Sunday, July 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ40 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የጅንስ ጨርቅና ክር ማምረቻ ማምረት ሊጀምር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓመት አንድ ሚሊዮን ሜትር ብትን ጅንስ ጨርቅ ያመርታል

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ የህንድ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ካኖሪያ አፍሪካ ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ 40 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጌበታለሁ ያለውን ብትን የጅንስ ጨርቅና የስፌት ክር ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ አጠናቆ ወደ ምርት እየገባ ነው፡፡

በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ከአዲስ አበባ 44 ኪሎ ሜትር ቢሾፍቱ ከተማ የተገነባው የካኖሪያ ግዙፍ ፋብሪካ ከጥቂት የኮንስትራክሽን ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራ በስተቀር ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ ዘመናዊ መሣሪያዎች ሙሉ ለሙሉ ተተክለው ተጠናቀዋል፡፡

ውስን የግንባታ መጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ ይቀረዋል የተባለው ፋብሪካው የስፌት ክር ማምረቻ ግን ካለፈው ወር ጀምሮ ምርት ጀምሯል፡፡ ብትን የጅንስ ጨርቅ ማምረቻ ክፍሉ ደግሞ በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር አሺሽ አግራውል ገለጻ፣ በጉጉት እየተጠበቀ ነው ያሉትን የብትን ጅንስ ማምረቻ መሣሪያዎች ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ማምረት ይጀምራሉ፡፡

የአገር ውስጥና የውጭ ገበያን ታሳቢ በማድረግ የተገነባው ይህ ፋብሪካ፣ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ሜትር በላይ የጅንስ ጨርቅ ማምረት የሚችል ነው፡፡ ባለፈው ወር ምርት የጀመረው የስፌት ክር ማምረቻው ደግሞ በዓመት ከ25 ሚሊዮን ሜትር በላይ የማምረት አቅም አለው ተብሏል፡፡

ካኖሪያ ግሩፕ በህንድ በጨርቃ ጨርቅ፣ በኬሚካል፣ በንግድ፣ በኃይል ማመንጫ መሣሪያዎችና ተያያዥ ቢዝነሶች ላይ የተሰማራ ግዙፍ ኩባንያ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከህንድ ውጭ በአውሮፓ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተሰማራ ነው፡፡

የአውሮፓ ኢንቨስትመንቱ ከአውቶሞቲቭና መሰል ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እንደ ቢኤምደብልዩ ካሉ ትላልቅ መኪና ማምረቻ ኩባንያዎች ጋር የሚሠራ ስለመሆኑም የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይገልጻሉ፡፡

የኢንቨስትመንት ግሩፑ ኢንቨስትመንቱን ወደ አፍሪካ ለማስፋት ሲወስን እግሩን ያስገባው በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ መዋለ ንዋዩን በማፍሰስ ነው፡፡ የአፍሪካ ኢንቨስትመንቱንም በኢትዮጵያ በገነባው የጅንስና የክር ፋብሪካ ግንባታ አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡ ኩባንያው የአፍሪካ ኢንቨስትመንቱን በኢትዮጵያ የጀመረው በበቂ ምክንያት ስለመሆኑ ሚስተር አሺሽ ይናገራሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ቀደም ብሎ እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሌሎች አገሮችን በመዟዟር ጥናት ማድረጋቸውን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ምርጫ ያደረጉት በአገሪቱ ውስጥ የተመለከቱት ምቹ የኢንቨስትመንት ድባብ መኖሩን በማረጋገጣችን ነው ይላሉ፡፡ የተረጋጋና በሰላም መሥራት የሚቻልበት አገር መሆንዋንም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ለውጭ ኢንቨስተሮች ያለው ዕድልና ለሥራው የሚሆን የሰው ኃይል ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ግንባታቸው ኢትዮጵያን በቀዳሚነት ለመምረጥ አስችሏቸዋል፡፡ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም ከመንግሥት እያገኙ ያሉት ድጋፍ ኩባንያቸው በሚታወቅባቸው ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የሚያነሳሳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 530 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት በመውሰድ ወደ ሥራ የገባው ይህ ፋብሪካ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የክርና የጂንስ ጨርቅ ለማምረት እንዲያስችለውም የተከላቸውን መሣሪያዎች በሙሉ ከአሜሪካ፣ ከጀርመን፣ ከጃፓንና ከመሳሰሉት አገሮች በመግዛት ነው ያስገባቸው፡፡

ፋብሪካው ከተመሳሳይ ፋብሪካዎች በተለየ የሚያደርገው በርካታ ይዘቶች እንዳሉትም የኩባንያው ሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ በተለይ ከብክለት ነፃ የሆነ ምርት ለማምረት የሚያስችለውን መሣሪያ መትከሉ አንድ ምሳሌ ነው ይላሉ፡፡ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ነው የተባለው ይህ መሣሪያ የውኃ፣ የአፈርና የአየር ብክለት እንዳይኖር ይረዳል፡፡

ኩባንያው በመጀመርያው ምዕራፍ 550 ሠራተኞችን ይዞ መንቀሳቀስ ላይ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀምር ደግሞ ከአንድ ሺሕ የላነሱ ሠራተኞች ይኖሩታል፡፡ በመጀመርያው የምርት ዘመን የሚያስፈልጉትን 26 ኢንጂነሮች ከውጭ የሚያስመጣ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሒደት ግን እነዚህን የውጭ ባለሙያዎች በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የመተካት ዕቅድ አለው ብለዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የጅንስ ጨርቅ የሚያመርት ኩባንያ ያለመኖሩን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ፋብሪካው የሚያመርታቸውን ምርቶች ለአገር ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጅንስ ስፌትና ዝግጅት ለሚታወቁ ኩባንያዎች ያቀርባል፡፡ በተለይ ብትን የጅንስ ጨርቁንና የስፌት ክሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጅንስ አልባሳትን በማዘጋጀት ለሚታወቁት ሊ፣ ራንግረር፣ ሊቫይስና ኤች ኤንድ ኤም ላሉ ኩባንያዎች ያቀርባል ተብሏል፡፡

ኩባንያዎቹም ምርቱን መቀበል እንደሚችሉ ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ለፋብሪካው ዋነኛ ጥሬ ዕቃ የሚሆነውን የጥጥ ምርት ከአገር ውስጥ ለማግኘት እንደሚችል ማረጋጥ ችለናል የሚሉት የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች፣ ሁመራ አካባቢ ካሉ የጥጥ አምራች አርሶ አደሮች ጋር የጥጥ ምርት እንዲያቀርቡለት ተስማምቷል፡፡

በአካባቢው ያለውም የጥጥ ምርት ዝርያ የጥራት ደረጃ ኩባንያው ከሚፈልገው የጥጥ ምርት ደረጃ ጋር የሚስማማ ነውም ተብሏል፡፡ ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ኢንቨስትመንቱ በቀጥታ ኢንቨስትመንት ካስገባው ገንዘብ ባሻገር ለሥራ ማስኬጃ የሚውል ብድር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማግኘቱ ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ከ600 በላይ ኩባንያዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኩባንያዎቹም ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት መዋለ ንዋይ የሚፈስባቸው ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች