Monday, February 26, 2024

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር ከየት ወዴት?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በ1998 ዓ.ም. የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር የነበሩት አቶ ለማ አርጋው፣ መሥሪያ ቤታቸውን በሕዝብ ዘንድ ምን እንደሚሠራ በመጥፎ አጋጣሚም ቢሆን ያስተዋወቁ ናቸው፡፡ በሰኔ ወር 1998 ዓ.ም. በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተመራጮች በፓርላማ መቀመጫቸው ታድመዋል፡፡ በስተግራ በኩል ካለው የተቃዋሚ ተወካዮች የፓርላማ መቀመጫ ውጪ ያሉት የገዥው ፓርቲ መቀመጫዎችም በሙሉ ተሞልተዋል፡፡ ዕለቱ የ1999 ዓ.ም. በጀት የሚፀድቅበት በመሆኑ፣ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም ቦታቸውን ይዘዋል፡፡

አቶ መለስ በጀቱን አስመልክቶ ከሚቀርቡ ጥያቄዎች በተጨማሪ ሌሎች የበጀት አፈጻጸምን የተመለከቱ ጥያቄዎችንም በአግባቡ መመለስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በወቅቱ የፓርላማውን ትርጉም ያለው ወንበር የያዙት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችም፣ የመንግሥት የበጀት አፈጻጸም ላይ አነጣጥረዋል፡፡ ለዚህም በዚያው ሰሞን አካባቢ በዋና ኦዲተር የቀረበውን የኦዲት ሪፖርት መሠረት አድርገዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ አቶ ለማ አርጋው በወቅቱ ያቀረቡት ሪፖርት በ1997 ዓ.ም. የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የሰጠውን 7.2 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጐማ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ይገልጻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሌሎች ቢሊዮን ብሮች የፋይናንስ ሕጋዊነት ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ ይህንን በማንሳት ሥራ አስፈጻሚው መንግሥትን የወቀሱት ተቃዋሚዎቹ በትክክልም የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር መንካት ችለዋል፡፡

አቶ መለስ፣ ‹‹ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት የሚያገኙትን የበጀት ድጐማ ከፈለጉ ማቃጠል ይችላሉ፤›› በማለት በቀጥታ በቴሌቪዥን እየተላለፈ በሚገኘው ፕሮግራም ላይ የተናገሩ ሲሆን፣ የዋና ኦዲተሩ አቶ ለማን የኦዲት ሥነ ምግባር ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን የጣሱ ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡

ይህ ክስተት በሰኔ ወር ከተፈጠረ ወራት በኋላ በኅዳር ወር 1999 ዓ.ም. አቶ ለማ ባልታወቀ ምክንያት ራሳቸውን ከኃላፊነት እንዳነሱ ተነገረ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አስደንጋጭ ከመሆኑም ባሻገር፣ የፓርላማው ረዳት የሆነውን የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በዚህ መልክ መናገር በተቋሙ ነፃነት ላይ ጉዳት ማድረስ ነው ሲሉ በወቅቱ ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡

ከዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትችት በኋላ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር አቅሙን ተጠቅሞ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ በጀመረ ጊዜ ሁሉ፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ደስተኛ የሚሆን አይመስልም፡፡

ለዚህ የሚሆኑ ማሳያዎችም ታይተዋል፡፡ በመጀመሪያ በ2000 ዓ.ም. የታየው የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መንግሥት ከሕግ ውጪ የተበደረውን ገንዘብ ማጋለጡን ተከትሎ የተፈጠረ ነው፡፡ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ መበደር ያለበት የበጀት ጉድለቱን 25 በመቶ ብቻ እንደሆነ በሕግ ተደንግጐ እያለ፣ በ1999 ዓ.ም. የተበደረው ግን ከዚህ በላይ መሆኑን የሚጠቁም ነበር፡፡ ይህ የኦዲት ግኝትን መንግሥት ሊቀበለው ባለመቻሉ ፓርላማው ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ አጣሪ ኮሚቴው በመጨረሻ ይዞ የመጣው ሪፖርት መንግሥት ከሕግ ውጪ አለመበደሩን የሚገልጽ ቢሆንም፣ በዚያው ዓመት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የፈለገውን ያህል መበደር እንደሚችል የሚገልጽ ሕግ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በተደረገ ማሻሻያ እንዲለወጥ ተደርጐ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ፀድቋል፡፡

ከዚህ በኋላ በነበሩት ዓመታት በቀረቡት የዋና ኦዲተር ሪፖርቶች፣ የፌዴራሉ መንግሥት የክልሎች የበጀት ድጐማ ኦዲት ተደርጐ አያውቅም፡፡

በ2004 ዓ.ም. የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ደግሞ የዋና ኦዲተርን ዳግመኛ ወደ ጥንካሬው መመለስ ያሳያል፡፡ በወቅቱ ኦዲት መደረግ ያልቻሉ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበ በጀትን ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዙት የደኅንነት ተቋማት ናቸው፡፡ በተለይም የመከላከያ ሚኒስቴርና የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት፡፡ በተጨማሪም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አብዛኞቹ በኦዲት ችግር ውስጥ ተዘፍቀው የነበረ በመሆኑ፣ በርካታ የገዥው ፓርቲ የፓርላማ አባላትን አስቆጥቶ ነበር፡፡

‹‹ይህ ኪራይ ሰብሳቢነት አይደለም፡፡ በስሙ ልንጠራው ይገባል ሌብነት ነው፤›› ያሉት በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው፡፡

በ2005 ዓ.ም. የቀረበው የኦዲት ሪፖርት የለወጠው ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ የደኅንነት ተቋማቱ ላይ ኦዲት መደረግ ያልቻለው ገንዘብ ከደኅንነት ሚስጥሮች ጋር የተገናኘ በመሆኑ እንዴት ኦዲት ይደረግ? ዓለም አቀፍ ተሞክሮው ምን ይመስላል? የሚሉት ጥያቄዎች ጐልተው ወጥተዋል፡፡ በመሆኑም ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሌሎች አገሮችን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር እነዚህ ተቋማት እንዴት ኦዲት መደረግ እንደሚችሉ በማጥናት ለፓርላማው የጥናት ውጤቱን ሪፖርት እንዲያደርግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይህንን ጥናት እያከናወኑ ባለበት ወቅት፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በ2006 ዓ.ም. የተለያዩ ወራት የመከላከያ ሚኒስቴርን፣ የመረጃ ደኅንነትና ኢሚግሬሽን፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጆች ላይ ለፓርላማው ባቀረበው ማሻሻያ ዋና ኦዲተር የደኅንነት ሚስጥሮችን የማየት ሥልጣን እንደሌለው በማሻሻያው አንስቶ አፅድቋል፡፡

ፓርላማው ይህንን አዋጅ ማፅደቁ ችግር እንደሌለው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ይህ አሠራር በዓለም አገሮች የተለመደ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ገለልተኛ በሆነ መንገድ በዋና ኦዲተር አሠራሩ እየተጠና ባለበት ወቅት ይህንን ኃላፊነት ጥሶ ሥራ አስፈጻሚው የራሱን ማሻሻያ ማቅረቡ፣ ተጠያቂነትን መፍጠር የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ካለው ፍላጐት ነው ብሎ መገመት አያስችልም ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በሥራ ላይ የሚገኙት ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ፣ ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ የዋና ኦዲተርን ሕጋዊ ሥልጣን ለመግፈፍ ነው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡

ከቀድሞው ዋና ኦዲተር አቶ ለማ አርጋው ጋር ተነስቶ የነበረውም ክርክር፣ ‹‹ተገቢ አልነበረም፡፡ በኦዲተሩም በሥራ አስፈጻሚው መንግሥትም ዘንድ ስህተት ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ ኦዲት ማድረግ ስላልቻሉት የበጀት ድጐማ ያቀረቡት ምክንያት ክልሎቹ ሒሳባቸውን የሚሠሩት በራሳቸው ቋንቋ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ምክንያት ግን ሚዛን የሚደፋ አይደለም በማለት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ይከራከራሉ፡፡

