Thursday, October 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሠራተኞች መልቀቅ ችግር ሆኖብኛል አለ

  ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሠራተኞች መልቀቅ ችግር ሆኖብኛል አለ

  ቀን:

  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በክፍያና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ማነስ ምክንያት፣ በጣም በርካታ ሙያተኞች መልቀቃቸውንና በምትካቸውም ብቁ ሙያተኛ ለመቅጠር ክፍያው ሳቢ አለመሆኑን ገለጸ፡፡

  የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ያለፉትን አሥራ አንድ ወራት የኮሚሽኑን የዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው ይኼንን ችግር ያነሱት፡፡

  እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ 12 ወንዶችና ሰባት ሴቶች በድምሩ 19 ሠራተኞች ሥራቸውን ለቀዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች መልቀቅና በምትካቸው መቅጠር ባለመቻሉ ባለፉት 11 ወራት ያጋጠመው ችግር በማለት ለፓርላማው አባላት አስረድተዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ለኮሚሽኑ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ከመንግሥት የተፈቀደው የመደበኛ በጀት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ፣ በየወሩ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሚለቀቀው ወይም አንድ-አሥራ-ሁለተኛ የሚባለው አሠራር፣ በተለይም በኮሚሽኑ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሠራር ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ሌላው ኮሚሽኑን ያጋጠመው ተፅዕኖ እንደሆነ ኮሚሽነሩ  አስረድተዋል፡፡

  በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙት እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም፣ ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራት መኖራቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ በዚህም ረገድ በአጠቃላይ የ2007 ዓ.ም. አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ሕገ መንግሥቱን፣ የምርጫ ሕጎችንና ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን መሠረት ባደረገ ሁኔታ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶችን ጨምሮ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲፈጸም ክትትል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

  የሴቶችና የሕፃናት መብትን ለማስጠበቅ እንዲቻል፣ በተለይም የመብት ጥሰት መንስዔ የሆኑትን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የግል ጥቃቶች ለመከላከል ብሎም ለማስወገድ የተጀመሩ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችና መድረኮች እንዲጠናከሩ ኮሚሽኑ ያደረገው ድጋፍ እንዲሁ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ጠንካራ ክንውኖች መሀል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

  ላለፉት አምስት ዓመታት ኮሚሽኑን በኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አባላት በአዲስ ለመተካት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅብረተሰቡ የዕጩዎች ጥቆማ እንዲያደርግ ያስነገረ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በአዲሱ የፓርላማው የመጀመሪያ ዓመት  አዲስ ኮሚሽነር የሚመረጥ በመሆኑ፣ ይህ ሪፖርት በአምባሳደር ጥሩነህ አማካይነት የቀረበ የመጨረሻው ነው፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img