Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቢኮኔክትድ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ተቀላቀለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲስ ገሠሠ የሚለው ስም ከመዝናኛው ዘርፍ ይልቁንም ከሙዚቃ ሥራዎች ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ በተለይ የዕውቁ የሬጌ ስልት አቀንቃኝ ቦብ ማርሊይ ልጆች (የዚጊ ማርሊይና ሪታ ማርሊ) ማናጀር በመሆን መሥራታቸው ይጠቀሳል፡፡ አዲስ ገሠሠ የድምፃዊ የቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) እና የወንድማቸው ዘለቀ ገሠሠ ማናጀር ሆነው አገልግለዋል፡፡

በቅርቡም በሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሙዚቃዎችን የቀመረው የጃኖ ባንድ መሥራችም መሆናቸው ሲታሰብ አቶ አዲስና የመዝናኛ ዘርፍ ትስስርን አጉልቶ ያሳያል፡፡ ሰሞኑን ግን ከመዝናኛ ዘርፍ ብዙ ርቀት ባለው ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሦስት የውጭ ዜጎች ጋር በጥምረት ያቋቋሙትን ፋብሪካ አስመርቀዋል፡፡ ከ27 ዓመታት በላይ ከቆዩበት የመዝናኛ ዘርፍ ብዙ በሚርቅ ሥራ ውስጥ መግባታቸው ያልተለመደ ቢመስልም፣ አቶ አዲስ ግን ‹‹እኔ እኮ በተለያዩ ኢቨስትመንት ውስጥ የገባሁት ዛሬ አይደለም፡፡ ራሴን በመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ ብቻ የከለልኩ አይደለሁም፤›› ይላሉ፡፡ በሆቴል፣ በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ላይ ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር በጥምረት ባቋቋሟቸው ኩባንያዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንና አሁንም እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመሆን በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ላይ የመሰማራት ምኞታቸውም ዛሬ የተጀመረ ያለመሆኑን የገለጹት አቶ አዲስ፣ ከ12 ዓመታት በፊት በመሰል ዘርፍ ለመሰማራት ሞክረው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ያኔ የውጭ ኩባንያዎችን በማግባባት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢቨስት እንዲያደርጉ ያደርጉት ጥረት አልተሳካም፡፡ በእንጥልጥል ቆይቶ የነበረውን ምኞታቸው ግን ቢዘገይም አሁን ተፈጻሚ ማድረጋቸው ግን እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ፡፡

ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በዱከም ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ በይፋ ሥራ የጀመረው ፋብሪካ ቢኮኔክትድ ኢንዱስትሪያል የሚል መጠሪያ ያለው ነው፡፡ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ግብዓቶችን በማምረት የሚታወቀውን ቢኮኔክትድ ኢንዱስትሪያል የተባለውን የሆላንድ ኩባንያ በፊታውራሪነት በመያዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የጀመረው አዲሱ ፋብሪካ በጨርቃ ጨርቅ ኅትመትና የሌብሊንግ የሚመረትበት ነው፡፡ ቢኮኔክትድ የሚል ስያሜ የያዘው ይህ ኩባንያ እንዲመሠረት ከተወሰነ በኋላ ለሥራው የሚያስፈልጉ ማሽኖችን በማስመጣትና በመገጣጠም ወደ ሥራ ለመግባት የወሰደበት ጊዜ ዘጠኝ ወራት ብቻ ነው፡፡

አቶ አዲስን ጨምሮ በአራት ባለድርሻዎች በጋራ የተቋቋመው ቢኮኔክትድ ኢንዱስትሪያል በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ መግባት የተቻለው ለማሽነሪዎቹ ተከላ የሚሆን የተጠናቀቀ የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ማምረቻ ሥፍራ በመከራየታቸው ነው፡፡ በመጀመርያው ምዕራፍ ኢንቨስትመንቱ 2.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል፡፡

በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በኪራይ ለሚጠቀሙት የማምረቻ ቦታም በወር ከ22 ሺሕ ዶላር በላይ ይከፈልበታል፡፡ ቅድሚያም የሁለት ዓመት ክፍያ የተፈጸመበት መሆኑንም ከአቶ አዲስ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የዚህን ያህል ቢከፈልበትም አዋጭ የሆነ ሥራ ይሠራል ይላሉ፡፡ ይህንንም ሥራ በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ኩባንያዎችና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ አዳዲስ አገልግሎት የሚሰጡ ማምረቻዎችን መፍጠር እንደተቻለ ያመለክታሉ፡፡

በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ያልተሞከሩ ናቸው የተባሉትን ሌብሊንግና የጨርቃ ጨርቅ ኅትመት ሥራዎች በጥምረት በአንድ ታዛ ሥር የሚያመርት ነው፡፡

እንደኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ በእያንዳንዱ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ላይ የምርቱን ዓይነት፣ የተመረተበትን አገርና ኩባንያ፣ የተመረተበትን ጥሬ ዕቃ፣ የአስተጣጠብና ሌሎች የምርቱን ይዘት የሚያመለክቱ መረጃዎችን የሚገልጸው ወይም ሌብሊንግ ምርት እስካሁን በኢትዮጵያ ያልተመረተ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የሌብሊንግ ምርት በኢትዮጵያ ውስጥ መመረቱ የአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ከውጭ ያስመጡ የነበረውን ይህንን ምርት እዚሁ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችላቸው እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

ከሌብሊንግ ምርቱ ጎን ለጎን የኅትመት ሥራዎችን የሚሠራው ይህ ፋብሪካ አዲስ ነገር ይዞ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ የሚላኩ ቲሸርቶች እሴት ተጨምሮባቸው እንዲላኩ ያደርጋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመረቱ ቲሸርቶች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተለያዩ ኅትመቶችን ይዘው ለሽያጭ የሚቀርቡ መሆኑን የሚገልጹት የኩባንያው ኃላፊዎች፣ 30 በመቶው የሚሆኑት ደግሞ ምንም ዓይነት ኅትመት ሳይኖራቸው ለገበያ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ቲሸርቶች ግን ምንም ዓይነት ኅትመት የሌለባቸው በመሆኑ ቲሸርቶቹን የሚገዙ ኩባንያዎች ቲሸርቶቹ የበለጠ ዋጋና ውበት እንዲኖራቸው ለማድረግ የተለያዩ ኅትመቶችን አክለውበት ይሸጣሉ፡፡ የኩባንያው ዋነኛ ባለድርሻና የቢኮኔክትድ ኢንዱስትሪያል ባለቤት ሚስተር ማርቲን ቫን አልፈን እንደገለጹት፣ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ቲሸርቶች ምንም ዓይነት ኅትመት የሌለባቸው በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ለመሥራት ተገፋፍቻለሁ ይላሉ፡፡  ኅትመት የሌለባቸው ቲሸርቶችን ከመላክ እሴት በማከል ለገበያ ማቅረብ አዋጭ መሆኑን የገጹለት ሚስተር ማርቲን፣ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችን ተዘዋውረው በተመለከቱበት ወቅት ለምርቶቻቸው ግብዓት የሚሆናቸውን ሌብሊንግ ከቱርክና ከቻይና እንደሚያስመጡ በመረዳታቸው ሁለቱንም ሥራ አጣምሮ ለመሥራት እንዲወስኑ አድርጓቸዋል፡፡