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አደረጃጀትና የሰው ኃይል አገሪቷን መምሰል አለበት ብለዋል፡፡ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኩል የቀረበው ክርክርም ተገቢና ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ አቶ ገመቹ ይነቅፋሉ፡፡ መንግሥት ስህተቱን በመገንዘቡም ስህተቱን አርሟል ብለዋል፡፡

አቶ ገመቹ ይህን ይበሉ እንጂ የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጐማ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ትችት በኋላ ኦዲት መደረግ የቻለው በ2000 ዓ.ም. ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ በመለስ ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ አንድም ጊዜ የክልል በጀት ድጐማን ኦዲት አድርጐ አያውቅም፡፡

አቶ ገመቹ ግን ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ግምጃ ቤት ለክልሎች የሚሄደውን በጀት በዋና ኦዲተር የአቅም ችግር ምክንያት ኦዲት ማድረግ ባይችልም፣ የውጭ ዕርዳታ ሰጪዎች በዓለም ባንክ በኩል ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ በፌዴራል መንግሥት በኩል ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍ ኦዲት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የፌዴራሉ መንግሥት ገንዘብ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ ገንዘብ ከፌዴራል መንግሥት ግምጃ ቤት ከሚወጣው የታክስ ከፋዩ ኅብረተሰብ ገንዘብ ጋር ሲወዳደር ትርጉም ያለው ነው ማለት አይቻልም፡፡ ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት ለፓርላማ የቀረበው የ2008 ዓ.ም. በጀት ላይ ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ የቀረበው ለክልሎች የሚተላለፍ ገንዘብ 12 ቢሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ ከግምጃ ቤት ለክልሎች በጀት ድጐማ የተመደበው ግን 76.3 ቢሊዮን ብር ከአጠቃላይ 223.3 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ውስጥ የ34 በመቶ ድርሻ ያለው ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ ‹‹በአስተዳደራዊ ሰበብ ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጐማን ኦዲት አለማድረግ ተቀባይነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡

የፊስካል ፌዴራሊዝም ባለሙያ ዶ/ር ሰለሞን ንጉሤ፣ ‹‹ለክልል የሚሰጥ ድጐማ በጀትን የግድ ኦዲት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ክልሎችን ለሚያገኙት በጀት ተጠያቂ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ክልሎች የሚያገኙትን ድጐማ ዝም ብለው እንዲጠቀሙ በተፈቀደ ቁጥር፣ በፌዴራል መንግሥት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ማበረታታት ነው በማለት ያክላሉ፡፡

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዘንድሮ ያለፈባቸው ሒደቶች ከላይ የተገለጸውን ይመስላሉ፡፡ ከላይ የተገለጹት የሆኑና የተፈጠሩ እውነቶች ናቸው፡፡ አሁንስ ይህ ተቋም ከሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ምን እየገጠመው ነው?

አቶ ሱፊያን አህመድ ያነሱት ጥያቄ

በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የ2008 ረቂቅ በጀትን ለማቅረብ ፓርላማ የተገኙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ፣ አዲስ የሆነ ጥያቄ በዋና ኦዲተር ላይ አንስተዋል፡፡

የፓርላማ አባላት በ2006 ዓ.ም. በጀት አፈጻጸም ላይ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያቀረበላቸውን የኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ ይህ የ2008 በጀት በአግባቡ እንዴት ሊውል እንደሚችል ጥያቄ አንስተውላቸዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን፣ ‹‹ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እንደሌላው ተቋም ሁሉ የአቅም ችግር አለበት፡፡ ከዚህ አልፎም የግንዛቤ ችግር ይታይበታል፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሚያደርገውን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲትና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የሚያደርገውን ኦዲት ቀላቅሎ ለፓርላማው ማቅረቡ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ የሰጡት ምክንያትም ሁለቱም ተቋማት የሚተዳደሩት በተለያዩ ሕጐች በመሆኑ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ፓርላማው ባለበጀት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችንም ሆነ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን መቆጣጠር ይችላል የሚሉት አቶ ሱፊያን፣ ዋና ኦዲተር ግን የኦዲት ሪፖርቱን አደባልቆ በማቅረብ ፓርላማው ላይ ውዥንብር መፍጠር እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት አቶ ገመቹ ግን መሥሪያ ቤታቸው በአገሪቱ የመጨረሻው የኦዲት ባለሥልጣንና ተጠሪነቱም ለመጨረሻው የሥልጣን አካል ለሆነው ፓርላማ በመሆኑ፣ ማንኛውንም የመንግሥት መሥሪያ ቤት እንዲሁም የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው የግል ድርጅቶችም ቢሆኑ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ይገልጻሉ፡፡

የአቶ ሱፊያን መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ (የተሻሻለው) 669/2002 አንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ አራት ‹‹የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ማለት ሚኒስቴር፣ ኮሚሽን፣ ባለሥልጣን፣ ተቋም፣ ኤጀንሲ ወይም ማናቸውም ሌላ የፌዴራል መሥሪያ ቤት ነው፤›› ይላል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን ያነሱት ክርክር ቀየር ብሎ ለፓርላማ ቀረበ እንጂ አዲስ አይመስልም፡፡ እሳቸው የሚመሩት መሥሪያ ቤት የትኛውም ጊዜ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ወጪ ተቀላቅሎ ሲቀርብ ጠንከር ባለ መልኩ ነው የሚቃወመው፡፡

ይህ በአብዛኛው የሚገለጸው ደግሞ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ስታትስቲክስ በሚዘረዝርበት ወቅት፣ የባለበጀት መሥሪያ ቤቶችንም ሆነ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን የውጭ ብድር አንድ ላይ ደምሮ የሚሠራ በመሆኑ ነው፡፡

አቶ ሱፊያንም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህ ዓይነቱን ሪፖርት በተደጋጋሚ ሲተቹ ይደመጣሉ፡፡ የሚሰጡት ምክንያትም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ የልማት ድርጅቶች ያለመንግሥት ዋስትና የሚበደሩ በመሆናቸው፣ የእነሱ ዕዳ ከመንግሥት ጋር መቀላቀል የለበትም የሚል ነው፡፡ አቶ ሱፊያን አሁን ዋና ኦዲተር ላይ ያነሱት ጥያቄም የዚህ መንትያ ይመስላል፡፡

ይህ የመንግሥት አቋም ዛሬስ የዋና ኦዲተርን አዋጅ በድጋሚ እንዲሻሻል፣ አልያም ዋና ኦዲተር እነዚህ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ላይ የሚያደርገው ኦዲት ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ ሕግ ያወጣ ይሆን የሚለው አሳሳቢ ሆኗል፡፡

ቀጣዩና ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግ ተመራጮች ብቻ ይሞላል ተብሎ የሚጠበቀው ፓርላማ፣ አሁንስ ለእሱ ተጠሪ የሆነውን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሥልጣንን አክብሮ ይሠራ ይሆን የሚል ጥያቄን የአቶ ሱፊያን አስተያየት ጭሮ አልፏል፡፡ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻ ከፍተኛ በሆነበት አገር፣ የመንግሥት በጀት (ገቢና ወጪ) ላይ ግልጽነት የሰፈነበትና ተጠያቂነትን የሚያስከትል አሠራር አለማስፈን ለአገር ህልውናም ጭምር የሚያሰጋ ችግር በመሆኑ፣ የኦዲተሩን ሥራ በቀናነትና በኃላፊነት የሚመለከት ፓርላማ አስፈላጊ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

        

  

     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -