቢ የሚለው ደግሞ ተጨማሪ ምክንያት ነው፡፡ ሁለቱ ተፅዕኖዎች ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ ምቹ የሥራ አካባቢን በተመለከተ መንግሥት የራሳችን የሆነ ሕንፃ እንዲኖረን በግንባታ ላይ ነው፡፡ ወደዚህ ሕንፃ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ እንዘዋወራለን፡፡ ግን አሁንም ችግር ሆኖ እየቀጠለ ያለው ቀደም ሲል የገለጽኳቸው ናቸው፡፡ እዚህ መሥሪያ ቤት የምናመጣቸው ባለሙያዎች በአብዛኛው ከሒሳብ ሥራ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሙያዎች የሠለጠኑትን ነው፡፡ በተለይ አካውንቲንግና ኦዲቲንግ የመሳሰሉትን ማለት ነው፡፡

እነዚህ ባለሙያዎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ በገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ናቸው፡፡ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ደግሞ እነዚህን በጣም በከፍተኛ ደመወዝ  እየቀጠራቸው ነው ያለው፡፡ በሌላ በኩል የእነዚህ ባለሙያዎች አቅርቦት የተመጣጠነ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህም ተፅዕኖ አለው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን እኛ አሁን እየከፈልን ያለነው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እነዚህን ባለሙያዎች ከገበያ ለመሳብ የሚያስችል አይደለም፡፡ መሠረታዊ ችግሩ ይኼ ነው፡፡ መሳብ ብቻ ሳይሆን ውስጥ ያሉትንም ማቆየት አያስችልም፡፡ ይህንን ማሟላት ካልተቻለ የተሰጠንን ከፍተኛ ኃላፊነት በአግባቡ በጥራት ለመሥራት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥቱም ሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ የራሳችሁን መዋቅርና በጀት በመሥራት ለፓርላማ እንድታፀድቁ ነው የሚፈቀደው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ የእናንተን የደመወዝ ጉዳይ ፓርላማው በቀጥታ ከማፅደቅ እናንተ ወደ ምትቆጣጠሩት የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ለምክር ጥየቃ መሄድ አግባብ ነው ወይ? ለምንድነው ፓርላማው ራሱ ማፅደቅ የማይችለው?

አቶ ገመቹ፡- አሁን በቀጥታ የእኛን የደመወዝ ጥያቄ የሚወስነው ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ፓርላማውም የእኛን የደመወዝ ጥያቄ ተቀብሎ እያፀደቀ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል አሁን ባለው ሁኔታ፡፡ ምክንያቱም እኛ መዋቅር ሠርተን፣ የደመወዝ ስኬል አጥንተን ቀጥታ የምናቀርበው ለፓርላማ ነው፡፡ ቀደመ ሲል እንዳልኩት ፓርላማው የራሱ የሆነ ባለሙያ የለውም፡፡ እንግዲህ ስለመዋቅርና ስለደመወዝ ስኬል ስናስብ ባለሙያ ሊሠራው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አደረጃጀት ወይም አጥኚ ባለሙያ ፓርላማው የለውም፡፡ በመሆኑም ፓርላማው ይህንን የሙያ አገልግሎት ወይም ምክር የሚሰጠውን አካል ያማክራል፡፡ በዚሁ መሠረት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርን እያማከረ ነው፡፡ በዚህ ላይ ችግር የለብንም፡፡

ነገር ግን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርን አማክሮ የእኛን ችግር ተረድቶ መወሰን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥያቄያችንን አቅርበን በፓርላማውና በሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር መካከል የሚደረግ ምልልስ አለ፡፡ ይህ አሠራር መለወጥ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፓርላማው የራሱ ባለሙያ ከሌለው መሆን ያለበት ከሌሎች አገሮች አሠራር ልምድ ወስደን የእኛን አዋጅ ማሻሻል እንዳለብን እናስባለን፡፡ በሌሎች አገሮች ኮሚሽን የሚባል አወቃቀር አለ፡፡ በኮሚሽኑ የሚወከሉት ጡረታ ከወጡ በመስኩ ልምድ ካላቸው ሰዎች የተሰባሰቡ ባለሙያዎች ይህንን መዋቅርና የደመወዝ ስኬል እንዲሠሩ ነው፡፡ ፓርላማው ይህንን የደመወዝ ስኬልና መዋቅር እንዲያፀድቅ በሕግ የተወሰነበት ዋና ዓላማ የኦዲተር ጄኔራል መሥሪያ ቤት ነፃ ሆኖ ሥራውን አቅዶ እንዲሠራ ነው፡፡ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ነገሮች ሊኖሩ አይገባም፡፡

ከዚህ አንፃር ፓርላማው ይህንን ማድረግ አለበት፡፡ የሚያማክረው አካልም ሊኖር ይገባል፡፡ እስካሁን ይህ የለም፣ በአዋጃችንም አልተገለጸም፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የሚደረጉ ምልልሶች አሉ፡፡ በመሆኑም ችግራችን እንዳይፈታ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ፓርላማው መወሰን አለበት የሚል ፅኑ አቋም አለን፡፡ አዋጁም የሚለው ይህንን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር ከተቋቋመ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ እስኪ ይህ ተቋም በተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ሥርዓት ውስጥ የነበረውን ተቋማዊ ጥንካሬና የሕግ ድጋፍ እንዴት ያነፃፅሩታል?

አቶ ገመቹ፡- ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የተቋቋመው በ1937 ዓ.ም. ነው፡፡ ኦዲት ኮሚሲዮን የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡ ተጠሪነቱም ለገንዘብ ሚኒስቴር ነበር፡፡ ኃላፊነቱም የገንዘብ ሚኒስቴርን ሒሳብ ኦዲት ማድረግ ነበር፡፡ የሌሎች የመንግሥት ተቋማትን ሒሳብ አያደርግም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አዋጁ ተሻሽሎ ለጠቅላይ ማኒስትሩ ተጠሪ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በደርግ ጊዜ ደግሞ ለፕሬዚዳንቱ ተጠሪ እንዲሆን ተደረገ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለከፍተኛ የአገሪቱ የሥልጣን አካል ተጠሪ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛው የመንግሥት የሥልጣን አካል ማለትም ለፓርላማው ነው ተጠሪነቱ፡፡ የሕግ ድጋፍ ደረጃን ስንመለከት አሁን ያለበት የተሟላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንደኛ ተጠሪነቱ ለፓርላማ ነው፡፡ የዋና ኦዲተሩም አሿሿም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋና ኦዲተሮች ማኅበር በሚቀበለው መሥፈርትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሠረት ነፃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ጥሩ ቁመና ላይ እንገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን መፈታት ያለበት ችግር አለ፡፡ ቀደም ሲል የገለጽኩት ነው፡፡ ከሰው ኃይልና ከበጀቱ ጋር በተያያዘ ፓርላማው በቀጥታ አስፈላጊውን መወሰን አለበት፡፡ በሕግም የተደነገገ ስለሆነ መሟላት አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ አደረጃጀቱንና ሕጋዊ መሠረቱ)ን በምናይበት ጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህንንም ለፓርላማው እያቀረብን ለአገሪቱ የተመደበው በጀት በአግባቡ ለዓላማው እየዋለ ነው ወይ የሚለውን የተመለከተ በቂ መረጃ እያገኘ ነው፡፡ እየተወያየበትም ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም የኦዲት ሪፖርታችንን አዳምጠውና ተመልክተው ለግብር ከፋዩ ሕዝብ መረጃ እያደረሱ ነው፡፡ ስለዚህ በእኔ እምነት ይህ ትልቅ እመርታ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ አሁንም መቀረፍ ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ብዙ ርቀት መጥተናል ብዬ ነው የምረዳው፡፡

ከማውቃቸው የአፍሪካ አገሮችም ሳወዳድር ጠንካራ ተቋምና ሥራ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ፓርላማውም ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ ኦዲትን የተመለከተ ቋሚ ኮሚቴ ዘግይቶ ቢያቋቁምም ጠንካራ ክትትሎችን እያካሄደ ነው ያለው፡፡ በተለይ አሁን ያለው ቋሚ ኮሚቴ ጠንካራ ክትትል እያደረገ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ 95 የሚደርሱ ይፋዊ ውይይቶችን የኦዲት ችግር ካለባቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር አድርጓል፡፡ ብዙ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው ያለው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የመንግሥት ተቋም ኃላፊዎች እንጠየቃለን ወደሚል አስተሳሰብ እንዲመጡ ግፊት አድርጓል፡፡   

ሪፖርተር፡- የዋናው ኦዲተር የሥልጣን ክልል የት ድረስ ነው?

አቶ ገመቹ፡- የመንግሥት ኦዲትን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉት አሠራሮች  ሁለት ናቸው፡፡ የ‹‹ዌስት ሚኒስትር ሲስተም›› እና የ‹‹ኮርት ሲስተም››፡፡ ‹‹የኮርት ሲስተም›› በሚባለው የኦዲት ሥርዓት ውስጥ ሁለት ክንፎች አሉ፡፡ አንደኛው የኦዲት ክንፍ ሲሆን፣ ሌላኛው የፍርድ ቤት ክንፍ ነው፡፡ የራሱ ፍርድ ቤት አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ራሱ ከሶ ራሱ ፍርድ ቤት አስቀርቦ ዕርምጃ ያስወስዳል፡፡ እኛ የምንከተለው ‹‹የዌስት ሚኒስቴር ሲስተም›› ስለሆነ ይህ ሥልጣን የለውም፡፡ በእኛ ሥርዓት በኦዲት የተገኘውን ግኝት ለፓርላማ በማቅረብ ፓርላማው ዕርምጃ እንዲወስድበት ያስደርጋል፡፡ ነገር ግን ለዋና ኦዲተሩ የተተወም ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለ፡፡ ዋና ኦዲተሩ ኦዲት አድርጐ በሚያቀርበው ሪፖርት ላይ ተቋማት መፍትሔ መስጠት አለባቸው፣ ግዴታ ነው፡፡ ተቋማት ያለ በቂ ምክንያት ዕርምጃ ካልወሰዱ በሕግ ያስጠይቃል፡፡ እስከዚህ ድረስ መጓዝ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ያለ ፓርላማው ጣልቃ ገብነት በራሳችሁ ማለት ነው?

አቶ ገመቹ፡- አዎ፡፡ የፓርላማው ጣልቃ ገብነት በዚህ ላይ የለም፡፡ ነገር ግን በቀጥታ እኛ አንከስም፡፡ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ነው፡፡ የእኛ የሕግ ክፍል ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ሆኖ እንደዚህ ያሉ ተቋማትን በሕግ መጠየቅ እንችላለን፡፡ ተጠያቂው ተቋሙ ነው፡፡ ነገር ግን በሕግ አግባብ የተቋሙ ኃላፊ የሕግ ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በተደጋጋሚ የኦዲት ግኝቶችን ማስተካከል አልቻለም ተብሎ በሕግ አግባብ ፍርድ ቤት ሊቆም ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከወሰነ እስከ አሥር ዓመት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ እርስዎ በየዓመቱ የኦዲት ሪፖርት ለፓርላማው ሲያቀርቡ በየዓመቱ ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት የሚታይባቸው የመንግሥት ተቋማት አሉ፡፡ ለአብነት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በየዓመቱ በተመሳሳይ የኦዲት ግኝት በሪፖርቱ ይጠቅሳሉ፡፡ ነገሮች አለመስተካከላቸውን እየተገነዘባችሁና በሕግ የማስጠየቅ ሥልጣን እያላችሁ ለምን ይህንን ማድረግ አልፈለጋችሁም?