በድርጅቱ እምነት አዲሱ የሌብሊንግና የኅትመት ፋብሪካ ሥራ መጀመር ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የአልባሳት ምርቶች የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ጭምር ይረዳል፡፡ ‹‹ምንም ዓይነት ኅትመት የሌለበት የአንድ ቲሸርት ዋጋ አንድ ዶላር አካባቢ ቢያወጣ ነው›› ያሉት አቶ አዲስ፣ ኅትመት ያለበት ከሆነ ግን አራትና አምስት ዶላር  የሚሸጥ በመሆኑ በአገሪቱ ጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድ ገቢ ዕድገት ላይ የማይናቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኅትመት ክፍሉ በዘመናዊ መሣሪያዎች የተደራጀ ነው ያሉት ሚስተር ማርቲን፣ በቀን 80 ሺሕ ነጠላ ኅትመቶችን በተለያዩ አልባሳቶች ላይ የማተም አቅም ሲኖረው ይህንን ምርት በቀላሉ ዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚችል ያረጋግጣሉ፡፡ የኅትመት ሥራው የሚያካሂደው 840 ሜትር ጥንድ የፕሪንቲንግ ስክሪን ባለው ዘመናዊ መሣሪያ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የፋብሪካው የአመራረት ስልት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባላቸውና ደረጃዎችን በጠበቁ ሒደቶች የሚከናወን ከመሆኑም በላይ፣ ዓለም አቀፉን ገበያ መሠረት አድርጎ የሚመረት ነው ተብሏል፡፡ በአውሮፓ የሚገኙ ትላልቅ የአልባሳት ኩባንያዎች ምርቱን ለመውሰድ ከወዲሁ ጠንካራ ግንኙነት መፈጠሩን የሚገልጹት አቶ አዲስ፣ ቢኮኔክትድ ኢንዱስትሪያል ደግሞ በዚህ ዘርፍ ከ58 ዓመታት በላይ የቆየ ልምድ ስላለው የገበያ ችግር አይኖርበትም፡፡ የኅትመት ሥራው የሚሠራው ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት ጭምር ነው፡፡ ኩባንያዎቹ በተለያዩ ምርቶቻቸው ላይ የሚሹትንና ፈቃድ የወሰዱባቸውን የኅትመት ዓይነቶች ያሳትማሉ፡፡ ሚስተር ማርቲን ኩባንያ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ የ50 ኩባንያዎች ፈቃድ ያላቸው በመሆኑ፣ በዚያ ፈቃድ መሠረት በየትኛውም አገር ገበያ ተቀባይነት ያለው የኅትመት ሥራ ይሠራሉ ተብሏል፡፡ ይህ የኅትመት ሒደት ዝም ብሎ የሚሠራ ሳይሆን ፈቃድ የተገኘባቸውን ፕራንዶች ብቻ የሚመለከት ነው፡፡

እንደ አቶ አዲስ ገለጻ ይህንን ፋብሪካ በአጭር ጊዜ ማቋቋም ቢችሉም ሸሪኮቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መዋለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ከመወሰናቸው በፊት እንደማንኛውም የውጭ ኢንቨስተር በኢትዮጵያ ውስጥ መሥራታችን ያዋጣናል ወይ? የሚል ጥናት አድርገዋል፡፡ በተለያየ አቅጣጫ መረጃዎችን አሰባስበውም ነበር ብለዋል፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣናት የተሰጣቸው መረጃ ያስደሰታቸው ቢሆንም፣ ይህንን የሚያረጋግጥላቸው ገለልተኛ ወገን ያስፈልግ ነበርና በኢትዮጵያ መሥራት ምን ያህል ያወጣል የሚለውን አሳማኝ መረጃ ለማግኘት ወደ ዓለም ባንክ ጭምር ሄደው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካይን በቀጥታ ማግኘት በመቻላቸውም ተወካዩ የሰጡዋቸው መልስ ኢትዮጵያ ውስጥ በትክክል መሥራት እንደሚቻል ማረጋጫ በማግኘታቸው ፋብሪካውን ዕውን ለማድረግ መቻሉን አቶ አዲስ ገልጸዋል፡፡

ቢኮኔክትድ ኢንዱስትሪያል ከአውሮፓ ውጭ በሰባት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች በተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ፋብሪካዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡ በፋብሪካው ምረቃ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታው ዶ/ር መብርሃቱ መለስ ፋብሪካው ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

የቢኮኔክትድ ኃላፊዎች እንደገለጹት ደግሞ ከፋብሪካው ማሽነሪ ግዥና ተከላ ጎን ለጎን በማምረቻ መሣሪያዎቹ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በተለያዩ አገሮች ሠልጥነው ተመልሰዋል፡፡

በቤልጂየም፣ በቻይናና በሲውዘርላንድ ሥልጠና ወስደው የመጡት ኢትዮጵያ ውስጥ ማሽኖችን ከማንቀሳቀስ በላይ ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም ያሠለጥናሉ ብለዋል፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡ ሁለት የተለያዩ ምርቶችን በአንድ ማምረቻ ሥፍራ ለማምረት ወደ ሥራ የገባው ቢኮኔክትድ ለ400 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች