Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኤሌክትሪክ አቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት የተመረተ ውኃ ለተጠቃሚ መድረስ አልተቻለም

በኤሌክትሪክ አቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት የተመረተ ውኃ ለተጠቃሚ መድረስ አልተቻለም

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የገነባቸውን ፕሮጀክቶች ቢያጠናቅቅም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያት ማምረት የሚቻለውን ንፁህ ውኃ ለተጠቃሚው ማድረስ እንዳልቻለ አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ እስካሁን ለከተማው ነዋሪዎች በቀን ሲያቀርበው ከቆየው 350 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ፣ ባካሄደው መጠነ ሰፊ ግንባታ አማካይነት በቀን 600 ሺሕ ሜትር ኩብ የሚጠጋ ውኃ ማቅረብ የሚቻልበትን ፕሮጀክት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ ይህ 70 በመቶ የነበረውን የአዲስ አበባ ከተማ ንፁህ ውኃ አቅርቦት፣ ወደ 90 በመቶ የሚያሳድግ ነው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቶቹ ከአንድ ወር በፊት ቢጠናቀቁም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምክንያት የተመረተውን ውኃ ለተጠቃሚዎች ማድረስ አልተቻለም፡፡ ‹‹በእርግጥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ትራንስፎርመሮችን በመትከል ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የኃይል አቅርቦት ግንባታውም ሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ፈጣን ባለመሆኑ፣ መመረት የሚቻለው ውኃ ሳይመረት ተቀምጧል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በዋናነት አራት ፕሮጀክቶችን አጠናቋል፡፡ ከእነዚህም አንዱ አቃቂ አካባቢ በቀን 70 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ማምረት የሚችለው እና ለ700 ሺሕ ሰዎች 24 ሰዓት አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለው ፕሮጀክት በሁለት ቢሊዮን ብር ተገንብቷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ለደቡብ በከፊል ደግሞ ለምዕራብና ለማዕከላዊ አዲስ አበባ የሚከፋፈል ውኃ ያመነጫል፡፡

 ሁለተኛው በለገዳዲ አካባቢ ከተካሄደ የጉድጓድ ቁፋሮ 40 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ በቀን ማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት 1.5 ቢሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን፣ በምሥራቅና በሰሜን ለሚገኙ 400 ሺሕ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ የሚቀርብበት ፕሮጀክት ነው፡፡

ሦስተኛው ደግሞ በአቃቂ የተካሄደው ሦስተኛው ፕሮጀክት 18 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ማመንጨት የሚያስችል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከ180 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው፡፡

ሌላኛውና አራተኛው ፕሮጀክት በተለይ ኪስ በሚባሉ ቦታዎች ለሰሜን አዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚሆን 20 ጉድጓዶችን ለመቆፈር የተያዘ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት እስካሁን 16 ጉድጓዶች የተቆፈሩ ሲሆን፣ አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡

ነገር ግን የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ፕሮጀክቶቹ ቢጠናቀቁም የከተማው ነዋሪዎች ውኃውን ማግኘት አልቻሉም፡፡ አቶ አወቀ እንዳሉት፣ ከዚህ የኃይል አቅርቦት በተጨማሪ በከተማው በየጊዜው በሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት በመስመር ውስጥ  የሚገኘው ውኃም ወደ ተጠቃሚው እንዳይደርስ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለአዲስ አበባ ከተማ ከሚያቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 33 በመቶ የሚሆነውን የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ይጠቀማል፡፡ ውኃ ለማመንጨትና ለተጠቃሚው ለማድረስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

አቶ አወቀ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ቢስተካከል በአንድ ወር ውስጥ  የሙከራ ሥራ ተሠርቶ ውኃው ለተጠቃሚ ይሰራጫል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...