አቶ ገመቹ፡- እኔ ወደዚህ ሹመት ስመጣ የመጀመርያ ሥራዬ የነበረው የኦዲት ሽፋኑን ማሳደግ ትልቅ ትኩረት የሰጠሁት ነው፡፡ ሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኦዲት ማድረግ የምንችልበት ሥርዓትን መዘርጋት ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ያተኮርኩት ግንዛቤ መፍጠርን ነበር፡፡ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት፣ ተጠሪ የሆነለት ፓርላማው፣ እንዲሁም ሚዲያውን ጨምሮ ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ነው ትኩረት አድርገን የነበረው፡፡ ምክንያቱም የኦዲት ሥራ በኢትዮጵያ ብዙም አይታወቅም፡፡ ሚዲያውም አይከታተለውም፣ ብዙም አይዘግበውም ነበር፡፡ በሁሉም ዘንድ ፓርላማውንም ጨምሮ ወደሚፈለገው የግንዛቤ ደረጃ አምጥተን በኦዲት ጉዳይ ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ፡፡ የሕዝብ ሀብትና ንብረት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውልና የታለመለትን ውጤት እንዲያመጣ፣ ሁሉም አስተዋጽኦ ሊያደርግ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ማምጣት ነበር ትኩረት የሰጠናቸው መሠረታዊ ጉዳዮች፡፡ በዚህ ምክንያት እስካሁን ወደዚያኛው ምዕራፍ አልተሻገርንም፡፡ ነገር ግን የ2004 ዓ.ም. በጀት ኦዲት ላይ ጉዳዩም አሳሳቢ ስለነበር በወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ፣ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳና የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቦርድ ኃላፊዎች ባሉበት ትልቅ ስብሰባ በዚህ ችግር ላይ አድርገን ነበር፡፡ ስብሰባውን ባደረግንበት ወቅት የ2005 ዓ.ም. ኦዲት ተጠናቆ መረጃውን እናውቀው ነበር፡፡ የተሻሻለ ነገር በዩኒቨርሲቲዎቹ አልታየምና ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚጠየቁ ግልጽ ተደርጐላቸው ነበር፡፡ የኦዲት ግኝት ይህንን ዓይነት ትኩረት ያገኘው ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ፓርላማው ለእነዚህ ተቋማት በሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ዕርምጃ መውሰድ ይጀምራል ብለን እናስባለን፡፡ እኛም ባለን የሕግ ሥልጣን ውስጥ ሆነን ከዚህ በኋላ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመሆን መሻገር እንዳለብን አቋም ወስደናል፡፡ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በአሁኑ ወቅት ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ምክንያቱም ብቻችንን ፍርድ ቤት ቆመን መክሰስ ስለማንችል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ግንዛቤ ይፈጠር የሚባለውን ደረጃ ከአሁን በኋላ ያለፉ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ማረም የሚችለው ያርማል፣ የማይችለው መጠየቅ ባለበት አግባብ መጠየቅ እንጀምራለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መንግሥትን የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በአግባቡና ተፅዕኖ መፍጠር በሚችል ደረጃ መወጣት ሲጀመር ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ደስተኛ ነው ይላሉ? ለዚህ ጥያቄ ጥቂት ማሳያዎችን ልጥቀስልዎት፡፡ በ1998 ዓ.ም. ለፓርላማው የኦዲት ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የቀድሞው ዋና ኦዲተር አቶ ለማ አርጋው የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የሰጠውን የድጐማ በጀት ክልሎቹ በአግባቡ ለታለመለት ሥራ እንዳዋሉት ለማረጋገጥ እንዳልቻሉ ሪፖርት ቢያደርጉም፣ በወቅቱ ጠቅላይ ማኒስትር ከፍተኛ ትችት ደርሶባቸው ነበር፡፡ ሪፖርቱን ባቀረቡ በወራት ውስጥም ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ በመቀጠልም የዋና ኦደተር ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲሻሻል ተደርጐ ለክልሎች የሚሰጥ ድጐማን ኦዲት የማድረግ ሥልጣኑ እንዲሸረፍ ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጹት እርስዎ ከተሾሙ በኋላ በ2004 ዓ.ም. ያቀረቡት ሪፖርት ከፍተኛ ንቅናቄ ፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህ ሪፖርት የመንግሥት የደኅንነት ተቋማት ወጪዎችን ትክክለኝነት በአንድነት ማረጋገጥ እንዳልተቻለ የሚገልጽ ነበር፡፡ የእነዚህ ተቋማት ባህርይ ከአገር ደኅንነት ጋር የተያያዙ ሚስጥሮች የሚያካትት በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በማጥናት እንዴት ኦዲት መደረግ እንደሚገባቸው እንዲያጠኑ ኃላፊነት ተሰጥቶዎት ነበር፡፡ ነገር ግን የወሰዱትን ኃላፊነት እየተወጡ ባሉበት ወቅት በ2005 ዓ.ም. የሦስት የደኅንነት ተቋማትን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ፀድቆ ዋናው ኦዲተር በቀጥታ ኦዲት እንዳያደርግ የሚገድቡ አንቀጾች ተካተዋል፡፡ እነዚህን ማሳያዎች በመውሰድ መንግሥት የዋና ኦዲተርን እንቅስቃሴ ባስፈለገው ጊዜ ያውካል ማለት አይቻልም?

አቶ ገመቹ፡- እኔ እስከማውቀው ድረስ ለክልሎች የሚደረግ የበጀት ድጐማን ኦዲት በማድረግ ረገድ የተለወጠ ነገር የለም፡፡ እኔ ወደዚህ መሥሪያ ቤት ከመምጣቴ በፊት ፓርላማ ውስጥ አንድ የተነሳ ክርክር ነበር፡፡ ልክ እኔ ወደዚህ ስመጣ አገር አቀፍ ኮሚቴ በነበረው ክርክር ላይ ተቋቁሞ ጥናት ሲያደርግ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔንም አነጋግሮኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ውጤታቸውን ለፓርላማው አቅርበዋል፡፡ በእኔ እምነት ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትም ጋ ችግር ነበረ፡፡ በመንግሥትም በኩል ችግር ነበር፡፡ ለክልሎች የሚሰጥ ድጐማን ኦዲት ማድረግ እንደሚገባ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተደነገገ ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት እስካልተለወጠ ድረስ ሌሎች ሕጐች ይህንን ሊለውጡት አይችሉም፡፡ በወቅቱ የነበረው ክርክርን በተመለከተ በዋና ኦዲተር በኩል ይቀርብ የነበረው ክልሎች ሒሳባቸውን በራሳቸው ቋንቋ ስለሚሠሩ ኦዲት ለማድረግ መቸገሩን ይገልጽ ነበር፡፡ ወደዚህ ተቋም እኔ ስመጣ ቢፒአር የተባለው ሥርዓት ይጠና ነበር፡፡ ለዚህ ጥናት የሌሎች አገሮችን ልምድ ለማየት ወደ አሜሪካ ሄጄ ነበር፡፡ የአሜሪካ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አጠቃላይ አደረጃጀቱ በአገሪቱ ያሉትን አናሳ ሕዝቦች (Minorities) ጭምር ያገናዘበ ነው፡፡ የእኛም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ስሙ እንደሚገልጸው ፌዴሬሽኑን መምሰል አለበት፡፡ ቢቻል ሁሉንም የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚችሉ ሠራተኞችና ባለሙያዎች እዚህ መኖር አለባቸው፡፡ ስለዚህ በቋንቋ ምክንያት ኦዲት ማድረግ አልቻልንም ተብሎ በዚህ ተቋም በወቅቱ ሊነሳ አይገባም ነበር፡፡     

ሪፖርተር፡- የቋንቋ ችግር የሚለው ምክንያት በይፋ አይታወቅም፡፡ ክልሎች ኦዲት አናስደርግም እንዳሉ ነው ሪፖርት የተደረገው፡፡ የቱ ነው ትክክል?

አቶ ገመቹ፡- ሁለቱም ምክንያቶች ነበሩ፡፡ በየራሳቸው ቋንቋ ክልሎቹ ስለሚሠሩ ኦዲት ማድረግ አልቻልንም ነበር አንዱ ምክንያት፡፡ በወቅቱ ከመንግሥት የተሰጠው ምላሽ ገንዘባቸውን እንደፈለጉ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ነበር፡፡ ክልሎቹ ግን መንግሥት ያለውን በመቀበል ኦዲት አናስደርግም አሉ፡፡ በእርግጥ በኋላ ላይ መንግሥት ይህንን ንግግሩን በስህተትነት ተቀብሎታል፡፡ ኦዲት ካላስደረጉ አምስት ሳንቲም ለክልሎች እንዳይተላለፍ ተባለ፡፡ ይህ የሆነው ከፓርላማው ክርክር በኋላ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔ ምክንያት ነገሮች ወደነበሩበት ተመለሱ፡፡ ስለዚህ በሕግ የተለወጠ ነገር የለም፡፡ አሁንም ሕጉ ይሠራል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ዋና ኦዲተር ለክልሎች የሚሰጥን የበጀት ድጐማ በቀጥታ ኦዲት ማድረግ ይችላል እያሉ ነው?

አቶ ገመቹ፡- አዎ ይቻላል፡፡ አሁንም እያደረግን ነው፡፡ በጀት በሚታወጅበት ጊዜ የክልሎች ድጐማ አካል የሆነ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ የተባለ በጀት አለ፡፡ ይህንን በጀት ትኩረትና ቅድሚያ ሰጥተን ኦዲት እያደረግን ነው፡፡ ምክንያቱም በየሩብ ዓመቱ ኦዲት እየተደረገ ለገንዘብና ለኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እየቀረበ በቀጣይ መለቀቅ ያለበት የዚህ በጀት ቀሪ ገንዘብ እየተለቀቀላቸው ነው፡፡ ግን በሒደት የምናስበው ከአሜሪካን ተሞክሮ የወሰድነውን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ እነሱ እንደኛ ጥቅል የድጐማ በጀት አይደለም ለክልሎቻቸው (States) የሚሰጡት፡፡ ለጤና ሚኒስቴር ወይም ለትምህርት ሚኒስቴር ይሰጡና ነው በእነሱ ሥር ወደ ስቴቶቹ የሚሄድ የነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ክልሎቹ የተለቀቀውን ገንዘብ ኦዲት ያስደርጋሉ፡፡ ሚኒስቴሮቹም የለቀቁትን ገንዘብ በራሳቸው ያስደርጋሉ፡፡ ሌላ ገንዘብ የሰጣቸውም አካል ኦዲት ያስደርጋል፡፡ በእነዚህ ተደራራቢ ኦዲቶች በመቸገራቸው ግን “Single Audit Act” ወይም አንድ የተጠቃለለ የኦዲት ሥርዓት አወጡ፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አገር አቀፍ የኦዲት ደረጃ ያወጣው በዚህ ደረጃ መሠረት ማንም ኦዲት ያድርግ ወደሚል አሠራር መጡ፡፡ ይህንን አሠራር ይዘን መጣንና በእኛም አገር አንድ የተጠቃለለ የኦዲት ሥርዓት (Single Audit Act) የሚያበጅ ሕግ አርቅቅን አሁን በሥልጣን ላይ ካለው ፓርላማ በፊት ለነበረው አቅርበናል፡፡ እኛ የኦዲት ደረጃ እናበጃለን፡፡ ከዚያ በኋላ ክልሎችም ሆኑ ማንም ኦዲት ያድርግ ውጤቱን ይዘን እኛ ለፓርላማ እናቀርባለን ብለን ነበር ያረቀቅነው፡፡ ይህ መሆኑ ዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ጊዜና ገንዘቡን ለሌላ ሥራ እንዲያውልም የሚረዳ ነው፡፡ ይህ ቢሆን ትኩረታችንን ወደ ክዋኔ ኦዲት ማድረግ እንችል ነበር፡፡ ይህ ረቂቅ ግን አልፀደቀም፡፡ በመሆኑም ክልሎችም ኦዲት ያደርጋሉ፡፡ እኛም ያንኑ ሒሳብ ኦዲት እያደረግን ነው፡፡ ይህ አዋጅ ፀድቆ ቢሆን ኖሮ የክልል ኦዲት መሥሪያ ቤቶችን አቅም ገንብተን አስተማማኝ መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ፣ የኦዲቱን ሥራ ለእነሱ መስጠት እንችል ነበር፡፡ መሆን የሚገባውም ይህ ነበር፡፡      

ሪፖርተር፡-  ስለዚህ አሁን የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጐማ ኦዲት እየተደረገ ለታለመለት ዓላማ መዋሉ እየተረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል? ክልሎቹ ራሳቸውን ኦዲት እያደረጉ እየላኩላችሁ ነው? ወይስ ዋና ኦዲተር በቀጥታ ራሱ ኦዲት እያደረገ ነው? ይህንን ማወቅ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት የፌዴራሉ መንግሥት በየዓመቱ ለክልሎች የሚደጉመው በጀት ግዙፍ በመሆኑ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ፓርላማው ከ223.3 ቢሊዮን ብር የ2008 ዓ.ም. በጀት ውስጥ 34.4 በመቶ ወይም 76.8 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለክልሎች የሚደጐም ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይህ ገንዘብ በአግባቡ መዋሉን በማረጋገጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ወሳኝ ጠቀሜታ ስላለው ነው፡፡

አቶ ገመቹ፡- ክልሎቹ ሪፖርት አያደርጉልንም፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር በመካከላችን የለም፡፡ እነሱ ኦዲት አድርገው ለየራሳቸው ክልል ምክር ቤት ያቀርባሉ፡፡ በራሳቸው መንገድ እየሄዱ ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀሱት ረቂቅ አዋጅ ፀድቆ ቢሆን ኖሮ ይህንን አሠራር መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ እኛ ውክልናውን ሰጥተን የሚያቀርቡልንን ሪፖርት መመርመር ብቻ ይሆን ነበር ሥራችን፡፡ ከአቅም አንፃር ከ700 በላይ ወረዳዎችን ማዳረስ አንችልም፡፡ በየዓመቱ 300 ወረዳዎችን በመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ እናካልላለን፡፡ ኦዲቱም በዋናነት የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓቱን በተመለከተ እንጂ ለፓርላማ እያቀረብን እንዳለው አጠቃላይ (Comprhensive) ኦዲት አይደለም፡፡ ስለዚህ ክልሎቹ ለእኛ እየላኩ አይደለም፣ እንዲልኩ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም በሕግ የታሰረ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርላማው ይህንን አዋጅ ለማፅደቅ ምንድነው ችግር የሆነበት?

አቶ ገመቹ፡- ረቂቅ አዋጁን በተሳሳተ መንገድ መረዳቱ ይመስለኛል፡፡ የተወሰኑ የፓርላማ አባላት የክልል ሥልጣን ውስጥ ጣልቃ ገባችሁ ነው የሚሉት፡፡ ረቂቅ አዋጁን ስናዘጋጅ የክልል ፕሬዘዳንቶችን ሁሉ አወያይተናል፡፡ እነሱ ተስማምተው ሂዱበት ብለውን ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንቶች ይህንን ለመፍቀድ ሥልጣን የላቸውም የሚል ክፍፍል ሁሉ ነበር፡፡ እኔ ራሴ አምስትና ስድስት ጊዜ ነው ኮሚቴውን ለማስረዳት የቀረብኩት፡፡ ነገር ግን ሳይቀበሉት መቅረት ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ወደመራላቸው የፓርላማው አጠቃላይ ጉባዔ እንኳን ሳይመልሱት ነው የሄዱት፡፡ አሁን ያለው ፓርላማ ቋሚ ኮሚቴም ለረቂቅ አዋጁ ትኩረት አልሰጠውም፡፡ በእኔ እምነት ግን ተገቢው አሠራር በረቂቅ አዋጁ የተመለከተው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እያሉኝ ያሉት ረቂቅ አዋጁን ለቋሚ ኮሚቴው የመራው ፓርላማም ጉዳዩ ተመልሶ ቀርቦለት ረቂቁ መፅደቅ የለበትም በሚል ድምፅ እንዳልሰጠበት ነው?

አቶ ገመቹ፡- በትክክል፡፡ ረቂቅ አዋጁ አልሞተምም፣ አልፀደቀምም፡፡

ሪፖርተር፡- የደኅንነት ተቋማትን ኦዲት የማድረግ ሥልጣናችሁ መሸረፉን አስመልክቶ ወዳነሳሁት ጥያቄ እንመለስ?

አቶ ገመቹ፡- ወደ ደኅንነት ተቋማት ኦዲት በምንሄድበት ጊዜ ዋና ኦዲተር እነዚህን ተቋማት ሙሉ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን ነበረው፡፡ አዋጁም ክፍት ነው፡፡ ሕጋችን የደኅንነት ተቋማትን ኦዲት አድርጉ ይለናል፡፡ እነሱ ደግሞ ካለባቸው የአገር ደኅንነት ኃላፊነት አታድርጉ ይሉናል፡፡ ምክንያቱም የሚገዙት የደኅንነት መረጃ ነው፡፡ የትም አገር የደኅንነት መረጃ በሚገዛበት ጊዜ ግልጽ አይደረግም፡፡ አሜሪካኖች በርካታ ደኅንነት ተቋማት አሏቸው፡፡ የእነሱን በጀት አፈጻጸም ማንም አያውቀውም፡፡ ሌሎችም አገሮች ያደጉት የሚባሉትን ጨምሮ ማለት ነው ሚስጥራዊ መረጃ ከአገር ደኅንነት አንፃር በአግባቡ ይጠብቃሉ፡፡ እኔም በዚህ ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ መጀመሪያ በአግባቡ በሕጉ ይህ መረጃ ግልጽ እንዳይሆን መደንገግ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ክፍት ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን የደኅንነት ተቋማቱ ማቋቋሚያ አዋጆች ላይ በተደረገው ማሻሻያ ይህንን የኦዲት ገደብ አስቀመጠ፡፡ በዚህም መሠረት የደኅንነት ተቋማቱ ኦዲት መደረግ የሚችሉትንና የማይችሉትን ለይተው ለኦዲት እንዲያቀርቡ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ብቻ ነው በወጪ ርዕስ ለይቶ እነዚህ ኦዲት መደረግ የሚችሉ ናቸው፣ እነዚህ ደግሞ ኦዲት መደረግ የማይችሉ ሚስጥራዊ መረጃዎች ናቸው ብሎ ለይቶ ያስቀመጠው፡፡ መከላከያ ሚኒስቴርና ሌላው ተቋም በዚህ ደረጃ አላቀረቡም፡፡ በዚህ መልኩ እንዲያዘጋጁ አሳስበናቸዋል፡፡ በእነዚህ ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሥራ አስፈጻሚው ማሻሻያ በማቅረብ ይህንን አሠራር መፍጠሩ፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን መብት መግፈፍ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ የተለመዱ አሠራሮች ናቸው፡፡ በሚስጥር መጠበቅ ያለበትን መረጃ፣ እንዲሁም መረጃውን ያቀረበውን አካል ወይም ሰው ግልጽ ካደረግኩኝ የመረጃው ሚስጥርነት ይቀራል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአገር ደኅንነትን ይጎዳል፡፡ መረጃውን የሚያቀብሉ ሰዎችን ሕይወትም አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ ስለዚህ አዋጁ በዚህ ደረጃ መሻሻሉ ተገቢ ነው፡፡ የተለመደ አሠራርም ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥቱም ላይ ሆነ በእናንተ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የፌዴራል መንግሥት ኤጀንሲዎች፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችንና ማናቸውንም የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ኦዲት ማድረግ እንደምትችሉ ይገልጻል፡፡ ይህንን ያብራሩልኝ የት ድረስ ነው ሥልጣናችሁ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ሲባል?

አቶ ገመቹ፡- ሁሉንም ይመለከታል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን፣ የልማት ድርጅቶችን፣ የመንግሥት ፕሮጀክቶችንም ይጨምራል፡፡ ማንኛውንም የፌዴራል መንግሥትና የሕዝብ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣን አለን፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ማለትም የሕዝብና የመንግሥት ጥቅም ተነክቷል ተብሎ ከታመነ የግል ድርጅቶችንም ይጨምራል፡፡ ገደብ የለውም፡፡ ለዚህም ነው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የተባለው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ያነሳሁበት ምክንያት ሰሞኑን ለፓርላማው የ2008 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት ያቀረቡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አንድ አወዛጋቢ ጉዳይ በማንሳታቸው ነው፡፡ ረቂቅ በጀቱን ባቀረቡበት ወቅት በዋና ኦዲተሩ ስለቀረቡ የኦዲት ችግሮች የተጠየቁት ሚኒስትሩ ያነሱት አንድ አወዛጋቢ ጉዳይ፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እንደ ማናቸውም ተቋማት የአቅም ችግር ያለበት ከመሆኑም ባሻገር አልፎ አልፎ የግንዛቤ ችግር ይታይበታል ብለዋል፡፡ ለዚህ የሰጡት ምክንያት ዋና ኦዲተር ለፓርላማ በሚያቀርበው የኦዲት ሪፖርት ውስጥ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችንና የልማት ድርጅቶች የሚተዳደሩት በተለያየ ሕግ በመሆኑ የኦዲት ሪፖርቱ ተቀላቅሎ መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡ ዋና ኦዲተር ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት ኦዲት የማድረግ ሕጋዊ ሥልጣን ካለው ሚኒስትሩ ይህንን ጥያቄያቸውን ለምን ያነሱት ይመስልዎታል? ተቀላቅሎ መቅረቡስ ምን ጉዳት ያመጣል?

አቶ ገመቹ፡- ያነሱትን ነጥብ ሰምቼዋለሁ፡፡ ከሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ ጋር እንነጋገራለን ብዬ ነው፡፡ ሚኒስትሩ የታያቸውን ችግር ባውቅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ቢሆንም ግን የእኛ አዋጅ ግልጽ ነው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስንል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን ነው፡፡ የልማት ድርጅቶችንም ኦዲት የማድረግ ሥልጣን እንዳለን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ምናልባት የሚኒስትሩ ክርክር ሊሆን ይችላል ብዬ የምገምተው፣ የባለበጀት መሥሪያ ቤቶቹ ዓመታዊ በጀት ፓርላማ ቀርቦ የሚፀድቅ መሆኑና የልማት ድርጅቶቹ በጀት ግን በፓርላማ የማይፀድቅ በመሆኑ፣ ለፓርላማው ተቀላቅሎ የማይፀድቅ ስለሆነ ለፓርላማው ተቀላቅሎ ሊቀርብ አይገባም ከሚል መነሻ ያቀረቡት ክርክር ሊሆን ይችላል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ይህ ማለት ፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን እንደማይቆጣጠር የሚገልጽ አይደለም፡፡ በእኛ አዋጅ ላይ ግልጽ ነው፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ከዚያም አልፎ ሕዝባዊ ድርጅቶችንም ለምሳሌ የተለያዩ ስፖርት ፌዴሬሽኖችን ጭምር ኦዲት ማድረግ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ ከዋና ኦዲተር ውጪ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን ያለው ማንም የለም፡፡   

ሪፖርተር፡- የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 101 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በማድረግ ፓርላማው ያፀደቀላቸውን በአግባቡ መጠቀማቸውን በመመርመር መልስ ለፓርላማ ሪፖርት ያደርጋል ነው የሚለው፡፡ የእናንተ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይም ይህንኑ እንጂ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የምታደርጉትን ኦዲት ለፓርላማ ሪፖርት እንደምታደርጉ አያሳይም፡፡

አቶ ገመቹ፡- ተሳስተሃል፡፡ የእኛ አዋጅ ይላል፡፡ አዋጁ በግልጽ ማንኛውም ዓይነት ኦዲት ማድረግ እንደምንችል ሥልጣን ይሰጠናል፡፡ ኦዲት አድርገን የምናዘጋጀውን ሪፖርት ደግሞ ለፓርላማ ያቀርባል ይላል፡፡ እኛ ብቻ ኦዲት ያደረግነውን ሳይሆን ኦዲት ያስደረግነውንም በክልል የኦዲት ተቋማት ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ውክልና በምንሰጣቸው ኦዲተሮች የሚደረጉ ኦዲቶችን ጭምር ሪፖርት ያደርጋሉ ይላል፡፡ ፓርላማው የመጨረሻው የሥልጣን አካል ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉንም የሕዝብ ንብረትና ገንዘብ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን አለው፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን አይቆጣጠርም አይልም፡፡ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ከፋፍሎ ሳይደባልቁም ለፓርላማው ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ለፓርላማው የምናቀርበው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የሚኒስትሩ ክርክር ከምን የመነጨ ይመስልዎታል? ምናልባት የባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት ኃላፊነትን ብቻ ነው እኔ የሚመለከተኝ ማለታቸው ይሆን? እርስዎ የሚገምቱት ምንድነው?

አቶ ገመቹ፡- በጥርጣሬ ላይ ተመሥርቼ ባልናገር እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ካልተሳሳትኩ በቅርቡ ባቀረብኩት የ2006 ዓ.ም. የኦዲት ኮርፖሬሽን ላይ ያገኘናቸውን የኦዲት ውጤቶች ሪፖርት አድርገናል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በአንድ የባቡር ፕሮጀክት ላይ የፀደቀለት የፕሮጀክት በጀት ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ከፀደቀለት በጀት በላይ ተፈራረመ፡፡ ከፍ ያለውን በጀት ኮርፖሬሽኑ የተፈራረመው በሕጉ መሠረት ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ሳያስፈቅድ መሆኑን በአስተያየታችን ገልጸናል፡፡ አቶ ሱፊያን ይህንን ከበጀት ጋር አገናኝተውት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ አገር ማንኛውም ፕሮጀክት እንዲፈቀድና ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርገው ፕሮጀክት የሚያስተዳድረው ይህ ሚኒስቴር ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ፕሮጀክት ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በሚኒስቴሩ አዋጭ መሆኑ መገምገም ይኖርበታል፡፡ አዋጭ ከሆነ የፋይናንስ ምንጩ መታወቅ አለበት፡፡ ብዙ ሒደቶችን ማለፍ አለበት፡፡ ሚኒስትሩ ከምን ተነስተው ይህንን እንዳሉ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በግል አናግራቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዋና ኦዲተር በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ እያደረገ ከሚገኘው የክዋኔ ኦዲት በተጨማሪ፣ የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት በእነዚህ ተቋማት ላይ ማድረግ ይችላል?

አቶ ገመቹ፡- ይችላል፡፡ እስካሁን ግን እየሠራን አይደለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ላይ የምናደርገውን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት እናስፋ በሚል ነው፡፡ እስከ 2002 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የዋና ኦዲተር 30 በመቶ የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን ብቻ ነበር ኦዲት ማድረግ ይችል የነበረው፡፡ ይህንን ከፍ ማድረግ የመጀመሪያው ትኩረታችን ነው፡፡ እነዚህን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የግል ኦዲተሮችም ኦዲት ያደርጓቸዋል፡፡ የመንግሥት ኦዲት ኮርፖሬሽንም ያደርጋቸዋል፡፡ የእነሱን ሪፖርት አንዳንዴ እኛ ጋ እናካትተዋለን፡፡ በሒደት ግን እነዚህ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ላይ የፋይናንስ ኦዲት ማድረግ እንጀምራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የዋና ኦዲተርን የሚከታተለው የፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የሚመራው በተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጭ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በገለልተኝነትና በነፃነት መንግሥትን ለመቆጣጠር ነው፡፡ ዋና ኦዲተርስ ምን ያህል ነፃ ነው?

አቶ ገመቹ፡- ዋና ኦዲተር ነፃ ነው ነፃ አይደለም ብላችሁ መመስከር ያለባችሁ እናንተ ናችሁ፡፡ በእኔ እምነት ግን ተቋሙ ነፃ ነው፡፡ ከተሾምኩኝ ሰባት ዓመት ሞልቶኛል፡፡ ይኼንን አድርግ፣ ይኼንን አታድርግ ተብዬ አላውቅም፡፡ የፈለገውን ማቀድ ይችላል፣ የፈለገውን ኦዲት ማድረግ ይችላል፡፡ ከሪፖርትህ ላይ ይህችን ነገር በዚህ ቀይራት ተብሎ አይታወቅም፡፡ ለፓርላማ የምናቀርበው የኦዲት ግኝት ሪፖርት ለሕዝብ የሚቀርብ ነው፡፡ ይህንን ሪፖርት ከፓርላማ ውጪ ለሥራ አስፈጻሚው አንልክም፡፡ ፓርላማውም አንዲት ቃል አይቀይርብንም፡፡ እኔ የማረጋግጥላችሁ ተቋሙ ነፃ ነው፡፡ መንግሥትም ራሱን ለኦዲት ክፍት አድርጓል፡፡ የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብና የኦዲት ችግር ያለባቸው መሥሪያ ቤቶች በፓርላማው ሲጠሩ ሚዲያዎች እንዳይገኙ ቢደረግ ነው ነፃ አይደለም ብሎ መጠራጠር የሚቻለው፡፡ ሌላ አገር ግን የኦዲት ሪፖርቶችን ለፓርላማ እንኳን የሚያቀርቡት ተመራጮች ናቸው፡፡ የእኛ አገርና ምናልባትም ደቡብ አፍሪካ ብቻ ናቸው ከአፍሪካ ዋና ኦዲተሩ ራሱ በቀጥታ ፓርላማ እየቀረበ ሪፖርት የሚያደርግባቸው አገሮች፡፡ ስለዚህ ነፃነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነገር የለም፡፡ ቋሚ ኮሚቴውን በተመለከተ የሁለቱንም የፓርላማ ዘመኖች ቋሚ ኮሚቴዎች አይቻለሁ፡፡ የኦዲት ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሌሎች የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች በፖለቲካ ላይ፣ በሕግ ላይ፣ በፖሊሲ ላይ ይከራከራሉ፡፡ ይህ ቋሚ ኮሚቴ ግን ሕግ በትክክል ተተግብሯል አልተተገበረም ወይ የሚለውን ነው የሚመለከተው፡፡ ስለዚህ በተቃዋሚና በገዥው ፓርቲ የፓርላማ አባላት መካከል ልዩነት በፍጹም ሊነሳ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ስለ ሕግ መፈጸም ነው ሁለቱም የሚያወሩት፡፡ መጀመሪያ የደረስኩበት ቋሚ ኮሚቴ ላይ በተወሰነ ደረጃ አለመግባባት ነበር፡፡ ቅድም ያልኩትም አዋጅ ማለፍ ያልቻለበት ምክንያትም አንዱ ይህ አለመግባባት ነው፡፡ በየትኛውም አገር የሚገኝ የበሰለ ቋሚ ኮሚቴ በሕግ መከበር ላይ ልዩነት ሊኖረው አይችልም፡፡ አሁን እኛን በሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴ ውስጥም የማየው ይህንኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ መከበርና ያለመከበር የመጨረሻ ውጤት ፖለቲካዊ የሚሆን ይመስለኛል፡፡

አቶ ገመቹ፡- አይደለም፡፡ ሕግ አልተከበረም ማለት እውነት ነዋ፣ ማንም ሊቀይረው አይችልም፡፡ ሊሸፍነውም አይችልም፡፡ አንድ በጨረታ መገዛት ያለበት ግዥ ያለጨረታ ተገዛ፡፡ ይህ የሕግ ጥሰት ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው የምትነጋገረው፡፡ ወደ ፖሊሲ አማራጭ ልትሄድ አትችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤቶች የሚያሳዩት ገዥው ፓርቲ ከፍተኛውን አብላጫ ስለመያዙ ነው፡፡ ምናልባትም በመጪው ፓርላማ ተቃዋሚን የሚወክል ተመራጭ ላይታይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቋሚ ኮሚቴውም ሊመራ የሚችለው በገዥው ፓርቲ ተመራጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምን ዓይነት ሁኔታ ይፈጠራል ብለው ይገምታሉ? በእናንተ ሥራ ላይ ተፅዕኖ ይኖረው ይሆን?

አቶ ገመቹ፡- እኔ ተፅዕኖ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ሁለቱም ቋሚ ኮሚቴዎች ላይ ደርሻለሁ፡፡ ሁለቱም በተቃዋሚ ተወካዮች ነበር የሚመሩት፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው ቋሚ ኮሚቴ በአቶ ግርማ ሰይፉ ነው የሚመራው፡፡ እሳቸው እንዲያውም ኦዲተር ናቸው፡፡ የዚህ መሥሪያ ቤት ባልደረባ ነበሩ፡፡ የሆነው ሆኖ መንግሥት ግልጽነትን አሰፍናለሁ ብሎ መቁረጡ ላይ ነው መሠረታዊ ጉዳዩ ያለው፡፡ መንግሥት ቁርጠኛ ከሆነ በተቃዋሚ ፓርቲ ተመራ ወይም የተለያዩ ፓርቲዎች በቋሚ ኮሚቴው መገኘት ፋይዳው ይኼን ያህል አይደለም፡፡ አሁን ያለው ቋሚ ኮሚቴ በተቃዋሚ የሚመራ ቢሆንም፣ ሥራውን እየሠሩና ኮሚቴውን በአብዛኛው እየሰበሰቡ ያሉት ምክትል ሰብሳቢውና የገዥው ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ተሾመ እሸቱ ናቸው፡፡ ይህንንም በሚገባ የሚዲያ ተቋማት የተገነዘባችሁት ይመስለኛል፡፡ ለመንግሥት ወግነው እንደሆነ እናንተ ምስክሮች ናችሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ይህንን ተቋም እየመሩ ባሉበት ወቅት ትልቁ ፈተናዬ የሚሉት ምንድነው?

አቶ ገመቹ፡- ትልቁ ፈተና ነው ብዬ የማስበው ይኼ ከሰው ኃይል ጋር የተያያዘው ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር ቢፈታ የበለጠ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡ የበለጠ እሴት መጨመር እንችላለን፡፡ አሁን የመጣንበት ጉዞ መልካም ቢሆንም ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ ስለኦዲት ስናስብ ቁጥር ብቻ አይደለም ብቃት ያለው የሰው ኃይል ቢኖርህ ፈልፍሎ የሚያወጣቸው ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች አሁን ከምናቀርበው የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ችግራችን ቢፈታ የበለጠ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የኦዲት ሥራችንን እናሰፋለን፡፡ ሁለተኛው አሁንም ትልቅ ፈተና እየሆነ ያለው የኦዲት ግኝቱን ሥራ አስፈጻሚዎች ያለመቀበል፣ ስህተትን ያለመቀበል ባህርይ አሁንም አልጠፋም፡፡ የእኛ ዓላማ ስህተትን አጉልቶ ያ መሥሪያ ቤት ወይም ኃላፊ እንዲጠፋ አይደለም፡፡ ዓላማችን ሕግና ሥርዓት ተጠብቆ ሥራዎች እንዲከናወኑ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ደግሞ ራሳቸው ተቋማቱ የበለጠ ተልዕኳቸውን እንዲያሳኩ ያለባቸውን ክፍተቶች መጠቆም ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ፈተና በኦዲት ግኝት ላይ ዕርምጃ ያለመውሰድ ነው፡፡ እኔ ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ ግን ሥራዬን አልጨረስኩም፡፡ ሥራዬ የመጨረሻውን ውጤት ሲያመጣ ነው መርካት ያለብኝ፡፡ የመጨረሻውን ውጤት አላስገኘም፡፡ የእኛ የኦዲት ግኝት በሚዲያ ስለተሰማ ሥራ ተሠርቷል ማለት አይደለም፡፡ ስህተቱ ታርሞ ሳይ ነው ተሳክቶልኛል ብዬ መናገር የምችለው፡፡ ይህ አለመሆኑ ለእኔ ትልቅ ፈተና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእናንተን የኦዲት ውጤት ይዞ ፓርላማው ለምንድነው ዕርምጃ የማይወስደው? በዚህ ጉዳይ ላይ አልተወያያችሁም?

አቶ ገመቹ፡- ፓርላማው ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ጥረቱ መቋጫው ላይ ግን አልደረሰም፡፡ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፣ በይደር አሳልፏል፡፡ ከአሁን በኋላ ነው ፓርላማው ዕርምጃ ወስዷል አልወሰደም ብዬ መናገር የምችለው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...